Thursday, June 20, 2024

ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር ቁርስ እየበሉ ነው]

 • ብዪ እንጂ፡፡
 • ተወኝ ባክህ፡፡
 • ምን ሆነሻል?
 • እ…
 • በጠዋቱ ፈዘሻል እኮ፡፡
 • ለምን አልፈዝ?
 • ምን ተገኘ?
 • እ…
 • በሽታውን ፈርተሽ ነው?
 • ምነው እሱን ባደረገልኝ?
 • ታዲያ ምንድነው?
 • ይኼን ጋዜጣ አንብበኸዋል፡፡
 • እነዚህ እኮ ወሬኞች ናቸው፡፡
 • ምን እንደተደገሰልህ መቼ ገባህ?
 • ማለት?
 • አንብበው እስቲ?
 • አንቺ ለምን አትነግሪኝም?
 • ምኑን?
 • ያነበብሽውን ዜና ነዋ፡፡
 • ስማ ጉድ ልንሠራ ነው ባክህ?
 • እንዴት?
 • ያው ሰሞኑን ያወጣችሁት መመርያ ጉድ ሊያፈላ ይችላል፡፡
 • የቱ መመርያ?
 • ይኼ የገንዘብ እንቅስቃሴን የሚገድበው ነዋ፡፡
 • ምን አስፈራሽ?
 • ለምን አልፈራ?
 • ቤታችን በቂ ካዝናዎች አሉን አይደል እንዴ?
 • ችግሩ እኮ እሱ ነው፡፡
 • ማለት?
 • ሊጀመር ነዋ፡፡
 • ምን?
 • የቤት ለቤት አሰሳ፡፡
 • እ…
 • ስማ ጎል ሊከቱን ነው፡፡
 • እስቲ መድኃኒቴን ስጪኝ፡፡
 • ተረጋጋ እስቲ፡፡
 • እንዴት ነው የምረጋጋው?
 • ተረጋጋ አልኩህ፡፡
 • ልንታሰር እንችላለን እያልሽኝ እንዴት ልረጋጋ?
 • መፍትሔ መፈለግ ነው የሚያዋጣው፡፡
 • ምንድነው መፍትሔው?
 • እኔ እንጃ፡፡
 • ቆይ ለምን ለሰው አንሰጠውም?
 • ይኼን ሁሉ ገንዘብ በዚህ ወቅት ማን ይቀበልሃል?
 • እሺ እናቃጥለው፡፡
 • ይኼን ሁሉ ገንዘብ ስናቃጥል የእሳት አደጋ መከላከያ ራሱ ማጥፋት አይችልም፡፡
 • ካልሆነ ይቀበራ፡፡
 • ምን?
 • ምነው?
 • ከእሱ አንድ ነገር እመርጣለሁ፡፡
 • ምን?
 • ራሴው ብቀበር!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ዲፕሎማት ስልክ ደወለላቸው]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰላም ነኝ፡፡
 • ተጠፋፋን እኮ፡፡
 • ምን ታደርገዋለህ ይኼ በሽታ ከብዙ ነገር አስተጓጎለን እኮ?
 • የእሱንስ ነገር አያንሱት፡፡
 • ምን አዲስ ነገር አለ?
 • ደንግጬ እኮነው የደወልኩልዎት፡፡
 • ምን አስደነገጠህ?
 • ሪፖርቱ ነዋ፡፡
 • የኮሮናው ነው?
 • ኧረ የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ፡፡
 • ተወው ባክህ፡፡
 • እንዴት?
 • እነሱ እኮ ልማዳቸው ነው፡፡
 • ማለት?
 • ያው እኛን ካልከሰሱ ማን ፈንድ ይሰጣቸዋል ብለህ ነው?
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • ስልህ ፈንድ ለማግኘት ያው መንግሥትን መክሰስ አለባቸዋ፡፡
 • ስለዚህ ሪፖርቱ ውሸት ነው እያሉኝ ነው?
 • ምን ጥያቄ አለው?
 • ክቡር ሚኒስትር በሪፖርቱ ላይ የተጠቀሱት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሉም እያሉ ነው?
 • እ…
 • አብዛኞቹ እኮ እኔ ራሴ የማውቃቸው ናቸው፡፡
 • ማለት ይኼን ያህል ማካበድ ምን አስፈለገ ብዬ ነው፡፡
 • የመብት ጥሰቶቹ  የተካበዱ ስለሆኑ ነዋ፡፡
 • ፈረንጆች ስትባሉ የእኛን ጥቁሮች ነገሮች ማካበድ ትወዳላችሁ፡፡
 • ምን ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኼው የእናንተ አገር እየታመሰ አይደል እንዴ?
 • እ…
 • የሥልጣኔ ቁንጮ ላይ ነን ብላችሁ እንደ አውሬ እየተበላላችሁ አይደል እንዴ?
 • ክቡር ሚኒስትር ያ ሌላ ይኼ ሌላ፡፡
 • መጀመርያ የራሳችሁ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ ሳታዩ የእኛን ስንጥር ለማውጣት አትሞክሩዋ፡፡
 • ተው እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምነው?
 • እናንተ ዓይን ውስጥ ያለው ስንጥር ነው ግንድ?
 • ስማ እኛ በብዙ  ነገር ተለውጠናል፡፡
 • እኔም ተለውጣችኋል ብዬ አምን ነበር፡፡
 • አሁን ታዲያ ምን ተፈጠረ?
 • ሥራችሁና ወሬያችሁ ለየቅል ነዋ፡፡
 • ለማንኛውም አሁን እናንተ መናገር አትችሉም፡፡
 • ለምን?
 • አያምርባችሁማ፡፡
 • እንዴት ሆኖ?
 • እየተመፃደቃችሁ ስለሆነ…
 • እ…
 • ጥሪ አንቀበልም!

[ለክቡር ሚኒስትሩ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ስልክ ደወለላቸው]

 • ያሳፍራል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ?
 • የወጣባችሁ ሪፖርት ነዋ፡፡
 • ምኑ ነው የሚያሳፍረው?
 • አበላሸባችሁ እኮ፡፡
 • ምኑን?
 • ነጠላ ዜማችሁን ነዋ፡፡
 • የምን ነጠላ ዜማ ነው?
 • ይኼ ለውጥ ምናምን የሚለውን ነዋ፡፡
 • እ…
 • ተለውጠናል ምናምን የምትለውን ጨዋታ ከዚህ በኋላ ታቆሟታላችሁ፡፡
 • ለምን ሲባል?
 • ያው በአሮጌ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ ነዋ የገባው፡፡
 • እ…
 • ለነገሩ ዘፋኙም አዲስ ንጉሥ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ ብሏል አይደል፡፡
 • እንግዲህ እናንተም ይኼን ነጠላ ዜማ ይዛችሁ አላዝኑ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ምን ተሰማችሁ ግን?
 • በምኑ?
 • በሪፖርቱ ነዋ፡፡
 • እነሱ የለመዱት እኮ መንግሥትን መተቸት ነው፡፡
 • እሱማ ሥራቸው ነው፡፡
 • የአንድ ወገን ሪፖርት ብቻ እኮ ነው፡፡
 • የሌላ የማንን ሪፖርት ያካትቱ?
 • በተቃዋሚዎች ስንትና ስንት በደል ሲፈጸም አልነበር እንዴ?
 • ምን እያሉ ነው?
 • በተቃዋሚዎች ችግር በርካታ ሰዎች መሞታቸውን እናውቃለን፡፡
 • ወዴት? ወዴት?
 • ያ መቼ ሪፖርቱ ውስጥ ተካተተ?
 • እ…
 • ለዚያ እኮ ነው የውሸት ሪፖርት ነው የምንለው?
 • ተቃዋሚዎች በፈጠሩት ችግር ሰዎች መሞታቸውን እናንተ እርግጠኞች ናችሁ?
 • ምን ይኼ ሁሉም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ አይደል እንዴ?
 • ታዲያ ለምን ዝም አላችሁ?
 • እንዴት?
 • ማለቴ ችግሩን የፈጠሩትን ተቃዋሚዎች ለምን ተጠያቂ አላደረጋችኋቸውም ነበር?
 • እ…
 • ምነው አፍዎ ተሳሰረ?
 • ኧረ አልተሳሰረም፡፡
 • ለማንኛውም የሚሻለው አንድ ነገር ነው፡፡
 • ምን?
 • መዋጥ፡፡
 • ምኑን?
 • ሒሱን!

[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]

 • እሳቱ እንዴት ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የምን እሳት?
 • ሰሞኑን የተጣዳችሁበት ነዋ፡፡
 • ምን አዲስ ነገር መጣ ብለህ ነው?
 • ይኸው በዓለም አቀፍ መድረክ እየተዋረዳችሁ ነው፡፡
 • ማን አዋረደን?
 • ከዚህ በላይ ምን ትሆኑ?
 • እንዴት?
 • እንግዲህ እነሱ እንደ ሸለሟችሁ ሁሉ ሲያዋርዱም እንዲህ ነው፡፡
 • ይኼ የተለመደ ሪፖርት ነው፡፡
 • እናንተ ተለውጠናል ብላችሁ አይደል እንዴ አገር የተረከባችሁት?
 • ምን አጓደልን ታዲያ?
 • እኛ ላይ በፊት ከሚያወጡት ሪፖርት ቢበስ እንጂ የተሻለ አይደለም እኮ አሁን ያወጡት፡፡
 • ምን ይጠበስ ታዲያ?
 • ለማንኛውም አንጀታችን ቅቤ ጠጥቷል፡፡
 • አረቄ እንጂ ቅቤ ከየት አምጥታችሁ ነው የምትጠጡት?
 • ቀድሞውን እንደማትዘልቁ ገብቶን ነበር፡፡
 • እስቲ እውነት በል?
 • ከእነሱ እኮ እኛ እንሻላችኋለን፡፡
 • ይቺ ጎንበስ ጎንበስ ዕቃ ለማንሳት አሉ፡፡
 • ማን እኛ አይነካካንም?
 • እንዴት?
 • ለማንም አጎንብሰን አናውቅም፡፡
 • ሊሆን ይችላል፣ እኛ ግን አንድ ነገር አድርገናችኋል፡፡
 • ምን?
 • አንበርክከናችኋል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት ሐዘን ለመድረስ ጎረቤት ተገኝተው ለቀስተኛው በሙሉ የሚያወራው ነገር አልገባ ብሏቸው ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ባለቤታቸውን ስለጉዳዩ እየጠየቁ ነው] 

ጎረቤታችን ሐዘን ለመድረስ ብሄድ ለቀስተኛው በሙሉ በሹክሹክታ ያወራል። ግን የሚያወሩት ነገር ሊገባኝ አልቻለም። ምንድነው የሚያወሩት? እኔ ምን አውቄ? እንዴት? የሚያወሩትን ምንም አልተሰማሽም? እኔ እንድሰማ የፈለጉ አይመስልም ግን ... ግን...

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት የሚታወጁ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ማለቴ ነው። ምን ታወጀ? አንዴ ከዕዳ ወደ ምንዳ አላችሁ፡፡ እሺ? የእሱን ውጤት እየጠበቅን ሳለ ደግሞ... እ...? ኢትዮጵያ ታምርት...

[ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን በተጀመረው አገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ስለተላለፉ መልዕክቶች በተመለከተ ከባለቤታቸው ጋር እያወጉ ነው] 

እኔ ምልህ? እ... አንቺ የምትይው? አለቃህ በምክክር መድረኩ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት አደመጥክ? አዎ፡፡ የሚገርም እኮ ነው አልተገረምክም? ምኑ ነው የሚያስገርመው? ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ምከሩና አምጡ ብለው የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ...