Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በገጠመን ችግር ምክንያት ፖሊሲዎቻችንን መከለስ ያስፈልገናል›› ተገኘወርቅ ጌጡ (ዶ/ር)፣ የቀድሞ የተመድ ዋና ጸሐፊ ረዳት

ተገኘወርቅ ጌጡ (ዶ/ር) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ረዳት፣ እንዲሁም በ170 አገሮች ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን የተመድ የልማት ፕሮግራም ተባባሪ አስተዳዳሪ በመሆን እ.ኤ.አ. ከ2015 እስከ 2019 አገልግለዋል፡፡ የተመድ የልማት ፕሮግራምን ዓለም አቀፍ የልማት ሥራዎችና እንቅስቃሴዎች መምራት ዋናው ኃላፊነታቸው እንደነበር የሥራ ታሪካቸው ያሳያል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2015 የተመድ ዋና ጸሐፊ ረዳት በመሆን የጠቅላላ ጉባዔና የኮንፈረንስ አስተዳደር ጉዳዮችን መርተዋል፡፡ በዚህ ኃላፊነታቸው ወቅት የተመድን ጠቅላላ ጉባዔዎች፣ የፀጥታውን ምክር ቤት ስብሰባዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ ጉባዔዎችንና ስብሰባዎችን ከማዘጋጀት ባሻገር የትርጉምና የገለጻ፣ የሰነድ ዝግጅትና መሰል የጉባዔ ሥራዎችን በኒውዮርክ፣ በጄኔቫ፣ በቪዬና፣ እንዲሁም በናይሮቢ በሚገኙት የተመድ መሥሪያ ቤቶች በኩል አስተዳድረዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በተመድ ውስጥ ከሠሩባቸው ኤጀንሲዎች መካከል ዋናው የተመድ የልማት ፕሮግራም ነው፡፡ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆኑት ተገኘወርቅ (ዶ/ር)፣ እ.ኤ.አ. ከ2009 እስከ 2013 የተመድ ዋና ጸሐፊ ረዳትነት ሚናቸው ላይ ደርበው የተመድ የልማት ፕሮግራም የአፍሪካ ዳይሬክተር፣ እንዲሁም የዚሁ ተቋም የጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ ብሎም የተቋሙ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር በመሆንም ሠርተዋል፡፡ በናይጄሪያ የዚሁ ተቋም ቋሚ ወኪል በመሆን እ.ኤ.አ. ከ2003 እስከ 2006 ከማገልገላቸውም በተጨማሪ የሴራሊዮን ተጠባባቂ ወኪል በመሆን እ.ኤ.አ. ከ1997 እስከ 1999 ሠርተዋል፡፡ በዚምባብዌም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሙያ በመሆን ረዘም ላለ ጊዜ ማለትም እ.ኤ.አ. ከ1989 እስከ 1997 ያገለገሉ ናቸው፡፡ ተመድን ከመቀላቀላቸው ቀደም ብሎ በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ፣ በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሮይቼስተር ረዳት ፕሮፌሰርና መምህር ሆነው ሠርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም አስተምረዋል፡፡ በጊዜው የፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ይባል በነበረው የአሁኑ የገንዘብ ሚኒስቴር ባልደረባም ነበሩ፡፡ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስና በፖለቲካ ከማግኘታቸውም ባሻገር፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነት መስክ ብሎም በኢኮኖሚክስና በፖለቲካ ሁለት የማስትሬት ዲግሪዎችን ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ በአፍሪካን ስተዲስ የጥናት ዘርፍም ሰርተፊኬት እንዳላቸውና የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በዴቨሎፕመንት አድሚኒስትሬሽን ዘርፍ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ በቅርቡ በጻፉት አንድ ሐተታዊ ትንታኔ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ሊደርስ ስለሚችለው ተፅዕኖ አስፍረዋል፡፡ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ 3.5 በመቶ ዝቅ እንደሚል፣ የሦስት ቢሊዮን ዶላር የክፍያ ሚዛን ጉድለት ሊያጋጥም እንደሚችል ትንበያቸውን አስፍረዋል፡፡ በዚህና በተጓዳኝ ሐሳቦች ዙሪያ ከሪፖርተር ጋር ያደረጉትን ቆይታ ብርሃኑ ፈቃደ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በጻፉት ጽሑፍ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ይጠበቅ ከነበረው ወደ ስምንት በመቶ ወደ 3.5 በመቶ ዝቅ እንደሚል፣ የአገሪቱ ንጥር የክፍያ ሚዛን (Net Balance of Payment) በሦስት ቢሊዮን ብቻ እንደሚርድ ግምትዎን አስቀምጠዋል፡፡ የዚህ ግምትዎ ሥሌት ምን ላይ እንደተመሠረተ ቢያብራሩልን?

ተገኘወርቅ ጌጡ (ዶ/ር)፡- የኢኮኖሚ ዕውቀት ያለው ሰው እንዲህ ያለ ግምታዊ ትንታኔ መስጠት ይችላል፡፡ ይህ ግምታዊ ሥሌትም ከማነበው፣ ከማየውና ከምረዳው ተነስቼ ያስቀመጥኩት ነው፡፡ የብዙዎች ግምት የኮሮና ቫይረስ ለስድስት ወራት ቢቆይ ተብሎ የወጣ ነው፡፡ በመንፈቅ ላይ ተመሥርቶ የቀረበው ግምትና አስተሳሰቡ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ትክክል አልመሰለኝም፡፡ ከስድስት ወራት አልፈን በዘጠኝ ወራት ወይም በአንድ ዓመት ዕይታ ውስጥ መመልከት መቻል አለብን፡፡ በዚያ መንገድ ካየነው፣ እስከ ምን ያህል ጊዜ ይቆያል የሚለውን እኔም በዚሁ አግባብ ለአንድ ዓመት በሽታው ቢቆይ ብዬ በማሰብ ነው ሥሌቱን የሠራሁት፡፡ ሌላው አሁን ባለንበት ሁኔታ በሽታውን እንቆጣጠረው ይሆን ወይ ብዬ ራሴን ስጠይቅ፣ የሚደረገውን ጠንካራ ቁጥጥር ሳልዘነጋ ከአንድ ወር ጥቂት እልፍ ብለን አሁን ላይ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ100 በላይ ሆነዋል፡፡ አሁንም ገና መነሻው አካባቢ ስለምንገኝ፣ የስድስት ወራት ግምት ማስቀመጥ ብዙም የሚያስኬድ አይመስለኝም፡፡ በኢትዮጵያ የበሽታው ሥርጭት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሊደርስ የሚችለው በሌሎች አገሮች ያለው ሥርጭት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ነው፡፡ አንዳንድ አገሮችና ከተሞች ኒውዮርክ ሳይቀር በሽታው እየቀነሰልን ነው፣ የተጎጂዎች ቁጥርም በመደበኛ ደረጃ ወይም ደልዳላ ሁኔታ ላይ ነው ይላሉ፡፡ እኛ ዘንድ የተለየ ሊሆን ይችላል፡፡ የኢኮኖሚ ሥርዓታችን፣ የሲቪል ሰርቪሱ ሁኔታ፣ የኢንተርኔትና የቴሌኮም ቀርፋፋ መሆንና ሌሎችም ጉዳዮች ተደማምረው ጉዳቱን በሚመለከት የሚቀርበውን የግምት ሥሌት እንዲጨምር ማድረግ ትክክል ይመስለኛል፡፡ ሌላው ጉዳይ የክፍያ ሚዛን ጉድለት ችግራችን ከባድ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ወደ ውጭ የምንልካቸው አንዳንድ ምርቶች መቀነሳቸውና ገቢ መታጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ የአበባ፣ የጨርቃ ጨርቅና መሰል ምርቶች ገበያ እየቀነሰባቸው ነው፡፡ የውጭ ሐዋላ ገቢ ይቀንሳል፡፡ የአየር መንገድ እንቅስቃሴና ገቢ ይቀንሳል፡፡ ከውጭ ሊገኝ የሚችለው ዕርዳታም ፈተና ይገጥመዋል፡፡ በዚህ ምክንያት የክፍያ ሚዛናችን ከዘጠኝ ወራት ንፅፅር አኳያ ስናየው ወደ ታች መውረዱ የማይቀር ነው፡፡ ለእኔ የሥሌት መሠረቱ ከእነዚህ ችግሮች የመነጨ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሌሎችም ትንበያዎች በባለሙያዎች እየወጡ ነው፡፡ ለአብነት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ለስድስት ወራት የሚቆይ ጫና ቢፈጠርና ኢትዮጵያም አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ የሚያስገድድ ሁኔታ ውስጥ ብትገባ፣ የኢኮኖሚዋን አሥር በመቶ ዕድገት ልታጣ እንደምትችልና የ200 ቢሊዮን ብር ኪሳራ ሊያጋጥማት እንደምትችል ትንበያ ሠርተዋል፡፡ ይህንን እንዴት ያዩታል?

ተገኘወርቅ ጌጡ (ዶ/ር)፡- ይህንን ትንበያ አላየሁትም፡፡ የ200 ቢሊዮን ብር የኢኮኖሚ ጉዳት ሊደርስ ይችላል ያልከውም ከምን መነሻ ምን ምን ታሳቢዎች ተካተው እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የእኔ ግምት ወግ አጥባቂ የሚባለው ወይም ‹‹ራዲካል›› ወይም ሥር ነቀል ዓይነትም አይደለም፡፡ ‹‹ሞደሬት›› ወይም መካከለኛውን ግምት ለመውሰድ እንዲያስችል ብዬ ያወጣሁት ነው፡፡ ሌሎችም ከግምት ውስጥ ያስገባኋቸው ጉዳዮችም አሉ፡፡ ለምሳሌ በእኛ ሁኔታ ገጠሩና ከተማው ተለያይቶ የሚኖር ነው፡፡ በፀባዩ የገጠሩ ክፍላችን አኗኗር ለይቶ ማቆያ ከሚባለው አሠራር ጋር የሚቀራረብ ነው፡፡ ተራርቆ የሚኖር ስለሆነ በከተማ እንደሚታየው ዓይነት ችግር እዚያ ላይታይ ወይም ላይበዛ ይችላል፡፡ ሥጋቴ ከከተማ ወደ ገጠር በሽታው እንዳይዛመት ነው፡፡ ይህንን መከላከል ከቻልን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የግብርና ኢኮኖሚ በመሆኑ፣ በአብዛኛው በገጠር አካባቢ በሚኖረው ሕዝብ የግብርና ውጤት ላይ የተመሠረተው የምርት ሒደት ብዙም እንደማይቀንስ ይጠበቃል፡፡ የግብርና ምርት ካልቀነሰ ደግሞ እንደ ገና አንጥሮ የሚያስነሳን ዕድል አለን ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳ የወጪ ንግዳችን፣ የክፍያ ሚዛናችንና የሐዋላ ገቢያችንን የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ቅናሽ ቢኖርም ወደ ከፋ ጉዳት ላንገባ የምንችልበት ዕድል አለን፡፡

ሪፖርተር፡- ግብርና እርስዎም እንዳሉት መንግሥትም ጉዳት የማይደርስበት ዘርፍ ነው ብሎታል፡፡ ነገር ግን ግብርናን ጨምሮ ከሦስቱ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች በተለይም አገልግሎትና ኢንዱስትሪ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች በመንግሥትም ተተንትነዋል፡፡ ይህንንስ እንዴት ቃኝተውታል?

ተገኘወርቅ ጌጡ (ዶ/ር)፡- ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ አገልግሎት ዘርፉ ይጎዳል፡፡ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ቱሪዝም፣ አስጎብኝ ድርጅቶችና ግለሰቦች፣ ታክሲዎች፣ የግል ንፅህናና ውበት መጠበቂያ ሳሎን ወይም ፀጉር ቤቶች ብሎም በየመንደሩ ያሉ ትንንሽና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ይጎዳሉ፡፡ ጨከን ያለ ጉዳት ያጋጥማቸዋል፡፡ ሆቴልና ሬስትራንት ከጠቅላላ ኢኮኖሚው ያላቸው ድርሻ 2.6 በመቶ ገደማ ነው፡፡ የግብርና ድርሻ ከ76 በመቶ በላይ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው 20 በመቶ ገደማ ነው፡፡ በመሆኑም ጠቅላላ የኢኮኖሚ መነቃነቅን የሚያስከትል ጉዳት የማድረሳቸው አዝማሚያ የተወሰነ ነው፡፡ ከኢንዱስትሪው ውስጥ ጉዳት ሊደርስበት የሚችለው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍም ኢከኖሚያዊ ድርሻው አራት በመቶ ነው፡፡ ትልቅ ከሚባሉ የአገልግሎት መስኮች አንዱ የአየር ትራንስፖርት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሊያጋጥመው የሚችለው ጉዳት ትልቅ ነው፡፡ እዚህ ላይ ግን አየር መንገዱ እየደረሰበት ያለው ጥቃት ትክክል ያልሆነና ከመስመሩ የወጣ በመሆኑ መስተካከል አለበት፡፡ ብቸኛው ዘመናዊና በዓለም ተወዳድሮ ስኬታማ መሆን የቻለ ድርጅታችን ነው፡፡ አንዳንዴ ፖለቲካዊ በሆነ ምክንያት ሌላ ጊዜም እንዲሁ መሠረት በሌለው ሁኔታ አየር መንገዱ ጥቃት ሲደርስበት እያየን ነው፡፡ አየር መንገዱ ወደ 500 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማጣቱን አስታውቋል፡፡ ይኼ አሳሳቢ ነው፡፡ በነገራችን ላይ አየር መንገዱ በደርግ ሥርዓት ውስጥ ሳይቀር በጫና ውስጥ ሆኖም እንኳ፣ ያለ ችግር መነሳትና ማረፍ የሚችል በፈጠራ አስተሳሰብ የተሞላ ድርጅት ነው፡፡ የተለያዩ አመራሮች ቢመጡም ድርጅቱ ግን በውጤታማነቱና በስኬታማነቱ ሲጓዝ የቆየ ነው፡፡ በታሪኩ ሦስት ጊዜ ብቻ ነው ኪሳራ የደረሰበት፡፡ ሌሎች እንደ ቲደብሊውኤ፣ አሜሪካን ኤርዌይስ ያሉት የአሜሪካ አየር መንገዶች፣ እንደ ሉፍታንዛ ያሉት ሁሉ ችግር ሲገጥማቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ታሪክ እየሠራ የተጓዘ ድርጅት ነው፡፡ ሠራተኛው አገር ወዳድና ብሔራዊ ስሜት ያለው ነው፡፡ ሌላው ኢኮኖሚውን የሚያሠጋው የቱሪዝም ዘርፉ ነው፡፡ የዚህ ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ድርሻ አምስት በመቶ ገደማ ነው፡፡ አበባ 0.4 በመቶ ድርሻ አለው፡፡ ነገር ግን ከ150 ሺሕ በላይ ሠራተኞች ይዟል፡፡ ይህ ትልቅ ተፅዕኖ ቢኖረውም ጠቅላላ ኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ግን ይህን ያህል አይደለም፡፡ በአጠቃላይ እንዲህ ያሉትን ነጥቦች ስንመለከት ችግር የሚያጋጥማቸው ዘርፎች ላይ መንግሥት የማነቃቂያ ድጋፎች ማድረግ አለበት፡፡ በእኔ ግምት የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድኑ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን እየተከታተለ የሚሠራ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ የኢኮኖሚ ዘርፎች ሙሉ በሙሉ ጉዳት ላይ እንዳይወድቁ መከላከል ይቻላል፡፡ አነስተኛ ጉዳት ግን አይቀሬ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንዴት ነው ይህንን ችግር የምንወጣው ካልን፣ ድጋፍና ማነቃቂያ ድጋፎችን ማድረግ መሠረታዊ መፍትሔ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የድጎማና የማነቃቂያ ድጋፍ ሲነሳ እርስዎ ለዝቅተኛ፣ ለአነስተኛና ለመካከለኛ የንግድ ተቋማት፣ መደበኛ ባልሆነው የንግድ ዘርፍ ለሚንቀሳቀሱ መንግሥት ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ጽፈዋል፡፡ ምን ዓይነት ድጋፍ እንዴት ያድርግ እያሉ ነው?

ተገኘወርቅ ጌጡ (ዶ/ር)፡- ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ የምንላቸው ዘርፎች ቀድሞውንም በድጋፍ ሥርዓት ውስጥ የነበሩ ናቸው፡፡ ይህንን ማጠናከር ነው፡፡ መንግሥት በኢትዮጵያ ልማት ባንክ አማካይነት፣ ለአነስተኛ ኢንተርፕራይዞች፣ ለአነስተኛ የገንዘብ አቅራቢ ተቋማት፣ ለሴቶች ሥራ ፈጣሪዎች፣ ወዘተ. የሚሰጡ የሊዝ ፋይናንስና ሌሎችም የድጋፍ መስጫ ሥርዓቶች አሉ፡፡ እነዚህን አሻሽሎና አጠናክሮ የመደገፍ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገንዝቤያለሁ፡፡ በኮማንድ ፖስት የሚንቀሳቀሰውና የሪፎርም ፕሮግራሞችን የሚመራው አካል ይህንን ሥራ እያከናወነ ነው፡፡ ለምሳሌ ልማት ባንክን በማማከር እነዚህ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በምን መንገድ ድጋፍ ማግኘት እንደሚችሉ፣ እስካሁን ሲደረግ ከነበረው የበለጠ በምን አግባብ በርካታ ድጋፎች ባንኩ መስጠት እንደሚችል ጥያቄ ቀርቦለታል፡፡ ልማት ባንክ በአነስተኛ ኢንተርፕራይዞችና በሴቶች ለተደራጁ፣ በሊዝ ፋይናንስና መሰል ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ድጋፍ እንደሚሰጥ ይታወቃል፡፡ እስከ 30 ሚሊዮን የሚገመቱ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ዜጎች አሉ፡፡ ከእነዚህም ላነሱ ጥቃቅን ዘርፎች ደግሞ በየቀበሌው እስከ 500 ሺሕ ብር የሚደርስ የብድር ድጋፍ ያገኛሉ፡፡ ቁጠባም ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ብዛታቸው እስከ ሁለት ሚሊዮን ይገመታሉ፡፡ በእኛ አገር ያለው እውነታ ይህ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የድጋፍ ማዕቀፋችንን ማስፋፋት ይገባናል፡፡ ልማት ባንክ በራሱም በሌሎች ባኮችና አስነተኛ የገንዘብ አቅራቢ ተቋማትና ባንኮች አማካይነት የፋይናንስ ድጋፍ እየሰጠ ነው፡፡ አካታች በሆነ መንገድ እንዴት ይተገበራል የሚለው ግን አሁንም መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ የቀበሌዎቹ ችግር የለበትም፡፡

ሪፖርተር፡- መደበኛ ያልሆነ የንግድ ዘርፍ ድጋፍ ያሻዋል ሲሉ የተገነዘብኩት በራሳቸው ሥራ ፈጥረው፣ ጉልት የሚቸረችሩ፣ ቡና አፍልተው የሚሸጡ፣ ፀጉር ቤት የከፈቱና መሰሎቻቸውና መንግሥት እስከ ሦስት ሚሊዮን የሚገምታቸው ዜጎች ከፍተኛ ጉዳት የሚደርስባቸው ናቸው ተብለዋልና እርስዎም የጠቀሷቸው እነዚህን መስሎኝ ነበር፡፡

ተገኘወርቅ ጌጡ (ዶ/ር)፡- እነዚህንም ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ መደበኛ ባልሆነ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ናቸው ብለህ ገሸሽ ልታደርጋቸው አትችልም፡፡ ድጋፍ ይሻሉ፡፡ እስካሁን የነበረንን አሠራር እንደ ገና ከልሰን፣ ሙስና የተንሰራፋበትና ግልጽነት የጎደለውን አሠራር እየተቆጣጠርን ድጋፍ መስጠት አለብን፡፡ ይህን ሥራ ፖለቲካዊ ከማድረግ መቆጠብ አለብን፡፡ ይህ የኢኮኖሚና የአገር ጉዳይ ነው፡፡ በየሠፈሩ ልጆቻቸውን በጉያቸው ይዘው የሚነግዱትን ታያለህ፡፡ እነዚህን እንደሚገባው መድረስ ባይቻል እንኳ በየቀበሌው ያሉትን ትንንሽ ሱቆች ግን ማግኘትና መደገፍ ይቻላል፡፡ ተዘዋዋሪ ፈንድ በማቋቋም በዚያ መሠረት መደገፍ እንደሚቻል ልምዱ አለን፡፡ አንዳንዶቹ የሥራ ማስኬጃ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ጥሬ ዕቃ ያስፈልጋቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ የሥራ ደመወዝ የሚፈልጉ፣ ሌሎች ደግሞ ኪሳራቸውን መደጎም የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ስለዚህ እንደ ዕዳታቸው ተለይተው ድጋፍ የሚያገኙበትን መንገድ ለመፈለግ ቡድን አቋቁመን የድጋፍ ሥራ መሥራት አለብን፡፡ የጉዳቱን መጠን ሙሉ በሙሉ ባናስቀረውም፣ በከፊል መፍታት የምንችልበት ዕድል አለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ መስኮች የአስቸኳይ ድጋፍ በመንግሥት ይፋ ተደርጓል፡፡ የአምስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌ ከመታወጁ አኳያ ይህ ምን ያህል በቂ ነው? ምን ያህልስ ያስኬዳል?

ተገኘወርቅ ጌጡ (ዶ/ር)፡- በቂ ነው በቂ አይደለም ከሚለው ይልቅ፣ ማኅበራዊ ወጪ የሚደረግባቸው ጉዳዮች ቀድሞም ያሉ ናቸው፡፡ 20 ቢሊዮን ብር የአስቸኳይ ድጋፍ በጀት ተያዘ እንጂ ቀውሱ በየት አቅጣጫ ሊወስደን እንደሚችል ለማየት ጊዜው ገና ነው፡፡ መንግሥት ግብረ ኃይል አቋቁሞ በየፊናው እየተመለከተው ነው፡፡ ቅድም እንዳነሳሁት አነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች እንዴት ድጋፍ ያግኙ በሚለው ላይ ልማት ባንክ እየተጠየቀ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ገንዘቡ ለመጀመርያ ደረጃ የተመደበ መጠባበቂያ ነው፡፡ ዋናው ወሳኙ ነገር አቅማችን ነው፡፡ እንዲህ ላሉት ሥራዎች መንግሥት ተጨማሪ በጀት መያዝ አለበት፡፡ ይጨምራል ብዬም አምናለሁ፡፡ ብልኃት በተላበሰ መንገድ ዕርዳታ እያሰባሰበ ይመስለኛል፡፡ እንደ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ እንደ ቻይና ያሉ አገሮች ዕርዳታ እየሰጡ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ለሁሉም ለመድረስ የሚያስችል በቂ ገንዘብ አይኖርም፣ ማግኘትም አይቻልም፡፡ ለተጠባባቂነት ከተያዘው ገንዘብ በተጨማሪ ምን ያህል ሊያስፈልግ እንደሚችል ከወዲሁ ማሰብና ማቀድ ተገቢ ነው፡፡ ሌላው ከውጭ የሚመጡትን ዕርዳታዎች በአግባቡ ባለው ላይ እየጨመሩ መሄድ ነው፡፡ ከአገር ውስጥ ሊሰባሰብ የሚችለውን ሁሉ መሰብሰብ መቻል ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን በጣም አሳሳቢ ነገር ሲፈጠር፣ በማንኛውም አገር እንደሚደረገው ብሔራዊ ባንካችን የፋይናንስና የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት መዘጋጀት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ዓለም ባንክ ያሉ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የአስቸኳይ ጊዜ ብድር ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቀዋል፡፡ እንደ ቡድን 20 ያሉትም የዓለምን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት አምስት ትሪሊዮን ዶላር መድበዋል፡፡ በቅርቡም የደሃ አገሮች የብድር ዕዳ ክፍያ ለጊዜው እንዲቆም ወስነዋል፡፡ ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሃ አገሮች በምን አግባብ እነዚህን ድጋፎች በአፋጣኝ ሊያገኙ ይችላሉ?

