Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኮሮና መዛመት አሳሳቢ ያደረገው የዋጋ ንረት

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ የኮሮና ወረርሽኝ አስደንጋጭ በሆነ ፍጥነት እየተዛመተ ይገኛል፡፡ ከበሽታው መከሰት ማግሥት ጀምሮ ሲወሰዱ በነበሩ ዕርምጃዎች ሳቢያ የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እየተገደቡ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ገደቦች በምርቶች አቅርቦትና ዋጋ ላይ ጫና ከማሳረፋቸውም ባሻገር የዋጋ ንረት እያስከተሉ ይገኛሉ፡፡

ቀድሞውን ሲንር የሰነበተው የሸቀጦች ዋጋ፣ ኮሮና ሲጨመርበት እየተጋጋመ መጥቷል፡፡ ከበቆሎ ጀምሮ በመሠረታዊ ለምግብ ፍጆታነት በሚውሉና ምግብ ነክ ባልሆኑ   ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ መንግሥትን የሕግ ማስከበር ዕርምጃ እንዲወስድ ቢያስገድደውም የታሰበውን ያህል የዋጋ መረጋጋት አልታየም፡፡ በአሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩ የንግድ መደብሮችን በማሸግ፣ የበርካታ ነጋዴዎችን ፈቃድ በመሰረዝና በማገድ ጭምር የተወሰደው ዕርምጃ፣ በምርት አቅርቦትም ሆነ በዋጋ ላይ ያመጣው ለውጥ እምብዛም ነው፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፣ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ቴሌቪዥን የቀጥታ ውይይት ላይ ተገኝተው ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንደታየውም ከቀረቡላቸው በርካታ ጥያቄዎች መካከል ምርቶች እንደ ልብ ማግኘት እንዳልተቻለ፣ ሲገኙም ዋጋቸው ከፍተኛ ጭማሪ እንደታየበት የሚጠቁም ነበር፡፡ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት እንዲደርሳቸው በኮታ የተደለደለላቸው የሸቀጥ መጠን እንደማይደርሳቸው፣ የደረሳቸው ማኅበራትም ለሸማቾች ከማድረስ ይልቅ በጎን ለነጋዴዎች እንደሚያከፋፍሉ የሚጠቅሱ ቅሬታዎች ለሚኒስትሩ ቀርበውላቸዋል፡፡

የሚያዝያ ወር አጠቃላይ አገር አቀፍ ተንከባላይ የዋጋ ግሽበት 23 በመቶ እንዳስመዘገበ ታይቷል፡፡ ይህ ጭማሪም ካለፉት ስምንት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛው እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ የዋጋ ግሽበት ውስጥ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ ከ19 በመቶ በላይ ሲያስመዘገብ፣ የእህልና የዳቦ ዋጋ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ በ31.2 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን፣ የመንግሥትን አኃዞች መነሻ በማድረግ የተለያዩ ተቋማት ያወጧቸው ትንታኔዎች ያሳያሉ፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ያወጣው ትንታኔም ካለፈው ዓመት እንዲሁም ካለፉት አምስት ዓመታት አማካይ ዋጋ አኳያ ሲነፃፀር፣ በሚያዝያ ወር የታየው የምግብ ዋጋ ጭማሪ በተለይም በአገዳ ብርዕና ጥራጥሬ ሰብሎች ላይ የታየው ለውጥ ከፍተኛ እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡ ለአብነት ያህልም የጤፍ ዋጋ ከ52 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በእህል ችርቻሮ መሸጫዎችና በወፍጮ ቤቶች አካባቢ የአንድ ኩንታል አንደኛ ጤፍ ዋጋው ከ4,000 እስከ 4,500 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡

በሁለት ወራት ውስጥ ብቻ የ500 ብር ጭማሪ እንደታየበት በአዲስ አበባ አካባቢዎች የሚታየው የዋጋ ለውጥ ይጠቁማል፡፡ ቀይ ጤፍ ከ3,000 ብር በታች በኩንታል ሲሸጥ ቆይቶ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ደረጃው ከ3,800 እስከ 3,900 ብር በኩንታል እየተሸጠ ይገኛል፡፡

በበቆሎ በመከተል ሁለተኛው ዋና የምግብ ሰብል የሆነው ጤፍ ከታኅሳስ ወር እስከ መጋቢት ባለው ጊዜ በኪሎ 37 ብር ሲሸጥ እንደቆየ፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም አጥንቷል፡፡  ከወር እስከ ወር የዘጠኝ በመቶ ጭማሪ ሲያሳይ እንደመጣም አጣቅሷል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከነበረው አማካይ የጤፍ ዋጋ አኳያ፣ በአሁኑ ወቅት የተመዘገበው ጭማሪ ወደ 93 በመቶ አሻቅቧል፡፡ ለዋጋው ጭማሪ የምርቱ አቅርቦት እጥረት እንዲሁም የደላሎች የገበያ ዋጋን ሆነ ብለው ማዛባት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የዓለም ምግብ ድርጅት ትዝብቱን አስፍሯል፡፡

ከነዋሪዎች እንደሚገለጸው፣ በሌሎች ሰብሎችም ላይ የጎላ የዋጋ ጭማሪ እየታየ ነው፡፡ የአጃ ቂንጬ፣ ቦሎቄና መሰል የምግብ እህሎች ላይ በቀናትና በሳምንታት ልዩነት የሚታየው የዋጋ ለውጥ እንዳስመረራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ለአብነት የአጃ ቂንጬ በኩንታል ከ800 እስከ 850 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ጭማሪውም በኩንታል እስከ 300 ብር አሻቅቧል፡፡ በተለምዶ አባ ጮማ የተሰኘው የቦሎቄ ዓይነት በኩንታል እስከ 600 ብር ሲሸጥ ቢቆይም፣ በተለያዩ የገበያ ማዕከላት የወቅቱ ዋጋው 850 ብር ድረስ ጭማሪ ይታይበታል፡፡ ለበርካቶች እንቆቅልሽ የሆነው የሰሞንኛው የሽንኩርት ዋጋ ጭማሪ ነው፡፡ በኪሎ እስከ 32 ብር ድረስ እየተሸጠ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለሚኒስትሩም ይህ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡

የምርት እጥረት እንዳይፈጠር መንግሥት በተለይም በአዲስ አበባ በቂ ክምችት በመያዝ፣ ለኅብረት ሥራ ማኅበራት እያዳረሰ እንደሚገኝ አቶ መላኩ አብራርተዋል፡፡ ይህ ይባል እንጂ፣ በተለይ በጤፍ የችርቻሮ ሽያጭ ላይ ካለፈው ታኅሳስ ወር ጀምሮ የታየው ከፍተኛ ጭማሪ በሚያዝያ ወር ብሶበት መገኘቱን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስፍሯል፡፡ በተለይም እንደ በቆሎና ማሽላ ባሉት ሰብሎች ላይ የታው የዋጋ ጭማሪ ከምርት አቅርቦት እጥረት ጋር በተያያዘ ምክንያት እንደተፈጠረ፣ የአቅርቦት መስተጓጎሉም በእንቅስቃሴ ላይ በተጣለው ገደብ ሳቢያ እንደተከሰተ ተቋሙ በትንታኔው አስፍሯል፡፡

እንዲህ ያሉ የዋጋ ለውጦች ግን በቋሚ የምግብ ሰብሎች ብቻ ላይ አልተወሰኑም፡፡ ለምሳሌ በፍራፍሬዎች ላይ የ25 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ሲከሰት፣ በአትክልት ምርቶች ላይ የ24 በመቶ፣ በሥጋ ላይ የ32 በመቶ፣ በዘይትና ቅቤ ላይ የ12 በመቶ እንዲሁም በወተት ላይ የ13 በመቶ የዋጋ ጭማሪ መመዝገቡ፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቅኝት ካካሄደባቸው የገበያ ሥፍራዎች በመነሳት ያወጣው ትንታኔ ያሳያል፡፡ በሚያዝያ ወር በጠቅላላው በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ተንከባላይ የምግብ ዋጋ ንረት መታየቱ፣ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ቤተሰቦችን ለከፋ የምግብ ዋስትና አደጋ እንደሚዳርጋቸው አሳይቷል፡፡ 

የዋጋ ጭማሪዎቹ የሚታዩት በምግብ ሰብሎች፣ አትክትልትና ፍራፍሬዎች ላይ ብቻም ሳይሆን፣ የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት በሚረዱ የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችም ላይ ነው፡፡ እንደ ሳኒታይዘርና አልኮል ባሉ ምርቶች የፋብሪካ ዋጋና የችርቻሮ ዋጋ ከዕጥፍ በላይ ልዩነት ይታይበታል፡፡ አንድ ሊትር አልኮል በ50 ብር ገደማ የሚያከፋፍሉ ፋብሪካዎች ቢኖሩም፣ ገበያው ላይ ከ135 እስከ 140 ብር ይጠራበታል፡፡ የመድኃኒት መደብሮችም በዚህ ዋጋ ሲሸጡ ይታያል፡፡ ቴክኒካል አልኮል የሚባለውንና ለሳኒታይዘር አምራቾች ከመንግሥት የሚቀርበው ምርት ላይ መጠነኛ እሴት ጨምረው የሚያቀርቡ ፋብሪካዎች የሚሸጡበት ዋጋ ግነት እንደሚታይበት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ ማስተካከያ ሊደረግ ስለሚችልበት አግባብ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች