Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ የባንክ ዕዳ የሚፈለግባቸው ሆቴሎች ለብድር ማራዘሚያ ጥያቄአቸው ምላሽ እየጠበቁ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብሔራዊ ባንክ ለሥራ ማስኬጃና ለሠራተኛ ደመወዝ 3.3 ቢሊዮን ብር ብድር ፈቅዶላቸዋል

የኮሮና ወረርሽኝ ከባድ ተፅዕኖ ያሳደረባቸው ሆቴሎች ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ የባንክ ዕዳ እንደሚፈልግባቸው በማስታወቅ፣ መንግሥት እስካሁን ከተሰጣቸው አዎንታዊ ምላሾች መካከል የአንድ ዓመት የብድር ማራዘሚያ ድጋፍ እንዲደረግላቸው በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ፣ የሆቴሎችና መሰል አገልግሎት አሠሪዎች ፌደሬሽን አስታወቀ፡፡

የሆቴሎችና መሰል አገልግሎቶች ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ፍትሕ ወልደ ሰንበት ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ እንደ መክፈያ ጊዜው የሚለያይ ቢሆንም በጠቅላላው ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ይሁን እንጂ በተከሰተው ወረርሽኝ ምክንያት በተቋረጠው የሆቴል ገበያና የኮንፈረንስ ቱሪዝም አገልግሎት ምክንያት ችግር ውስጥ ከገቡት መካከል፣ ለ1,200 ሆቴሎች ሥራ ማስኬጃና ከ142 ሺሕ በላይ ለሚገመቱ ሠራተኞቻቸው ለስድስት ወራት የደመወዝ ክፍያ የሚውል 3.3 ቢሊዮን ብር ብድር ተፈቅዷል፡፡ ይህ ከአራት ዋና ዋና ጥያቄዎች መካከል ምላሽ ያገኘው አንዱ ሲሆን፣ ቢያንስ ለአንድ ዓመት ብድር ከእነ ወለድ ዕዳው ሳይከፈል እንዲቆይ ይደረግ ለሚለው ጥያቄ የመንግሥት ምላሽ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡

ለአንድ ዓመት እንዲራዘም የተጠየቀው የብድር መጠን ምን ያህል እንደሆነ ዝርዝሩን አሁን ማስቀመጥ ቢቸግርም፣ ሆቴሎች ከያዙት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይልና ከወረርሽኙ ሥጋት አኳያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደነበሩበት መመለሳቸው እንደሚያጠራጥር አቶ ፍትሕ ገልጸዋል፡፡ 

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ስለሺ ግርማ ከዚህ ቀደም ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በኮከብ ደረጃ ለሚገኙ ሆቴሎች ለ100 አስገብኚ ድርጅቶች ከ2.5 ቢሊዮን እስከ ሦስት ቢሊዮን ብር የሚገመት የአንድ ዓመት የባንክ ብድር ዕዳ ክፍያ እንዲዘገይላቸው ጠይቀዋል፡፡ ባንኮች ለአንድ ዓመት ብድር ሳይከፈል እንዲቆይ ከማድረግ ባሻገር፣ የመክፈያ ጊዜ ላይም ማራዘሚያ እንዲሰጡ ፌደሬሽኑ ጥያቄ በማቅረብ ምላሽ እየተጠባበቀ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ የተወሰኑ ባንኮች በተናጠል ምላሽ እየሰጡ ነው፡፡ እንደ አዋሽ ባንክ ያሉት የሦስት ወራት የብድር ማራዘሚያ መፍቀዳቸውን ያወሱት አቶ ፍትሕ፣ እንዲህ ያሉት የሚበረታቱ ዕርምጃዎች ለዘርፉ ህልውና ሲባል በተጠየቀው ልክ ምላሽ እንደሚያስፈልጋቸው ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ይህ ይባል እንጂ በአገሪቱ የሚገኙ ሆቴሎችን፣ ሬስቶራንቶችንና ካፊቴሪያዎችን አካቶ ከ1,200 በላይ ለሆቴል ነክ አገልግሎት ሰጪዎች፣ መንግሥት ለአንድ ዓመት የሚውል 6.6 ቢሊዮን ብር የሥራ ማስኬጃ ብድር ያለ ወለድ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ነበር፡፡ መንግሥት በበኩሉ በስድስት ወራት ውስጥ የሚከፈል 3.3 ቢሊዮን ብር ብድር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኩል በማቅረብ፣ ከአምስት በመቶ በማይበልጥ ወለድ እንዲያቀርቡላቸው ለ17 የንግድ ባንኮች በደብዳቤ አሳውቋቸዋል፡፡ ከተፈቀደው 3.3 ቢሊዮን ብር ውስጥ ለሆቴሎች 2.9 ቢሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን፣ አስጎብኚ ድርጅቶች 600 ሚሊዮን ብር ጠይቀው ግማሹ እንደተፈቀደላቸው አቶ ፍትሕ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የታክስ ዕዳ ላለባቸው ሆቴሎችና አስጎብኚ ድርጅቶች የታክስ ዕዳ ምሕረት ማድረጉ በሌላ በኩል ሲታይ፣ ሆቴሎች ከጠየቁት በላይ ምላሽ ያገኙት በመንግሥት ድጋፍ እንደሆነ አቶ ፍትሕ ገልጸዋል፡፡ የታክስ ዕዳ የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘም ጥያቄ ቢቀርብም፣ መንግሥት የታክስ ዕዳ ምሕረት በማድረግ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ይህ በፌደራል ደረጃ ምላሽ የተሰጠበት በመሆኑ፣ ክልሎችም ተመሳሳይ ዕርምጃ እንዲወስዱ ፌደሬሽኑ ጥያቄ እያቀረበ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ የአማራ ክልል ከፌደራል መንግሥት ጋር ተመሳሳይ ዕርምጃ መውሰዱ ተሰምቷል፡፡

ከተከሰተው የኮረና ወረርሽኝ በተጨማሪ ለአራት ዓመታት በፖለቲካ ውጥንቅጥ ውስጥ የከረመው የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ፣ በዚህ ዓመት ማገገም እየጀመረ በሚገኝበት ወረርሽኙ ባስከተለው ጉዳት ሆቴሎች ከወደቁበት ለመነሳት የሚያስፈልጋቸው ወጪ ከፍተኛ እንዳይሆን፣ ከወዲሁ መዘጋጀት ያስፈልጋል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች