Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት ከ20 እስከ 40 በመቶ የክፍያ ጭማሪ ማድረጉን...

ሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት ከ20 እስከ 40 በመቶ የክፍያ ጭማሪ ማድረጉን ወላጆች ተቃወሙ

ቀን:

ትምህርት ሚኒስቴር የዋጋ ጭማሪውን በመቃወም ለውጭ ጉዳይ ደብዳቤ መጻፉን አስታውቋል

ሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት መንግሥት ያወጣውን ሕግ በመተላለፍ ለመጪው ዓመት ምዝገባ ከመጀመሩም በላይ፣ በኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ላይ የ20 በመቶ፣ በፈረንሣይና በሌሎች ዜጎች ላይ እስከ 40 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉን በመቃወም ወላጆች አቤቱታ አቀረቡ፡፡

መንግሥት በኮሮና ወረርሽኝ ሥጋት ምክንያት ተማሪዎች በቤታቸው እንዲቆዩ ውሳኔ ባስተላለፈበት ወቅት ትምህርት ቤቶች ከ50 እስከ 75 በመቶ የትምህርት ክፍያ እንዲያስከፍሉ ቢሉም፣ ሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት ይህንን በመተላለፍ ሙሉ ክፍያ አስከፍሎናል በማለት ወላጆች ቅሬታ አሰምተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ትምህርት ቤቱ በዚህ ሳይወስን፣ ወላጆች ልጆቻቸውን በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በአካል በመገኘት ካልተመዘገቡ በቀር፣ በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት እንደማይችሉ በትምህርት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ተፈርሞ ለወላጆች የወጣው ደብዳቤና የክፍያ መጠየቂያ ፎርም አመላክቷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዚህ መሠረት በመጀመሪያው ዙር ማለትም እ.ኤ.አ. ከጁን 1 እስከ ጁን 5 ቀን 2020 ተማሪዎች በትምህርት ቤቱ በመገኘት እንዲዘመገቡ ታዘዋል፡፡ በሁለተኛው ዙር ከጁን 8 እስከ ጁን 12 ቀን 2020 መመዝገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ላይ የ20 በመቶ ጭማሪ የተደረገበት የመጪው ዓመት የትምህርት ክፍያ ወደ 116 ሺሕ ብር አሻቅቧል፡፡ ይህ ክፍያ የዓመቱን መመዝገቢያ 3,800 ብር ሳይጨምር ሲሆን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ልጆቻቸውን የሚያስመዘግቡ ወላጆችም 55 ሺሕ ብር የመመዝገቢያ ክፍያ ይጠበቃቸዋል፡፡ ይህም ጭማሪው ይመለከተዋል፡፡ በፈረንሣውያን ተማሪዎችም ላይ የ40 በመቶው ጭማሪ በፊት ከነበረበት ወደ 4,600 ዩሮ ከፍ የተደረገ ሲሆን፣ የመመዝገቢያ 118 ዩሮ እንዲሁም ለመጀመሪያ ጊዜ ልጆቻቸውን የሚያስመዘግቡ ወላጆች ከ1,700 ዩሮ በላይ መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ እንዲህ ያለውን የዋጋ ጭማሪ ያደረገው ወላጆችን ሳያማክር መሆኑን ለሪፖርተር የገለጹ የወላጆች ኮሚቴ ተወካይ አቶ ቢንያም ዘውዴ፣ ትምህርት ቤቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ ሕግ መተላለፉና ዋጋ መጨመሩ ሳያንስ፣ ልጆችና ወላጆችን ለኮሮና ወረርሽኝ ሊያጋልጥ በሚችል መንገድ በአካል ተገኝታችሁ ተመዝገቡ ማለቱም ወላጆችን አስቆጥቷል ብለዋል፡፡

በትምህርት ቤቱ ላይ ቅሬታ ያደረባቸው ወላጆች የተቃውሞ ፊርማ በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ እስከ ማክሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ከ886 በላይ ወላጆችና የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ለፊርማ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

መንግሥት በጉዳዩ ላይ መፍትሔ እንዲሰጥበት ወላጆች አቤት ማለታቸውን፣ ትምህርት ሚኒስቴርም ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደብዳቤ በመጻፍ ጉዳዩ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እልባት እንዲያገኝ መጠየቁን አስታውቀዋል፡፡

ሪፖርተር በትምህርት ሚኒስቴር ሥር የኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤቶችን ጉዳይ ለሚከታተለው ክፍል የውጭ ትምህርት ቤቶች እያደረጉት ስላሉት የዋጋ ጭማሪ ጉዳይ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ አቶ አስፋው መኮንን የዚሁ ክፍል ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ መደረግ እንደሌለበት የሚያሳስብ ደብዳቤ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደተጻፈ አረጋግጠዋል፡፡

በሌላ በኩል ወላጆች ለፈረንሣይ ኤምባሲም ስለጉዳዩ ጥያቄ በማቅረብ የትምህርት ቤቱ አድራጎት እንዲታረም መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡ ሌላው ቢቀር ለኮሮና ወረርሽኝ ሊያጋልጥ የሚችለው በአካል ተገኝታችሁ ተመዝገቡ የሚለው የትምህርት ቤቱ ግትር አቋም በኦንላይን እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

በሊሴ ገብረማርያም ከሚማሩ ከ1,800 ገደማ ተማሪዎች መካከል 80 በመቶ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ያስታወሱት አቶ ቢንያም፣ የኮሮና ወረርሽኝ ከመምጣቱ በፊት የ11 በመቶ የዋጋ ጭማሪ በመጪው ዓመት ይደረጋል የሚል ሐሳብ ትምህርት ቤቱ አቅርቦ አግባብ እንዳልሆነ ክርክር ሲደረግበት ነበር ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ የወረርሽኙን መከሰት አስታኮ የተደረገው ጭማሪ፣ ወቅቱን ያላገናዘበና ጭራሽ ቅናሽ ማድረግ ሲጠበቅበት ጭማሪ ማድረጉ አግባብ አይደለም ሲሉ አክለዋል፡፡

በተማሪዎች ወላጆችና በትምህርት ቤቱ አስተዳደር መካከል እየተካረረ የመጣው አለመግባባት ትምህርት ቤቱ የወላጆች ኮሚቴን ከተሳትፎ ውጪ ማድረግ ከጀመረ በኋላ እንደሆነ፣ በኅዳር ወርም ወላጆች ስብሰባ ጠርተው በትምህርት ቤቱ ላይ ስለሚታዩ የአስተዳደር ችግሮች መወያየታቸውን አቶ ቢኒያም አስታውሰዋል፡፡

የወላጆች ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አቶ ግሩም አበበ ትምህርት ቤቱ ስለሚታዩበት የተለያዩ አስተዳደራዊ ችግሮች ውይይት ተድርጎ የወላጆች ቅሬታዎችም መስተናገዳቸውን በማውሳት ለአዲስ አድማስ ገልጸው ነበር፡፡ 54 ዓመታት ያስቆጠረው ሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት፣ ‹‹ሚሲዮን ላይከ ፍራንሴይስ›› በተሰኘና በዓለም የሚገኙ 200 የፈረንሣይ ትምህርት ቤቶችን በሚያስተዳድር ኮሚሽን የሚመራ ቢሆንም፣ ወላጆቹ እንደሚያቀርቡት ቅሬታ ከሆነ በውጭ ኦዲት ተደርጎ አያውቅም፡፡ ምንም እንኳ ይህ ኮሚሽን በሁሉም ትምህርት ቤቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንደማይደረግ ይፋ ቢያደርግም፣ ሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት ግን ጭማሪ መደረጉን ወላጆች ይገልጻሉ፡፡

ምንም እንኳ የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ሪፖርተር በስልክም በኢሜይልም ላቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም፡፡ ነገር ግን የበጀት ጉድለት እንዳጋጠመው በመግለጽ ጭማሪ ማድረግ እንዳስፈለገው ወላጆች ለሪፖርተር ገልጸው፣ ይህ ይበል እንጂ አጣዳፊና አሳሳቢ የበጀት ጉድለት እንደሌለበት ይሞግታሉ፡፡ ትምህርት ቤቱ የስፖርት ማዘውተሪያ እያስገነባ እንደሚገኝና እስካሁንም 1.2 ሚሊዮን ዩሮ ማውጣቱን የወላጅ ከሚቴ ፕሬዚዳንቱ ይገልጻሉ፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2012 ወዲህ በቀድሞ አሠራሩ ላይ ለውጥ ያደረገው ሊሴ ገብረ ማርያም ከኢትዮጵያ መንግሥት ያገኝ የነበረው ዓመታዊ ድጎማም ከዚያን ጊዜ ወዲህ መቋረጡን መነሻ በማድረግ፣ በትምህርት ክፍያ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ማድረጉን ወላጆች ያወሳሉ፡፡ በትምህርት ቤቱ አስተዳደር ማዕቀፍ ውስጥ የወላጆች፣ የተማሪዎችና የመንግሥት ተወካዮች የሚሳተፉበት ቦርድ እንደሚቋቋም ስምምነት ቢደረስም ሊሴ ገብረ ማርያም ግን ይህን ወደ ጎን እንዳለው ወላጆች ያስረዳሉ፡፡

ከ54 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያና በፈረንሣይ መንግሥታት ለ50 ዓመታት በሚቆይ የጋራ ስምምነት የተመሠረተው ሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት፣ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ በርካታ ስመ ጥር ኢትዮጵያውያንን ያፈራ ተቋም ነው፡፡

 ከሊሴ ገብረ ማርያም ባሻገር ሌሎችም የኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤቶች የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ እያኮበኮቡ እንደሚገኙና አንዳንዶቹም ለወላጆች ማስታወቂያ መላክ መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...