Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመጪው ዓመት በጀት ግማሽ ትሪሊዮን ብር እንደሚደርስ ይጠበቃል

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዘንድሮ ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት የጠየቀው መንግሥት፣ በመጪው ዓመት እስከ 70 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ገንዘብ የሚጠይቅ በጀት እንደሚያፀድቅና በጠቅላላው 500 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለ2013 ዓ.ም. በጀት እንደሚመድብ ይጠበቃል፡፡

እየተጠናቀቀ በሚገኘው የዘንድሮ በጀት ዓመት ከ387 ቢሊዮን ብር በላይ ተመድቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያ አጀንዳዎችን ለማስፈጸምና እያጋጠሙ ያሉ የኑሮ ጫናዎችን ለማቃለል የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ በየካቲት ወር 28 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አፀድቆ ነበር፡፡ ዓርብ ግንቦት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ተጨማሪ 48 ቢሊዮን ብር ለማፅድቅ መገደዱን አስታውቋል፡፡ ይህ ተጨማሪ በጀት በአሁኑ ወቅት በኮሮና ሳቢያ እያጋጠሙ የሚገኙ የጤናና የኢኮኖሚ ጫናዎችን ለመቋቋም እንዲያስችል የተፈቀደ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

መንግሥት ባጋጠመው የገቢ መቀነስና የወጪ ጭማሪ ሳቢያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀውን 48 ቢሊዮን ብር አካቶ፣ በአራት ወራት ውስጥ ያፀደቀው ጠቅላላ ተጨማሪ በጀት 76 ቢሊዮን ብር እንዳስፈለገ መዘገባችን ይታሳቃል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በተለይ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳስታወቁት፣ ተጨማሪ በጀት ያስፈለገው በኮሮና ሳቢያ የመንግሥት ገቢ እየቀነሰ በመምጣቱና ወጪውም በከፍተኛ መጠን በመጨመሩ ነው፡፡

ለዓመታት ተጨማሪ በጀት ሲጠይቅ የቆየው መንግሥት በዚህ ዓመት የጠየቀው በጀት ላይ ከ76 ቢሊዮን ብር በላይ ከማካተቱም በተጨማሪ፣ በመጪው ዓመትም ከዚህ የማይተናነስ ገንዘብ እንደሚበጅት አስታውቋል፡፡ የዘንድሮው ጫና በመጪው ዓመት ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር በመታመኑ፣ በጀቱ ከወትሮው ጊዜ በተለየ መንገድ እንደሚበጀት ኢዮብ (ዶ/ር) አብራርተው ነበር፡፡ ይህም ማለት ለ2011 ዓ.ም. የነበረው በጀት ላይ በ2012 ዓ.ም. የአሥር በመቶ ጭማሪ በማድረግ ሲዘጋጅ የነበረው በጀት፣ አሁን ግን ለአስቸኳይ ጊዜ የአደጋ መከላከያ በጀት ታክሎበትና የመጠባበቂያ ሥሌት ተካቶበት ወደ ግማሽ ትሪሊዮን እንደሚጠጋ ከወዲሁ ታውቋል፡፡

ይኸውም በገንዘብ ሚኒስቴር ማብራሪያ መሠረት በዘንድሮ በጀት ላይ እንዳለ የ70 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ብቻ ቢታከልበት 458 ቢሊዮን ብር ይደርሳል፡፡ በዚህ በጀት ላይ የአሥር በመቶ ማሻሻያ ቢታልከበት የ2013 ዓ.ም. በጀት ከ496 ቢሊዮን ብር ያላነሰ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ለፓርላማው ፀድቆ እንደሚወጣ የሚጠበቀው የ48 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት በመጪው ዓመትም ተካቶ እንዲቀርብ የፓርላማውን ውሳኔ ይጠብቃል፡፡

ለሕክምና ቁሳቁሶች ግዥዎች የሚለውን ጨምሮ ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ፣ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች፣ ለአነስተኛ ገንዘብ ተቋማት፣ እንዲሁም ለኅብረት ሥራ ማኅበራትና ለሌሎችም መስኮች የሚውል ተጨማሪ 48 ቢሊዮን ብር ማስፈለጉን ኢዮብ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

በዋቢነት ከተጠቀሱት ከእነዚህ የወጪ መስኮች መካከል ጤና ሚኒስቴር በየጊዜው የሚወስደው የ15 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት እንደሚያስፈልገው ማስታወቁን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡

‹‹ምክር ቤቱ ያፀደቀው የበጀት ማስተካከያ ያስፈለገው ወጪያችን በከፍተኛ መጠን ጨምሮ ገቢያችን በመቀነሱ ነው፡፡ በሽታውን ለመከላከል የምናወጣቸው ከፍተኛ ወጪዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ጤና ሚኒስቴር በየጊዜው የሚወስደው ሆኖ 15 ቢሊዮን ብር ጠይቋል፤›› ያሉት ኢዮብ (ዶ/ር)፣ በርካታ ያልታሰቡ ወጪዎች በማጋጠማቸው ተጨማሪ በጀት ማፅደቅ እንዳስፈለገ ገልጸዋል፡፡ ለምግብ ዕርዳታ የሚውል 600 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ የግዥ ጨረታ በቅርቡ መውጣቱን ያስታወሱት ኢዮብ (ዶ/ር)፣ መንግሥት ቀደም ብሎ ባስቀመጠው ትንበያ መሠረት 15 ሚሊዮን ተጨማሪ ዜጎች የምግብ ዕርዳታ ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

በሴተፍቲኔት እየተረዱ የሚገኙትን ጨምሮ በጠቅላላው 30 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው መንግሥት ይፋ አድርጓል፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንም ይህንኑ አረጋግጧል፡፡ ለዚህ የሚያግዝ የ600 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ በ4.1 ቢሊዮን ብር ወይም በ128 ሚሊዮን ዶላር ግዥ ለመፈጸም እንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በዓመቱ ግዥ እንዲፈጽም ጥያቄ የቀረበለት ጠቅላላ የስንዴ መጠን 800 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እንደሆነ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡  

በተጨማሪም ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች፣ ለአነስተኛ የገንዘብ ተቋማት፣ እንዲሁም ለኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየኖች የሚውል በድምሩ 4.5 ቢሊዮን ብር ማስፈለጉን፣ ሦስቱ ዘርፎች እያንዳንዳቸው የ1.5 ቢሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ታሳቢ መደረጉን ከሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች