Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለ400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ ላይ 134 ሚሊዮን ብር የዋጋ ጭማሪ የሰጡ ኩባንያዎች ጨረታ ማሸነፋቸው ቅሬታ አስነሳ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግዥ ተቋሙ የቀረበለት ቅሬታ እንደሌለና የዋጋ ልዩነቱም በአንድ የጨረታ ሒደት ላይ እንዳልታየ ገልጿል

መንግሥት በዚህ ዓመት እንዲገዛለት ካቀረበው 800 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ውስጥ 600 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ ጨረታ ባለፈው ሳምንት ወጥቶ፣ በተለይ ለ400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በቀረበው ዋጋ ላይ 134 ሚሊዮን ብር ወይም አራት ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ ስላለው ለአሸናፊዎች መሰጠት የለበትም የሚል ቅሬታ ተነሳ፡፡

በሁለት የተለያዩ የጨረታ ሥርዓቶች የ200 ሺሕና የ400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ ጨረታው በገንዘብ ሚኒስቴር መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ግንቦት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ተከናውኗል፡፡ የጨረታው አሸናፊዎች ማሸነፋቸው የተገለጸላቸውም ግንቦት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ነበር፡፡

በጨረታው ከተሳተፉ ኩባንያዎች መካከል ሦስት የውጭ አቅራቢዎች፣ 600 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴውን ለማቅረብ ያስገቡት የቴክኒክና የዋጋ ደረጃ ተገምግሞ አሸናፊ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ በዚህ መሠረት በመጀመሪያው ዙር በሁለት ምድብ ወይም ሎት የተካሄደው 200 ሺሕ ሜትሪክ ቶን (በእያንዳንዱ ምድብ 100 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ለግዥ ቀርቧል) ስንዴ ግዥ ጨረታ ላይ ከተሳተፉ አቅራቢዎች መካከል ዝቅተኛ ዋጋ ያቀረበው ጄምኮርፕ 202.33 ዶላር በቶን፣ እንዲሁም 204.97 ዶላር በቶን በማቅረብ አሸናፊ ሆኗል፡፡

ይሁን እንጂ ለ400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ የቀረቡት ዋጋዎች ከላይ ከቀረቡት አሸናፊ ዋጋዎች ይልቅ ከፍ ያሉ ሆነው በመገኘታቸው፣ ውድቅ ሊደረጉ ይገባቸዋል የሚል መከራከሪያ ያነሱ ወገኖች ቅሬታ አሰምተዋል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ሪፖርተር በደረሰው መረጃ መሠረት፣ ለ400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ ጨረታ በመጀመሪያው ሎት ላይ ዝቅተኛ ዋጋ ያቀረበው ኦላም ኢንተርናሽናል የተሰኘው ኩባንያ መሆኑ ሲገለጽ፣ በዚህ ምድብ 100 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለማቅረብ የሰጠው ዋጋ፣ በቶን 212.70 ዶላር ሒሳብ እንደሆነ ታይቷል፡፡ ለተቀሩት ሦስት የጨረታ ሒደቶች ማለትም 300 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለማቅረብ የተሰጡት ዋጋዎች፣ በቶን 219.35 ዶላር፣ 219.13 ዶላር፣ እንዲሁም 219.99 ዶላር ናቸው፡፡

ይህንን መነሻ በማድረግ ለ400 ሺሕ ቶን ሜትሪክ የቀረበው ዋጋ ለ200 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ከቀረበው ዝቅተኛ ዋጋ አኳያ፣ የአራት ሚሊዮን ዶላር ወይም የ134 ሚሊዮን ብር ጭማሪ የታየበት በመሆኑና የመንግሥትንም ጥቅም ስለሚያነሳ መሰረዝ አለበት የሚል ቅሬታ ተነስቷል፡፡ ለዚህ ቅሬታ ሌላው መከራከሪያ ደግሞ ሁለቱም ጨረታዎች በተለያየ ሰዓት ቢካሄዱም፣ ለሁለቱም ግዥዎች የቀረበው መሥፈርትና የማቅረቢያ ጊዜ ተመሳሳይ በመሆኑ ውጤቱ መሰረዝ አለበት የሚል አቋም ከቅሬታ አቅራቢዎቹ ወገን እንደተንጸባረቀ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ቅሬታ ያሰሙ አካላት የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 649/2001 አንቀጽ 30 መሠረት፣ ከዝቅተኛ ዋጋ በላይ ያቀረቡ ተጫራቾችን ውጤት የመሰረዝ ሥልጣን ያለው በመሆኑ፣ ከዚህ ቀደምም የ400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ጨረታን በዚሁ ምክንያት በመሰረዙ፣ አሁንም ላወጣው የግዥ ጨረታ የቀረበው ዋጋ ባስከተለው የ134 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ሒሳብ መሠረት ውጤቱ መሠረዝ አለበት ማለታቸው ታውቋል፡፡ ይህ ጉዳይ እንዲሁ መታለፍ እንደሌለበት በማሳሰብ፣ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ከምትገኝበት ችግር አኳያ በርካታ የልማት ሥራዎችን ልታከናውን የምትችልበት ገንዘብ፣ ለተጫራቾቹ ሲሳይ መሆን የለበትም የሚሉ አካላት ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህንኑ ቅሬታ በሚመለከት ሪፖርተር ለመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጥያቄ አቅርቧል፡፡ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፅዋዬ ሙሉነህም ሆኑ፣ በተቋሙ የግዥ ክፍል ዳይሬክተር ወ/ሮ አበባ ዓለማየሁ ለተቋሙ በይፋ የቀረበ ቅሬታ እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱም ጨረታዎቹ በተለያየ ማዕቀፍ የተካሄዱና ልዩነት ያላቸው በመሆኑ አንድ ዓይነት ዋጋ ሊቀርብባቸው እንደማይችል ያስገነዘቡት ወ/ሮ አበባ፣ ‹‹እስካሁን ምንም የቀረበ ቅሬታ የለም፡፡ ሆኖም የግዥ ሒደቱ በተለያየ ሎት የተካሄደ ነው፡፡ የአንዱን ሎት ዋጋ ከሌላው ሎት ዋጋ ጋር ማወዳደር አይቻልም፡፡ ከራሱ ጋር ብቻ ነው ማወዳደር የሚቻለው፤›› በማለት፣ በ200 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የስንዴ ግዥ ላይ በወጣው የሁለት ምብድ ጨረታ ላይም የተወሰነ የዋጋ ልዩነት እንዳለው አስታውሰዋል፡፡

‹‹እኛ ጨረታውን ስናወጣ ለግዥ አሠራሩ እንዲያመች፣ የተወሰኑ አቅም ያላቸው ተጫራቾች ብቻቸውን በሞኖፖል እንዳይዙት ለማድረግ ነው አራቱንም ሎት እንዲለያይ ያደረግነው፤›› ያሉት ወ/ሮ አበባ፣ የግዥ ሒደቱ በአንድ ጨረታ ምድብ ብቻ ተጨፍልቆ ቢካሄድ ኖሮ፣ ከፍተኛ ገንዘብና አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ የሚፈለገውን ውጤት ላያስገኝ ይችል ነበር ብለዋል፡፡ የግዥውን ጨረታ የተለያየ በማድረግ ተፎካካሪዎች እንዲበራከቱ በማድረግ መንግሥት የዋጋ ተጠቃሚነት ያገኛል ያሉት ወ/ሮ አበባ፣ የጨረታውም ሒደት በተለያዩ ምድቦች የተካሄደውም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

እንዲያውም ከጨረታ የሚገኘውን ጠቀሜታ ብቻም ሳይሆን ቅሬታዎችንም ጭምር ለመቀነስ የሚያስችል አዲስ አሠራር በመዘርጋት፣ ከዚህ ቀደም በአንድ ፖስታ ይቀርቡ የነበሩ የቴክኒክና የፋይናንስ ምዘና መሥፈርቶች በሁለት ዙር ተለያይተው፣ በመጀመሪያው ዙር የቴክኒክ ምዘናዎችና የፋይናንስ ምዘናዎች ተለይተው እንዲቀርቡ በማድረግ የጨረታ ሥርዓቱ ግልጽነት እንዲሰፍንበት የሚያስችል አሠራር፣ በ600 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ግዥ ሒደትም ይህ መተግበሩን ገልጸዋል፡፡ በግምታዊ ዋጋው 135 ሚሊዮን ዶላር ሊያስወጣ እንደሚችል ቀድሞ ሲገለጽ የነበረው የ600 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ በ128 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንዲፈጸም፣ ጨረታውን ላሸነፉ ኩባንያዎች እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች