Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ብድር የመመለስ አቅም ጥያቄ ፈጥሯል

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት እንደማያሳስበው አስታውቋል

የየአገሮችን የብድር ዕዳ የመሸከም አቅም ብሎም በወቅቱ የመክፈል ችሎታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ደረጃ የሚያወጡ ኤጀንሲዎች፣ ባለፉት ሦስት ወራት የኢትዮጵያን የብድር ዕዳ ሁኔታ በመገምገም ቀድሞ የነበራትን ደረጃ ዝቅ አድርገዋል፡፡

ሙዲስ፣ ፊች እንዲሁም ስታንዳርድ ኤንድ ፑር (ኤስ ኤንድ ፒ) የተሰኙት ተቋማት፣ የኢትዮጵያን ደረጃዎች ዝቅ ማድረጋቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ እርግጥ የኢትዮጵያን ብቻም ሳይሆን፣ የበርካታ አገሮች ደረጃ ዝቅ ተደርጓል፡፡ ሙዲስ የተሰኘው ተቋም ቢ2 ደረጃ ላይ የነበረውን ወደ ቢ1 ዝቅ አድርጓል፡፡ ይህም ማለት የአገሪቱ የተሻለው ነባር ደረጃ ከነበረበት ወደ ታች ዝቅ ተደርጓል ማለት ነው፡፡

ደረጃው ዝቅ ካለባቸው ምክንያቶች መካከል ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገሮች በተደቀነባቸው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሥጋት ምክንያት ያለባቸውን የብድር ዕዳ ለመክፈል እንደሚቸገሩ ማሳወቃቸውን ተከትሎ ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ለአበዳሪና ለለጋሽ አገሮች የዕዳ ስረዛ ጥያቄ መቅረቡ ይታወሳል፡፡ ለአፍሪካ አገሮች በጠቅላላው ከ200 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ እንዲደረግ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በይፋ ጥያቄ ከማቅረቡም ባሻገር፣ አብዛኛው የዚህ ክፍል በዕዳ ስረዛና ቅነሳ እንዲሁም በዕዳ ማዘግየት ጭምር እንዲታገዝ የሚጠይቅ ነበር፡፡

የቡድን 20 አገሮች ለአፍሪካ ጥያቄዎች ከፊል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ለዘጠኝ ወራት የዕዳ ክፍያ ሳይፈጸም ባለበት እንዲቆም መወሰኑን እንዳስታወቀ፣ በሳዑዲ የተመራው የቡድን 20 የዘንድሮው ስብሰባ ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የአፍሪካውያኑ ጥያቄ የዕዳ ስረዛ እንዲደረግ በመሆኑ፣ ውሳኔው በቂ እንዳልሆነ ጠቅላዩ በጋዜጦች ጽፈው ነበር፡፡

አገሮች ዕዳ ይሰረዝልን ማለታቸውን ተከትሎ የብድር ጫና መሸከምና የመክፈል አቅማቸው ከግምት እየገባ ደረጃ በሚያወጡት ኤጀንሲዎች ዝርዝራቸው ይፋ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ የእነዚህ ተቋማት ሚና ለውጭ ኢንቨስትመንት መስፋፋት ድርሻ አለው፡፡ ይሁን እንጂ በኮሮና ጫና ሳቢያ በርካታ አገሮች ለብድር ክፍያም ሆኖ ለኢንቨስትመንት በማይመች ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያም አንዷ ነች፡፡

ይህን ተከትሎም ተቋማቱ ሥጋታቸውን በመተንተን ኢትዮጵያ የነበራትን ደረጃ ዝቅ አድርገዋል፡፡ ያለፉት ሦስት ወራት ደረጃዎች ዝቅ ተደርገዋል፡፡ የግንቦት ወር ደረጃዋም በመገምገም ላይ ይገኛል፡፡ ይህ አሳሳቢ ነው ከሚሉት ወገን የሆኑት የስትራቴጂና የኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ ፋኑኤል ተክለ ጊዮርጊስ፣ የወጣው የኤጀንሲዎቹ ሪፖርት የአገሪቱን ደካማ የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር ብሎም የገንዘብ ችግር አመላካች ነው ይላሉ፡፡

በእሳቸው ምልከታ ኤጀንሲዎቹ ያወጡት ዝቅተኛ ውጤት፣ ከሕክምና ምርመራ ጋር ይመሳሰላል፡፡ ይኸውም ለሕመም ጠቋሚ የሆኑ በርካታ አመላካቾች ይኖራሉ፡፡ ምርመራ ሲደረግም ከእነዚህ የሕመም ጠቋሚዎች በመነሳት መፍትሔ እንደሚሰጥ ሁሉ፣ ለኢትዮጵያ ሁኔታም የኤጀንሲዎቹ ሪፖርት የኢኮኖሚውን በሽታ የሚያመላክቱ ጠቋሚዎች ስለመሆናቸው ይሞግታሉ፡፡

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን የሚወስን መመርያ በዋቢነት ሲያሱ፣ አገሪቱ በገጠማት የገንዘብ እጥረት ሳቢያ ጭምር የወጣው ይህ መመርያ በግለሰብና በድርጅቶች አማካይነት በየዕለቱ ከባንኮች ወጪ በሚደረገው ጥሬ ገንዘብ ላይ የመጠን ገደብ አስቀምጧል፡፡ መንግሥት ይህን ያደረገው በአንድ በኩል ኢኮኖሚው ውስጥ ከሚገባው በላይ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ፣ ባንኮች የማያውቁት ገንዘብ በመሆሩ ነው ቢባልም፣ የመመርያው ሌላ መገለጫ ግን የገንዘብ እጥረት በማጋጠሙ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ነው፡፡ አቶ ፋኑኤል ግን መመርያውን ከሙዲስ እንዲሁም ከሌሎቹ የብድር ደረጃ አውጪዎች የወቅቱ የኢትዮጵያ ደረጃ ማሽቆልቆል ጋር እንደሚያያዝ ይሞግታሉ፡፡ ኤጀንሲዎቹ ያወጡት ደረጃ አገሪቱ ደካማ የማክሮ ኢኮኖሚና የገንዘብ አስተዳደር ችግር እንዳለባት አመላክቷል ያሉት አማካሪው፣ አገሪቱ ያለባትን ዕዳ የመክፈሏ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ መውደቁን ይጠቅሳሉ፡፡

ይህ ይባል እንጂ መንግሥት በወጣው ዝቅተኛ ደረጃ ምክንያት ኢትዮጵያ የሚያጋጥማት ችግር እንደማይኖር አስታውቋል፡፡ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ ኤጀንሲዎቹ ያወጡትን ሪፖርት መነሻ በማድረግ ከኤጀንሲዎቹ ጋር ውይይት መደረጉን ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ወቅት አስታውቀዋል፡፡ ይህ የመጣው ከወቅቱ የአደጋ ጊዜ ጋር በተገናኘ እንደሆነ፣ ይህንኑ መነሻ በማድረግም በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ  አህመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የአፍሪካ አገሮች የኮሮና ወረርሽኝ በጋረጠባቸው አደጋ ምክንያት ኢኮኖሚያቸው ችግር ውስጥ መግባቱን በማስገንዘብ የዕዳ ስረዛ ጥያቄ ማቅረባቸውን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ዕዳ ለመክፈል እንደሚቸገሩ በመግለጻቸው ምክንያት ኤጀንሲዎቹ ይህንን ወስደው የአፍሪካ አገሮች ዕዳቸውን የማይከፍሉ ከሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ተቀባይነት ጥያቄ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል በመሥጋት ያወጡት ሪፖርት ነው ብለውታል፡፡

ኢትዮጵያ ለትርፍ ከሚያበድሩ ወይም ከብድር ገበያ የገዛችውና የአንድ ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ዩሮ ቦንድ ዕዳ እንዳለባት ያስታወሱት ኢዮብ (ዶ/ር)፣ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ብዙ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ነች ማለቱ እንደማያስኬድ፣ ይልቁንም ጊዜያዊ ችግር የፈጠረው በመሆኑ ችግሩ ሲቀረፍ የብድር ደረጃውም እንደሚስተካከል አስታውቀዋል፡፡ በአንፃሩ እንደ ኬንያ ያሉት አገሮችም የወጣው ደረጃ ብድራቸውን ላይከፍሉ ይችላሉ ከሚል መነሻ የወጣ መሆኑን በማስተዋል፣ ብድር ከመክፈል ወደ ኋላ እንደማይሉ ምላሽ በመስጠት ኤጀንሲዎቹ ያወጡት ሪፖርት የብድር ገበያው ላይ ተዓማኒነት እንዳያሳጣቸው ለማድረግ ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች