Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አርባ የልዩ ጣዕም ቡናዎች ለመጨረሻው ዓለም አቀፍ ውድድር ታጭተዋል

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአሜሪካው አሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ አዘጋጅነት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ ዝግጅት ሲደረግበት የከረመው የቡና ጥራት ውድድር፣ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በአሜሪካ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ከጥቂት ቀናት በፊት 40 የልዩ ጣዕም ቡናዎች ተለይተው ለዓለም አቀፍ ውድድር የታጩ ሲሆን ከሰኞ፣ ሚያዝያ 26 ቀን እስከ ሚያዝያ 29 ቀን 2012 ዓ.ም. በአሜሪካ፣ በእንግሊዝና በብራዚል በሚገኙ ስድስት ላቦራቶሪዎች ተልከው የጥራት ምዘናዎቹ የሚያስገኙት ውጤት ይፋ እንደሚደረግ አሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ በድረ ገጹ አስፍሯል፡፡ የቡናዎቹ ውጤት ይፋ የተደረገው፣ ወደ አሜሪካ ተልከው ከየካቲት 28 ቀን እስከ ሚያዝያ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደ ውድድር 40ዎቹ ቡናዎች ከ148 ናሙናዎች ተለይተው ለተከታዩ ዙር በማለፋቸው ነው፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ በተፈጠሩ የበረራ ክልከላዎችና በሎጀስቲክስ ችግሮች ምክንያት በአዲስ አበባ ሊካሄድ የነበረው የቡና ቅምሻ ውድድር ተሰርዞ በአሜሪካ እንዲካሄድ መደረጉ አይዘነጋም፡፡

አሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ ቀደም ሲል እንዳስታወቀው፣ በኢትዮጵያ ሊካሄድ የታቀደው የቡና ጥራት ቅምሻ ውድድር በዓለም አቀፍና በአገር ውስጥ ዳኞች አወዳዳሪነት እንዲካሄድ ሰፊ ዝግጅት ሲደረግበት ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ የቡና ጥራት ውድድሩ እንደታሰበው በኢትዮጵያ ሊካሄድ አልቻለም፡፡ በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛ የቡና ናሙና በማቅረብ የኢትዮጵያ ቡና አምራቾች ሪከርድ የሰበሩበትን ተሳትፎ ነበር፡፡

የኮሮና ቫይረስ ባሽመደመዳት ዓለም ወቅታዊ ሁኔታ ሳቢያ በኢትዮጵያ ዝግጅት ሲደረግበት የሰነበተው የቡና ጥራት ውድድር የዚሁ ጦሰኛ በሽታ ሰለባ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣንና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) በሥሩ በሚደገፈው ፊድ ዘ ፊውቸር ተቋም አማካይነት ዝግጅት ሲደረግበት የቆየው ይህ ውድድር በአሜሪካ፣ ፖርትላንድ እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡

የመጨረሻው የጥራት ውድድር በበረራ ክልለከላና በሎጂስቲክስ ችግሮች ምክንያት በኢትዮጵያ ባይካሄድም፣ ለውድድሩ የቀረቡ ናሙናዎች ወደ አሜሪካ ተልከው ነበር፡፡ በዚህም ከቀረቡ 1,450 በላይ ናሙዎች ውስጥ በቅድመ ልየታ 40 ቡናዎች ተለይተዋል፡፡ በላቦራቶሪ ተፈትሸው አሸናፊዎቹ ናሙናዎች ለባለቡናዎቹ እንዲገለጹ የሚደረግበት ተለዋጭ ዕቅድ እየተተገበረ ይገኛል፡፡

አሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ የሚያሳነዳው የቡና ጥራት ውድድር የኮሮና ሥጋት ቢያጠላበትም፣ ከፍተኛ የቡና ናሙና የቀረበበትና ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥም ለመጀመርያ ጊዜ የቀረበ ከፍተኛው አኃዝ እንደነበር ሲነገር ቆይቷል፡፡ በወረርሽኙ ሥጋት ምክንያት ግን በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን፣ በሌሎች ከአሥር ያላነሱ አገሮች ሊካሄድ የታቀደው የቡና ቅምሻ ውድድር የመሰረዝ ዕጣዎች እያጋጠሙት ይገኛል፡፡

ውድድሩ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ የተያዘለት ጊዜ መቅረቱና በአሜሪካ እንደሚካሄድ ይፋ በተደረገበት ወቅት የኮሮና ወረርሽኝ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በማጥቃት ከ60 ሺሕ በላይ ለሞት ዳርጎ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሦስት ሚሊዮን በላይ ቫይረሱ የተገኘባቸው፣ ከ250 ሺሕ በላይ ሰዎችን ለሞት አብቅቷል፡፡ አስከፊው ወረርሽኝ የዓለም ኢኮኖሚን በማሽመድመድ ላይ ይገኛል፡፡ ለዚህ ተግባር የሚጠበቁ ዳኞችን በሙሉ ማሳተፍ ባይቻልም፣ የተመረጡና ልምድ ያላቸው የዳኞች ስብስብ ከኢትዮጵያ የተላኩትን የቡና ናሙናዎች የጥራት ደረጃ ሲመዝኑ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ በጥራት ቅምሻ ውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ከጥር 25 ቀን እስከ ጥር 29 ቀን 2012 .. በጅማ፣ በሐዋሳ፣ በድሬዳዋና በአዲስ አበባ ለውድድር የሚቀርቡ ቡናዎችን ለመሰብሰብ በተደረገው ጥሪ 1,450 በላይ የቡና ናሙናዎች ወደ ማዕከላቱ ገቢ ተደርገው ነበር፡፡የባለ ልዩ ጣዕም ቡናዎች የጥራት ውድድር ላይ እስካሁን ከተመዘገበው ይልቅ ለመጀመርያ ጊዜ የታየና ከፍተኛ ቁጥር ያለው የቡና ናሙና በኢትዮጵያ መቅረቡን ያረጋግጣል፡፡

የጥራት ቅምሻ ውድድሩ በአሥራ አንድ ቡና አምራች አገሮች ውስጥ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ውድድሩ እ... 1999 በብራዚል ተጀምሮ፣ በኮሎምቢያ፣ በፔሩ፣በኤልሳልቫዶር፣ በኮስታሪካ፣ በኒካራጓ፣ በጓትማላ፣ በሆንዱራስ፣ በሜክሲኮ፣ በብሩንዲና በሩዋንዳ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት የዚህ ውድድርና የሽያጭ መርሐ ግብር ብቻም ሳይሆን፣ ከአገሪቱ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የቡና ምርትም ለሎጂስቲክስና ለጉዞ ክልከላ ችግሮች እንደሚጋለጥ ቀደም ብለው ሲነገሩ የነበሩ ሥጋቶች በተቃራኒው ዕድል ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በበሽታው ወረርሽኝ ሳቢያ በርካታ አገሮች የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች ላይ ገደብዕገዳ ቢጥሉም፣ የቡና ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን መንግሥት እያስታወቀ  ይገኛል፡፡ ላኪዎች የዘንድሮው የቡና የወጪ ንግድ ከባድ አጣብቂኝ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ሥጋት አድሮባቸው እንደነበር ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ በዚህ ዓመት ከ300 ሺሕ ቶን ያላነሰ የቡና ምርት ለውጭ ገበያ ቀርቦ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ሊገኝ መታቀዱ ይታወቃል፡፡

በቅርቡ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ይፋ ባደረገው መረጃ፣ በስምንት ወራት ውስጥ ለውጭ ከቀረበ ከ167 ሺሕ ቶን በላይ የቡና ወጪ ንግድ ከ465 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ መገኘቱን አስታውቋል፡፡ ከታቀደው የገቢ መጠን ከ100 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ቅናሽ አስተናግዷል፡፡

ባለሥልጣኑ ለሪፖርተር ልኮ በነበረው መግለጫ መሠረት፣ ለውጭ ገበያ የቀረቡት ቡናን ጨምሮ የሻይና የቅመማ ቅመም ምርቶች ሲሆኑ፣ በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት ውስጥ 176,249.80 ቶን የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ውጤቶችን በመላክ 577.70 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የዕቅዱን 100 በመቶ ያሳካበትን የ176,360.82 ቶን ምርት አፈጻጸም በማስመዝገብ የምርት አቅርቦቱን ቢያሳካም፣ በገቢ ረገድ ግን የሁሉም ምርቶች ውጤት ከ478 ሚሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱን 81 በመቶ ያህል ገቢ አስገኝቷል፡፡

ከዚህ አፈጻጸም ውስጥ የቡና ድርሻ በምርት ብዛት መጠን 167,132 ቶን ነበር፡፡በዕቅድና በአፈጻጸም ሲመዘን፣ ከ2011 .. ስምንት ወራት አኳያ፣ በመጠን ረገድ የ37,893.22 ቶን ወይም የ27.37 በመቶ፣ በገቢ በኩልም የ28.2 ሚሊዮን ዶላር ወይም 6.3 በመቶ ጭማሪ ማስመዝገቡ ተጠቅሷል፡፡

በስምንት ወራት ከተላከው የቡና ምርት ውስጥ 138 ቶን ቡና እሴት ተጨምሮበት ለውጭ ገበያ ሲቀርብ፣ ከገቢ አኳያም ከ900 ሺሕ ዶላር ገደማ  አስገኝቷል፡፡ ከ8,534 ቶን በላይ የቅመማ ቅመም ምርት ውስጥ 4,811 ቶን እሴት ተጨምሮበት ተልኳል፡፡ ቅመማ ቅመም ዘርፍ ካስገኘው የ11.653 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ውስጥ 4.44 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እሴት ተጨምሮበት ከተላከ ምርት የተገኘ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች