Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለማለት ያህል ተብለው የቀረቡ የድጋፍ ጥሪዎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኮሮና ወረርሽኝ ዓለምን እንደ ሰደድ እሳት ማዳረስ ሲጀምር ወደ አፍሪካ የመጣው  ዘገምተኛ ሆኖ ነበር፡፡ ከተከሰተ አምስተኛ ወራት በማስቆጠር ከ4.5 ሚሊዮን በላይ የዓለም ዜጎች በዚሁ በሽታ ተይዘዋል፡፡ ከ300 ሺሕ በላይ ለሞት ተዳርገዋል፡፡ በአፍሪካም ሰደዱ እየሰፋና በርካቶችን እያዳረሰ መጥቷል፡፡ ወደ 90 ሺሕ የተጠጋው የኮሮና በሽታ ተጎጂዎች ቁጥር፣ የሟቾችን ቁጥርም ወደ 3000 እያሻቀበው እንደሚገኝ የአፍሪካ በሽታ መከላከልና ቁጥጥር ተቋም (አፍሪካ ሲዲሲ) መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በኢትዮጵያም የሥርጭቱ መጠን በዕለቱ ከሚደረገው የምርመራ ቁጥር መጨመር ጋር እያደገ መጥቷል፡፡ የጤና ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ይፋ ባደረጓቸው መረጃዎች መሠረት፣ ከ62 ሺሕ በላይ የላቦራቶሪ ምርመራዎች ተከናውነው ከ362 በላይ ዜጎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡ አምስት ዜጎች በበሽታው ለሞት ተዳርገዋል፡፡

ከጤና ባሻገር በኢኮኖሚና በማኅበራዊ መስኮች ያስከተለው ቀውስ ለአፍሪካ አገሮች የበለጠ የአደጋ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ የበሽታው መንሰራፋት በአፍሪካ ላይ ሁለንተናዊ የህልውና አደጋ እንደሚሆን በመታሰቡ፣ በርካታ አጥኚዎችና ተቋማት በሽታው ሊያደርስ ስለሚችለው አስከፊ ጉዳት በየፊናቸው ሲያሳስቡና ሲጽፉ ከርመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአሜሪካ ጋዜጦች ሳይቀር አፍሪካ የመጨረሻዋ የበሽታው የዘመቻና የድል ማዕከል መሆኗ ለዓለም መድኃኒት እንደሆነ በመሞገት ተማጸኑ፡፡ አሳሰቡ፡፡ ቀደም ብለውም የ150 ቢሊዮን ዶላር አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግ ጠየቁ፡፡ እሳቸውን ተከትለው የአፍሪካ የፋይናንስ ሚኒስትሮችም የ100 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ያስፈልጋል አሉ፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ከፋይናንስ ሚኒስትሮቹም ከቀረበው የገንዘብ ድጋፍ ይሰጠን ጥሪ የተቀዳ የሚመስለው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ በጤና ጥበቃ ሥራዎች መስክ 100 ቢሊዮን ዶላር፣ በኢኮኖሚያና ሌሎችም ማኅበራዊ መስኮች የ100 ቢሊዮን ዶላር፣ በጠቅላላው የ200 ቢሊዮን ዶላር ለአፍሪካ በአስቸኳይ እንደሚያስፈልግ የሚተነትን ጽሑፍ አስነበበ፡፡ ከሌሎች ተቋማትና አጥኚዎች ይልቅ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተብራራና በምክንያት የተደገፈ ትንታኔ የቀረበበት የድጋፍ ጥያቄና ምላሹ አልተገናኙም፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽንም ለአፍሪካ በሚያስፈልጋት ድጋፍ ላይ ይህ ነው የሚባል ሥራ አለመሥራቱን ምሁራን እየተቹ ነው፡፡ ለመሆኑ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ያወጣው ትንታኔ እንደምን ያለው ነበር?

የውኃ ሽታው የ200 ቢሊዮን ዶላር ጥያቄ

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ሚያዝያ በባተ በሁለተኛው ሳምንት መጀመሪያ ሰሞን ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ አፍሪካ ለአስቸኳይ የጤናና የኢኮኖሚ ድጋፎች የሚውል 200 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት አስታውቋል፡፡ በኮሮና ምክንያት ሊደርስ የሚችለውን ሰብዓዊ ጉዳት በአራት የጉዳት መላምቶች ላይ በመመሥረት 300 ሺሕ እስከ 3.3 ሚሊዮን አፍሪካውያን ሊሞቱ እንደሚችሉም አስጠንቅቆ ነበር፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ‹‹ኮቪድ-19 ሴቪንግ ላይቭስ ኤንድ ኢኮኖሚስ›› ወይም የሰዎችን ሕይወትና ኢኮኖሚን ከኮቪድ-19 አደጋ መታደግ በሚል ርዕስ ባወጣው ሪፖርት መሠረት፣ ያስፈልጋል ካለው 200 ቢሊዮን ዶላር አስቸኳይ ድጋፍ ውስጥ 100 ቢሊዮን ዶላር ለጤና ሥርዓትና ለበሽታው ሥርጭት መከላከያ ብሎም ለማኅበራዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ እንደሚውል አስፍሯል፡፡ ይኸውም ሊሞቱ ይችላሉ ተብለው ከሚገመቱት 300 ሺሕ እስከ 3.3 ሚሊዮን አፍሪካውያን ባሻገር፣ 2.3 እስከ 22.5 ሚሊዮን አፍሪካውያን በሆስፒታል ተኝተው መታከም ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል አመላክቷል፡፡ በሪፖርቱም በአፍሪካ 500 ሺሕ እስከ 4.4 ሚሊዮን ጽኑ ሕሙማን ሊኖሩ እንደሚችሉ በመገመቱ እነዚህን ለመታደግ ሲባል መንግሥታት እንደሚሰጡት የፖሊሲ ምላሽ የተጎጂው ቁጥር ሊቀንስና ሊጨምር እንደሚችል ቢገመትም፣ በጥቂቱ 100 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ድጋፍ አፍሪካ በአስቸኳይ ያስፈልጋታል ተብሏል፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እንዳሰፈረው፣ በአፍሪካ በተፋፈገ ሁኔታ የሚኖረው ከተሜ ለኮሮና ወረርሽኝ ከፍተኛ ሥርጭት ምቹ እንደሚሆን ሥጋቱን አስፍሯል፡፡ በአፍሪካ ከሚኖረው 1.3 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ መካከል 600 ሚሊዮኑ በከተሞች እንደሚኖር ይገመታል፡፡ ከዚህ ሕዝብ ውስጥም 56 በመቶው በተፋፈጉና ለኑሮ በማይመቹ አካባቢዎች ስለሚኖር ለኮሮና ሥርጭት የተመቻቸ ዕድል እንደሚፈጠርለት ከፍተኛ ሥጋት አሳድሯል፡፡ ከሰሜን አፍሪካ በቀር ባሉት በሌሎች ቀጣናዎች በተፋፈገና ለኑሮ በማይመች ሁኔታ የሚኖረው ይህን ያህል ሕዝብ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ ከሚኖረው ሕዝብም 74 በመቶው በተቸመቸሙና በማይመቹ መኖሪያ መንደሮች ተፋፍጎ ይኖራል፡፡ የበሽታው ሥርጭት ከዕለት ዕለት ፍጥነቱ እየጨመረ ከመምጣቱ አኳያ ይህ ዓይነቱ አኗኗር ከባድ ሥጋት ያሳደረው፣ ሕዝቡም ጥግግትን ለጊዜው በማስቀረት በሽታውን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ድጋፍ ቸልታ በማብዛቱ ጭምር ነው፡፡ በመላው አፍሪካ 34 በመቶ ቤተሰቦች ብቻ የእጅ መታጠቢያ የውኃ አቅርቦት ያላቸው በመሆናቸውና ሌሎችም መሠረታዊ አገልግሎቶች እጥረት የወረርሽኙን መስፋፋት እንደሚያፋጥነው ሥጋት በማሳደሩ የገንዘብ ድጋፉ በአፋጣኝ ሊደረግ እንደሚገባ የአፍሪካ ኢኮሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ የመሩት የጥናት ቡድን ያወጣው ሪፖርት አመላክቷል፡፡

70 በመቶ አፍሪካውያን መደበኛ ባልሆነ የሥራ መስክ ውስጥ በመሰማራት ኑሯቸውን ይገፋሉ፡፡ በእያንዳንዱ የአፍሪካ አገር ውስጥ ያለው የጤና ሥርዓት ደካማ ከመሆኑ ባሻገር፣ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ሙሉ ሙሉ ሊባል በሚያስችል ደረጃ ከውጭ በሚያስገቧቸው የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁሶች ላይ ጥገኞች ናቸው፡፡ በዚህም ሳቢያ 94 በመቶው የአፍሪካ የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቀስ ክምችት ከውጭ የገቡ ናቸው፡፡ ይህ ተጋላጭ ያደረጋቸው ሲሆን፣ 71 አገሮች የሕክምና ቁሳቁሶችና መድኃኒቶች የወጪ ንግድ ላይ ገደብ በማስመቀጣቸው አፍሪካን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷታል፡፡ እነዚህንና ሌሎችም መነሻዎችን ይዞ ኢምፔሪያል ኮሌጅ የተሰኘው ተቋም ኤፒድሚዎሎጂካል ሞዴል በመሥራት ያወጣቸውን አራት ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን የጤና ጉዳቶች በመላ ምት አስቀምጧል፡፡

ከአራቱ መላምቶች አንደኛው የኮሮና አደጋ አስከፊ ሊሆን ይችላል ከሚል ግምት የሚነሳና በአፍሪካ ደረጃ ምንም ዓይነት የመከላከል ዕርምጃ ባይወሰድ ሊያጋጥም የሚችለው አደጋ ያሳያል፡፡ በዚህ መሠረት 1.23 ቢሊዮን ሕዝብ የኮሮና በሽታ ተጠቂ ሊሆን ይችላል ተብሏል፡፡ በዚህ ሳቢያ 22.5 ሚሊዮን ሕዝብ የአልጋ ቁራኛ ለመሆን፣ 4.4 ሚሊዮን ሕዝብ ለጽኑ ሕመም እንዲሁም 3.3 ሚሊዮን ሕዝብ ለሞት ሊዳረግ እንደሚችል በአስከፊ ግምት ውስጥ አስቀምጧል፡፡

ሁለተኛው የይሆናል ግምት፣ 842 ሚሊዮን ሕዝብ በበሽታው ተጠቅቶ፣ 16 ሚሊዮን ሕዝብ ለሆስፒታል ተዳርጎ፣ 3.1 ሚሊዮን ሕዝብ በጽኑ ሕመም መያዙ ሳያንስ፣ 2.4 ሚሊዮን ሕዝብ ሊሞት እንደሚችል ያመላክታል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው መጠነኛ የሰዎች ንክኪና የጥግጊት መቀነስ እንዲኖር ሲደረግ የሚኖር ውጤት ነው፡፡ ሰዎች ጥግግትን በመቀነሳቸው ምክንያት የበሽታው ሥርጭት እስከ 45 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ተገምቷል፡፡

ሦስተኛው የሊሆን ይችላል ግምት፣ 520 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በበሽታው ቢያዝ፣ 9.9 ሚሊዮኑ ለሆስፒታል፣ 1.9 ሚሊዮን ለጽኑ ሕመም፣ 1.5 ሚሊዮን ሕዝብ ለሞት እንደሚያሠጋው አስቀምጧል፡፡ አስገዳጅ የሰዎች ጥግግትን የማስቀረት ዕርምጃ በመውሰድ የበሽታውን ሥርጭት እስከ 75 በመቶ መቀነስ ቢቻል ሊኖር የሚችል የበሽታው ጉዳት በዚህ ደረጃ ነው የተገመተው፡፡ የሰዎች ጥግግት በዚህ ደረጃ ቀነሰ ማለት 100 ሺሕ ሰዎች ውስጥ በሳምንት ሁለት (1.6 በአኃዛዊ ቋንቋ) ሰው ብቻ ሊሞት እንደሚችል በቀረበ ግምታዊ ሥሌት መሠረት መሆኑ ነው፡፡

አራተኛው ሊሆን ይችላል ግምት፣ 123 ሚሊዮን የአፍሪካ ሕዝብ ለበሽታው ተጋልጦ፣ 2.3 ሚሊዮን ሆስፒታል ገብቶ፣ 500 ሺሕ በጽኑ ታሞ፣ 300 ሺሕ ለሞት እንደሚዳረግ የሚያስብ ነው፡፡ መራራቅና የሰዎችን ጥግግት በአስገዳጅ ሁኔታ መቀነስ ቢቻልና በሳምንት ውስጥ ሊመዘገብ የሚችለውን የሞት መጠን 100 ሺሕ ሰዎች መካከል ወደ 0.2 በመቶ ማውረድ ቢቻል ሊከሰት የሚችለውን የጉዳት መጠን አመላካች ግምት ነው፡፡

በአራተኛው መላምታዊ ግምት ደረጃ አፍሪካ በሽታውን ለመግታት ለጤና ክብካቤ ብቻ 44 ቢሊዮን ዶላር  ያስፈልጋታል፡፡ በመጀመርያው መላምታዊ ግምትና የበሽታ ሥርጭት ግምት ከተሰላ ግን 446 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ የሕክምና አቅርቦት ወጪ ይጠይቃል፡፡ ከሁለተኛው ግምት አኳያ 335 ቢሊዮን ዶላር ሲያስፈልግ፣ በሦስተኛው ግምት መሠረት ከታሰበ ደግሞ 189 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡

ለጤና ክብካቤ ከሚያስፈልገው ባሻገር 100 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ገንዘብ ለአስቸኳይ የኢኮኖሚ ማነቃቂያ አስፈላጊ እንደሆነ ያመላከተው ኢሲኤ፣ የኮሮና ቫይረስ ባደረሰው ተፅዕኖ ምክንያት የአፍሪካ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት 3.4 በመቶ ይልቅ 1.8 እስከ 2.6 በመቶ እንደሚቀንስ አስታውቋል፡፡ ይህ ከተከሰተም እስከ 27 ሚሊዮን ሕዝቦች ዳግመኛ ወደ ድህነት አረንቋ እንደሚያወርዳቸው ይጠበቃል፡፡ ይህንን አደጋ ለመከላከል አፍሪካ አገሮች የብድር ክፍያ ቢያንስ በሁለት ዓመታት እንዲራዘምላቸው ማድረግ የሚቻልበት ዕድል ያስፈልጋቸዋል፡፡ ተጨማሪ ገንዘብ ለግሉ ዘርፍ በማቅረብ ዜጎች ከሥራ ገበታቸው እንዳይፈናቀሉ ለማገዝ ይረዳቸዋል፡፡

የበሽታው መስፋፋትና ከፍተኛ ሥርጭት ያሳሰባቸው የበለፀጉ አገሮች በትሪሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ በመመደብ የሕዝባቸውን ጤና ከማስጠበቅ ባሻገር፣ ለማኅበራዊ ሴፍቲኔትና ለኢኮኖሚያቸው ማነቃቂያነት ሲመድቡ ታይተዋል፡፡ በአፍሪካ ይህ ቅንጦት ነው፡፡ በአራት ዋና ዋና ምክንያቶች አፍሪካ እንደ ሌላው ዓለም የተለጠጠ የአስቸኳይ ጊዜ በጀት መመደብ አልቻለችም፡፡ አንደኛው ከኢኖሚያቸው ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ድርሻ አኳያ ከፍተኛ የዕዳ መጠን መሸከማቸው አንዱ ነው፡፡ ከፍተኛ የበጀት ጉድለት ያለባቸው መሆናቸው ሁለተኛው ነው፡፡

ኢትዮጵያ 2.7 በመቶ በላይ ጉድለት አለባት፡፡ የበሽታው መስፋፋት የታክስ ገቢያቸውን ከሚጎዳባቸው አገሮች መካከል አንዷ ያደርጋታል፡፡ በዚያም ላይ ከፍተኛ የታክስ ዕፎይታዎችን፣ ቅናሾችንና ለውጦች በማደረግ በአንፃሩ ምርትና ገቢ እንዲጨምር ለማድረግ ሲሞክሩ ከሰነበቱ አገሮች አንዷ በመሆኗ፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ተጋላጭነት ያባብሰዋል፡፡ ሦስተኛው በከፍተኛ ወለድና የአገልግሎት ክፍያ መበደራቸው ነው፡፡ አራተኛው የመገበያያ ገንዘቦቻቸው የምንዛሪ ተመን በኢኮኖሚ መዳከም ሳቢያ (ዲፕሪሺዬት) ከዶላርና ከዩሮ አኳያ ሲታይ መዳከማቸው ነው፡፡

ቀጥተኛ ያልሆኑ ጉዳቶች ተብለው የተቀመጡት ኢኮኖሚያዊ ኪሳራዎችን በተመለከተ እንደሰፈረው፣ የፔትሮል ወጪ ንግድ 40 በመቶ ይቀንሳል፡፡ የጥሬ ብረት ማዕድን የወጪ ንግድ 12 በመቶ፣ የምግብ ሸቀጦች 11 በመቶ፣ የወርቅ ወጪ ንግድ ሰባት በመቶ፣ የጨርቃ ጨርቅ ወጪ ንግድ አራት በመቶ፣ እንዲሁም ሌሎች የወጪ ንግድ ምርቶች አቅርቦት 27 በመቶ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ተጋላጭነት

