Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የእንግሊዙ ኩባንያ ከሸቀጦች አቅርቦት ባሻገር በኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ፍላጎት አሳይቷል

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቅርቡ ከተካሄደው የ600 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ አቅርቦት ጨረታ ላይ በመሳተፍ 200 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ከ 40 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ዋጋ ለማቅረብ የእንግሊዙ ጄምኮርፕ አሸናፊ መሆን ችሏል፡፡

ለብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ይህንኑ ስንዴ በሁለት ወራት ውስጥ እንደሚያቀርብ የሚጠበቀው ይህ ኩባንያ፣ እንዲህ ያለውን ጨረታ ሲያሸንፍ ለሁለተኛ ጊዜው እንደሆነ ገልጿል፡፡

ኩባንያው በኢትዮጵያ ለማከናወን ስላለው ፍላጎት ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳደረገው፣ በንግድ ሥራና በኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ተስፋፍቶ የመሥራት ፍላጎት አለው፡፡ ጄምኮርፕ የኢትዮጵያን ገበያ የተቀላቀለው በ2010 ዓ.ም. ሲሆን፣ ከዚያን ጊዜ ወዲህ 900 ሺሕ ቶን ፉርኖ ዱቄት እንዲሁም ከ23 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት አቅርቧል፡፡ ባለፈው ዓመት በተካሄደው ጨረታ 900 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ በ155.6 ሚሊዮን ዶላር ሒሳብ ለማቅረብ አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ኩባንያው ለኢትዮጵያ ግዙፍ የስንዴ አቅርቦት አዲስ በመሆኑ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ሲገለጽ ቢቆይም፣ ካለፈው ዓመት በተጨማሪ ዘንድሮም አቅራቢ መሆን የሚችልበት አቅም እንዳለው አሳይቷል፡፡

በኢትዮጵያ የጄምኮርፕ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ኮስታስ አርሜናኪስ እንዳስታወቁት፣ ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ ያህል ኩባንያው የግብርና ምርቶች የንግድ ሥርዓትን በኢትዮጵያ ለመዘርጋት በርካታ ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ስንዴ ዱቄትና የምግብ ዘይትን ለመንግሥት እንዲሁም ለግል አስመጪዎች በማቅረብ ሥራ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ጄምኮርፕ በአዲስ አበባና በጅቡቲ ቅርንጫፎቹን ከፍቶ መንቀሳቀስ እንደ ጀመረ ያስታወሱት ኃላፊው፣ ይህም በአቅርቦት መስክ ያሉ የሎጂስቲክስ ሥራዎችን ለማቀላጠፍ፣ ወጥነት ያለው አሠራርና ቁጥጥር ለመዘርጋት እንዲያስችል በማስፈለጉ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ ዕቃዎች ወደ አገር ውስጥ በሚገቡበት፣ በመላው ኢትዮጵያ በሚንቀሳቀሱበትና ለተጠቃሚዎች በሚሠራጩበት ወቅት ግልጽነት ላይ የተመሠረተ ተግባቦት እንዲኖር ኩባንያው ሚናውን እንደተወጣ አስታውቋል፡፡ 200,000 ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለማቅረብ በሁለተኛ ዙር ጨረታ ማሸነፉ፣ በዘመናዊ አሠራሮች ታግዞ በአጭር ጊዜ በገበያው ውስጥ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት በመቻሉ እንደሆነም ተገልጿል፡፡  

የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ እንደሚገልጹት፣ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንትና የንግድ አማራጮች ውስጥ ብሎም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት በሚያስችሉ ሥራዎች ላይ የመሳፍ ፍላጎት አለው፡፡ በተጓዳኝም አስፈላጊ ምርቶችና ሸቀጦችን በዘላቂነት ለአገር ውስጥ ገበያ የማቅረብ ሒደት ላይ በንቃት ይሳተፋል ብለዋል፡፡

ጄምኮርፕ አዳዲስ የንግድ ተቋማትን በተለይም የፋይናንስ እጥረት በሚታይባቸው መስኮች ላይ የማገዝና ብድር በማመቻቸት ሥራ ውስጥም የመሳተፍ ፍላጎት አለው፡፡ ተቋሙ ለመንግሥትና ለግሉ ዘርፍ ተዋንያን ብድር የማቻቸትና የማቅረብ፣ የሸቀጦች አቅርቦትና ሥርጭት ሒደቶች ላይ ድጋፍ የሚሰጥ የአንድ መስኮት አሠራር መዘርጋቱን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከስንዴ አስመጪነት በመውጣት በአገር ውስጥ ምርት አቅርቦትን የማሟላት ዕቅዱን ይፋ አድርጓል፡፡ በስንዴ ምርት አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለው ክፍተት ሁልጊዜ ሊጣጣም ስለማይችል፣ በተለይም ለፓስታና ማካሮኒ አምራቾች የሚውለውን ዱቄት ለማምረት የግድ ከውጭ ስንዴ ማስገባት ሊያስፈልግ እንደሚችል  ይጠበቃል፡፡

በአገር ውስጥ የሚመረተው ስንዴ መጠን 460 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ገደማ ይገመታል፡፡ በአንፃር የስንዴ ፍላጎት ከ680 እስከ 700 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ባለው መጠን ደረጃ ስለሚገመት በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል የሚታየውን ክፍተት ከውጭ በማስገባት ማሟላት ብቻም ሳይሆን፣ ድርቅና ሌሎችም አደጋዎች የሚደቅኗቸው የምግብ እጥረት ሥጋቶች ከውጭ የሚገባ ስንዴን በቶሎ የማቆም አቅም ላይፈጠር እንደሚችል ይጠበቃል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች