Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከ110 ሺሕ በላይ ዜጎች በጎርፍ አደጋ ተፈናቀሉ

ከ110 ሺሕ በላይ ዜጎች በጎርፍ አደጋ ተፈናቀሉ

ቀን:

ከ200 ሺሕ በላይ ዜጎች ከመካከለኛው ምሥራቅ ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል

ከመበደኛው መጠን በላይ እየጣለ በሚገኘው የበልግ ዝናብ ምክንያት፣ ከ220 ሺሕ ዜጎች በላይ መጎዳታቸውና ከ110 ሺሕ በላይ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ተገለጸ፡፡

ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ይፋ ባደረገው መሠረት፣ በበልግ ዝናብ ምክንያት በደረሰው የጎርፍ አደጋ ዜጎች ለሞት ተዳርገዋል፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለልዩ ልዩ ጉዳትና ለመፈናቀል መዳረጋቸውን፣ የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳመና ዳሮታ አስታውቀዋል፡፡ በጎርፍ ከተጎዱ አካባቢዎች መካከል በድሬዳዋ አራት ሰዎች ሞተው፣ 53 ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ከመፈርሳቸውም ባሻገር ከሁለት ሺሕ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ስለዚሁ ጉዳይ ለሪፖርተር ያብራሩት የኮሚሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበብ ዘውዴ፣ በኢትዮጵያ ከድርቅ ቀጥሎ ከባድ ጉዳት በማድረስ የሚታወቀው የጎርፍ አደጋ ነው፡፡ ጎርፍ በደቡብ ክልል በርካቶችን ለሕልፈት መዳረጉን አስታውሰዋል፡፡ በቅርቡም በስልጤ ዞን ሁለት ኪሎ ሜትር የሚደርስ ስፋት ያለው ስንጥቃት በጎርፍ ምክንያት መከሰቱን አስረድተዋል፡፡

ሚያዝያ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. በጣለው ዝናብ ሳቢያ በደረሰ የጎርፍ አደጋ፣ በድሬዳዋ ከተማ ከተጠቀሱት አደጋዎች በተጨማሪ 212 ቤቶች በከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በሰባት ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ 397 አባወራዎች ወይም ሁለት ሺሕ ገደማ ቤተሰቦች ለምግብ እጥረት ተጋልጠዋል ብለዋል፡፡

ሚያዝያ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. በጣለው ዝናብ በጂንካ ከተማ ነሪ የተሰኘው ወንዝ ሞልቶ በመፍሰሱ፣ በእንስሳትና በመሠረተ ልማት ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ በሶማሌ ክልል በሽንሌ ዞን፣ 15 ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ በውኃ መጥለቅለቃቸውን አቶ ደበብ  ገልጸዋል፡፡ ከ34,500 በላይ ሰዎች ጉዳት ሲደርስባቸው፣ ከ3,000 ሔክታር በላይ የአትክልት፣ የበቆሎና የሰሊጥ ማሳዎች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡ ከ200 በላይ የእርሻ ውኃ ማጠጫ ሞተሮች በጎርፍ ሲወሰዱ 1,200 ፍየሎች፣ ግመሎች፣ አህዮችና ሌሎች የቁም እንስሳት በጎርፍ ተወስደዋል ብለዋል፡፡

ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ፣ ከውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከወንዞች ተፋሰስ ባለሥልጣን ከሚመጡ መረጃዎች በመነሳት ትንበያዎች እንደሚወጡ የገለጹት አቶ ደበብ፣ በእነዚህ መረጃዎች መነሻነት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎችና የአደጋ ሥጋት ማሳሰቢዎች እንደሚለቀቁ አስረድተዋል፡፡ በዚህ መሠረት በግንቦት ወር ብቻ ተጨማሪ ከ21 ሺሕ በላይ ዜጎች የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እንደሚሆኑ፣ ከ19 ሺሕ በላይ ዜጎችም ከቤት ንብረታቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ኮሚሽኑ አስጠንቅቋል፡፡ አዲስ አበባና ድሬዳዋን ጨምሮ ደቡብ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ትግራይ፣ አፋርና ሐረሪ የጎርፍ አደጋ ሥጋት እንዳጠላበቸው ተነግሯል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ባወጣው ሪፖርት፣ በመጪዎቹ ሰባት ወራት ውስጥ ከ220 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ተባረው ሊመጡ እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡ ተቋሙ ይፋ እንዳደረገው፣ የኮሮና ቫይረስ ሥጋት መነሻ የሆነው የስደተኞች መፈናቀልና መመለስ አይቀሬ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በቅርቡ ከ9,400 በላይ ከስደት ተመላሾች በለይቶ ማቆያ ጣቢዎች፣ በተለይም በዩኒቨርሲቲዎችና መሰል ተቋማት እንደሚገኙ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም (አይኦኤም) ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ስደተኞችን ጨምሮ እስካሁን ከሁለት ሚሊዮን ዜጎች በላይ በኢትዮጵያ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ያስታወቀው የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ለመጪዎቹ ስድስት ወራት ከ220 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ እንደሚያስፈልገውም አስታውቋል፡፡

በጎርፍ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ተጠይቀው ከመግለጽ የተቆጠቡት አቶ ደበብ፣ ይልቁንም መንግሥት ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ከመጠለያ ጭምር በማቅረብ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ድርቅና ጎርፍ እየተፈራረቁ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ፡፡ በድሬዳዋ አስከፊውና አይረሴው የጎርፍ አደጋ ያስከተለው የሰዎች ሕይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት መድረሱ ይታወሳል፡፡ በሌላ በኩል በ2007 ዓ.ም. በደረሰው ድርቅ ሳቢያ 10.2 ሚሊዮን ዜጎች ለችግር መዳረጋቸው አይዘነጋም፡፡ በዚህ ወቅት መንግሥት 16.5 ቢሊዮን ብር በመመደብ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ማድረጉም እንዲሁ፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...