Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ማቀዱ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአራት ወራት ውስጥ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ታክስ እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2013 በጀት ዓመት ከታክስና ማዘጋጃ ቤታዊ ገቢዎች የ60.2 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ ማቀዱ ተገለጸ፡፡ ከታክስ ገቢ ከ43 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በሥሩ ከሚገኙ የክፍለ ከተማና የወረዳ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ጋር በመጪው ሐምሌ ወር ጀምሮ ስለሚሰበሰበው የታክስ ገቢ፣ ማክሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ተወያይቷል፡፡ ከሐምሌ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ባሉት አራት ወራት ውስጥ እንዲሰበሰብ ስለሚጠበቀው ብሎም ለዓመቱ ስለታቀደው የከተማው ገቢ ውይይት አካሂዷል፡፡

የታክስ ቢሮው ኃላፊ አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ ስለዚሁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በከተማው ከሚታየው የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አኳያ፣ ለበጀት ዓመቱ የታቀደውን ገቢ ለማሰባሰብ የሚያስችል አቅም እንዳለ በመታየቱ፣ ከ43 ቢሊዮን ብር በላይ ከታክስ፣ ከ13 ቢሊዮን ብር ያላነሰ የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ፣ ብድርና ዕርዳታን ጨምሮ በጠቅላላው በከተማው አስተዳደር የሚሰበስበው ገቢ 60.2 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

ባለፈው ዓመት የታክስ ማሳወቂያ አራት ወራት ውስጥ ማለትም ከሐምሌ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ከ16 ቢሊዮን ብር አሰባስቧል፡፡ ያቀደው 17 ቢሊዮን ብር ያህል ነበር፡፡ በ2010 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት 14.8 ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ አቅዶ፣ 14.2 ቢሊዮን ብር እንዳሰባሰበ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ባለፈው ዓመት የከተማው አስተዳደር 41 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ አቅዶ እንደነበር ሲታወስ፣ ከዚህ ውስጥ ከታክስ የሚሰበሰብው 34.5 ቢሊዮን ብር እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ከዚህ የታክስ ገቢ ዕቅድ ውስጥም ከ95 በመቶ ያላነሰው መሳካቱን አቶ ሺሰማ መግለጻቸውን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ከቀድሞው ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በመውጣት ራሱን ችሎ ለከተማው አስተዳደር ተጠሪ በመሆን እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የከተማው ገቢዎች ቢሮ፣ ለመጪው ዓመት እንደሚሰበስበው ያቀደው የገቢ መጠን ምንም እንኳ በኮሮና ሳቢያ ሥጋት ውስጥ ቢሆንም በርካታ አዳዲስ ግብር ከፋዮችን ወደ ታክስ ሥርዓቱ በማስባትና ትኩረት ሳይሰጠው የቆየውን የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ላይ በማተኮር የገቢ አድማሱን እንደሚያሰፋውና ዕቅዱን እንደሚያሳካ አስታውቋል፡፡

እንደ አቶ ሺሰማ ማብራሪያ የኮሮና ወረርሽኝ በመምጣቱ ቢስተጓጎልም፣ ቤት ለቤት የታክስ አሰሳ ሥራዎችን በማካሄድ ከ55 ሺሕ በላይ ቤት አከራዮችን ወደ ታክስ ሥርዓት ማስገባት እንደተቻለ፣ ከ15 ሺሕ በላይ ነጋዴዎችም በመደበኛነት ሕጋዊ ፈቃድ አውጥተው እንዲነግዱ በማድረግ ተጨማሪ ግብር ከፋዮች በመግባታቸው የታክስ መሠረቱ እየሰፋ እንደመጣ ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ሆኖ በከተማው ለታክስ ሕግና ሥርዓት ተገዥ ያለመሆን ከፍተኛ ችግሮች እንደሚታዩ፣ ኦዲት ለመደረግ የሚያንገራግሩ፣ እየተድበሰበሱ እንዲታለፉ የሚደረጉና እስከ 800 ሚሊዮን ብር ሽያጭ እያስመዘገቡ፣ ኦዲት የማይደረጉ፣ ታክስ አሳንሰው ወይም ከነጭራሹ ለማጭርበርና ላለመክፈል የሚያቅማሙ ነጋዴዎች በከተማው እንደሚታዩ በመግለጽ እንዲህ ያለውን ሥርዓት አልበኝነት የታክስ አስተዳደር ሠራተኞች ቸል ሊሉ እንደማይገባቸው አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል ነጋዴው ያልተገነዘበው አንድ ሚስጥር አለ የሚሉት አቶ ሺማ፣ ደረሰኝ አለመቁረጥ ማለት ሸማቹ ለሚገዛቸው ማናቸውም የፍጆታ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ነጋዴው ከራሱ ኪስ ለመክፈል እንደመስማማት እንደሚቆጠር ያብራራሉ፡፡ ‹‹ያለ ደረሰኝ መሸጥ ማለት፣ ነጋዴው ለሸማቹ የቫትና የተርን ኦቨር ታክስ እኔ እከፍልልሃለሁ እያለው እንደሆነ አልተገነዘበውም፤›› ብለዋል፡፡ አያይዘውም፣ ቫትና ተርን ኦቨር ታክስ የፍጆታ ታክሶች በመሆናቸው፣ የሚጠበቅበትን ታክስ ባለመክፈሉ የተጠረጠረ ነጋዴ ሒሳቡ ኦዲት በሚደረግበት ወቅት፣ ለመቀጫና ለወለድ የሚክፍለው ሒሳብ የሚሰላው ከእያንዳንዱ ሽያጩ መሰብሰብ ሲገባው ያልሰበሰበው የቫትና ተርን ኦቨር ታክስን ጨምሮ ከገቢው ላይ የ30 በመቶ ትርፍ ታሳቢ ተደርጎ እንደሆነ ገልጸው፣ የታክስ መጠን ለከፍተኛ ጫና እየዳረገው የሚፈጠረው ጫጫታ ብዙ ችግር ሲፈጥር እንደቆየ አብራርተዋል፡፡

ደረሰኝ የማይቆርጡ ነጋዴዎች ከሸማቹ የሚሰበሰበውን ቫትና ተርን ኦቨር ታክስ ከራሳቸው ለመክፈል እየተገደዱ እንደሆነ አልተገነዘቡትም ያሉት አቶ ሺሰማ፣ ሸማቹም ቢሆን ያለ ደረሰኝ የሚገዛው ዕቃ ብልሽት ወይም እንከን ቢኖርበት፣ ለሸማቾች በአዋጅ የተሰጠውን ሕጋዊ የመብት ከለላ በመተው ለሚድርስባቸው ጉዳት እንደመስማማት የሚቆጠር በመሆኑ፣ ያለ ደረሰኝ በሚደረግ ግብይት ሁለቱም ወገን ተጎጂ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ችግሮችን በመቅረፍ የዓመቱን የታክስ ገቢ ለማሳካት መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው ለቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ማሳሰቢያ ያስተላለፉት አቶ ሺሰማ፣ ከቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎቹ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል፣ ከፍተኛ የሰው ኃይል እጥረት መኖሩንና ከሁለት ሳምንት በኋላ የሚጀመረው ሰፊ የታክስ አሰባሰብ ሒደት ከኮሮና በሽታ ሥርጭት አኳያ ሥጋት እንደፈጠረባቸው የጠየቁበት ይጠቀሳል፡፡

በተለይም የደረጃ ‹‹ሐ›› ወይም ዝቅተኛ ታክስ ከፋዮች በአንድ ወር ጊዜ ብቻ የመስተናገዳቸው ጉዳይ ሥጋት እንደሆነባቸው የጠየቁት ኃላፊ፣ የገቢዎች ቢሮ ከሚያስፈልገው የሰው ኃይል 55 በመቶ ብቻ ተሟልቶለት እየሠራ በመሆኑ፣ የኮሮና መስፋፋትን ለመቀነስ የታክስ ሠራተኞች በፈረቃ እየሠሩ በመሆናቸው ጭምር እንዲህ ያሉ ችግሮች እንዴት እንደሚታረቁ አቶ ሺሰማ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡  

ከልኳንዳ ነጋዴዎች ጋር ባለፈው ዓመት ከፍተኛ ችግር ተፈጥሮ እንደነበርም ተነስቷል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ነጋዴዎች በጣም ከፍተኛ፣ ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ ተብለው የግብር ከፋይነት ደረጃ እንደወጣላቸው ገቢዎች ቢሮ ይጠቅሳል፡፡ ይሁን እንጂ፣ የሚፈለግባቸው የታክስ ዕዳ በአብዛኛው የሚሰላው ከቄራዎች ድርጅት በሚገኝ መረጃና ነጋዴዎቹ በሚይዙት የሒሳብ መዝገብ ላይ በመመሥረት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የኮሮና ወረርሽኝ አብዛኛውን የንግድ እንቅስቃሴያቸውን ከማዳከሙ አኳያ በቁርጥ ገቢ ግምት ታክስ የሚከፍሉት ላይ የገቢ ግምት ማስላት አስቸጋሪ ስለሆነ እንዴት ይታያል? የሚል ጥያቄም ተነስቷል፡፡

ልኳንዳ ነጋዴዎቹ ከዚህ ቀደም ለሪፖርተር በገለጹት ቅሬታ፣ በ2006 .. የወጣው መመርያ፣ ነጋዴዎችን በሁለት ክፍሎች ተለይተው ታክስ ሲከፍሉ ቆይተዋል፡፡ በአንደኛው ክፍል የተመደቡት በአነስተኛ እንዲሁም በሁለተኛው ክፍል የታቀፉት በከፍተኛ ዋጋ የሥጋ ምርት ለኅብረተሰቡ የሚያቀርቡ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት አነስተኛ ነጋዴዎች ከአንድ በሬ ላይ 1,053 ብር 15 ሳንቲም፣ መካከለኛና ከፍተኛ ነጋዴዎች ደግሞ ከአንድ በሬ 1,975 ብር 15 ሳንቲም ተጨማሪ እሴት ታክስ እየሰበሰቡ ገቢ እንደሚያደርጉ በመግለጽ፣ የከተማ አስተዳደሩ ይህንን ነባር መመርያ በአዲስ በመተካቱ ባለፈው ዓመት ግብር ለመክፈልም ሆነ ፈቃድ ለማሳደስ ሲሄዱ ችግር እንደገጠማቸውና ከከተማው ገቢዎች ቢሮ ጋር አለመግባባት ውስጥ እንደከተታቸው ነጋዴዎቹ ገልጸው ነበር፡፡ 

እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች የቀረቡላቸው አቶ ሺሰማ፣ ከ15 የታክስ ቢሮ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ለተውጣጡ ኃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ለአነስተኛ የልኳንዳ ነጋዴዎች የደረጃ ምደባ እየወጣላቸው እንደሆነ፣ ዓምና የተፈጠረውን ችግር ከአማራ ክልል በተገኘ የአሠራር መመርያ ልምድ ተወስዶ የከተማው የልኳንዳ ነጋዴዎች ታክስ የሚከፍሉበት ቀመር እንደተዘጋጀ ያብራሩት አቶ ሺሰማ፣ ይህም ሆኖ ነጋዴዎቹ በዚህ መመርያ ላይ ቅሬታ ይኑራቸው እንጂ በመሠረታዊነቱ የሒሳብ መዝገብ መያዝ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡ በርካታ ልኳንዳ ነጋዴዎች አሳማኝ የሒሳብ መዝገብ እንዳላቀረቡ በመጠቅስ፣ በጊዜያዊነት የ50 በመቶ የተርን ኦቨር ታክስ ማሻሻያ ተደርጎላቸው እንዲስተናገዱ የተረደገበትን መንገድ አስታውሰዋል፡፡ ዘንድሮ እንዲህ ያለ ማሻሻያ እንደማይደረግ ይልቁንም ተገቢውን የሒሳብ መዝገብ በመያዝ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

በሰው ኃይል በኩል ለሚታየው ዕጥረት፣ ከሌሎች ተጓዳኝ መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በማሟላት በተለይ ከፍተኛ ችግር በሚታይባቸው ወረዳዎች ላይ እንዲህ ያሉ አማራጮችን በመጠቀም መሥራት እንደሚገባ፣ በቅርቡ ግን ከ300 ያላነሱ የታክስ ሠራተኞች እንደሚቀጠሩ፣ አብዛኞቹም ለኦዲትና ለታክስ ምርመራ ሥራዎች እንደሚሰማሩ አስታውቀዋል፡፡ የቦታ ችግር፣ ታክስ ከፋዩን ያለ ወረፋ አካላዊ ርቀቱን ጠብቆ ለማስናገድ የሚያስችሉ ጊዜያዊ ዝግጅቶችን በማድረግ በድንኳን ወይም በየትምህርት ቤቱ ሁሉ አገልግሎቱን ማቅረብ የሚቻልባቸው አማራጮች እንደሚታሰቡ አቶ ሺሰማ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

 ዘንድሮ በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ከ5,700 ያላነሱ በቀጥታ ግብር ከፋዮችን የሚመለከት የታክስ ምሕረት፣ የወለድና የቅጣት ዕዳዎችን በማንሳት ከ5.7 ቢሊዮን ያላነሰ ገቢ ሊያጣ እንደሚችል የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ባለፈው ዓመትም ከ7,700 በላይ ታክስ ከፋዮች የታክስ ዕዳ ምሕረት ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) 2003 .. ጀምሮ የተጣለባቸው ግብር ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ እንዲታይላቸው ሲጠይቁ ለቆዩ 6,000 ነጋዴዎች፣ እንዲሁም በግብር ይግባኝ በኩል ተከራክረው ለተፈረደባቸው 1,780 ነጋዴዎችም ምሕረት እንዲደረግላቸው ካቢኔያቸው በመወሰነው መሠረት ምሕረት መደረጉን ማስወቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ምክትል ከንቲባው አስተዳደራቸው መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጡ የታክስ ሪፎርም ሥራዎች መጀመሩን በማስመልከት ምሕረት መደረጉን ባስታወቁ ጊዜ፣  ማንኛውም የከተማው ግብር ከፋይ በፍላጎቱ ላይ የተመሠረተ፣ መክፈል በሚችለው ልክና አቅም፣ በሠራውና በሚጠበቅበት መጠን የታክስ ዕዳ እንዲከፍል ይደረጋል ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች