Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናግብፅ የተመድን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ በመጣስ የሶማሊያን ጦር ማስታጠቋ እንዳሳሰበው የሶማሌላንድ መንግሥት...

ግብፅ የተመድን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ በመጣስ የሶማሊያን ጦር ማስታጠቋ እንዳሳሰበው የሶማሌላንድ መንግሥት አስታወቀ

ቀን:

በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ የተደቀነ ሥጋት በማለት የግብፅን ድርጊት ኮንኗል

በዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫ ውስጥ የከረሙት ሶማሊያና ሶማሌላንድ ዳግመኛ ያገረሸ ቁርሾ ውስጥ የገቡት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የጣለውን ማዕቀብ በመጣስ ግብፅ ለሞቃዲሾ መንግሥት የጦር መሣሪያ ዕርዳታ መስጠቷን የሚያመላክቱ መረጃዎች በመውጣታቸው ነው፡፡

ሪፖርተር ከሶማሌላንድ መንግሥት ምንጮች አማካይነት አፈትልኮ የወጣውን ደብዳቤ አግኝቷል፡፡ ይኸው ከጥቂት ወራት በፊት በሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር ተፈርሞ ለግብፅ መከላከያ ሚኒስቴር የተጻፈው ደብዳቤ፣ ርክክብ የተፈጸመባቸውን መሣሪያዎች ዝርዝር ያሳያል፡፡ የካቲት 21 ቀን 2012  (እ.ኤ.አ. ፌብሩዋሪ 29 ቀን 2020) የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር ሐሳን አሊ ሞሐመድ ለግብፅ መንግሥት በጻፉት ደብዳቤ፣ 50 አርፒጂ-7 ላውንቸሮች፣ 36 የአልሞ ተኳሽ ጠብመንጃዎች ከ1,000 ጥይቶች ጋር፣ እንዲሁም ሌሎች 13 ዓይነት በዝርዝር የጠቀሷቸው የጦር መሣሪያዎች እንደተረከቡ አረጋግጠዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዚህም መሠረት ብዛታቸው 1,200 ክላሽኒኮቭ (ኤኬ47) ጠመንጃዎች፣ 25 ፒኬኤም መካከለኛ አውቶማቲክ መሣሪያ ከ700 ጥይቶች፣ 175 ፒኬኤም ቀላል አውቶማቲክ መሣሪያ ከ700 ጥይቶች፣ 50 አርፒጂ-7 ላውንቸሮች፣ 36 ባለ 12.7 ሚሊ ሜትር ደሸከ (ዶሽቃ) ከባድ አውቶማቲክ መሣሪያዎች፣ ስድስት ባለ 82 ሚሊ ሜትር ሞርታር ከ550 ተተኳሽ ጥይቶች ጋር፣ እንዲሁም 12 ባለ 60 ሚሊ ሜትር ከባድ ሞርታሮች ከ636 ሽጉጦች ጋር ግብፅ ለሶማሊያ መከላከያ ሠራዊት መለገሷን ከደብዳቤው ለመረዳት ተችሏል፡፡  

የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር የተደረገለት የጦር መሣሪያ ድጋፍ ለአገሪቱ የፀጥታ ሥራ ብቻ እንደሚውል፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ ለሽያጭ ወይም ላልተፈቀደላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች እንደማይተላለፍ በመግለጽ ለግብፅ መከላከያ ሚኒስቴር ጽፏል፡፡

ይኼንን ተከትሎ የሶማሌላንድ መከላከያ ሚኒስትር አብዲቃኒ ሞሐሙድ አቲዬ በትዊተር ገጻቸው  የአፍሪካ ኅብረትን፣ ተመድንና የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሒን ጠቅሰው በጻፉት ማሳሰቢያ ግብፅና ሶማሊያን ኮንነዋል፡፡ የሶማሊያ መንግሥት ለዓመታት ተጥሎበት የቆየውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ አለማክበሩን ያወሱት የመከላከያ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የግብፅ መንግሥትም በሶማሊያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ሆን ብሎ በመጣሱ እንቃወመዋለን፡፡ ይህ ድርጊት በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ላይ ከፍተኛ ሥጋት ይፈጥራል፤›› ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ምን እንደሆነ ለማወቅ ሪፖርተር ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርቦ፣ የሁለቱ አገሮች ጉዳይ በመሆኑ ምንም ዓይነት ምላሽ መስጠት እንደማይችል አስታውቋል፡፡ ሚኒስቴሩ ይህን ይበል እንጂ፣ በቀጣናው የፀጥታና የደኅንነት ጉዳዮች ላይ የካበተ ተሞክሮ ያላቸው ባለሙዎች ግን፣ መንግሥት ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እያለዘበና ቸል እያለ የመጣውን የሁለትዮሽ የፀጥታ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጥበት ያሳስባሉ፡፡ ፖለቲካዊ አሠላለፎች መለወጣቸው የሰላምና መረጋጋት ችግሮች እንዳያስፋፋ ያስጠነቅቃሉ፡፡

ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደርና ለመተናኮስ የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም የሚሉት የዘርፉ ተንታኞች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወታደራዊ ትብብሮችን በመመሥረት ሰበብ ከደቡብ ሱዳን ጋር፣ አሁን ደግሞ ከሶማሊያ ጋር በግላጭ የጦር መሣሪያ ድጋፍ ማድረጓ መልዕክት አለው ይላሉ፡፡

ተመድ ከሶማሊያ በተጨማሪ በኤርትራ ላይ የጣለውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ከቅርብ ከሚከታተሉ ተቋማት አንዱ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ)፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክትትሉን እያቋረጠ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ከሁለት ዓመታት ወዲህም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር በኤርትራና በሶማሊያ ላይ በሚከተለው የፖለቲካ አሠላለፍ ለውጥ ምክንያት፣ እንዲህ ያሉ ጥሰቶች ለአደጋ እንደሚያጋልጡ ያስረዳሉ፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1991 ጀምሮ ከሶማሊያ በመገንጠል ራሷን የቻለች ነፃ አገር መሆኗን ያወጀችው ሶማሌላንድ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በይፋ ዕውቅና ባታገኝም፣ በተዘዋዋሪ ዲፕሎማሲያዊ ከ20 በላይ አገሮች ጋር ግንኙነት በመመሥረት እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡ በሞቃዲሾ መንግሥትና በሶማሌላንድ መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ አዲስ ያገረሸው አለመግባባት ወደ ቃላት መወራወር አምርቶ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ሁለቱን ወገኖች ለማሸማገልና በጠረጴዛ ዙሪያ ለማደራደር የጀመሩት ሙከራ መክሸፉ ይታወሳል፡፡

በሶማሊያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እ.ኤ.አ. ከ1992 ጀምሮ የፀና ሲሆን፣ በየጊዜው እየታደሰና እየተጠናከረ በመምጣት ከሁለት ዓመታት በፊት በከፊል እንዲሻሻል ቢደረግም፣ አሁንም ድረስ ባለበት እንዲፀና ተመድ ወስኗል፡፡

የጦር መሣሪያ ማዕቀቡ በሶማሊያና በኤርትራ ላይ እንዲፀና የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ሲወስኑ፣ ኢትዮጵያም በወቅቱ በተመድ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ተቀዳ ዓለሙ (ዶ/ር) አማካይነት የውሳኔውን አስፈላጊነት ካብራሩና ድምፅ ከሰጡ የ11 አባል አገሮች ተወካዮች መካከል ነበረች፡፡ ተመድ በሶማሊያ የሚገኘውን የሰላም አስከባሪ ጦሩን እ.ኤ.አ. እስከ ጁን 30 ቀን 2020 ድረስ እንዲቆይ መወሰኑ ይታወሳል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...