Thursday, June 20, 2024

የቀድሞ ሚኒስትር ለክቡር ሚኒስትሩ ስልክ ደወሉላቸው

[ለክቡር ሚኒስትሩ ደላላ ወዳጃቸው ስልክ ደወለላቸው]

 • በዛ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ?
 • የዚህ የበሽታ ነገር ነዋ፡፡
 • አልገባኝም?
 • በቁማችን ልትጨርሱን ነው እንዴ?
 • ምን እያልክ ነው?
 • ቤቴ ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ ነገር የለም እኮ፡፡
 • እየቀለድክ ነው?
 • እውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አንተ ከተማ ውስጥ የታወቅክ ደላላ አይደለህም እንዴ?
 • ብሆንስ  ታዲያ?
 • ማለቴ የዕለት ጉርሱን እንደሚፈልግ ሰው ቤቴ የሚላስ የሚቀመስ የለም ስትል ገርሞኝ ነዋ?
 • ክቡር ሚኒስትር በዚሁ ከቀጠልን ከእነ ልጆቼ መውጣቴ አይቀርም፡፡
 • ሠልፍ ነው የምትወጡት?
 • ኧረ ወደ ጎዳና ነው እንጂ፡፡
 • ትንሽ ግፍ አትፈራም?
 • ክቡር ሚኒስትር የእውነቴን ነው፡፡
 • አንተ እኮ ክቡር ደላላ ነህ፡፡
 • ማዕረጉ ምን ይጠቅመኛል ብለው ነው?
 • በማዕረግህ አይደል እንዴ ቢዝነስ የምትሠራው?
 • አሁን ሁሉም ነገር ቆሟል፡፡
 • በቃ ያጠራቀምከውን ተጠቀምበት፡፡
 • እሱ አይደል እንዴ እንቅልፍ የነሳኝ፡፡
 • እንዴት?
 • ገቢ የለም ወጪዬ ግን እየጨመረ ነው፡፡
 • ምን ታደርገዋለህ?
 • ስነግርዎት በዚህ መቀጠል አልችልም፡፡
 • ምን ይደረግ ታዲያ?
 • ሐሳብ መጥቶልኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የምን ሐሳብ?
 • ይኼ ወረርሽኝ በቀላሉ የሚፋታን አይመስለኝም፡፡
 • እሱ አይታወቅም፡፡
 • ስለዚህ በቁማችን ከማለቃችን በፊት የቻልነውን መፍጨርጨር አለብን፡፡
 • እኮ ምንድነው ሐሳብህ?
 • ከእርስዎ ጋር ተጣምረን መሥራት የምችላቸው ነገሮች አሉ፡፡
 • ምንድን ናቸው?
 • ያው አሁን ሁሉም ሰው ወደ ኮሮና ፊቱን አዙሯል፡፡
 • ሌላ  ነገር ምን አለ ብለህ ነው፡፡
 • ታዲያ ይኼ ለእኛ ጥሩ አጋጣሚ አይመስልዎትም?
 • ማለት?
 • በርካታ ጉዳዮችን ማስጨረስ እንችላለና፡፡
 • ምን ዓይነት ጉዳዮች?
 • የመሬት ቢሉ የታክስ ብቻ ሁሉንም፡፡
 • እ. . .
 • ክቡር ሚኒስትር ድምፃችንን አጥፍተን መሥራት ነው፡፡
 • ለመሆኑ በዚህ ወቅት መሬት ምናምን የሚፈልግ አለ?
 • ከፈለግን አይጠፋም፡፡
 • ስለዚህ?
 • ስለዚህማ እኔ ባለሀብቶችን ላፈላልግ እርስዎም ያመቻቹ፡፡
 • ምን ላመቻች?
 • መሬት ነዋ፡፡
 • ፈርቼ እኮ ነው፡፡
 • ምን ፈሩ?
 • ቀድመን መሬት እንዳንገባ!

[አንድ ባለሀብት ለክቡር ሚኒስትሩ ስልክ ደወለላቸው]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ?
 • ኧረ ምን እየታሰበ ነው?
 • ስለምን?
 • ስለበሽታው ነዋ፡፡
 • ምን ይታሰባል ብለህ ነው?
 • ግን ትክክል አልመሰለኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ?
 • እስካሁን 140 ሰዎች ናቸው እኮ በበሽታው የተያዙት፡፡
 • ተመሥገን ነዋ የሚባለው፡፡
 • በዚያ ላይ 75 እንዳገገሙ ተሰምቷል፡፡
 • ለዚያ እኮ ነው ተመሥገን ማለት ያለብን፡፡
 • ክቡር ሚኒትር ከ100 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ግን በሌላ በሽታ እየታመመ ነው፡፡
 • በምን?
 • በኢኮኖሚው ነዋ፡፡
 • ምን ይደረግ ብለህ ነው?
 • በቃ ትንሽ ለቀቅ አድርጉታ?
 • ምኑን?
 • እንቅስቃሴውን ነዋ፡፡
 • መዘናጋት አያስፈልግም፡፡
 • እንለቅ እንዴ ታዲያ?
 • መታገስ አለብን፡፡
 • ሁላችንም እኮ እኩል ልንሆን ነው፡፡
 • በምን?
 • በሀብት ነዋ፡፡
 • አልገባኝም?
 • እኛም የዕለት ጉርስ መፈለግ ልንጀምር እኮ ነው፡፡
 • ኧረ ሰው እንዳይሰማህ እባክህ?
 • ክቡር ሚኒስትር አካሄዳችን በጣም እያስፈራኝ ነው፡፡
 • ጭንቀትህ ይገባኛል፡፡
 • ሠራተኞች መቀነስ ልጀምር ነው፡፡
 • እሱንማ ማድረግ አይቻልም፡፡
 • እና ምን ልሁንልዎት?
 • መርሳት የሌለብህ ያለህን ሀብት ያገኘኸው በሠራተኞችህ ልፋት ነው፡፡
 • ታዲያ ሀብቴ ከዕለት ወደ ዕለት እየቀነሰ ነው እኮ፡፡
 • ቢሆንም ሁሉም ሰው እኮ ችግር ላይ ነው፡፡
 • መንግሥት ለምን አይረዳኝም?
 • መንግሥትማ የቻለውን እየረዳህ አይደል እንዴ?
 • ማለቴ ተጨማሪ ነገር ቢረዳኝ?
 • እኮ ምን ዓይነት ነገር?
 • ለምሳሌ ገቢዬ እንዲጨምር መሬቶች ቢሰጠኝ?
 • እ. . .
 • አዩ ሠራተኞቼን እንዳልበትን ይረዳኛል ብዬ ነው፡፡
 • አንተ እኮ አሁን ባለህ ሀብት ሠራተኞችህን ያለ ችግር ለዓመት ማሠራት ትችላለህ፡፡
 • ስነግርዎት ተጨማሪ ሥራዎችን ካልሠራሁ ሥራ ማቆሜ አይቀርም፡፡
 • እ. . .
 • ስለዚህ ሠራተኞቼን እንዳልበትን መንግሥት በአፋጣኝ ይርዳኝ፡፡
 • እንደገባኝ አንተን የያዘህ አንድ ነገር ነው፡፡
 • ምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ስግብግብነት!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ስልክ ደወለላቸው]

 • አካሄዳችሁ ትክክል አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የትኛው አካሄድ?
 • ምርጫው ይራዘም የሚለው ነዋ፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ምርጫው ከተራዘመ አገሪቱ ችግር ውስጥ ትገባለች፡፡
 • ይቅርታ አድርግልኝ፡፡
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • አንተ አልነበርክ እንዴ ምርጫው መራዘም አለበት ስትል የነበረው?
 • አሁን ሐሳቤን ቀየርኩዋ፡፡
 • ለምን?
 • ምርጫው ከተራዘመ ቀውስ ውስጥ የምንገባ ስለመሰለኝ፡፡
 • ለምን እንገባለን ነው እኮ ጥያቄዬ?
 • መንግሥት ሕጋዊ ስለማይሆን ነዋ፡፡
 • እኔ የምለው ግን. . .
 • እ. . . ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ከምርጫ በፊት ጤና አይቀድምም?
 • ክቡር ሚኒስትር እኛ ምርጫው ከኮሮና ጋር የሚያያዝ አይመስለንም፡፡
 • ወረርሽኙ እኮ ነገሮች እንደ ቀድሞ እንዲቀጥሉ አይፈቅድም፡፡
 • እኛ በሽታውን ሆን ብላችሁ ያመጣችሁት ነው የሚመስለን፡፡
 • ምን ይላል ይኼ በሽታው እኮ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ነው፡፡
 • ቢሆንም እናንተ አውቃችሁ እየተጠቀማችሁበት ነው፡፡
 • ለምንድነው የተጠቀምንበት?
 • የሥልጣን ጊዜያችሁን ለማራዘም ነዋ፡፡
 • እኛ እኮ ተመርጠን ነው ሥልጣን የያዝነው፡፡
 • እሱን እንኳን ተውት፡፡
 • በቀጣዩም ምርጫ እንደምናሸንፍ እርግጠኞች ነን፡፡
 • እሱ ህልም ነው ስልዎት፡፡
 • ለማንኛውም ምን ይደረግ ነው የምትለው?
 • ምርጫው መራዘም የለበትም ነዋ፡፡
 • እንዴት ይደረግ?
 • ለምን በኦንላይን አይደረግም?
 • እ. . .
 • ስብሰባ በኦንላይን ከተደረገ ቅስቀሳውስን በኦንላይን ማድረጉ ምን ይከብዳል?
 • ወይ ዘንድሮ?
 • የእናንተ ሐሳብ ሥልጣናችሁን ማራዘም እንደሆነ ደርሰንበታል፡፡
 • እኛም እኮ ሥልጣናችንን መልቀቅ የማንፈልገው እናንተን ስናስብ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • አሁን እንዴት ለአንተ ሥልጣን ይለቀቃል?
 • በምርጫ ነዋ፡፡
 • ምርጫ ይቅር እያልክ አይደል እንዴ?
 • ያው ሌላ ተለዋጭ ሐሳብ ስላለኝ ነዋ፡፡
 • የምን ሐሳብ?
 • ለምን በጋራ አናቋቁምም?
 • ምን?
 • የሽግግር መንግሥት ነዋ፡፡
 • እ. . .
 • ምን ችግር አለው?
 • ከእናንተ ጋር የሚቋቋመው መንግሥት የሽግግር መንግሥት ሳይሆን ሌላ ነው፡፡
 • ምን ዓይነት ነው?
 • የቀውስ መንግሥት!

[የቀድሞ ሚኒስትር ለክቡር ሚኒስትሩ ስልክ ደወሉላቸው]

 • የምን ጉድ ነው ያየነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምኑ?
 • ሰውየው ነዋ፡፡
 • እንዴት?
 • ሞቷል ብለን እያስወራን ነበር እኮ፡፡
 • አሁን ተነሳ፡፡
 • በዚህ አይቀለድም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምን?
 • ከእናንተ በላይ የእሱ ጉዳይ ነው እኮ ሌት ተቀን እንቅልፍ የሚነሳን፡፡
 • እናውቃለን፡፡
 • ደግሞ ለምን መጣ?
 • ሊጠይቀን ነዋ፡፡
 • ታዲያ በኦንላይን ለምን አትጠያየቁም?
 • በአካል መገናኘትስ ማን ይከለክለናል?
 • ኮሮና ነዋ፡፡
 • አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ነው፡፡
 • እየማሳችሁልን ነው እንዴ?
 • ምኑን?
 • መቀበሪያችንን ነዋ፡፡
 • እ. . .
 • ለማንኛውም በምትቆፍሩት ጉድጓድ ራሳችሁ እንዳትገቡ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እናንተ ምን ጉድጓድ እንደሚከታችሁ ታውቃላችሁ?
 • ምንድነው?
 • ሴራችሁ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት ሐዘን ለመድረስ ጎረቤት ተገኝተው ለቀስተኛው በሙሉ የሚያወራው ነገር አልገባ ብሏቸው ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ባለቤታቸውን ስለጉዳዩ እየጠየቁ ነው] 

ጎረቤታችን ሐዘን ለመድረስ ብሄድ ለቀስተኛው በሙሉ በሹክሹክታ ያወራል። ግን የሚያወሩት ነገር ሊገባኝ አልቻለም። ምንድነው የሚያወሩት? እኔ ምን አውቄ? እንዴት? የሚያወሩትን ምንም አልተሰማሽም? እኔ እንድሰማ የፈለጉ አይመስልም ግን ... ግን...

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት የሚታወጁ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ማለቴ ነው። ምን ታወጀ? አንዴ ከዕዳ ወደ ምንዳ አላችሁ፡፡ እሺ? የእሱን ውጤት እየጠበቅን ሳለ ደግሞ... እ...? ኢትዮጵያ ታምርት...

[ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን በተጀመረው አገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ስለተላለፉ መልዕክቶች በተመለከተ ከባለቤታቸው ጋር እያወጉ ነው] 

እኔ ምልህ? እ... አንቺ የምትይው? አለቃህ በምክክር መድረኩ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት አደመጥክ? አዎ፡፡ የሚገርም እኮ ነው አልተገረምክም? ምኑ ነው የሚያስገርመው? ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ምከሩና አምጡ ብለው የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ...