Monday, June 17, 2024

ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው

[ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላ ወዳጃቸው ጋር ስልክ እያወሩ ነው]

 • የምሥራች ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምሥር ብላ፡፡
 • እንኳን ደስ አለዎት፡፡
 • ምን ተገኘ?
 • እኔ ጋ ሁሌም መልካም ዜና አይደል እንዴ ያለው፡፡
 • ሚስትህ ወለደች እንዴ?
 • ኧረ ከዚያ በላይ የሚያስደስት ዜና ነው ያለኝ፡፡
 • የምን ዜና?
 • ተጠናቀቀ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ?
 • ያመጣነው ዕቃ፡፡
 • እየቀለድክ መሆን አለበት?
 • የእውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ሆኖ?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ብርድ ራሱን መሸጥ እንደምችል ያውቃሉ አይደል?
 • እሱስ እውነትህን ነው፡፡
 • በቃ ይኸው በአንድ ሳምንት ሁሉንም አጠናቅቄዋለሁ፡፡
 • እንዴት በአንዴ ሊያልቅ ቻለ?
 • መጀመርያውኑ ጥናት አድርጌ ነዋ ዕቃውን ያመጣሁት፡፡
 • እውነትም አንበሳ ነህ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ይኼ ኮሮና ለእኛ ነው የሆነን፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ይኸው ሰው ተስፋ ቆርጦ ቤቱ ተቀምጦ እኛ እየከበርን ነው፡፡
 • አኩርተኸኛል ስልህ፡፡
 • በዚያ ላይ ያመጣነው ዕቃ ተፈላጊ በመሆኑ በእጥፍ ነው ያተረፍነው፡፡
 • ቤቴን ጨረስኩት በለኛ?
 • እንዲያውም ሌላ መሥራት ይጀምሩ እንጂ፡፡
 • የእውነት ነው ያኮራኸኝ፡፡
 • ገና ከዚህ የበለጠ ሠርቼ አኮራዎታለሁ፡፡
 • ምን ልትሠራ አሰብክ?
 • በአፋጣኝ ያመጣነውን ዕቃ መድገም አለብን፡፡
 • ምን ችግር አለው ታዲያ?
 • ባንኩ እያስቸገረኝ ነው፡፡
 • ምን ብሎ?
 • የውጭ ምንዛሪ የለም እያለ ነው፡፡
 • እሱን በእኔ ጣለው፡፡
 • ሌላም ችግር አለ፡፡
 • ምንድነው?
 • ያመጣነው ዕቃ ገበያ ላይ ተፈላጊ ሆኗል፡፡
 • እሺ፡፡
 • ስለዚህ በርካታ ነጋዴዎች ዕቃውን ሊያመጡት እንዳሰቡ ሰምቻለሁ፡፡
 • ምን ችግር አለው ታዲያ?
 • እነሱ ካመጡት እንዳሁኑ ወዲያው ሸጠን ላንጨርሰው እንችላለን፡፡
 • እ…
 • በዚያ ላይ በፈለግነው ዋጋ መሸጥ አንችልም፡፡
 • ምን ተሻለ ታዲያ?
 • አንድ በአንድ መምታት ነው፡፡
 • እነ ማንን?
 • ተቀናቃኞቻችንን ነዋ፡፡
 • ምን አድርገን?
 • እኛ ልናመጣ የምናስበውን ዕቃ የሚያመጡትን ድርጅቶች ሊስት እሰጥዎታለሁ፡፡
 • እሺ፡፡
 • ከዚያማ አንድ በአንድ ያሰርዙላቸዋል፡፡
 • ምኑን ነው የማሰርዘው?
 • ንግድ ፈቃዳቸውን!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ የውጭ ኢንቨስተር ስልክ ደወለላቸው]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • የኮሮና ወረርሽኝ አራራቀን አይደል?
 • መገናኘቱስ ቀርቶብን በስልክም ጠፍተሃል እኮ፡፡
 • በመደወሉም ማኅበራዊ ርቀቴን ልጠብቅ ብዬ ነዋ፡፡
 • መቼም ቀልደኛ ነህ፡፡
 • ምን ላድርግ ብለው ነው?
 • ዛሬ ታዲያ ከየት ተገኘህ?
 • ኧረ በጣም ፈርቼ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ኮሮናን ነው?
 • እሱንማ ፈርቼ ፈርቼ አሁን ወጥቶልኛል፡፡
 • ታዲያ ምን ፈራህ?
 • ጦርነት፡፡
 • የምን ጦርነት?
 • በዓባይ ላይ ጦርነት እንዳይነሳ ነዋ፡፡
 • ለምን ይነሳል?
 • መግባባት አልቻላችሁማ፡፡
 • ባንግባባስ ጦርነትን ምን አመጣው?
 • ይኸው የግብፆችን ፉከራ እየሰማሁ ነው፡፡
 • እነሱ እኮ ልማዳቸው ነው፡፡
 • የአሁኑ ግን ያስፈራል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ ነው የሚያስፈራው?
 • በቃ ሁሉ ነገር ጠንከር ብሏል፡፡
 • ስማ የጥቁር ሕዝብ የነፃነት ምልክት መሆናችንን አትርሳው፡፡
 • እሱማ አውቃለሁ፡፡
 • ስለዚህ ሕዝባችንን ከድህነት የማላቀቅ ሙሉ መብት አለን፡፡
 • እኔም እስማማለሁ፡፡
 • የአገራችን 65 በመቶ በላይ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሌለው አታውቅም?
 • ኧረ ያለውን ኃይል ለማግኘት እኛ ራሳችን ምን ያህል እንደምንቸገር አውቃለሁ አይደል እንዴ?
 • እንግዲህ ግብፅ ከ95 በመቶ በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ኖሯት ነው እኛን እንዲህ መግቢያ መውጫ የምታሳጣን፡፡
 • የእነሱም የበዛ ስግብግብነት ነው እኮ፡፡
 • ነገሩ እኮ ከዚያም በላይ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ግብፆች ዓባይን ለፖለቲካ ዓላማ ነው የሚጠቀሙበት፡፡
 • እሱማ ትክክል ነዎት፡፡
 • ግድቡም እንደማይጎዳቸው በሚገባ ያውቁታል፡፡
 • ታዲያ ይኼን ያህል ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉት ለምንድነው?
 • ፖለቲካ ነዋ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • የውስጥ የፖለቲካ ሽኩቻቸውን በዓባይ ነው የሚያበርዱት፡፡
 • እኛ በመሀል ተሸበርና፡፡
 • ምንም መሸበር አያስፈልግም፡፡
 • እኔ እኮ ኢንቨስትመንቴን ለማስፋፋት አስቤ ፈራሁ፡፡
 • ለምን?
 • ነገ ጦርነት ቢነሳ ብዬ ነዋ፡፡
 • አይሞክሩትም አታስብ ስልህ?
 • እናንተም ጦርነት አታነሱም ክቡር ሚኒስትር?
 • አንድ ነገር ልንገርህ፡፡
 • ንገሩኝ፡፡
 • እኛ ፀብ አንጭርም፡፡
 • አውቃለሁ፡፡
 • ከነኩን ግን…
 • እ…
 • ዋጋቸውን እንሰጣቸዋለን!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ የአገር ሽማግሌ ስልክ ደወሉላቸው]

 • ምን ተሻለ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምኑ አባቴ?
 • መካረሩ ነዋ፡፡
 • በጊዜው ይረግባላ፡፡
 • ሊበጠስም ይችላል እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ይደረግ ታዲያ?
 • እናንተም ትንሽ ለስለስ ብትሉ ብዬ ነው፡፡
 • እኛ መቼ ሻከርን ብለው ነው?
 • ያው እነሱም እኮ እናንተን ነው የሚከሱት፡፡
 • መክሰስ እኮ ልማዳቸው ነው፡፡
 • የአሁኑ መካረር ግን ያስፈራል ብዬ ነው፡፡
 • ምኑ ነው የሚያስፈራው?
 • እስከ መጨረሻው ድረስ እንሄዳለን እያሉ ነው፡፡
 • ማን ይቀበላቸዋል?
 • እ…
 • ከዚህ በኋላ በሕዝብ እየነገዱ መቀለድ አይቻልም፡፡
 • ቢሆንም ልጆቼ ነገሮችን ሰከን ባለ አዕምሮ ማየቱ መልካም ነው፡፡
 • አባቴ እኔም በሚሉት ሐሳብ እስማማለሁ፡፡
 • ታዲያ ለምን ቁጭ ብላችሁ አትደራደሩም?
 • ከግብፅ ጋር ነው?
 • ኧረ ከእነሱ ጋር እንጂ፡፡
 • ከእነሱ ጋር የምን ድርድር ነው የምንቀመጠው?
 • ስለሁሉም ነገር ነዋ፡፡
 • እነሱ ሕግና ሥርዓትን ማክበር ነው እንጂ የሚጠበቅባቸው ድርድር አንቀመጥም፡፡
 • እነሱም እኮ ሕግና ሥርዓት ይከበር ነው የሚሉት፡፡
 • ቀድሞውኑ የት ሲያውቁት?
 • ያው እንደ ሽማግሌ አንተም ተው አንቺም ተው ማለት ነው ኃላፊነታችን፡፡
 • እነሱ አልሰማ አሉዋ አባቴ፡፡
 • ቢሆንም እናንተም ትንሽ ቻሏቸው፡፡
 • በአገሪቱ እንደራደር አባቴ?
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • እነሱ ከሥልጣን ስለወረዱ ለምንድነው ቁጭ ብለን የምንደራደረው?
 • እ…
 • እነሱ ሥልጣን ላይ እያሉ ከማን ጋር ተደራድረው ያውቃሉ፡፡
 • እሱን እኔ አላውቅም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዚህ አባቴ መደረግ ያለበት አንድ ነገር ነው፡፡
 • ምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ሕግና ሥርዓትን ማክበር ነዋ፡፡
 • እምቢ ካሉስ?
 • ምን ችግር አለው ታዲያ?
 • ወደ ጦርነት ሊገባ?
 • ኧረ እዚያ አንደርስም፡፡
 • ምን ልታደርጉ?
 • ልክ እናስገባቸዋለን!

[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]

 • እያበቃልን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ?
 • የእናንተ ነገር ነዋ፡፡
 • እናንተ ግን ትንሽ አታፍሩም?
 • ምንድነው የሚያሳፍረን?
 • እኛ ካልገዛን አገር ትፈራርሳለች ስትሉ ነዋ፡፡
 • እውነት ስለሆነ ነዋ፡፡
 • ማን ነው ያለው?
 • እኛ፡፡
 • እናንተን የሁሉ ነገር አድራጊ ፈጣሪ ማን አደረጋችሁ?
 • ራሳችን፡፡
 • ችግሩ እኮ እሱ ነው፡፡
 • ምኑ?
 • ሁሉም ነገር በራሳችሁና በራሳችሁ ብቻ ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡
 • ሌላ ምን ነገር አለ ብለው ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ሕዝብ የሚባል ነገር ነዋ፡፡
 • ለሕዝቡማ እኛ እናውቅለታለን፡፡
 • ይህ አስተሳሰባችሁ እኮ ነው ችግሩ ውስጥ የከተታችሁ፡፡
 • እኛ እኮ ችግር ላይ አይደለንም፡፡
 • ውኃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው አሉ፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • ሥልጣናችሁንም ያጣችሁት እኮ ደህና ነን እያላችሁ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አሁን ሁሉም ነገር ገብቶናል፡፡
 • ምንድነው የገባችሁ?
 • ሕዝባችን ምን እንደሚፈልግ እናውቃለን፡፡
 • ምንድነው የሚፈልገው?
 • እኛን፡፡
 • በምን አወቃችሁ?
 • ስለምናውቅ አልኩዎት እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይኼ አመለካከታችሁ እኮ ነው ያሳጣችሁ፡፡
 • ምን?
 • ሥልጣናችሁን!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት የሚታወጁ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ማለቴ ነው። ምን ታወጀ? አንዴ ከዕዳ ወደ ምንዳ አላችሁ፡፡ እሺ? የእሱን ውጤት እየጠበቅን ሳለ ደግሞ... እ...? ኢትዮጵያ ታምርት...

[ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን በተጀመረው አገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ስለተላለፉ መልዕክቶች በተመለከተ ከባለቤታቸው ጋር እያወጉ ነው] 

እኔ ምልህ? እ... አንቺ የምትይው? አለቃህ በምክክር መድረኩ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት አደመጥክ? አዎ፡፡ የሚገርም እኮ ነው አልተገረምክም? ምኑ ነው የሚያስገርመው? ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ምከሩና አምጡ ብለው የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን ቅሬታውንም አልሰማሁም። እንዴት? አልሰማሁማ? የምን ቅሬታ ቀርቦባቸው ነው? ሰሞኑን ወደ አሜሪካ ለመጓዝ ውድና ቅንጡ አውሮፕላን ተከራይተዋል የሚል ቅሬታ...