የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በፖለቲካ ውይይቶች፣ በሕግ ክርክሮች፣ በትምህርታዊ ጥናቶችና ዲስኩሮች የትኩረትና የስህበት ማዕከል ሆኖ ቆይቷል፡፡ የአገሪቱ አራተኛው ሕገ መንግሥት ሆኖ በ1987 ዓ.ም. የፀደቀውና እስካሁን ድረስ በሥራ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት ከትልሙ፣ ከዓላማው፣ ከግቡና ከዕሳቤው አንስቶ እስከ ይዘቱ በርካት አከራካሪ ጉዳዮችን ያስተናገደና እያስተናገደ የሚገኝ ሰነድ ነው፡፡ በአሥራ አንድ ምዕራፎች ተከፍሎ በ106 አንቀጾች የተሸበበው ሕገ መንግሥት በኢትዮጵያ የብሔር ተኮር ፌዴራሊዝምን ያስተዋወቀና አገሪቱን በዚሁ አግባብ ቅርፅ ያስያዘ ነው፡፡ የመንግሥትን ሥልጣን፣ የሕዝቦችን መብቶችና ተጓዳኝ ድንጋጌዎችን የያዘ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ይኼ የፖለቲካና የሕግ ሰነድ ሁሉንም እኩል የማያግባባ፣ የወካይነት ጥያቄዎች የሚነሱበት፣ እንዲሁም በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ዝምታን ያበዛ ሕገ መንግሥት ነው ተብሎ በሰፊው የሚተች እንደሆነ በርካቶች የሚያስገነዝቡ ሲሆን፣ የሕገ መንግሥቱ ክፍተቶችና ዝምታዎች በአገሪቱ የሚከሰቱ ሁነቶችን ተከትለው መግለጻቸው አልቀረም፡፡ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ ቀደም ብሎ አንስቶ በተለይ በደቡብ ክልል የተነሱና እየተነሱ ያሉ የብሔሮችን የክልልነት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ያለው የሕግ ማዕቀፍ በቂ አለመሆኑን፣ ሕገ መንግሥቱም በቂ ድንጋጌዎችን የያዘ አለመሆኑን በመጥቀስ በርካታ ተመራማሪዎች የሰነዱን ክፍተቶችና ዝምታን ሲያሳዩ ቆይተዋል፡፡ አሁን ደግሞ በዓለም የጤና፣ የሰብዓዊና የደኅንነት ቀውስን እያስከተለ ያለውን የኮሮና ወረርሽኝ ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. የድምፅ መስጫው እንዲከናወን ቀን ቆርጦለት የነበረው ስድስተኛው አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ መከናወን እንደማይችል ከተገለጸበት ጊዜ አንስቶ፣ የፓርላማውና የአስፈጻሚው ሥልጣን ምርጫ ሳይደረግ ሲቀር እንዴት ይሆናል የሚለው ጥያቄ አዳዲስ ክርክሮችን እያሰማ ነው፡፡ በቫይረሱ ሥርጭት ሳቢያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀው የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ሰበብ የተስተጓጎለው ስድስተኛ ምርጫ ባለመደረጉ የፓርላማውና የአስፈጻሚው አካል የሥልጣን ዘመን ካበቃ በኋላ የሥልጣን ክፍተት እንዳይኖር፣ እንዲሁም ያልተመረጠ መንግሥት እንዳይመራና ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ እንዳይፈጠር ሲል አራት አማራጮችን አቅርቦ ነበር፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የመጨረሻው ምርጫ ከተደረገ በአምስተኛው ዓመት የማይደረገው ምርጫ የሚፈጥረውን ክፍተት ያሳልፈኛል ሲል መንግሥት ያቀረባቸው አማራጮች ሕገ መንግሥት ማሻሻል፣ ፓርላማውን በአንቀጽ 60 መሠረት መበተን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማራዘም፣ እንዲሁም የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ የሚሉት ናቸው፡፡ መንግሥት የመጨረሻውን መርጦ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ መርቷል፡፡ ጉባዔውም ለውሳኔ ሐሳብ ይረዱኛል ያላቸውን ሦስት የውይይት መድረኮችን አድርጎ ውሳኔውን በቅርቡ እንደሚያሳውቅ ተናግሯል፡፡ ይኼንንና የተለያዩ የሕገ መንግሥት ጉዳዮችን በማስመልከት ብሩክ አብዱ በመቱ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህርና ተመራማሪ ከሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን ካሳሁን ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- የሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊነት ጉዳዮች ብዙ የተባለላቸው ቢሆንም፣ እነዚህን ሁለት ጽንሰ ሐሳቦች በመበየን ብንጀምር፡፡ ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊነት ማለት ምን ማለት ነው?
ሙሉቀን (ረዳት ፕሮፌሰር)፡- ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊነት የሚባሉት የተለያዩ ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥት ሁሉን የሚያስማማ ትርጉም የለውም፡፡ ይሁንና የተለያዩ ሰዎች የሚሰጧቸው ትርጉሞች የጋራ የሆኑ ይዘቶች አሏቸው፡፡ ከእነዚህ አንዱ ሕገ መንግሥት የአንድ አገር መሠረታዊ ሕግ ነው የሚለው ነው፡፡ ከዚህ በዘለለ ሕገ መንግሥት የአንድን አገር የመንግሥታዊ አስተዳደርና ፖለቲካዊ ቅርፅ የሚይዝ ሰነድ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሕገ መንግሥት፣ የመንግሥት መዋቅር የሚገለጽበትና ተቋማቱ የሚቋቋሙበት ሰነድ ነው፡፡ በተጨማሪም የአንድ አገር ሉዓላዊ የበላይ ሥልጣን የማን ነው የሚለውም በሕገ መንግሥት የሚቀመጥ ነው፡፡ በንጉሣዊ ሥርዓት ሉዓላዊ ሥልጣን የንጉሥ ወይም የንግሥት ይሆናል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲሆን ደግሞ የሕዝብ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ሕገ መንግሥት ሲበየን እነዚህን ጉዳዮች ያካትታል፡፡ ሕገ መንግሥታዊነት ስንል ደግሞ አንድ አገር ውስጥ ሕገ መንግሥት መኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ ሕገ መንግሥቱ ተግባር ላይ መዋሉ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ሲቀረፅ ጀምሮ ሕዝቡ የተሳተፈበትና የተለያዩ ባለድርሻዎች አምነው የቀበሉት ሲሆን ነው፡፡ መንግሥትም በሕገ መነግሥቱ የተቀመጠውን ይፈጽማል፣ ሕዝቡ ደግሞ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ ሲሆን ሕገ መንግሥታዊነት አለ ለማለት እንችላለን፡፡ ለሕገ መንግሥታዊነት መስፈን ራሱን የቻለ ማሳያዎች አሉት፡፡ አንደኛው የመንግሥት ሥልጣን በሕግም ሆነ በፖለቲካ የተገደበ መሆኑ ሲሆን፣ መሠረታዊ የሆኑ መብቶችና በሕገ መንግሥቱ ተደንግገው ይተገበራሉ፡፡ ሌላው የመንግሥት ኃላፊዎች ለሚፈጽሙት ጥፋት ተጠያቂነት ያለባቸውና ሥራቸውም በግልጽነት መከናወን ያለበት መሆኑ ነው፡፡ ሌላው የሥልጣን ክፍፍል ነው፡፡ በሦስቱ የመንግሥት አካላት መካከል ፍፁም ባይሆንም፣ የሥልጣን ክፍፍሎች በግልጽ ይቀመጣሉ፡፡ ግን እነዚህ ከአንደኛው ወደ ሌላኛው የመንግሥት ሥርዓት ስንሄድ ይለያያሉ፡፡ ተቋማትን በሚመለከት ነፃና ገለልተኝነት እንዲኖርና በተለይ የሕግ ትርጓሜው ሁለቱን የመንግሥት አካላት የሚቆጣጠር መሆን አለበት፡፡ እነርሱ ሲሳሳቱ የሚያርምና የማስተካከያ ዕርምጃ የሚወስድ ከሆነ ሕገ መንግሥታዊነት አለ ማለት እንችላለን ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በሕገ መንግሥትና በሕገ መንግሥታዊነት ዙሪያ የኢትዮጵያ ልምድ ምን ይመስላል?
ሙሉቀን (ረዳት ፕሮፌሰር)፡- የኢትዮጵያን ልምድ በሦስት ከፍለን ልንመለከተው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው የንጉሣዊ ሥርዓት፣ ሁለተኛው የወታደራዊ መንግሥት ሲሆን፣ ሦስተኛው ደግሞ አሁን ያለው የፌዴራል መንግሥት ሥርዓት ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የተጻፈ ሕገ መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሠራው በንጉሡ ሥርዓት እ.ኤ.አ. በ1931 ነው፡፡ ከዚያ አስቀድሞ የነበረውን ታሪካዊ ዳራ ስንመለከት፣ የሰሜንና የደቡብ ኢትዮጵያ ክፍሎችን ማስተዋልና መቃኘት ያስፈልጋል፡፡ በደቡብ ያለውን ታሪክ ስናይ ከአንዱ ወደ ሌላው በሥነ ቃል ሲተላለፍ የቆየ ሲሆን፣ በሰሜን ደግሞ በብዛት የነገሥታቱ ሥፍራ ስለሆነ የተጻፈና ንጉሣዊ ሥርዓትን የሚከተሉ ናቸው፡፡ በደቡብ የነበረው አስተዳደራዊ ሥርዓት ደግሞ ንጉሣዊና ዴሞክራሲያዊ መልኮችን የተላበሰ ነበር፡፡ እንደ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ከሚወሰዱት ውስጥ አንደኛው የገዳ ሥርዓት በኦሮሞ፣ በሲዳማና በጌዴኦ ሕዝብ ሲተገበር የቆየ ነበር፡፡ ይኼ የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ የዴሞክራሲያዊ ተቋም ተብሎ ዕውቅና ያገኘ ነው፡፡ ሥልጣን በውርስ ሳይሆን የሚገኘው ከሕዝብ በሚመጣ ምርጫ ነው፡፡ ሥርዓቱ ከዘመናዊ ዴሞክራሲ አንፃር ስናየው ጉድለቶች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሥልጣን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ በሕዝብ መመረጥና የሥልጣን ገደብም ያለባቸው በመሆናቸው የሕገ መንግሥታዊነት ባህርያት አሉት፡፡ ይሁንና ይኼ ሥርዓት በውስጡ በተፈጠሩ ችግሮች ሊዳከም ችሏል፡፡ ለአብነትም በገዳ ሥርዓት ውስጥ የንጉሣዊ ሥርዓት ሊያብብ በመቻሉ ሊዳከም ችሏል፡፡ የጅማ አባ ጅፋርንና የወለጋ ቱምሳ ሞረዳን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከውጭ የነበሩ ተፅዕኖዎችን ስንመለከት ደግሞ የሃይማኖትና የግዛት መስፋፋት ዘመቻዎች ብሎም የባሪያ ንግዶች ይጠቀሳሉ፡፡
ወደ ንጉሣዊ ሥርዓት ስንመጣ ብዙው ነገር በጉልበት የሚሆን ነው፡፡ ሁለተኛው ሥልጣን ከፈጣሪ የተሰጠና በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ብቻ የሚተላለፍ ነው ይባላል፡፡ ስለዚህ አሁን ካሉ የዴሞክራሲ መርሆዎች አንፃር በንጉሣዊ ሥርዓት ሕገ መንግሥታዊነት አለ ለማለት አንችልም፡፡ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ1931 ጀምሮ ሲቆጠር አራት ሕገ መንግሥቶች ነበሯት፡፡ ሕገ መንግሥት መኖሩ ጥሩ ነው ጅማሮው፡፡ ነገር ግን ከሕገ መንግሥታዊነት አንፃር ስናየው ችግር ያለበት ጅማሮ ነው፡፡ ከምዕራባውያን ጋር ብናነፅፅርና የአሜሪካን የነፃነት አዋጅና የእንግሊዝን ያልተጻፈ ሕገ መንግሥት ብንመለከት፣ ሕዝብ ታግሎ የመንግሥትን ተጠያቂነት ለማምጣት የሠራቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያን የመጀመሪያ ሕገ መንግሥት ብናየው የሕዝብ ውጤት ሳይሆን፣ ንጉሡ ለሕዝቡ እንደ ስጦታ ያበረከቱት ነው፡፡ ያ ማለት ደግሞ ሥልጣናቸውን መደበኛ ለማድረግና ካሁን ቀደም ያልተጻፈ ሥልጣናቸውን ወደ ተጻፈ ሕገ መንግሥት ለመለወጥ ነው እንጂ የሕዝቡ ውጤት አልነበረም፡፡ መንግሥትንም የመቆጣጠር ትልምም አልነበረውም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተቀባይነቷን ለመገንባትና መልካም ምሥል እንዲኖራት በማለም እኛም እንደ ሌሎች አገሮች ሕገ መንግሥት አለን ለማለት የተሠራ ነው፡፡ ስለዚህ ከጅማሮው የተፈጠረው ችግር ሕገ መንግሥታዊነት እንዳይኖር አድርጓል፡፡ ይኼ መሆኑ ደግሞ ከዛ በኋላ የመጡ ሕገ መንግሥቶች ሁሉ በሕዝብ ተሳትፎ ሳይሆን ሥልጣን ላይ በወጡ ኃይሎች ተፅዕኖ ሥር እንዲወድቁ አድርጓል፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ያሻሻሉትን እ.ኤ.አ. በ1951 የወጣው ሕገ መንግሥትንም ሆነ የደርግ ሕገ መንግሥት ብንመለከት ሥልጣን ላይ የነበሩ ሰዎችን ፍላጎት ነው እንጂ የሚያንፀባርቁት፡፡ የደርግ ሕገ መንግሥት በሕዝበ ውሳኔ ቢፀድቅም ይዘቱ ግን ያንን ሕዝባዊነት አያሳይም፡፡ ያ ማለት ግን አንዳንድ ይዘቶቹ የሕዝብን ፍላጎት አያንፀባርቁም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ከተሳትፎ አንፃር ግድፈቶች ይታያሉ፡፡ እዚህ ግድፈቶች መኖራቸው ሕገ መንግሥት ቢኖርም፣ ሕገ መንግሥታዊነት እንዳያድግ ተፅዕኖ አድርጓል፡፡ ስለዚህም ሕገ መንግሥቶች ቢኖሩም፣ ሕገ መንግሥታዊነትን ለማምጣት አልቻሉም፡፡
ሪፖርተር፡- ሕገ መንግሥት በይዘቱም በአሠራር ሒደቱም እጅግ አከራካሪና አጨቃጫቂ የሚሆንበት ምክንያት ምንድነው? በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች ውስጥ?
ሙሉቀን (ረዳት ፕሮፌሰር)፡- ሕገ መንግሥት ስንል ሰነዱን ማለታችን ሲሆን፣ ሕገ መንግሥታዊነት ማለት ደግሞ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠው ነገር መተግበሩ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሕገ መንግሥት መኖር ለሕገ መንግሥታዊነት መኖር ዋስትና አይሆንም፡፡ አንድ የኬንያ ፕሮፌሰር እንደሚሉት፣ የአፍሪካ አገሮች አንዱ መለያቸው ሕገ መንግሥት ያለ ሕገ መንግሥታዊነት ያለባቸው መሆኑ ነው፡፡ ይህ ማለት ሕገ መንግሥት አለ፣ ግን ሕገ መንግሥታዊነት የለም ማለት ነው፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ሕገ መንግሥት ሳይኖራቸው ሕገ መንግሥታዊነት ያለባቸው አገሮች አሉ፡፡ በእንግሊዝ የተጻፈ ሕገ መንግሥት የለም፣ ግን ሕገ መንግሥታዊነት አለ፡፡ ስለዚህ የሕገ መንግሥት ሰነድ መኖር ለሕገ መንግሥታዊነት መኖር ማረጋገጫ አይሆንም፡፡ ሕገ መንግሥት ስለሌለም ሕገ መንግሥታዊነት የለም ማለት አይሆንም፡፡ የዓለም ሕገ መንግሥቶች በሦስት ተከፍለው መታየት ይችላሉ፡፡ አንደኛው የይስሙላ (Nominal) የሚባለው ነው፡፡ ይኼ ሕገ መንግሥት ሥልጣን ላይ ያለውን ኃይል ዕውቅና ለመስጠት የሚወጣ ነው፡፡ ብዙም ለሕዝቡ የሚጨምርለት ነገር የለም፡፡ ሁለተኛው የታይታ (Facade) ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ ሰነዱ ላይ የሚቀመጡ ነገሮች ትክክልና የሚያስደስቱ ሆነው ሳለ፣ በተግባር ላይ አይውሉም፡፡ ሦስተኛው እውነተኛ (Real) ሕገ መንግሥት የሚባለው ሲሆን፣ በሕገ መንግሥቱ ትክክል የሆኑ ጉዳዮች የሚቀመጡና በተግባር ላይም ይውላሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የተለያዩ አገሮችን ማየት የምንችል ሲሆን፣ ሁሉንም ሕገ መንግሥቶች ስናይ ሕገ መንግሥት የአገር የሕጎች ሁሉ የበላይ ሆኖ ነው የሚቀመጠው፡፡ ሕገ መንግሥት የሕጎች የበላይ ቢሆንም ግን የሥልጣን የበላይነት የሚታይበት ሁኔታም አለ፡፡
በዚህ አግባብ ሕገ መንግሥቶች ለምንድነው አከራካሪ የሚሆኑት ብለን ስንጠይቅ፣ አንደኛው ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች ተፅዕኖ ያደርጉበታል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሕገ መንግሥት በባህርይው የፖለቲካና የሕግ ሰነድ ስለሆነ፣ የፖለቲካ ሥልጣን ከእሱ ስለሚመነጭ በተፈጥሮው አከራካሪ ነው ማለት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የሕገ መንግሥት ሥሪት በሥልጣን ላይ ባሉ ቡድኖች ተፅዕኖ ሥር ስለሚወድቅ ሕገ መንግሥቱ አሳታፊ አይሆንም፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሥልጣን ሲፎካከሩ እንደ አንድ መወዳደሪያ ይዘው የሚወጡት ማኒፌስቶ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል የሚል ነው፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካን ሕገ መንግሥት ማሻሻል ለምርጫ መፎካከሪያነት አይቀርብም፡፡ በአፍሪካ አገሮች ግን አንዱ የፖለቲካ አጀንዳ ሆኖ የሚቀርበው የሕገ መንግሥት ይዘትን ማሻሻል ነው፡፡ ይኼም የሚያሳየው ሕገ መንግሥቱ ሲሠራ ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ መግባባት ይፈጠራል ባይባልም፣ ሰፊ መግባባት ስላልተፈጠረና በገዥዎች ተፅዕኖ ሥር እንደነበረ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከሌላ ሕግ በተለየ የአንድን አገር ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ስለሚወስን ሰፊ ተቀባይነት ማግኘት ስለሚኖርበትና ያ ተቀባይነት ስለሌለ የጭቅጭቅ መነሻ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሕዝብን ማሳተፍ ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝብን ፍላጎት የሚያስጠብቁ ጉዳዮችን ማካተትንም ይጠይቃል፡፡ ሕዝብ ሳይሳተፍባቸው ትውልዶችን የተሻገሩ የሌሎች አገሮችን ሕገ መንግሥቶች ማየት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የጀርመንን ሕገ መንግሥት የተባበሩት ኃይሎች (Allied Powers) ናቸው የሠሩት፡፡ ነገር ግን እስከ ዛሬ የተወሰነ ማሻሻያ በማድረግ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ በሥሪቱ ጀርመኖች አልተሳተፉም፡፡ ግን ይዘቱ ሕዙን የሚወክል ከሆነ በርካታ ትውልዶችንም ሁሉ ሊሻገር ይችላል ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ስንመለከት አራት ሕገ መንግሥቶች የነበሩ ሲሆን፣ አንዱ ኃይል ወደ ሥልጣን ሲመጣ የራሱን ሕገ መንግሥት ይዞ ይመጣል፡፡ ይህ ደግሞ ሕገ መንግሥት በገዥዎች ተፅዕኖ ሥር እንደሚወድቅ እንጂ፣ በሕዝቦች ፍላጎት እንደማይሠራ ማሳያ ነው፡፡ ሕገ መንግሥት የሕዝቡ ውጤት ከሆነ የተለያዩ ትውልዶችን ሊሻገር ይችላል፡ አንድ መንግሥት ስለተወገደ ከእሱ ጋር የሚወገድ አይደለም፡፡ በግለሰቦችም ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት አንስቶ አራት ሕገ መንግሥቶችን አስተናግዳለች፡፡ ከላይ ከጠቀስናቸው ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊነት ገለጻዎች አንፃር፣ አሁን አገሪቱ የምትጠቀምበት ሕገ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ከማስከበርና ሕገ መንግሥታዊነትን ከማስፈን አንፃር እንዴት ይገመገማል?
ሙሉቀን (ረዳት ፕሮፌሰር)፡- የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አሁን አገሪቱ እየተጠቀመችበት የሚገኝ ሲሆን፣ አተገባበሩ ካለፉት 20 በላይ ዓመታት ያየነው ነው፡፡ ከይዘት አንፃር ካየነው ሲዘጋጅ በዲዛይኑ የተለያዩ አካላት የተሳተፉበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚያው ልክ ግን ሥልጣን ላይ የነበረው የገዥው ኢሕአዴግ ተፅዕኖ እንዳለበት ይታመናል፡፡ ከአጠቃላይ መሠረታዊ ትልም ስናየው ከዚያ በፊት የነበሩ አካሄዶችን የመቀየርና ሲነሱ የቆዩ ጥያቄዎችን የማስተናገድ አዝማሚያዎች አሉት፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም. በፊት ማንነትን መሠረት ያደረጉ የነፃነት ታጋዮች ነበሩ፡፡ ይኼ ደግሞ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፍልስፍና ጥያቄዎች ውስጥ ማንነት አንዱ መሆኑን ያሳያል በማለት የሚከራከሩ አሉ፡፡ ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ ከዚያ አንፃር የተቀረፀ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ነገር ግን ጥያቄው ትክክል ነው ቢባልም፣ በሕገ መንግሥቱ የተሰጡ ምላሾች ግድፈት አለባቸው ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡ ለምሳሌ የብሔር ፌዴራሊዝም ወይም የብዝኃ ብሔር ማንነትን የተከተለ መዋቅር እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ጥያቄው በዚህ መልኩ ነበር መመለስ የነበረበት ወይስ ሌላ አማራጮች ነበሩ የሚለው አከራካሪ ነው፡፡ አሁንም የሚታይ ክርክር ነው፡፡ በተወሰነ ደረጃ ግን ኢትዮጵያ ያልተማከለ የሥልጣን ክፍፍልንና ፌዴራሊዝምን መከተሏ፣ የተለያዩ አስተሳሰቦችን ለማስተናገድና ለማቀፍ ያግዛል የሚሉ አሉ፡፡ ነገር ግን ምን ዓይነት ፌዴራሊዝም ነበር መከተል የነበረባት የሚለው አከራካሪ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
የሕግ የበላይነትን ከማስከበር አንፃር ደግሞ ስናየው ሦስት ማዕዘን ጫፎች አሉት፡፡ አንደኛው ሥልጣን፣ ሁለተኛው የሕዝብ መብት፣ ሦስተኛው ደግሞ ሕግ ናቸው፡፡ ሥልጣን የመንግሥትን ፍላጎት የሚያፀባርቅ፣ መብት የሕዝብን ፍላጎት የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በመሀል ደግሞ ሚዛን የሚስይዛቸው ሕግ ነው፡፡ ሥልጣን ከመብቶች በላይ ሆኖ ገደብ ካልተበጀለት ሕግን ለፖለቲካ ዓላማ መጠቀምን ያስከትላል፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ መብቶች ገደብ ካልተበጀላቸው ሥርዓት አልበኝነትን ያመጣሉ፡፡ ስለዚህ የሕግ የበላይነት ሁለቱንም ሚዛን ለማስጠበቅ የሚያስችል ነው፡፡ የመንግሥት ሥልጣን መገደብ አለበት፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ለግለሰቦች ሲባል መገደብ አለበት፡፡ የግለሰቦች መብት ደግሞ ለሕዝብ ፍላጎት ሲባል ይገደባል፡፡ እነዚህ አንድ ላይ ሲሆኑ የሕግ የበላይነት ይኖራል፡፡ ከዚህ ረገድ ሲታይ ግን ተቋማትም የራሳቸው አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ በአንድ ወቅት የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እንዳሉት፣ ለአፍሪካ የሚያስፈልጓት ጠንካራ ግለሰቦች ሳይሆኑ ጠንካራ ተቋማት ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት ፍርድ ቤቶች፣ ሚዲያ ወይም የሲቪል ማኅበረሰቦች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ተቋማቱ ሲኖሩ የሕግ የበላይነት የመጎልበት አቅም ይኖረዋል፡፡ ጠንካራ ተቋሟት ሲኖሩ በግለሰብ ላይ የሚመሠረቱ ሳይሆኑ፣ ግለሰቦችን ወደ ሥልጣን ለማምጣት መሣሪያ ይሆናሉ፡፡ ግለሰቦች በመጡ ቁጥር የሚቀይሯቸው አይሆኑም፡፡
ሪፖርተር፡ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ካለፉት ሕገ መንግሥቶች በአንፃሩ ዴሞክራሲያዊ፣ የሕዝቦችን ሉዓላዊነት የሚያንፀባርቅና ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶችን ያከበረ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ይሁንና በተለያዩ ሁነቶች ሳቢያ የሚገለጡ ክፍተቶችንና ዝምታዎችን እየተመለከቱ፣ ሕገ መንግሥቱ ባዶ ሰነድ ነው በማለት የሚተቹ አሉ፡፡ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ግን ይኼንን ለማለት የሚያስችል ሰነድ ነው?
ሙሉቀን (ረዳት ፕሮፌሰር)፡- እኔ የትኛውንም ሕገ መንግሥት ባዶ ነው ማለት አንችልም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሆነም አልሆነ፡፡ የትኛውም ሕገ መንግሥት ጉድለት ወይም ክፍተት ሊኖርበት ይችላል፡፡ ምክንያቱም አንድ አገር ያለ መንግሥት እንዳትኖር በማለም የሚዘጋጅ ነውና፡፡ ለዚህም የሥልጣን ምንጭ ማን እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ በየአገሮች ቢለያይም መብቶችን ይገልጻል፣ የመንግሥትንም የሥልጣን ገደብ ያስቀምጣል፡፡ ነገር ግን ክፍተቶች ሊኖሩት ይችላል፡፡ ነገር ግን አገሮች የተጻፈ ሕገ መንግሥት ቢኖራቸውም፣ ሁሉንም ነገር ጽፈዋል ማለት አይቻልም፡፡ በዓለማችን ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ ሕገ መንግሥት ነው የሚባለው የሕንድ ሕገ መንግሥት ሳይቀር ብዙ ክፍተቶች አሉት፡፡ ስለዚህ እነዚህ ክፍተቶች ለምንድነው የሚፈጠሩት የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ አንደኛው ምክንያት ሕገ መንግሥት በተፈጥሮው ጠቅላላ ነው፡፡ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ድንጋጌ ያስቀምጥና ሌሎችን ጉዳዮች ደግሞ በዚያ ማዕቀፍ እንዲሠሩ በማለት ይተዋቸዋል፡፡ ሁለተኛው በሕገ መንግሥቱ ሥሪት ጊዜ የማይገመቱ ነገሮች፣ ምናልባትም ከሰው ልጅ አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ሕገ መንግሥቶች ሲሠሩ ከዚያ በፊት የነበሩ ሁነቶች ላይ ነው ትኩረት የሚደረገው፡፡ ጊዜ ይዟቸው የሚመጡ ጉዳዮች ላይገመቱ ይችላሉ፡፡ ለአብነትም የአሜሪካን ሕገ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ1987 ሲረቀቅ የኑክሌር፣ የህዋ ሳይንስ፣ እንዲሁም አሁን ያሉት የማኅበራዊ ትስስር ገጾች አልነበሩም፡፡ ስለዚህም በዚያ ሕገ መንግሥት ውስጥ አይገኙምና ያልተገመቱ ጉዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ሕገ መንግሥቱን የሚያረቅቁ ግለሰቦች ጉዳዮችን ጠቃሚ አይደሉም ብለው ሊያልፏቸው ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ አሁን በኢትዮጵያ ያጋጠመውን የሕገ መንግሥት ቀውስ ብንመለከት፣ ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ ተነስቶ የነበረ ጉዳይ ለውይይት ቀርቦ ብዙም አስፈላጊ አይደለም ተብሎ ስለተተወ ነው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ የመንግሥታት ፍላጎት ካለባቸውም ሆን ተብለውም ሊተው ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ሌላ ጥያቄ ሊያስከትሉ ይችላሉ በሚል፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ምክንያቶች ክፍተቶች ወይም ዝምታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ካነሱት አይቀር አሁን አገሪቱ የገባችበትን የሕገ መንግሥት ቀውስ እንመልከት፡፡ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን እያወጡ ያሉ የተለያዩ ክስተቶች ናቸው፡፡ አንደኛውና የቅርቡ ክስተት የዓለም አቀፍ የጤናና የደኅንነት ሥጋት የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በማድረግ፣ እንደማይካሄድ በተገለጸው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሳቢያ የተስተዋለው ነው፡፡ መንግሥት በምርጫው መራዘም ሳቢያ ሊከተል የሚችለውን የሥልጣን ክፍተት እንዳይፈጠር ለማድረግ፣ እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ቀውሱን ለማለፍ አራት አማራጮችን አቅርቦ የራሱን ውሳኔ አሳልፋል፡፡ እነዚህ አማራጮች ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል፣ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ማድረግ፣ ፓርላማውን መበተን፣ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማራዘም የሚሉት ናቸው፡፡ መንግሥት የሕገ መንግሥት ትርጉምን ቢመርጥም እነዚህን የመንግሥት አማራጮች አግባብ ናቸው ይላሉ?
ሙሉቀን (ረዳት ፕሮፌሰር)፡- ሕገ መንግሥታዊ ቀውሶችና የሕገ መንግሥት ክፍተቶች በኢትዮጵያ ብቻ የሚከሰቱ እንዳልሆኑና በሌሎችም አገሮች የሚታዩ እንደሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ክፍተቶችም ሁነት ላይ ተመርኩዘው የሚታዩ ናቸው፡፡ ክፍተቶቹ መታየታቻው እንደ ግድፈት ሳይሆን ሕገ መንግሥቱ እየዳበረ እንዳለ ማሳያ ናቸው፡፡ አንድ ሕገ መንግሥት ከተረቀቀ በኋላ እንዲህ ያሉ ክፍተቶች እየተፈጠሩ ሲሄዱ፣ መፍትሔውም በዚያው ልክ ይዳብራል፡፡ ለምሳሌ አሁን ያለው የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት የፀደቀው ከኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በኋላ እ.ኤ.አ. በ1996 ነው፡፡ ነገር ግን ከዚያ በኋላ በኢትዮጵያ አንድም መደበኛ የሆነ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሳይደረግ፣ የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት 17 ጊዜ ተሸሽሏል፡፡ ነገር ግን በእኛ አገር አንድ ፓርቲ ብቻ ሲያስተዳድር ስለነበር በፓርቲው መስመር ብቻ ነበር የሚያልፈው፡፡ ማሻሻያ የሚጠይቁ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በአንድ ፓርቲ ውስጥ የተለያዩ ሐሳቦች የማስተናገድ ዕድሉ ጠባብ ስለሚሆን፣ ሕገ መንግሥታዊነታቸው ተነስቶ መከራከር አይኖርም፡፡ ሌሎች አገሮችን ስንመለከት ደግሞ፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሳይደረግ በትርጉም የተፈቱ ጉዳዮችን እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ በጀርመን ያልተወለዱ ልጆች (የጽንስ) የመኖር መብትን በሚመለከት የነበረ ክርክር፣ በሕገ መንግሥት ትርጉም ነው የተፈታው፡፡ በተመሳሳይ በካናዳ የኪዩቤክ ግዛት የመገንጠል ጥያቄን በተመለከተ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠ ነገር ባለመኖሩ፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ነው የተፈታው፡፡ ስለዚህ አንድ ነገር በሕገ መንግሥት ውስጥ ተጽፎ ስላልተገኘ መፍትሔ የለውም ማለት አይደለም፡፡ ዋናው ለሕገ መንግሥታዊ ችግር ሕገ መንግሥታዊ መፍትሔ ብሎ መነሳቱ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ያው ሕገ መንግሥቱ በራሱ መፍትሔ ባይሰጥም አጠቃላይ መርሆዎችን ስለሚያስቀምጥ በዚያ መልኩ ሊፈታ ይችላል፡፡
አሁን በአገራችን ያለውን ጉዳይ ስንመለከት ካሁን ቀደም የነበሩን ልምዶች ምን ያሳያሉ ማለትና መለስ ብሎ መቃኘት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በአራቱም ሕገ መንግሥቶች አሁን እንዳለው ዓይነት ችግር ቢፈጠር ምን መደረግ እንዳለበት ምን ይላሉ በማለት ተመልክቼ ነበር፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አሁን ያለንበትን ሁኔታ ይገልጸዋል የምለውን ያገኘሁት የደርግን ሕገ መንግሥት ነው፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 69 አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ ላይ ወይም በጦርነት ላይ ከነበረች በወቅቱ ሕግ አውጪ የነበረው ብሔራዊ ሸንጎ የሥልጣን ጊዜውን ሊያራዝም ይችላል የሚል ድንጋጌ ይዟል፡፡ የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት ያረቀቁ ሰዎች ይኼንን እንደ አንድ ትምህርት መውሰድ ይችሉ ነበር፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት ሥራዎች ያለፉ ልምዶችን የመቀመር ባህርይ ስላላቸው፡፡ ለምሳሌ የመንግሥትና የሃይማኖት መለየት ከደርግ ሕገ መንግሥት የተወሰደ ነው፡፡ የደርግ ሕገ መንግሥት ለዚህም ችግር መፍትሔ አስቀምጦ ነበር፡፡ አሁን ባለንበት የፌዴራል ሥርዓት ደግሞ በአገር ደረጃና በክልል ደረጃ ባይሆንም፣ የወረዳና የቀበሌን ምርጫ በሚመለከት የኦሮሚያና የአማራ ክልል ሕገ መንግሥቶች የሚሉት አላቸው፡፡ ሁለቱ ሕገ መንግሥቶች የቀበሌና የወረዳ ምርጫ ዘመን ሊራዘም እንደሚችልና ይኼም በክልሎቹ ምክር ቤቶች እንደሚወሰን ያስቀምጣሉ፡፡ ነገር ግን የክልል ምክር ቤቶችን ምርጫ በሚመለከት ሕገ መንግሥቶቹ ዝምታን መርጠዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች የሚጠቁሙት ነገር አለ፡፡ አሁን በመንግሥት የቀረቡት አማራጮች ሕገ መንግሥቱ ለቀውሱ መፍትሔ የሚሆን ድንጋጌን ባለመያዙ ምክንያት፣ ክፉ ምርጫ (The necessary evil) ውስጥ ነው የገባነው፡፡ ይኼ ማለት ሁሉም አማራጮች ጥሩ አይደሉም፣ ግን አሁን ያለንበትን ጊዜ ያሻግሩን ዘንድ አስፈላጊ ናቸው፡፡ አሁን ምርጫ እንዲራዘም ምክንያት የሆነው ግን ኮቪድ-19 ብቻ አይደለም፡፡ አገሪቱ የነበረችበት የፖለቲካ ሽግግር ምርጫውን በራሱ ከግንቦት ወደ ነሐሴ በማሸጋገር አዘግይቶታል፡፡ ይኼ ራሱ ተፅዕኖ አለው፡፡ ካሁን ቀደም እንደነበረው ሁሉ ግንቦት ላይ ቢደረግ ኖሮ በርካታ ክፍተቶች ይቃለሉ ነበር፡፡ እናም አሁን ካለው ዕውነታ አንፃር ሁሉም አማራጮች ተመራጭ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ከክፉዎች የትኛው ነው ያነሰው ክፉ የሚለውን መምረጥ ነው የሚሆነው፡፡
መንግሥት የሕገ መንግሥት ትርጓሜን መርጦ መፍትሔ ሽቷል፡፡ በዚህ ውስጥም ዋናው የፌዴራል ምክር ቤት (ፓርላማ) የሥልጣን ጊዜን ይመለከታል፡፡ ይሁንና የሕገ መንግሥት ትርጉም በመመረጡ ሳቢያ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው ወይስ ምን ዓይነት ውሳኔ ነው የሚወሰነው የሚለው ሊያስቸግር ይችላል፡፡ እንደ እኔ አመለካከት ምርጫው መተላለፉ ልክ ነው፣ የሚያከራክርም ጉዳይ ያለ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ምርጫው በመተላለፉ የሕገ መንግሥት ትርጉም በራሱ የመጨረሻ ውሳኔ ነው? ወይስ ሌላ አካል ነው የሚልክ የሚለው በራሱ አከራካሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ትርጉም የሚሰጠው አካል (የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔውና የፌዴሬሽን ምክር ቤት) በራሱ የሚወስን ከሆነ፣ ሕገ መንግሥቱን እያሻሻለ ነው ማለት ነው፡፡ ወይም ወደ ፓርላማው የሚልክ ከሆነና ፓርላማው በራሱ ጉዳይ ላይ ዳኝነት የሚሰጥ ከሆነ በራሱ ችግር ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዱ አከራካሪ ጉዳይ አሁን የቀረበው የሕገ መንግሥት ትርጉም፣ ረቂቅ ትርጉም (Abstract review) ነው ወይስ ምክረ ሐሳብ ነው የሚለው ነው፡፡ ረቂቅ ትርጉም በተለያዩ ጊዜያት ይጠየቃል፡፡ አንደኛው አንድ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳይ ተነስቶ በተከራካሪ ወገኖች የሚቀርብ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በፍርድ ቤቶች የማይታዩ የሥልጣን ክፍፍልንና ሌሎች የፖለቲካ ጉዳዮችን በተመለከተ በአዋጅ 798/2005 መሠረት ረቂቅ ትርጉም መጠየቅ የሚችሉት፣ የክልል ምክር ቤቶች ወይም አስፈጻሚ አካላት ናቸው፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ይወድቃል፡፡ መንግሥት ሲጠይቅ ግን ትርጉም ይሰጠው ከማለት በዘለለ የራሱን አቋም አላስቀመጠም፡፡ ከዚህ አንፃር ረቂቅ ትርጉም ከሆነ አስገዳጅነት ያለው ውሳኔ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክረ ሐሳብ ከሆነ ግን በሚያቀርቡት ሐሳብ ላይ በመመርኮዝ መንግሥት ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡ በዚህ ላይ ክፍተቶች አሉ፡፡ አንዳንዶች ምክረ ሐሳብ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ነገር ግን በዚህ ላይ መንግሥት የራሱን አቋም አስቀምጦ አይደለም ትርጉሙን የጠየቀው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ረቂቅ ትርጉም ከተባለ አስገዳጅ ሊሆን ይችላል፡፡ አጣሪ ጉባዔው ያካሄዳቸው አስተያየቶችን የመስማት ሒደቶችም እንደሚያመላክቱት ውሳኔው አስገዳጅ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ትርጉምን ከአራቱ አማራጮች መመረጡ ካለው እውነታ አንፃር ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ ተመራጭ ነው እላለሁ፡፡ ግን የትርጉም ውሳኔው ውጤት ነው ወይስ ወደ ውጤት የሚመራ ነው የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ ትርጉም ይሰጥበት መባሉ አንድ መፍትሔ ቢሆንም፣ በራሱ መጨረሻ ነው ወይስ ወደ ሌላ ያመራል የሚለው ያጠያይቃል፡፡
የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግም አንዱ አማራጭ ነበር፡፡ ነገር ግን ሰፋ ያለ ጊዜና ውይይትን ይፈልጋል፡፡ አንደኛ ከጊዜና ከወጪ አንፃር መንግሥት ያልመረጠው ይመስለኛል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደግሞ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ ምርጫውን ለማራዘም እንደማይቻልና ምርጫና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማይጣጣሙ በመሆናቸው ያልተመረጠ ይመስለኛል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መብቶችን ይገድባል፣ ምርጫ ደግሞ መብታችንን የምንጠቀምበት ነውና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ሆኖ መብቶችን ላስፈጽም ማለት ከተለያዩ ጫናዎች አንፃር አያስኬድም፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 60 መሠረት ፓርላማውን መበተን የሚባለው እኔ ለዚህ ዓላማና ሁኔታ የሚጠቅም አይመስለኝም፡፡ በአንቀጹ ድንጋጌ መሠረት ፓርላማ መበተን የሚቻለው አገሪቱን የሚያስተዳድር ጥምር መንግሥት መስማማት ካልቻለ ነው ወደዚያ የሚኬደው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ፓርላማ መበተን እንደሚቻል ቢደነግግም፣ ያልተስማሙት ፓርቲዎች በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ጥምር መንግሥት መመሥረት እንደሚችሉ በማስቀመጥ ነው ካልተቻለ እንዲበተንና በስድስት ወራት ውስጥ ምርጫ እንዲደረግ የሚለው፡፡ ነገር ግን አሁን ካለንበት ሁኔታ አንፃር እንደ አንድ መፍትሔ ቢቀርብም፣ አገሪቱ ካለችበት ሁኔታ ጋር የሚጣጣም አይመስለኝም፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ የሕገ መንግሥት ትርጉም ውጤቱ ማሻሻያ ቢሆንም ከሕገ መንግሥት ማሻሻያ ይመረጣል ይላሉ?
ሙሉቀን (ረዳት ፕሮፌሰር)፡- የክልሎች ሕገ መንግሥቶች በተለይም የኦሮሚያና የአማራ የወረዳና የቀበሌ ምክር ቤቶች ምርጫ በየአምስት ዓመታት ይካሄዳል ቢሉም፣ ከ1997 ምርጫ በኋላ በነበረው አመፅ ምክንያት ምርጫውን በጊዜው ማካሄድ ስላልተቻለ ምክር ቤቶቹ ሕገ መንግሥታቸውን አሻሽለዋል፡፡ አሁን ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ተገማችነት ያለውን መፍትሔ ሊሰጥ የሚችለው ማሻሻያ ነው፡፡ ትርጉም ግን ምን ዓይነት ውሳኔን ሊያስከትል እንደሚችል አይታወቅም፡፡ ይኼንን ችግር አስቀምጦ በተለየ ሁኔታ መፍትሔ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ነገር ግን ከማሻሻያ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን ለማለፍ ሲባል ወደ ትርጉም መሄድን መንግሥት የመረጠው ይመስለኛል፡፡
ሪፖርተር፡- በተወሰነ ደረጃ ቅድም ጠቀስ አድርገውታል፡፡ አሁን እየተኬደበት ያለው የሕገ መንግሥት ትርጉም ከውጤት አንፃር አስገዳጅነት ያለው ተፈጻሚነትን የሚያስከትል ከሆነ፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ እንደሆነ በማንሳት የሚከራከሩ አሉ፡፡ ስለዚህም ውጤቱ ማሻሻያ ከሆነ መንግሥት ለምን በቀጥታ ማሻሻያ አላደረገም የሚሉ አሉ፡፡ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ ይኼንን መሰል ውጤት ያስከትላል?
ሙሉቀን (ረዳት ፕሮፌሰር)፡- በአጠቃላይ ስናየው ሕገ መንግሥቱ ተሻሽሏል አልተሻሻለም ካልን፣ በመደበኛው አካሄድ ባይሆንም አሁንም ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡ ለመወሰን ነው እንጂ በሕገ መንግሥቱ መሠረት በየአምስት ዓመት መደረግ የነበረበት ምርጫ፣ በአምስት ዓመት ውስጥ እንደማይደረግ ታውቋል፡፡ መቼ እንደሚደረግ ባይታወቅም በአምስት ዓመት ውስጥ እንደማይደረግ ከታወቀ፣ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ተሻሽሏል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይኼኛው አስቸጋሪ የሚሆነው ፖለቲካዊ ይዘት ስላለው ነው እንጂ፣ ካሁን ቀደምም የነበሩ ተመሳሳይ ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በርካታ መደበኛ ያልሆኑ ማሻሻያዎች በርካታ ጊዜ ተካሂደዋል፡፡ ለምሳሌ የቅርብ ጊዜውን ብንመለከት የሕዝብና ቤቶች ቆጠራን ማንሳት እንችላለን፡፡ አጠቃላይ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በሕገ መንግሥቱ መሠረት በየአሥር ዓመቱ ነው መከናወን ያለበት፡፡ ያ ማለት ደግሞ በ1999 ዓ.ም. የተካሄደው በ2007 ዓ.ም. መካሄድ ነበረበት፡፡ ይሁንና በ2007 ዓ.ም. በፀጥታ ችግር ምክንያት አልተካሄደም፡፡ ባለፈው ዓመት ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአንድ ዓመት ሲራዘም የሕገ መንግሥታዊነት ጥያቄን ያነሳ አልነበረም፡፡ የፀጥታ ጉዳይ ተብሎ ነው የታለፈው፡፡ ያ ማለት መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሕገ መንግሥት ተሻሽሏል ማለት ነው ባይገለጽም፡፡ መደበኛውን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሒደት ተከትሎ አይደለም የተሻሻለው፡፡ የምርጫውንና የሕዝብና ቤቶች ቆጠራውን አንድ የሚያደርጋቸው በጊዜ አለመካሄዳቸው ነው፡፡ የሕገ መንግሥት ትርጉም ሒደቱ ውጤት ማሻሻያ ይሆናል የሚለው የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚሰጡት የትርጉም ውሳኔ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ውጤት ይኖረዋል ወይስ አይኖረውም የሚለው መቼ ምርጫው ይደረጋል ለማለት ነው እንጂ፣ ሕገ መንግሥቱ ቀድሞውኑ ምርጫው በጊዜው እንደማይደረግ ሲታወቅ ተሻሽሏል፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥት የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄውን ያቀረበለት የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ጉዳዩን ለመረዳትና ለመወሰን ያስችለኛል ያላቸውን ባለሙያዎች በመጥራት፣ ሐሳባቸውንና ትንታኔያቸውን ሲያዳምጥ አስተውለናል፡፡ እነዚህ በሦስት ዙር የተከናወኑ ስሚዎች (Hearings) ከአካታችነትና ከተፅዕኖ በፀዳ መንገድ መካሄዳቸውን በተመለከተ በርካቶች ወቀሳና ሥጋቶችን አቅርበዋል፡፡ በእርስዎ ግምገማ ውይይቶቹ ከእነዚህ ነጥቦች አንፃር እንዴት ይታያሉ?
ሙሉቀን (ረዳት ፕሮፌሰር)፡- አጠቃላይ ስናየው እንዳነሳኸው በሦስት መድረኮች የተካሄዱ ውይይቶች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከዚህ አንፃር ሕጉ ምን ይላል ከሚለው ነው መነሳት አለብን፡፡ ያንን በሚገዛው አዋጅ 798/2005 እንደተቀመጠው የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሲቀርብለት፣ ጉባዔው የባለሙያዎችን አስተያየት ሊጠይቅ ይችላል ይላል፡፡ በአዋጁ መሠረት በዚህ መንገድ መረጃዎችን ማሰባሰብ ግዴታ አይደለም፡፡ እንደ አማራጭና በጉባዔው ፍላጎት ላይ የሚመሠረት ተደርጎ ነው የተቀመጠው፡፡ እንዲሁም ስሚው ለሕዝብ እንዲታይ መደረጉ አስገዳጅ አይደለም፡፡ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች መደረጋቸውና ለሕዝብ ግልጽ መሆናቸው ሒደቱን ያዳብረዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ አካታችነቱን ስናየው ከተለያዩ አቅጣጫዎች አስተያየቶች እየቀረቡ ነበር፡፡ አንዳንዶች ከእነ አካቴው ትርጉም አያስፈልግም የሚሉት ነበሩ፡፡ ሌሎች ደግሞ ትርጉም ያስፈልጋልና ያስኬዳል የሚሉ ነበሩ፡፡ የቀረቡትን ሐሳብ ሰጪዎች ስንመለከት በብዛት በሕገ መንግሥት ትርጉም አስፈላጊነት ላይ የተስማሙ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ አንፃር የጉባዔው አባላት የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋል የሚለው ላይ የወሰኑና ምን ዓይነት ጉዳዮች አሉ የሚለውን ለመስማት የፈለጉ ይመሰለኛል፡፡ ነገር ግን የተለየ ሐሳብ ያላቸውና ትርጉም አያስፈልግም የሚሉ ሐሳቦች ሳይሰሙ የቀሩት፣ የጉባዔው ውሳኔ ስለሆነ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡
የጉባዔው ማቋቋሚያ አዋጅ ጉባዔው አስተያየት የሚቀበለው ከባለሙያዎች ነው ይላል፡፡ ያ ማለት ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሳተፍ አለባቸው ማለት አይደለም፡፡ ባለሙያ ሲባል ደግሞ ከተቋማት ወይም ከግለሰቦች ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለቱንም ወገኖች ያቀረበና ያከራከረ መድረክ አልነበረም፡፡ ትርጉም ያስኬዳል አያስኬድም በሚል የተደረጉ ክርክሮች የሉም፡፡ ነገር ግን ትርጉም እንዴት ያስኬደናል የሚለው ጥያቄ ላይ ነው ትኩረት የተደረገው፡፡ ከዚህ አንፃር ሌላውን ወገን አለማካተቱ የጉባዔው የራሱ ምርጫ ስለሆነ፣ ከሕጉ አንፃር ነው የተካሄደው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከተፅዕኖ የፀዳ ነው ወይ ለሚለው ደግሞ ውሳኔ መስጠት አይቻልም፡፡ ግን ይኼንንም ከሕግ ማዕቀፉ አንፃር ማየት ይቻላል፡፡ አንደኛ አሁን የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች በአንድ ፓርቲ ሥር ነው የሚገኙት፡፡ በእኛ አገር የሕገ መንግሥት ትርጉም ደግሞ ራሱን በቻለ ገለልተኛ ተቋም የሚከናወን አይደለም፡፡ እናም ተቋሙ በራሱ ፖለቲካዊ ተቋም በመሆኑ፣ ሒደቱ ሙሉ ለሙሉ ከተፅዕኖ ነፃ ላይሆን ይችላል፡፡ ጉባዔውን ስንመለከት አሥራ አንድ አባላት ያሉት ሲሆን፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ስምንቱ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ የተቀሩት ደግሞ ስድስቱ ሲመረጡ በፖለቲካ ተፅዕኖ የተመረጡ ናቸው ሊባል ይችላል፡፡ የጉባዔው ማቋቋሚያ አዋጅ በራሱ ስለገለልተኝነቱ የሚናገረው ምንም የለም፡፡ ተፅዕኖው ግን ተከስቷል ወይስ አልተከሰተም የሚለውን ለመመለስ አስቸጋሪ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ ከመድልዎ የፀዳ ከመሆን (Objectivity) አንፃር ሲታይ ደግሞ በስሚው ሒደት የተነሱ ጥያቄዎችን ማየት ግንዛቤ ሊሰጠን ይችላል፡፡ በብዛት አግባብነት ያላቸው ጥያቄዎች የተነሱ ቢሆንም፣ አግባብ ያልሆኑ ጥያቁዎችም ሲቀርቡ ነበር፡፡ ለምሳሌ የክልል ምክር ቤቶችን የሥልጣን ዘመን የሚመለከት ጥያቄ ተነስቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ለጉባዔው የቀረበው የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ግን ያንን የሚመለከት አይደለም፡፡ ጥያቄው የፌዴራል ምክር ቤትን (ፓርላማን) የሚመለከት ሆኖ ሳለ፣ የክልሎች ሥልጣን ምን ይሆናል የሚለው አከራካሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ይኼ ለጉባዔው የቀረበለት ጥያቄ አይደለም፡፡ ምናልባትም ከጭብጡ ወጣ ያለ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ፓርላማው ወደ ጉባዔው የትርጉም ጥያቄውን ሲልክ፣ ትርጉም የተጠየቀበት የሕገ መንግሥት ጥያቄ በራሱ ክፍተት አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ የተጠየቀው ጥያቄ አንደኛው የፓርላማውን የሥልጣን ዘመን የሚመለከት ነው፡፡ ከዚያ ጋር ተያይዘው ሊነሱ የሚችሉ ጉዳዮች ሲኖሩ፣ ሁለት ጉዳዮች ተያይዘው ሊተረጎሙ ይገባ ነበር፡፡ አንደኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በመሆናችንና አንዱ ምርጫው እንዲተላለፍ ምክንያት የሆነ ጉዳይ (አንቀጽ 93) ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የምርጫ ቦርድ ሥልጣን (አንቀጽ 102) ነው፡፡ እነዚህ በትርጉም ጥያቄው ውስጥ ተካትተው ሊቀርቡ ይገቡ ነበር፡፡ በጥያቄዎቹ ላይ እነዚህ ሐሳቦች ተንሸራሽረዋል፡፡ ግን መንግሥት ሲጠይቅ ፓርላማው ላይ ነው ትኩረት ያደረገው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ተካትተው ሰፋ ተደርጎ መታየት ነበረበት፡፡ በተጨማሪም በትርጉም ጥያቄው ሊነሳ ይገባው የነበረ ጥያቄ አንደኛው አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ናት፣ ሁለተኛው ደግሞ ያልተመረጠ መንግሥት የመቀጠል ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ስለዚህ ምርጫ የፖለቲካ መብት ጉዳይ በመሆኑ፣ በዚያው ልክ የሕግ አስፈጻሚና የሕግ አውጪ ተቋማት ሥልጣናቸው ያለቀ በመሆኑ፣ የሕግ ተርጓሚ ፍርድ ቤቶች ሚና ምን መሆን አለበት የሚለው ቢካተት ጥሩ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሕጋዊ የመንግሥት ተቋም ነው፣ ሁለተኛው ደግሞ ያልተመረጠና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ያለን መንግሥት የመቆጣጠር ሚናው ከፍ ሊል ይገባል፣ ከሌላው ጊዜ በተለየ፡፡ አሁን ስናየው ግን ፍርድ ቤቶች ተዘግተው ነው ያሉትና ዝግ መሆናቸው የግለሰብ ነፃነትን መንግሥት እንዲቆጣጠር አንዳንድ ክፍተቶች ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ የፍርድ ቤቶች ሁኔታ በዚሁ አግባብ መታየት ነበረበት፡፡ የፍርድ ቤቶች ሚና ከፍ ማለት የነበረበት በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ የግለሰቦችን መብትና የመንግሥትን ሥልጣን ሚዛን ከማስጠበቅ አንፃር ፍርድ ቤቶች፣ እንዲሁም ገለልተኛ ተቋማት አስፈላጊ ናቸው፡፡ እነዚህ እንዴት ሊጎለብቱ ይችላሉ የሚለው ከአስቸኳይ ጊዜ አንፃር መታየት ነበረበት፡፡
ሌላው ደግሞ መነሳት የነበረበትና ተረስቷል ብዬ የማስበው፣ ምርጫው ዘግይቶም ቢሆን ይካሄዳል፡፡ በመደበኛው አሠራር መስከረም መጨረሻ ላይ አዲስ የተመረጠ መንግሥት ሥራውን ይጀምራል፡፡ ነገር ግን በጥያቄው ላይ ያልተነሳውና በትርጉም ሒደቱ ላይ ሌላ ክፍተት ሊፈጥር የሚችለው ጉዳይ፣ የተራዘመው ምርጫ ከተካሄደ በኋላ መንግሥት በምን ያህል ጊዜ ነው ሥልጣኑን ማስተላለፍ ያለበት የሚለው ጉዳይም ሊታይ ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡ ምርጫው ላይ ነው ትኩረት እየተደረገ ያለው እንጂ አዲስ መንግሥት መቼ ነው የሚቋቋመው የሚለው ምላሽ ይፈልጋል፡፡ አሁን ያለው መንግሥት ሊቀጥልም ላይቀጥልም ይችላል፡፡ ካሁን ቀደም ከነበሩ ልምዶች አንፃር ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ሰላማዊ ላይሆን ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ ከምርጫ በኋላ የሚፈጠሩ ግጭቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ መንግሥት ያንን ተገን አድርጎ ሌላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያውጅ ከሆነ እንደ ድኅረ 1997 ምርጫ ዓይነት ችግር ቢፈጠር መቼ ነው መንግሥት ሥልጣኑን የሚያስረክበው የሚለው ክፍተትን ይፈጥራል፡፡ ለምሳሌ የክልልነት ጥያቄን በማቅረብ በሕዝበ ውሳኔ የወሰነው የሲዳማን የክልልነት ሒደት ብናየው፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ከሕዝበ ውሳኔ በኋላ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከክልሉ ጋር የሥልጣን ርክክብ ይደረጋል የሚለው የለም፡፡ ያ ደግሞ ለመንግሥት ፈቃድ ክፍት እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ እዚህም ተመሳሳይ ክፍተት ስላለ እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮችም ታይተው ቢሆን ብዬ አስባለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ጉባዔው ባለሙያዎችን ጠርቶ ማወያየት በሕግ የተሰጠውና በፈቃዱ ላይ የተመሠረተ መብት ነው፡፡ ይሁንና በጉዳዩ ላይ ባለሙያ ከሆኑ ሰዎች ውጪ በሕገ መንግሥቱ ማርቀቅና ማፅደቅ፣ እንዲሁም በረቂቁ ላይ ሕዝብን ማወያየት ላይ የተሳተፉ ግለሰቦችን በማቅረብ ውይይት አድርጓል፡፡ ይኼንን ከማድረግ ጀምሮ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሰዎች አስተያየት አለመስማቱ የአካታችነት ጥያቄ አያስነሳበትም?
ሙሉቀን (ረዳት ፕሮፌሰር)፡- በሕጉ የተቀመጠው የባለሙያዎችን አስተያየት መስማት የሚለው ለጉባዔው ብቻ የሚሠራ ሳይሆን፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አዋጅ ላይ እንደተቀመጠው ምክር ቤቱም ተመሳሳይ ሒደት ሊከተል ይችላል፡፡ ባለሙያዎች ሲባል ደግሞ ሕጉ ላይ ትርጉም አልተሰጠውምና እንደ አግባቡ ሊወሰን ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር ሕገ መንግሥቱን ያረቀቁት ግለሰቦች ባለሙያ ናቸው ወይስ አይደሉም የሚለው ብዙም አከራካሪ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ሕገ መንግሥቱን ሲያረቁ ባለሙያ ናቸው ተብሎ ነው የገቡት፡፡ ምንም እንኳን ባለሙያዎቹ የተመረጡበት አካሄድ ጥያቄ ሊነሳበት የሚችል ቢሆንም፣ እኔ ስለታሪኩ ብዙ ባላውቅም በሒደቱ እንዲሳተፉ የተደረጉት ባለሙያ ናቸው በሚል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እንዲሁም አሁን የተፈጠረውን ክፍተት በተመለከተ ሕገ መንግሥቱን ስላረቀቁ ከሌሎች የተሻለ ያውቃሉ ተብሎ ነው የሚወሰደው፡፡ ምናልባትም ሌሎቹን አለማሳተፉ የገልተኛነት ክፍተት አይፈጥርም ወይ ለሚለው፣ አንድ ውሳኔ ሲሰጥ ገለልተኝነት የሚታየው ከሁለት ጉዳዮች አንፃር ነው፡፡ አንደኛው የሚወሰነው ውሳኔ ይዘት ሲሆን፣ ሌላው ሌሎች ያንን ተቋም እንዴት ይመለከቱታል የሚል ነው፡፡ የውሳኔው ይዘት ገና ባይታወቅም በሒደቱ ላይ አንዳንድ ጥያቄዎችን የሚያነሱ አሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ እየተነሳ የነበረው ጉዳይ መንግሥት አራቱን አማራጮች ሲያዘጋጅ የተሳተፉ ሰዎች፣ በዚህም ተሳትፈዋል የሚል ወቀሳ ነው፡፡ እሱን ግን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ምናልባትም እንደዚያ ከሆነ ይኼ አንድ ክፍተት ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም እዚያ ላይ እንደ ባለሙያ ቀርበው በዚህኛው መድረክ ደግሞ ተከራካሪ የሚሆኑ ከሆነ፣ በሁለቱ ቦታ ላይ መገኘታቸው ገለልተኝነታቸውን አጠያያቂ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ባለሙያዎች ሲባል ገለልተኛ የሆኑ፣ የሚሰጡት ሐሳብ በሙያቸው ላይ የተመሠረተና ከሁለቱም ተከራካሪ ወገኖች ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ነው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እንደሚባለው በሁለቱም ሥራዎች የተሳተፉ ካሉ እንደ አንድ ክፍተት ሊነሳ ይችላል፡፡ ሌሎች ቡድኖች መሳተፍ ነበረባቸው የሚለው ይዘቱን ለማዳበርና ሚዛናዊ የሆነ ውሳኔ ለመስጠት ራሱን የቻለ ጥቅም ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ነገር ግን ተቋሙን የሚያስገድደው አግባብ እስከሌለ ድረስ ለዚህም ብቻ ሳይሆን፣ ለሌሎችም ጉዳዮች ተግባራዊ ስለሚሆን ሕጉ ላይ ቢስተካከል ለወደፊት እንደዚህ ዓይነት ክርክሮች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የተለዩ ሐሳቦች ቢመጡ የሚዳብሩበት ዕድል ይኖራል፡፡ ስለዚህ የተለዩ ሐሳቦች ቢካተቱ ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ባይካተቱ ጉዳቱ ምንድነው ለሚለው፣ አንደኛው የተሰሙት ላይ ጥርጣሬ ሊያድር ይችላል፡፡ ምክንያቱም መንግሥትም ማሰብ ያለበት፣ ሌላ አስተሳሰብ ያላቸው በዚህ ጊዜ እንዴት ነው የሚስተናገዱት የሚለው ቢታሰብበት ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- የሕገ መንግሥት ክፍተቶች ሁነቶችን ተከትለው ነውና ራሳቸውን የሚገልጡት፣ ይዘገያል እንጂ ወደ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማምራታቸው የማይቀር ይሆናል፡፡ አሁን መንግሥት በምርጫው ተቀባይነትን ካገኘ በኋላ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ ወደዚያ ይገባል የሚሉም አሉ፡፡ እርስዎም በቅርቡ ባሳተሙት ጥናት እንዳመለከቱት፣ የክልልነት ጥያቄዎች የሚነሱበትና የሚመለሱበት አግባብ ጭምር በርካታ ክፍተቶች ያሉበት ነው፡፡ እነዚህን ክፍተቶች እንዴት ነው ወደ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ሲገባ ማስተናገድና መሙላት የሚቻለው?
ሙሉቀን (ረዳት ፕሮፌሰር)፡- በአጠቃላይ ስናይ አንድ ሕገ መንግሥት ሲዘጋጅ የተለያዩ ትውልዶችን ያስተዳድራል ተብሎ ነው የሚወጣው፡፡ እናም ለእነዚህ ትውልዶች ጠቃሚ ሆኖ እንዲቀጥል ሁለት ጥቅም ላይ የሚውሉ አካሄዶች አሉ፡፡ አንደኛው የሕገ መንግሥት ትርጉም ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አስቸጋሪ ሊሆን የሚችለው ወደ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሲገባ፣ በራሱ አንድ የሕገ መንግሥቱ ክፍተት ማሳያ ሁነት ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን ወደ ተግባር ስላልገባን ነው እንጂ፣ ማሻሻያ ማድረጉ በራሱ በርካታ ክፍተቶች ያሉበት ነው፡፡ ሕገ መንግሥት ሲሻሻል እሱም የተለያዩ መነሻዎች አሉት፡፡ የማስጀመር፣ የማከራከርና የማፅደቅ ሒደቶች ናቸው፡፡
ነገር ግን የእኛ ሕገ መንግሥት እነዚህን ጉዳዮች የሌላ አገር ሕገ መንግሥቶች እንዳስቀመጡት ለያይቶና አፍታትቶ አላስቀመጠም፡፡ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማን ያስጀምራል ለሚለው ሕገ መንግሥቱ ምንም አይልም፡፡ ሕገ መንግሥቱ በቀረበው ማሻሻያ ላይ ፓርላማው ወይም የክልል ምክር ቤቶች ወስነው ወደ ክርክር መግባት ነው የተደነገገው እንጂ፣ ማን ነው ማቅረብ የሚችለው የሚል ድንጋጌ በግልጽ አያስቀምጥም፡፡ ፓርቲዎች ናቸው? ግለሰቦች ማቅረብ ይችላሉ? ወይስ ተቋማት ናቸው? የሚለውን በግልጽ አላስቀመጠም፡፡ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ስለማድረግ የሚደነግገው አንቀጽ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጥያቄን ስለማቅረብ የሚል ርዕስ ቢኖረውም፣ ውስጡ ስንገባ ግን የቀረበውን ጥያቄ ስለማፅደቅ ነው የሚያወራው፡፡ ወደ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ የሚገባው የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት በማለም ነው፡፡ ነገር ግን ከምርጫ በኋላ መንግሥት ወደ ማሻሻያ እገባለሁ ሲል፣ ከሕገ መንግሥት ማሻሻያ በላይ ነው የሚሆነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ሲባል የተወሰኑ አንቀጾችን መቀየር ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የሕገ መንግሥት ክለሳ የሚባል ነገር አለ፡፡ ሕገ መንግሥት ደግሞ ቅርፁና ይዘቱ የሚነካ ከሆነ፣ ምናልባትም ወደ ሕገ መንግሥት ክለሳ ሊያመራ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ደግሞ ስለሕገ መንግሥት ክለሳ ምንም አይልም፡፡ የሕገ መንግሥትን ክለሳ በሚመለከት እ.ኤ.አ. በ1955 የነበረውን የንጉሡን ሕገ መንግሥት ማየት እንችላለን፡፡ እንደ ሰብዓዊ መብት የመሳሰሉ ጉዳዮችን ያካተተ ሲሆን፣ ኤርትራ ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ስለተቀላቀለች እንዲህ ዓይነት ክስተቶችን ተከትሎ ክለሳ እንዲደረግ ሆኗል፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት በመጡ ነገሮችም ወደ ማሻሻያ ሲገባ ብዙ አከራካሪ የሆኑ ጉዳዮች ሊሆሩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ማሻሻያ ተስፋን ብቻ ሳይሆን ሥጋትንም ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ የግጭትም መንስዔ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም አሁን የታፈነ ቦምብ ላይ እንደመቀመጥ ከእነ ችግሩ ነው ያለው፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ባለበት መቀጠል አለበት የሚሉ አሉ፡፡ አይ መዋቅሩ መለወጥ አለበት የሚሉ አሉ፡፡ መጀመሪያ ወደ ማሻሻያው ሳይገባ ሒደቱ ላይ ውይይት ቢደረግና ከስምምነት ተደርሶ የሕገ መንግሥቱን ማሻሻያ የሚደነግገው አንቀጽ አስቀድሞ ቢሻሻል እጅግ የተሻለ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም ሒደቱ ላይ መግባባት ካልተቻለ ለብሔራዊ ደኅንነትም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበትን ሁኔታ ለመፍጠር፣ መጀመሪያ ሒደቱ ላይ መግባባት ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- ይኼንን ሒደትና ሥነ ሥርዓት ሊገዛ የሚችል የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀትስ መፍትሔ ሊሆን አይችልም?
ሙሉቀን (ረዳት ፕሮፌሰር)፡- ሕገ መንግሥት እንደ ሌሎች ሕጎች ባለመሆኑ ለእርሱ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ በሥልጣን ረገድ ለክልል ምክር ቤቶችና ለፌዴራል ምክር ቤት (ፓርላማ) ተከፋፍለው የተሰጡ ኃላፊነቶች አሉ፡፡ ሕገ መንግሥት ማሻሻል ግን ሁለቱንም የሚያሳትፍ ነው፡፡ ስለዚህ ሕግ ይውጣለት ቢባል የሁለቱም ፍላጎት የተስተናገደበት መሆን ስለሚገባው ማን ነው የሚያወጣው? የክልልና የፌዴራል መንግሥቱን ተሳትፎ ይፈልጋል፡፡ ፓርላማው ያውጣ ቢባል በዋናነት የፌዴራሉን ፍላጎት ነው የሚያንፀባርቀው፡፡ ክልሎች ያውጡ ቢባልም እንደዚያው፡፡ ስለዚህ በሒደቱ ላይ መግባባት ካልተቻለ መጀመሪያ በሕገ መንግሥቱ ላይ ያለው የማሻሻያ አንቀጽ በራሱ ቢሻሻል ጥሩ ነው፡፡ በሕገ መንግሥት ማሻሻያው ላይ የተቀመጡት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ አላባዎች አሉና የትኞቹ ክፍተት አላቸው፣ የትኞቹ መሻሻል አለባቸው የሚለውን መለየት ይቻላል፡፡ ሕገ መንግሥት ሲሻሻል የተለያዩ ጉዳዮች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ከመብቶች አንፃር ሲገመገም ከፌዴራላዊ ሥርዓት ይልቅ፣ ለኮንፌዴራላዊ ሥርዓት የቀረበ ነው ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡ ምክንያቱም በሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት ውስጥ የተቀመጡትን የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ለመጨመርም ሆነ ለማሻሻልም፣ ወይም ለመቀነስ ሁሉም ክልሎች በአብላጫ ድምፅ ማፅደቅ አለባቸው ይላል፡፡ በሌሎች አገሮች ግን የብዙኃን ውሳኔ ነው እንጂ ሁሉም ክልሎች የሚባል አሠራር የለም፡፡ ሁሉም ክልሎች ከተባለ ወደ ኮንፌዴራል ሥርዓት ነው የሚሄደው፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ከዚህ ምዕራፍ ውጪ ላሉት ድንጋጌዎች ደግሞ ከክልሎች ሁለት ሦስተኛውን (አሁን ባለው ሁኔታ ከዘጠኙ ስድስቱ) ማግኘት ለማሻሻያ በቂ ነው፡፡
ነገር ግን በዚህ ዙሪያ አከራካሪ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የመገንጠል ጥያቄ፣ የመሬት ጉዳይ፣ ወዘተ በመሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ድንጋጌ ሥር ተካትተው ነው ያሉት፡፡ ያ ማለት ለምሳሌ የአገሪቱን 99 በመቶ ሕዝብ የሚወክሉት ስምንቱ ክልሎች ተስማምተው፣ ሐረሪ ክልል እምቢ ካለ ውድቅ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይኼ ደግሞ የብዙኃን (Majority) መርህን ሊጥስ ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር የካናዳን ሕገ መንግሥት ብናየው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሲደረግ፣ ክልሎችም ፌዴራልም መንግሥትም ይሳተፋሉ፡፡ በክልሎች የማሻሻያ ውሳኔዎች እንዲያልፉ ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ማግኘት እንደሚጠበቅባቸው ቢደነግግም፣ ከጠቅላላ የአገሪቱ ሕዝብ ቢያንስ 50 በመቶ መወከል አለባቸው ብሎ ያስቀምጣል፡፡ ይኼ በእኛ ሁኔታ ሲታይ፣ የክልሎች ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ማግኘትን ብቻ ስለሚጠይቅ፣ ለምሳሌ ኦሮሚያና አማራ የአገሪቱን 50 በመቶ ሕዝብ የሚይዙ ቢሆኑም፣ ሌሎች ክልሎች የአማራና የኦሮሚያን ክልሎች ፍላጎት የሚጻረር ውሳኔ የሚያፀድቁ ከሆነ፣ ከሕግ አንፃር ውሳኔው ትክክል ቢሆንም፣ ፖለቲካዊ ተቀባይነቱ ግን ግድፈት ሊፈጥር ይችላል፡፡ እንዲሁም ማሻሻያው አንድን ክልል ብቻ የሚመለከት ውሳኔ ቢሆንና የክልሉ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል በሚለው ጉዳይ ላይ ክልሉ በራሱ ጉዳይ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት (ቬቶ) ይኖረዋል፣ አይኖረውም የሚለው ግልጽ አይደለም፡፡ ሌላው ጉዳይ ደግሞ ክልሎች ሲዋቀሩና አንድ ክልል እንደ አዲስ ሲመሠረት፣ በምን ያህል ጊዜ ነው ሥልጣኑን መረከብ ያለበትና የሕዝበ ውሳኔው መፈጸም ያለበት የሚለውም ግልጽ አይደለም፡፡ ነባር ክልሎች ሥልጣን እንዲያስተላልፉ የቀረበላቸውን ውሳኔ ምላሽ ሳይሰጡባቸው ቢያስቀሯቸውስ ምንድነው የሚሆነው የሚለው አልተመለሰም፡፡ የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት ያንን ጉዳይ የሚገዛበት ማዕቀፍ አለው፡፡ የእኛ ሕገ መንግሥት ግን ከዚያ አንፃር ምንም ስለማይል አንዱ በተግባር የሚታይ ፈተና ሊሆን ይችላል፡፡ የሕገ መንግሥት ማሻሻያን በዚህ ጊዜ መንግሥት ያልመረጠበት ምክንያት ብዙ ጉዳዮች ተያይዘው እንደሚመጡ ስለሚታወቅ ነው፡፡ ስለዚህ የተለያዩ ነገሮች አብረው ስለሚነሱና ይኼ በራሱ ሌላ ቀውስ ይዞ ስለሚመጣ፣ ያንን ለማስቀረት በማሰብ ይመስለኛል መንግሥት አሁን ወደ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ ያልገባው፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን ያለው ሕገ መንግሥት በቅራኔዎች የተሞላና በርካቶች አይወክለንም የሚሉት ሰነድ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ገዥው ፓርቲ ለራሱ ፖለቲካ ግቦች ማሳኪያ እንዲጠቅመው ተደርጎ የተዘጋጀ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ከአሁን በኋላ በአገሩቱ የሚደረጉ የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎች እንዲህ ያሉ ቅራኔዎችን እንዳያስከትሉና ዘመን ተሻጋሪ መሆን እንዲችሉ ምን ዓይነት ጥንቃቄዎች መደረግ ይኖርባቸዋል?
ሙሉቀን (ረዳት ፕሮፌሰር)፡- አሁን ያለው ሕገ መንግሥት የተለያዩ ቅራኔዎች እንደሚነሱበት ይታወቃል፡፡ በርካታ የማያስማሙ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ አይወክለንም ከሚለው አስተሳሰብ ጋር በተያያዘ፣ ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ አስቀድሞ እንደነበረው ሁሉ የመንግሥታት ተፅዕኖ ስለሚኖርበት ከዚያ የመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው ደግሞ እኛ አልተሳተፍንምና አይወክለንም የሚለው ነው፡፡ ነገር ግን እነርሱ ስላልተሳተፉ ሕገ መንግሥቱ ወካይነቱን ያጣል ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ቅድም እንዳነሳነው የጀርመንን ሕገ መንግሥት ጀርመኖች አይደሉም ያረቀቁት፡፡ ነገር ግን በሕገ መንግሥቱ ይዘት ስለተስማሙ እስከ ዛሬ እየተዳደሩበት ነው፡፡ ስለዚህ የተሳትፎ ጉድለት ቢኖርም ይዘቱ ላይ ለወደፊት ማሻሻያ ሲደረግ መሠራት ያለበት አካታችነትን ማረጋገጥ ነው፡፡ አካታችነት ሲባል አሁን ባለው የሕገ መንግሥት ማዕቀፍ ውስጥ ነውና የሚታየው፣ ያንን ከግንዛቤ በማስገባት ሁሉንም ያካትታል ወይ የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የሕዝብ ጉዳይ ከሆነ ማሻሻያውን ሕዝብም የሚጠይቅበት አግባብ እንዴት ይታያል? ከሌሎች አገሮች ሕገ መንግሥቶች ትምህርት መውሰድ ይቻላል፡፡ በኔዘርላንድስ ሕገ መንግሥት 100 ሺሕ ሰዎች የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እንዲደረግ ከጠየቁ ወደ ቀጣይ ሒደት ያልፋል፡፡ በእኛ ሕገ መንግሥት ግን ሕዝብ የሕገ መንግሥት ማሻሻያን ማንሳት ይችላል ወይ የሚለው ግልጽ አይደለም፡፡ ስለዚህ ማሻሻያን መጠየቅ የሚችለው ማን ነው የሚለው መታየት አለበት፡፡ ሌላው ጥንቃቄ መደረግ ያለበት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ ከቀጣይ ምርጫ በኋላ ይደረጋል የሚሉ አሉ፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጉዳዮች ካላቸው የአከራካሪነት ባህርይ አኳያ፣ በአምስት ዓመት እንኳን ላያልቁ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሰፊ ስለሆነ፣ ጊዜ ሊወሰድበትና ረጋ ተብሎ በርካታ ነገሮች ላይ እየተስማሙ መሄድ ቢቻል ጥሩ ይሆናል፡፡ በዚህም አካታችነትን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ይበልጥ ግን ሕገ መንግሥት የሕዝብ መሆን አለበት የሚለው ላይ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ አንድ መንግሥት ወይም ፓርቲ ወይም ግለሰብ ሥልጣን ላይ ስላለ በራሱ ማዕቀፍ የሚስቀምጠው ሳይሆን፣ የሕዝብ ሰነድ ስለሆነ ሕዝቡ በብዛት የሚሳተፍበት፣ ሕዝቡን የሚወክሉ የተለያዩ አካላት፣ መንግሥትም፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም፣ እንዲሁም ፖለቲካ ፓርቲዎችና ባለሙያዎች በስፋት ተሳትፎ ቢያደርጉ የሚያስማማ ጉዳይ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡ በተጨማሪ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እንደ ፍፃሜ ተደርጎ ባይወሰድ ጥሩ ነው፡፡ ሕገ መንግሥት እንደ ሌሎች ሕጎች በተፈለገው ጊዜ ሁሉ አይሻሻልም፡፡ ነገር ግን ሁነቶች ሲከሰቱ ማሻሻል እንዲቻል ሥርዓቶች ለዚህ ክፍት ቢሆኑ፡፡ ሥርዓቶች ክፍት ከሆኑ ችግሮች ሲፈጠሩ መፍትሔዎችም አብረው እየዳበሩ ይሄዳሉ፡፡ እናም በአንድ ጊዜ የሚሻሻል ሳይሆን ቀጣይነት ያላቸውን መፍትሔዎች እየሰጡ ለመሄድ እንዲቻል ሥርዓት ማበጀት ያስፈልጋል፡፡