Monday, June 17, 2024

ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው

[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ምነው ዛሬ?
 • ምነው?
 • አትነሽም እንዴ?
 • ተወኝ እባክህ፡፡
 • በጣም ረፍዷል እኮ፡፡
 • ብርድ ብርድ እያለኝ ነው፡፡
 • ያው ዝናብ ስለሆነ ነው የበረደሽ፡፡
 • እኔማ ፈርቼ ነው፡፡
 • ምንድነው የሚያስፈራሽ?
 • በሽታው ነዋ፡፡
 • አንቺ ደግሞ ሌላ ነገር አታውቂም እንዴ?
 • በሚዲያ ከጠዋት እስከ ማታ ከእሱ ውጪ ሌላ ምን ወሬ አለ ብለህ ነው፡፡
 • ምን እያልሽኝ ነው?
 • ማለቴ ከቀን እስከ ማታ ከበሽታው ውጪ ወሬ የለም፡፡
 • ያው ማኅበረሰቡን ለማሳሰብ ነዋ፡፡
 • ቢሆንም በየቀኑ ሙሉ ቀን በየሚዲያው የሚወራው ስለበሽታው ስለሆነ ሌላ ነገር ማሰብ ይከብደኛል፡፡
 • ስሚ ዜና በቀን የተወሰነ ሰዓት ብቻ ነው መመልከት ያለብሽ፡፡
 • ሰውዬ አሁን እኮ ዜናው ብቻ ሳይሆን ሁሉም ነገር ኮሮና ሆኗል፡፡
 • እሱስ ልክ ነሽ፡፡
 • ስለዚህ ከበሽታው ውጪ ማሰብ አልቻልኩም፡፡
 • ለማንኛውም ተነሽና ቁርስ እንብላ፡፡
 • በዚያ ላይ ትናንት የሰማሁት ዜና ከእንቅልፍ የሚነሳ ነው፡፡
 • ስለበሽታው ነው?
 • ኧረ አይደለም፡፡
 • ደግሞ ምን ሰማሽ?
 • ሊቀየር ነው አሉ?
 • ምኑ ነው የሚቀየረው?
 • ምንም አልሰማሁም እንዳትለኝ?
 • ስለምንድነው የምታወሪው?
 • የብር ኖት ሊቀየር ነው እየተባለ ነው፡፡
 • እ…
 • ታዲያ ይኼ ከእንቅልፍ የሚያስነሳ ወሬ ነው?
 • እኛ ገንዘባችንን በዶላር ቀይረናል አይደል እንዴ?
 • ከግማሽ በላይ ገንዘባችን ግን እዚሁ ነው ያለው፡፡
 • የት?
 • ቤት ነዋ በካዝና፡፡
 • እ…
 • ይኼ ዜና በሽታ አያስይዝም ትላለህ?
 • ይኸው እኔንም አሳመምሽኝ እኮ፡፡
 • እሱን እኮ ነው የምልህ፡፡
 • ምን ተሻለ ታዲያ?
 • እኔ ሁሉ ነገር ጨላልሞብኛል፡፡
 • ለምን ወደ ዶላር የሚቀይርልን ሰው አንፈልግም?
 • በዚህ ጊዜ ማን ይደፍራል ብለህ ነው?
 • ማለት?
 • ማለቴ ገንዘብ እንደፈለጉ ማንቀሳቀስ የሚገድበው መመርያ ከወጣ በኋላ ሰው መፍራት ጀምሯል፡፡
 • ስንት ነገር ያቀድኩበት ገንዘብ እኮ ነው፡፡
 • አውቃለሁ፡፡
 • ሕይወታችንን ያሞቅልናል ብዬ አስብ ነበር እኮ፡፡
 • አሁን እንኳን ማድረግ የምንችለው አንድ ነገር ነው፡፡
 • ምን?
 • ገንዘቡን ቀደን…
 • እ…
 • አቃጥለን መሞቅ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ዲፕሎማት ስልክ ደወለላቸው]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • መቼም በዚህ ጊዜ  ቢሮ አይመጣም ብዬ ነው፡፡
 • ልክ ነህ አስፈሪ ጊዜ ላይ ነን፡፡
 • ለነገሩ የእናንተም ሁኔታ እያስፈራን ነው፡፡
 • ምኑ?
 • ጦርነት እንዳትጀምሩ ነዋ፡፡
 • ከወንድሞቻችን ጋር እንዴት ጦርነት እንጀምራለን?
 • የቃላት ልውውጣችሁ ያስፈራል ብዬ ነው፡፡
 • እነሱ እኮ ልማዳቸው ነው፡፡
 • ምኑ ነው ልማዳቸው?
 • ጭር ሲል አይወዱም፡፡
 • እንዴት?
 • ያው ሥልጣን ከተቀሙ በኋላ ሁሉ ነገር ጭር ብሎባቸዋላ፡፡
 • እኔ እኮ ስለግብፅ ነው የማወራው፡፡
 • ነው  እንዴ?
 • እርስዎ ስለማን ነው የሚያወሩት ክቡር ሚኒስትር?
 • ግድ የለም ጣቢያ ተቀላቅሎብኝ ነው፡፡
 • ለማንኛውም የግብፅ ዲስኩር አስፈሪ ሆኗል፡፡
 • እነሱም ቢሆን ልማዳቸው ነው፡፡
 • እንዴት?
 • በዓባይ ጉዳይ ሁሌ ጦርነት እናነሳለን እንዳሉ ነዋ፡፡
 • አሁን ግን የተለወጠ ነገር አለ እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ተለወጠ?
 • ግድቡ ነዋ፡፡
 • ታዲያ ወንዙን መገደብ እኮ መብታችን ነው፡፡ 
 • እሱማ መብታችሁ ነው ግን ምክክር ያስፈልገዋል፡፡
 • ሁሌም ለምክክር በራችን እኮ ክፍት ነው፡፡
 • ታዲያ መስማማት ለምን አልቻላችሁም?
 • እነሱ ሁሌም አፍራሾች ናቸዋ፡፡
 • አልገባኝም?
 • ያው የናይል ወንዝ ለእነሱ የሕይወትና የሞት ጉዳይ እንደሆነ ነው የሚለፈልፉት፡፡
 • ልክ ናቸው እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አሁን የዓባይ ወንዝ ለእኛም የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው፡፡
 • ታዲያ ተቀራርቦ መወያየቱ አያዋጣም ይላሉ?
 • እነሱ ውይይት መቼ ይፈልጉና?
 • ምንድነው የሚፈልጉት?
 • ውኃውን በብቸኝነት ያለ ከልካይ መጠቀም ነዋ፡፡
 • ውኃው እኮ ለሁላችሁም ይበቃል፡፡
 • እነሱ ግን ለብቻቸው ነው መጠቀም የሚፈልጉት፡፡
 • ለምን?
 • የእኛን ዕድገት ስለማይፈልጉ ነዋ፡፡
 • ይቀናሉ እያሉኝ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የእነሱ እንኳን ከቅናትም ይልቃል፡፡
 • ማለት?
 • ምቀኞች ናቸው፡፡
 • በዚህ ዘመን ግን ሁሉን ነገር በጠረጴዛ ዙርያ ተደራድሮ መፍታት ነው የሚሻለው፡፡
 • እነሱ በድርድር መቼ ያምኑና፡፡
 • ታዲያ በምንድነው የሚያምኑት?
 • የጦርነት አዋጅ በማስነገርና በማስፈራራት ነዋ፡፡
 • እሱማ ለማንም አያዋጣም፡፡
 • ይኸው እንግዲህ ሰሞኑን ገንፈል ገንፈል እያሉ ነው፡፡
 • እኔም እኮ እሱ አሳስቦኝ ነው፡፡
 • ችግር የለም መፍትሔ አለው፡፡
 • ምንድነው መፍትሔው?
 • ጥጋባቸውን…
 • እ…
 • እናስተነፍስላቸዋለን!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ስልክ ደወሉላቸው]

 • ምንድነው የምሰማው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ሰማህ?
 • ምርጫ እናደርጋለን እያሉ እኮ ነው?
 • እንተያያለና፡፡
 • አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት?
 • ጠይቀኝ፡፡
 • ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ስንት መንግሥት ነው ያለው?
 • አንድ ነዋ፡፡
 • እርግጠኛ ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • መጠርጠሩስ?
 • ግራ ገብቶኝ እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ለምን ግራ ትጋባለህ?
 • ማለቴ አንዱ ተነስቶ ሁለት መንግሥት አለ ይለናል፡፡
 • እ…
 • አሁን ደግሞ ምርጫ የለም ከተባለ በኋላ እኛ ክልል ምርጫ አለ ይባላል ብዬ ነው፡፡
 • ማንም እኮ የፈለገውን ማውራት ይችላል፡፡
 • ግራ ተጋባን ብዬ ነዋ፡፡
 • ጥያቄው የፈለጉት ሁሉ ይሆናል ወይ የሚለው ነው፡፡
 • እሱስ ልክ ነዎት፡፡
 • ስለዚህ ማንም ሲቃዥ አብሮ መቃዠት አያዋጣህም፡፡
 • የመንግሥት ዝምታ እኮ ጥያቄ ፈጥሮብኝ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስማ መንግሥት እኮ ብዙ ሥራ አለበት፡፡
 • እሱማ ይገባኛል፡፡
 • ስለዚህ ካበደው ሁሉ ጋር አብሮ ያብዳል ብለህ እንዳትጠብቅ፡፡
 • ስለዚህ ምርጫ የለም እያሉኝ ነው?
 • አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ?
 • እሺ ጠይቀኝ፡፡
 • አሁን ይደረጋል የሚባለውን የክልል ምርጫ ማን ነው የሚያስፈጽመው?
 • እኔም የገረመኝ እሱ ነው፡፡
 • በጀቱንስ ማን ነው የመደበው?
 • እኔ ምኑን አውቄው?
 • ለነገሩ በጀቱስ በፊት ከተዘረፈው ሊመጣ ይችላል፡፡
 • መጠርጠሩ አይከፋም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ግን ይኼ ቅዠት ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሰዎቹ ግን ወደኋላ የሚሉ አይመስልም፡፡
 • እንተያያለን አልኩህ እኮ፡፡
 • ለማስፈራሪያ ብቻ የሚሉ ይመስልዎታል?
 • እኔ እነሱን ብሆን በዚህ ወቅት ስለምርጫ አይደለም የማስበው፡፡
 • ስለምን ነበር የሚያስቡት?
 • ስለምልጃ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]

 • ምንድነው የላካችሁልን ክቡር ሚኒስትር?
 • ለእናንተ ደግሞ ምን ይላካል?
 • ሽማግሌ ነዋ፡፡
 • ኧረ ስፌቴን እንዳታስለቅቅብኝ፡፡
 • የምን ስፌት ክቡር ሚኒስትር?
 • ባለፈው ኦፕራሲዮን ተደርጌ የተሰፋሁትን ነዋ፡፡
 • ምን አድርጌ ነው የማስለቅቅብዎት?
 • በሳቅ ነዋ፡፡
 • እንዴት?
 • እኛ ነን ለእናንተ ሽማግሌ የምንልከው?
 • ይኸው  የላካችኋቸው ሽማግሌዎች እኮ እኛ ጋ ደርሰዋል፡፡
 • ሽማግሌዎቹን እኛ ሳይሆን የላክናቸው በራሳቸው ነው የመጡት፡፡
 • ምን ሊያደርጉ?
 • ያው እንግዲህ አያዋጣችሁም ሊሏችሁ ይሆናላ፡፡
 • ምኑ ነው የማያዋጣን?
 • እየሄዳችሁበት ያለው መንገድ ነዋ፡፡
 • የምን መንገድ ነው?
 • የጥፋት መንገድ ነዋ፡፡
 • መስመር አይለፉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እናንተ ናችሁ እኮ መስመር ያለፋችሁት፡፡
 • ምን አድርገን?
 • ይኸው ምርጫ እናካሂዳለን እያላችሁ አይደል እንዴ?
 • እሱማ የማይቀር ነገር ነው፡፡
 • ስታደርጉ እናያለና፡፡
 • መብታችን መስሎኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለነገሩ ለእናንተ ሕግ መጣስ መብት ነው የሚመስላችሁ፡፡
 • እናንተ እኮ ናችሁ ሕግ እየጣሳችሁ ያላችሁት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኛም ሕጉንና ሥርዓቱን ተከትለን ነው ምርጫው እንደሚራዘም ያሳወቅነው፡፡
 • እኛ ግን ምርጫ ከማድረግ የሚያግደን ነገር የለም፡፡
 • እንተያያለን፡፡
 • እያስፈራሩኝ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ሙያ በልብ ነው፡፡
 • ምርጫውን እናደርገዋለን፣ እናደርገዋለን፡፡
 • እንግዲያው የምርጫውን ውጤት የምትሰሙት የት እንደሚሆን እወቁት፡፡
 • የት ነው የምንሰማው?
 • ከርቸሌ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት የሚታወጁ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ማለቴ ነው። ምን ታወጀ? አንዴ ከዕዳ ወደ ምንዳ አላችሁ፡፡ እሺ? የእሱን ውጤት እየጠበቅን ሳለ ደግሞ... እ...? ኢትዮጵያ ታምርት...

[ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን በተጀመረው አገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ስለተላለፉ መልዕክቶች በተመለከተ ከባለቤታቸው ጋር እያወጉ ነው] 

እኔ ምልህ? እ... አንቺ የምትይው? አለቃህ በምክክር መድረኩ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት አደመጥክ? አዎ፡፡ የሚገርም እኮ ነው አልተገረምክም? ምኑ ነው የሚያስገርመው? ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ምከሩና አምጡ ብለው የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን ቅሬታውንም አልሰማሁም። እንዴት? አልሰማሁማ? የምን ቅሬታ ቀርቦባቸው ነው? ሰሞኑን ወደ አሜሪካ ለመጓዝ ውድና ቅንጡ አውሮፕላን ተከራይተዋል የሚል ቅሬታ...