በዚህ ረገድ ናይጄሪያ ከሁሉም አገሮች ይልቅ ተጋላጭ ስትሆን፣ ኢትዮጵያም በጨርቃ ጨርቅ መስክ፣ በቱሪዝም፣ በአበባና ፍራፍሬ፣ በቡናና በሌሎችም ምርቶች ወጪ ንግድ ላይ ሊደርስባት የሚችሉ ጉዳቶች እዚህም እዚያም እየተጠቀሱ ተመላክተዋል፡፡ 122 ያላነሱ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ያሏት እንደመሆኗ፣ 37 ሺሕ በላይ በመደበኛና 450 ሺሕ በላይ መደበኛ ባልሆኑ መስኮች ከዘርፉ በሚያገኙት የገቢ ምንጭ የሚተዳደሩ ኢትዮጵያውያን የሥጋት ቀለበት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አብዛኛው የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ውጤት ወደ አውሮፓ ኅብረትና አሜሪካ ይላካል፡፡ ይህ አሁን ላይ የማይታሰብ እየሆነ፣ አብዛኞቹ ገበያዎችም ምርት መቀበል በማቆማቸው ኢትዮጵያና ኬንያ 65 በመቶ ገበያቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ አሥግቷል፡፡ ኬንያ ሰባት በመቶ የወጪ ንግድ ድርሻዋን ከጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ስትሸፍን፣ ኢትዮጵያ የአራት በመቶ የወጪ ንግድ ምርቷ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ነው፡፡ የሞሪሺየስ 33 በመቶ የወጪ ንግድ ምርት የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ይሸፍናል፡፡

አበባ ፍራፍሬና አትክልት 200 ሚሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ ሲያስገኝ፣ በኬንያ 700 ሚሊዮን ዶላር ያስገኝ ነበር፡፡ ይህም አደጋ ውስጥ ወድቋል፡፡ 200 ሺሕ ዜጎች በኢትዮጵያ እንደተሰማሩበት የሚገመተው የሆልቲካልቸር ዘርፍ፣ 150 ሺሕ ዜጎች የሥራ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁ ሲገለጽ ሰንብቷል፡፡ 26 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ኸርብስ ላይ ለመሰማራት እንቅስቃሴ የሚያድጉበት፣ 46 የአገር ውስጥ፣ 76 የውጭ፣ እንዲሁም ሦስት የአገር ውስጥና የውጭ የንግድ አጋር ሆነው የሚሠሩበትና ልማት ባንክ በሰፊው በገንዘብ አቅርቦት የሚሳተፍበት መስክ ችግር ውስጥ በመውደቁ የመንግሥት ድጋፍ እንደሚያስፈልገው የአበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር መጠየቁ ይታወሳል፡፡ እስካሁንም 11 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ኪሳራ ያስተናገደው ዘርፉ፣ የባንክ ብድር ዕዳዎች ማራዘሚያና የወለድ ክፍያ እንዲነሳለት የተደረገ ዘርፍ ነው፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከዚህ ቀደም በፋይናንስ ሚኒስትሮች የቀረበውን 100 ቢሊዮን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ በእጥፍ አሳድጎ ባቀረበበት ሪፖርቱ፣ በአገሮች ላይ ሊደርስ ይችላል ያለውን ጉዳት ተንትኖ በማቅረብ አስቸኳይ ድጋፍ ለአፍሪካ ጠይቋል፡፡ ኢትዮጵያም በፊናዋ ሊደርስባት ስለሚችለው አደጋ በዚህም በዚያም እያለች ጥሪዋን አስተጋብታለች፡፡ ምላሹ እንደ በሽታው መስፋፋትና መሠራጨት ፍጥነት የጎደለው ከመሆኑ ባሻገር፣ ይህ ነው የሚባል ምላሽ የሰጠበት አካል ስለመኖሩ አልተሰማም፡፡

የቡድን 20 አገሮች የብድር ዕዳ ክፍያዎች ለጊዜው እንዲራዘሙ እንደሚያደርጉ ከማሳወቃቸው በቀር፣ የዓለም ገንዘብ ድርጅት አስቸኳይ ብድር በመልቀቅ ድጋፍ እንደሚሰጥ ከማስታወቁና ኢትዮጵያም ጥቂቱን ከማግኘቷ በቀር ያውም ከዚህ ቀደም ከኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ከተፈቀደው ሦስት ቢሊዮን ዶላር ላይ ታሳቢ የሚደረግ ድጋፍ ለመስጠት ካልሆነ በቀር ይህ ነው የሚባል አጣዳፊ ድጋፍ አልታየም፡፡

እርግጥ ነው ምሁራን እንደተቹት ቀድሞውንም ቢሆን የድጋፍ ጥሪው በበጎ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ እንጂ፣ ዕርዳታና ድጋፍ ሰጪዎችን ሊያስገድዳቸው የሚችልበት አቅም የሌለው በመሆኑ ከተጠየቀው ገንዘብ ውስጥ ጥቂቱ እንኳ መገኘቱ ትልቅ ዕድል እንደሚሆን ገልጸው ነበር፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች