Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዓለም ባንክ ለበጀት ድጋፍ የሚውል የ250 ሚሊዮን ዶላር ብድርና ዕርዳታ ፈቀደ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአውሮፓ ኅብረት በበኩሉ የ487 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አድርጓል

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የበጀት ድጋፍ የሚውል የ250 ሚሊዮን ዶላር ብድርና ዕርዳታ በመፍቀድ ከመንግሥት ጋር ስምምነት ፈረመ፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ግማሹ በዕርዳታ መልክ እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ ሐሙስ ሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴና በተሰናባቿ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ካሮሊን ተርክ መካከል የተፈረመው ስምምነት መሠረቱ የበጀት ማሟያ የፋይናንስ ድጋፍ ሆኖ፣ በሁለተኛ የኢትዮጵያ የዕድገትና ተወዳዳሪነት ፕሮግራም ልማት ፖሊሲ ማስፈጸሚያነት እንደሚመደም ተጠቅሷል፡፡

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የ250 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዲደረግ መፍቀዱን በማስመልከት የባንኩ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማፕላስ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ጋር መነጋገራቸውን አስታውቀዋል፡፡ በዚሁ መልዕክታቸውም፣ የኢትዮጵያ ስኬት የአፍሪካ ስኬት እንደሆነ ጽፈዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሁለት መሠረታዊ ነጥቦችንም ነካክተዋል፡፡ አንደኛው ከምንዛሪ ተመን አኳያ ባንኩ የሚያራምደው አቋም ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የምትከለተው ጥምር የምንዛሪ ተመን ከመሆኑ ባሻገር ከፍተኛ ምጣኔ ያለበት በመሆኑ ወደ አንድ ምጣኔ እንዲመጣ ይደረግ፣ ይታሰብበት ዓይነት መልክዕት ያዘለ ነው፡፡ የዓለም ባንክና የዓለም ገንዘብ ድርጅት ኢትዮጵያ የምንዛሪ ተመኗን ሙሉ በሙሉ ገበያ መር እንድታደርግ በመወትወት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሌላኛው አሜሪካ በኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያላትን አቋም በጎንዮሽ ያመላከቱበት ነው፡፡ ኢትዮጵያና ጎረቤቶቿ በውኃ ክፍፍል ላይ ትብብርና ገንቢ ምክክር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል የሚል መልዕክት አስፍረዋል፡፡ ይህን ይበሉ እንጂ አሜሪካ ያለ ድርድር ስምምነት የውኃ ሙሌት ማካሄድ አይቻልም የሚል አቋም በማንጸባረቅ ላይ መሆኗ በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን አስነስቷል፡፡ የዓለም ባንክ በግድቡ ዙሪያ በታዛቢነትም ቢሆን እንዲሳተፍ መጋበዙ ስህተት እንደነበር ከመነሻው ጀምሮ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ዘንድ በሰፊው ሲነቀፍ ቆይቷል፡፡  

ባንኩ የሰጠው ድጋፍ በአገሪቱ እየተካሄደ ለሚገኘው የሪፎርምና የትራንስፎርሜሽን እንቅስቃሴ ድጋፍ ለመስጠት ታስቦ እንደሆነ ሲገለጽ፣ አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራሙን ለማስፈጸም እንደሚውልም የሚኒስቴሩ መግለጫ አመላክቷል፡፡ የዓለም ባንክ ለኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያው ከተደረጉ የአሥር ቢሊዮን ዶላር ድጋፎች አብዛኛውን ሲሸፍን፣ የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በበኩሉ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ማበደሩ ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል የአውሮፓ ኅብረትና አባል አገሮች ለኢትዮጵያ ድጋፍ የሚውል የ487 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ እንደሚያድርጉ ማስታወቃቸውን በአዲስ አበባ የሚገኘው የኅብረቱ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

ጽሕፈት ቤቱ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንደተጠቀሰው፣ ድጋፉ የአገሪቱን የጤና ሥርዓትና የለይቶ ማቆያ ጣቢያዎች፣ የማኅበራዊ ዋስትና ማሻሻያ፣ በኮሮና ሳቢያ መተዳደሪያ ገቢያቸውን ላጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ የሚሰጥበት ሲሆን፣ በጠቅላላው የአገሪቱ የኢኮኖሚ ማገገሚያ ምላሾችን በገንዘብ ለመደገፍ በማሰብ ኅብረቱ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን አስታውቋል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ የቀውሱን ጉዳት ለመቀነስ፣ የአውሮፓ ኅብረትና አባል አገሮቹ በኤምባሲዎቻቸውና በኤጀንሲዎቻቸው አማካይነት ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከጤና ሚኒስቴር እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በቅርበት ሲሠሩ መቆየታቸው ተጠቅሷል፡፡

የአውሮፓ ኅብረትና አጋሮቹ ‹‹ቲም ዩሮፕ›› ለምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንገሥታት ባለሥልጣንም የ60 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር፣ እንደ ዓለም ጤና ድርጅት፣ የተመድና መሰል ዓለም አቀፍ ተቋማት የኅብረቱ ድጋፍ እንዳልተለያቸው ተመልክቷል፡፡

ቲም ዩሮፕ ለዓለም አቀፋዊነት ወይም ለግሎባላይዜሽን ያለውን አጋርነት ከማሳየት ባሻገር ዓለም ለገባችበት ቀውስ መፍትሔ ለመሻት፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች የሚደርስባቸውን ጫና ለመቋቋም እንዲችሉ የሚሰጠው ድጋፍ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች