Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም ማስፋፊያ የታጠረው ቦታ የውጭ ዜጎችን ሳይቀር በጠራራ ፀሐይ...

ለአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም ማስፋፊያ የታጠረው ቦታ የውጭ ዜጎችን ሳይቀር በጠራራ ፀሐይ ለዝርፊያ ዳርጓል ያሉ ነዋሪዎች አቤቱታ አቀረቡ  

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 በተለምዶ ሃያ አምስቱ አፓርታማዎች ተብሎ በሚታወቀው መንደር ውስጥ የሚኖሩ ከ450 በላይ አባወራዎች፣ ለአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም ማስፋፊያ የታጠረው ቦታ ለቆሻሻ መድፊያና ማከማቻ በመተው በጠራራ ፀሐይ ቅድሚያ፣ ዝርፊያና ድብደባ ለሚፈጽሙ አካላት መሸሸጊያ ሆኗል አሉ፡፡ የውጭ ዜጎችም ለዝርፊያና ለድብደባ እየተዳረጉ እንደሚገኙ በመግለጽ መንግሥት ለተፈጠረው ችግር ዕልባት እንዲሰጥ ጠየቁ፡፡

ላለፉት አምስት ዓመታት በአካባቢው ያላግባብ የተቀመጡ የቆሻሻ ማጠራቀሚዎችና የፕላስቲክ ጠርሙሶች ክምችት የሚገኝበት ይህ አካባቢ፣ ለአደይ አበባ ስታዲየም ማስፋፊያ እንዲሆን ተብሎ ለተነሺዎች ካሳ ተከፍሎበት ፕሮጀክቱ ይተገበራል ተብሎ ሲጠበቅ በመዘግየቱ ምክንያት አካባቢው በበርካታ ሰፋሪዎች ከመከበቡ በተጨማሪ፣ መንግሥት ባደራጃቸው የደረቅ ቆሻሻ አንሺዎች ጭምር የተፈጠረው ሠፈራ ለወንጀለኞች መበራከት ሰበብ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

በዚህ ሳቢያ በተደጋጋሚ ጊዜ የዝርፊያ ወንጀሎች መስፋፋታቸውና በእኩለ ቀን ሳይቀር መኪና የሚዘርፉ፣ በአካባቢው የሚተላለፉ እግረኞችን ቦርሳና ሞባይል መንትፈው ወደ ታጠረው ሜዳ የሚሮጡ የበርካታ ዘራፊዎች መኖሪያ እየሆነ መምጣቱን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ ለበርካታ ጊዜያት ክፍለ ከተማና ወረዳ ጽሕፈት ቤት ተመላልሰው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉ ይናገራሉ፡፡ ከክፍለ ከተማው አስተዳደር ጋር የተጻጻፏቸው በርካታ ደብዳቤዎችም ይህንኑ ያሳያሉ፡፡ የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ አዘል የማስፈጸሚያ ደብዳቤዎችንና ትዕዛዞችን ለወረዳው ቢያስተላልፍም፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለነዋሪዎቹ ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጥ የክፍለ ከተማውን መመርያዎች ተግባራዊ አለማድረጉ በነዋሪዎች አቤት ተብሎበታል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በነዋሪዎቹ የደኅንነት ካሜራዎች የተቀረፁ ምሥሎች በጠራራ ፀሐይ ዝርፊያና ንጥቂያ ሲፈጸም ያሳያሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ከዚሁ አካባቢ መኪና ሰርቀው ሲሄዱ የሚያሳይ ምሥል በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ተለቆ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ ሪፖርተር ከሰሞኑ ዝርፊያና ንጥቂያ ሲፈጽሙ የሚያሳዩ ምሥሎች ደርሰውታል፡፡ ይህንኑ በማስመልከት ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጉዳዩን አሳውቆ ማጣራት እንደሚደረግበት ተገልጾለታል፡፡

ነዋሪዎቹን በመወከል ከክፍለ ከተማውና ከወረዳው ኃላፊዎች ጋር በርካታ ምልልሶችን ሲያደርጉ የቆዩት አቶ አብርሃም ወርቅነህና 21 ጎረቤቶቻቸው፣ የወረዳ 03 አስተዳደር አዲስ ኃላፊ ከተሾመለት ወዲህ ላለፉት አምስት ዓመታት ሲመላለስ የቆየው ጥያቄ በቅርቡ ምላሽ ማግኘት እንደጀመረ ጠቅሰዋል፡፡ ይሁን እንጁ አሁንም ትልቅ እልባት የሚሻ ጉዳይ መኖሩን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በስታዲየሙ አጥር ሥር የተከማቸ የቆሻሻ ገንዳ እንዲነሳ መደረጉን፣ በመጪው ሳምንትም ሸራ ወጥረውና ዛኒጋባ ቤቶችን ቀልሰው የሚኖሩ ሰዎችን በማስነሳት አካባቢውን ሰላማዊ የማድረግ እንቅስቃሴ እንደሚጀመር በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 03 ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ዓለማየሁ ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡ ከነዋሪዎቹ የተውጣጣ ኮሚቴ በችግሩ ላይ በመነጋገር እልባት እንዲደረግለት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በስታዲየሙ ዙሪያ የሠፈሩ አካላትን ከማስነሳት ባሻገር ባዶ ቦታውን ለከተማ እርሻ ሥራ ለማዋል መታቀዱን አቶ ዋሱሁን ገልጸው፣ ለዚህ ሥራ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች ተመልምለው እንደሚሠማሩ ጠቁመዋል፡፡

ስፖርት ኮሚሽን በበኩሉ ለአደይ አበባ ስታዲየም የምዕራፍ ሁለት ግንባታ ባጠረው ሰፊ ይዞታው ውስጥ የሚገኙ፣ ‹‹ሕገወጥ ግንባታዎችና የሃይማኖት ተቋማት እንዲነሱልን በተደጋጋሚ መጠየቃችን ይታወሳል፤›› በማለት ለቦሌ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ጽፏል፡፡ ‹‹በቀን በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የዘረፋ ወንጀል የሚፈጽሙ ግለሰቦችም መሸሸጊያቸውን በእነዚሁ በሕገወጥ መንገድ የተገነቡ የፕላስቲክ ቤቶች ውስጥ መሆኑን ነዋሪዎች ጠቅሰው ለኮሚሽኑ በደብዳቤ ቅሬታ አቅርበዋል፤›› በማለት ኮሚሽኑ ለክፍለ ከተማው አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ ስፖርት ፋሲሊቲ ዳይሬክቶሬት የጻፈው ደብዳቤ አያይዞ ያነሳው ነጥብ፣ በስታዲየሙ ይዞታ ዙሪያ የተገነቡት የፕላስቲክ ቤቶች አለመነሳታቸው በተቋራጩ በሚቀርብ ተጨማሪ ክፍያና በፕሮጀክቱ አፈጻጸም ላይ በሚደርሰው መጓተት ሳቢያ መንግሥትን ለተጨማሪ ወጪ ከመዳረግ አልፎ፣ ነዋሪዎቹን ለአደጋ መጣሉ ስለተረጋገጠ ሕገወጥ ሰፋሪዎቹን በማንሳት ፕሮጀክቱ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ድጋፍ እንዲያደርግ ክፍለ ከተማውን ጠይቋል፡፡  

ለብሔራዊ ስታዲየሙ ግንባታ ከተመደበው የ2.5 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ የግንባታ ወጪ ውስጥ ለአነስተኛ የእግር ኳስ ሜዳዎች፣ የመሮጫ ትራክ (መም) እንዲሁም 3,500 መኪኖችን የሚያስተናገድ ፓርክ የሚገነባበት ይህ አካባቢ ለአደጋ ጊዜ የሚያገለግል የሔሊኮፕተር ማረፊያን ጨምሮ የመረብ ኳስ፣ የቅርጫት ኳስ፣ የባድሜንተን፣ የሜዳ ቴኒስ፣ የቴአትር አዳራሾች፣ ሰው ሠራሽ ሐይቆችና ደረጃቸውን የጠበቁ መፀዳጃ ቤቶች ግንባታን ያካትታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...