ተገኘወርቅ ጌጡ (ዶ/ር)፡- የእነዚህ ተቋማትና መሪዎቻቸውን አሠራር በሚገባ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ በአንደኛ ደረጃ አገሮቹም ሆኑ ተቋማቱ እንዲህ ያለ የድጎማና የድጋፍ ማዕቀፍ እያወጡ የሚገኙት የራሳቸውን ኢኮኖሚ ለመደገፍና ለማነቃቃት ነው፡፡ ከቀውስ ለመውጣት የሚያደርጉት ነው፡፡ አሜሪካ፣ ቻይና፣ አውሮፓ፣ ቡድን 20፣ ቡድን ሰባት፣ የዓለም ባንክና ሌሎቹም የመጀመርያ ትኩረታቸው በየራሳቸው ኢኮኖሚ ላይ ነው፡፡ ይህ እውነታ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በተሳሰረው የዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ገበያቸውና ለኢኮኖሚያቸው ጭማሪ የሚሆንና የተጠራቀመ ሀብት ላለማጣት ሲሉ የሚሰጧቸው ድጋፎች እንዳሉም ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ጀርመን የዓለም ገበያ ማዕከል ነች፡፡ አሜሪካ እንዲሁ የዓለም ኢኮኖሚ ማዕከል ነች፡፡ እነዚህ ግዙፍ አገሮች የዓለም ኢኮኖሚና ገበያ ከገባበት ቀውስ ቶሎ ካላገገመ እነሱም ችግር ውስጥ እንደሚገቡ በማሰብ ጭምር ነው ይህን የሚያደርጉት፡፡ ሌላው ጉዳይ ለታዳጊ አገሮች የሰብዓዊና የኢኮኖሚ ዕርዳታ ቢሰጣቸው መነቃቃቱን ለመደገፍ አጋዥ ይሆናል፡፡ የዓለም ኢኮኖሚ በቶሎ እንዲያገግም ያግዛል ከሚል የመነጨ ድጋፍም ነው፡፡ አሜሪካ ከሁለት ትሪሊዮን ዶላር በላይ የኢኮኖሚ ማነቃቂያ መመደቧ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ውስጥ 500 ቢሊዮን ዶላር ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚውል ነው፡፡ 58 ቢሊዮን ዶላር ለአየር መንገዶቻቸው የሚያውሉት ገንዘብ ነው፡፡ 29 ቢሊዮን ዶላር በድጎማ፣ ቀሪው 29 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ በብድር የሚሰጣቸው ነው፡፡ እኛ አየር መንገዳችን ይዘጋ እያልን እንጮሃለን እነሱ ግን ድጋፍ ያዘጋጃሉ፡፡ እያንዳንዱ አሜሪካዊ የ1‚200 ዶላር ድጋፍ፣ ቤተሰብ ሲሆን 2‚400 ዶላር፣ ልጆች ካሏቸውም ተጨማሪ 500 ዶላር ከመንግሥት ድጎማ ያገኛሉ፡፡ ይህ የሕዝቡ የኑሮ ሁኔታ ገቢ በማጣት እንዳይጎዳ የሚደረግ ድጋፍ ነው፡፡ ለሆቴልና መሰል ኢንዱስትሪው መደጎሚያ 100 ቢሊዮን ዶላር ድጎማ አስቀምጠዋል፡፡ ሥራ ለሌላቸው የሚሰጥ የድጎማ ድጋፍ እስከ አራት ወራት ድረስ የሚቆይ በየወሩ 600 ዶላር ደልድለዋል፡፡ ለንግድ ተቋማት የታክስ ዕፎይታ ሰጥተዋል፡፡ የአውሮፓ ኅብረትም እንደዚሁ ተመሳሳይ ድጋፍ አድርጓል፡፡ 37 ቢሊዮን ዩሮ በመመደብ ለዓለም ጤና ድርጅት፣ ሴኔጋል ለሚገኘው ፓስተር ኢንስቲትዩት፣ እንዲሁም ለግልና ለመንግሥት ተቋማት አጋርነት ድጋፍ የሚውል በርካታ ገንዘብ በመመደብ የኢኮኖሚ ማነቃቂያ እያደረጉ ነው፡፡ የቡድን 20 አገሮችም እንደጠቀስከው አምስት ትሪሊዮን ዶላር መድበዋል፡፡ ይህ የበጀት ፍሰት የዓለም ኢኮኖሚ የሚደርስበትን ተፅዕኖ ለመቋቋም ያደረጉት ሲሆን፣ ከዓለም ገንዘብ ድርጅት ጋር በመነጋገር አንድ ትሪሊዮን ብድር እንዲያቀርብም ስምምነት አድርገዋል፡፡ በማደግ ላይ ያሉ አገሮችም ልዩ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ እንዲያገኙ በቃል ደረጃ የሚናገሩት የድጋፍ መግለጫ ነው፡፡ በተግባር የሚታየው እንደ ሁኔታው የሚለያይ ነው፡፡ እነ ዓለም ባንክ ገንዘብ በነፃ እንደማይሰጡ መታወቅ አለበት፡፡ እርግጥ የተወሰነ ዕርዳታ ይሰጣል፡፡ የዓለም ገንዘብ ድርጅት ግን የክፍያ ሚዛን ድጋፍ የሚሰጥ፣ የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥም ተንቀሳቃሽ ገንዘብ የሚሰጥ ድርጅት ነው፡፡ በመሆኑም ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር ውስጥ ተቀናንሶ ለክፍያ ሚዛን የሚደጉም ገንዘብ አገሮች በድርድር ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ በቅርቡ 20 አገሮች የዚህ ዓይነት ድጋፍ ያለበት የዕዳ ማቃለያ ድጋፍ አግኝተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲያውም በዚህ ድጋፍ ኢትዮጵያ አልተካተተችም የሚለው መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡

ተገኘወርቅ (ዶ/ር)፡- ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም ምክንያት የክፍያ ሚዛን ድጋፍ ሰጥተውናል፡፡ ምናልባት በዚህኛው ድጋፍ ወቅት ተጨማሪ ድርድር ማድረግ ሊኖርብን ይችል ይሆናል፡፡ ከዚህ አኳያ ሊሆን ይችላል ያልተካተትነው፡፡ ድጋፉን ያገኙት አገሮች ግን አነስተኛ ኢኮኖሚ ያላቸው ትንንሽ አገሮች ናቸው፡፡ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ ወይም ኬንያ የሉበትም፡፡ እንደ ሩዋንዳና ብሩንዲ ያሉ አገሮች ናቸው፡፡ ይህ ሲባል ግን ትልልቆቹን አገሮች አይደግፉም ማለት አይደለም፡፡ ወደ እነሱም ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ዋናው ነገር ግን እንዴት ትደራደራለህ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ የዓለም ባንክም ለኢኮኖሚና ለማኅበራዊ ዘርፎች ነው የሚያበድረው፡፡ ይህም ቢሆን ቅድመ ሁኔታዎች የሚቀመጡበት የብድርና የዕርዳታ ድጋፍ ይመስለኛል፡፡ ይህ ፖሊሲያቸው ነው፡፡ ሁልጊዜ ዕርዳታ ተጠያቂ ከሆንክ እነሱም ከራሳቸው ሥሌት ተነስተው ስለሚመጡ፣ አንተ ለመቀበል በምትዘጋጅበት ወቅት ገንዘቡ የሚያስፈልግህ ለሞትና ለሽረት ጉዳይ ከሆነ አማራጭ አይኖርም፡፡ በቅድመ ሁኔታቸው መሠረት ትቀበላለህ፡፡ ለመደራደር የሚያበቃ ክፍተት ካለህ ግን የመከራከሪያ አቅምህን፣ ጥቅምና ጉዳትህን መዝነህ ትገባበታለህ ማለት ነው፡፡ ማሟላት የሚጠበቅብን ጉዳይ ይኖራል፡፡ አንድ ትሪሊዮን ዶላር እንሰጣለን ሲሉ ሁሉንም ይሰጣሉ ማለታቸው እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአፍሪካ በአስቸኳይ የ150 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዲሰጥ ጠይቀው ነበር፡፡ የአፍሪካ ፋይናንስ ሚኒስትሮችም የ100 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ለአፍሪካ እንዲለቀቅላት አሳስበው ነበር፡፡ ይሁንና ለእነዚህ ጥያቄዎች ቀጥተኛና ይፋዊ ምላሽ የሰጡ ብዙ አልታዩም፡፡ እርግጥ በቅርቡ የቡድን 20 አገሮች ለደሃ አገሮች የብድር ክፍያ እንዲዘገይ መወሰናቸው ተሰምቷል፡፡ የአፍሪካን ጥያቄ እርስዎ እንዴት ገመገሙት?

ተገኘወርቅ ጌጡ (ዶ/ር)፡- እኔ እንደማየው ጥያቄ ሳይሆን ድጋፍ ባይደረግ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ይባባሳል ከሚል መነሻ የቀረበ የመፍትሔ ሐሳብ ወይም ምክር ነው፡፡ ቅድም እንዳነሳሁት ገንዘብ እንዲሁ አይሰጡም፡፡ አገሮቹና ተቋማት ከ100 ወይም ከ150 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 500 ሚሊዮን ዶላር ቢገኝ ጥሩ ነበር፡፡ እርግጥ ነው 100 ቢሊዮን ዶላር እንደ ናይጄሪያ ወይም እንደ አንጎላ ላለ ትልልቅ ኢኮኖሚ እዚህ ግባ የሚባል ገንዘብ አይደለም፡፡ የተጠየቀው ገንዘብ በልገሳ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ቅድመ ሁኔታዎች ወይም ተቀጥላዎች አሉት፡፡ በነፃ የሚሰጥ ነገር የለም፡፡ ወይም ደግሞ ፔቲሽን በመፈረም የሚጠየቅም አይደለም፡፡ ዘመቻ በመክፈት ዓለም አቀፍ ጫና እንዲፈጠር ለመገፋፋት ትሞክር ይሆናል፡፡ አብዛኛው ነገር በብድር የሚሰጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የብድር ስረዛና ቅነሳ ጥያቄም በሰፊው ቀርቦ የተወሰነ ምላሽ ያገኘ ይመስላል?

ተገኘወርቅ (ዶ/ር)፡- ይህም ቢሆን በቀላሉ የማይሆን ነው፡፡ በእኔ ተሞክሮና ግምት መሠረት ካየሁት፣ አብዛኛው ብድር እየተከፈለ ሳያልቅ ቀሪው ላይ ብዙ ወለድ እየተከማቸ በቆየው ላይ ነው የዕዳ ስረዛ ሲያደርጉ የሚታዩት፡፡ አብዛኛውና ዋናው ብድር ግን ተከፍሏል፡፡ ከተሞክሮዬ የናይጄሪያን ጉዳይ እዚህ ላይ ላንሳ፡፡ በአንድ ወቅት አገሪቱ 60 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ነበረባት፡፡ አብዛኛው ዕዳ ሲከፈል ቢቆይም፣ መሪዎቿ በተቀያየሩ ቁጥርና ጥቂት መዘግየት ሲፈጠር በተቀረው ዕዳ ምክንያት የብድር ወለዱ ይጨምራል፡፡ ሦስት ወር ሳይከፈል የቆየ እንደሆነ መከፈል ያለበት ዕዳ መጠን ይጨምራል ማለት ነው፡፡ እንዲህ እየሆነ ዕዳው ተከማቸባቸው እንጂ ዕዳቸውን ከፍለው ጨርዋል፡፡ በአንድ ወቅት የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር ናይጄሪያም ከፍተኛ ክችምት ስላላትና በከፍተኛ መጠን መሸጥ በመቻሏ ደህና ሁኔታ ስለተፈጠረላት፣ ዕዳችንን ከፍለን እንገላገል ይሉ ነበር፡፡ የለም አንከፍልም፣ ምክንያቱም ከፍለን ጨርሰናል የሚሉ የመንግሥት ኃላፊዎችም ነበሩ፡፡ በወቅቱ በናይጄሪያ የተመድ ልማት ፕሮግራም ኃላፊ ስለነበርኩ እንክፈል ወይም አንክፈል ለሚለው ሙግት የሚረዳቸው ሐሳብ እንዲያገኙ ባለሙያዎች ቀጥሬላቸው ነበር፡፡ ይሁንና ከ60 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 30 ቢሊዮን ዶላር ከፍለው ሰርዘውላቸዋል፡፡ ይህ ግን ሽንጣቸውን ገትረው መከራከር በመቻላቸው የመጣ ነው፡፡ ይሁንና ደሃ አገሮች አብዛኛውን ዕዳቸውን ከፍለው ችግር እየገጠማቸው የተወሰነ ጊዜ ሲያቋርጡና ለመክፈል ሲቸገሩ፣ ዕዳቸው የባሰ እየተጠራቀመ ከከፈሉት በላይ እየተከማቸባቸው ለከፍተኛ ጫና ሲዳረጉ ይታያሉ፡፡ አበዳሪዎች ሲያበድሩም ለራሳቸው እንደ ኢንቨስትመንት ነው የሚቀጥሩት፡፡ እስካሁን ሲሰርዙ የቆዩት በጣም የሞቱ የብድር ዓይነቶችን ነው፡፡ ለምዕራብ አገሮች ወዳጃዊ ግንኙነትና መልካም አመለካከትና ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ያላቸው መንግሥታት ታሳቢ የሚደረግበት የተለየ ምልክታ አይጠፋም፡፡ ለምሳሌ ግብፅ በዓረቡ ዓለም ያላት ቦታ፣ በፍልስጤምና በእስራኤል መካከል የምትገኝ መሆኗ ብቻም ሳይሆን አሸማጋይነትም ስለምትሞክር በፖለቲካዊ አጀንዳ ተመራጭ አገር ሆና ድጋፍ ይቸራታል፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ከግምት ውስጥ ስለሚገቡ እንዲሁ በአንድ ጥቅል አካሄድ የዕዳ ስረዛ ይደረጋል የሚል ግምት የለኝም፡፡ ስለዚህ በድርድር ክህሎትና በጠንካራ ተደራዳሪ ቡድን ላይ የሚወሰን ሒደት ይሆናል፡፡ ናይጄሪያ በጣም ክህሎትና የመደራደር አቅም ያላቸው ኃላፊዎች ስለነበሯቸው ዕዳቸውን ማሰረዝ ችለው ነበር፡፡ የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም የናይጄሪያ ፋይናንስ ሚኒስትር የነበሩት ናይጄሪያዊት በጣም ክህሎት የነበራቸውና ቆፍጣና ተደራዳሪ ነበሩ፡፡ እነዚህን ነገሮች ከግምት ማስገባት ያለብን ይመስለኛል፡፡  

ሪፖርተር፡- ምሥራቅ አፍሪካ በድርቅ፣ በበረሃ አንበጣ፣ አሁን ደግሞ በኮሮና ቫይረስ መስፋፋት እየታመሰ የሚገኝ ቀጣና ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ምን ዓይነት መፍትሔ የሕዝቦችን ዕልቂት ሊታደግ ይችላል?

ተገኘወርቅ ጌጡ (ዶ/ር)፡- ምሥራቅ አፍሪካ በተለይም የአፍሪካ ቀንድ በጣም ከባድና ውስብስብ ችግሮች ውስጥ የከረመ አካባቢ ነው፡፡ የተቀናጀ ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ በየመን የሚከሰት ነገር እኛን ተፅዕኖ ውስጥ ይከተናል፡፡ የአንበጣውን መንጋ ካየን ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ እንደ ሱዳን ያሉ አገሮችም ወታደር በመላክና በመሰል ጣልቃ ገብነት ድርጊቶች ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ጫና ይፈጥራሉ፡፡ ስለዚህ የተቀናጀና አብሮ የመሥራት አካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት በራስ መተማመንን ይጠይቃል፡፡ ጥሩና መልካም አስተዳደርም ወሳኝነት አለው፡፡ አብዛኞቹ መንግሥታት ሙስና ያጨማለቃቸው በመሆናቸው የተጠናከረና የተናበበ ሥራ ለመሥራት አስቸጋሪ ነው፡፡ ከወዲሁ በቅደም ተከተል በመናበብ መሥራት ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የውጭ ድጋፍ በማግኘት ላይም አብሮ መሥራትና መተባበር ያስፈልጋል፡፡ በእኔ እምነት እንደ ግብፅ ያለ አገር የማበላሸት ሚና የሚጫወት ነው፡፡ ነገር ግን ሶማሊያን ልርዳ ሲል ወይም ደቡብ ሱዳን ሄዶ ወታደራዊ ሠፈር ልመሥርት ሲል ዓላማው ሌላ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ሁሉም አገር ከሚሰጠው ድጋፍ ጀርባ የየራሱ አጀንዳ አለው፡፡ ይኼንን በዕውቀትና በክህሎት መያዝ ያስፈልጋል፡፡ እንደ ደቡብ ሱዳን ያለ አገር አስቸጋሪ ነው፡፡ የነዳጅ ሀብት ያለው ብዙም ዕርዳታ የማይፈልግ አገር ቢሆንም፣ ሀብቱ እየተመዘበረና እየተዘረፈ የባሰውን ለሌሎች አገሮች ፈተና ይሆናል፡፡ አንዴ ከኤርትራ፣ ሌላ ጊዜ ከግብፅ ጋር እያለ ችግር ሲፈጥር የሚኖር መንግሥት ካለ የተቀናጀ ሥራ አብሮ መሥራት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ በቀጣናው ጠንካራ መንግሥት መኖር አለበት፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በቀጣናው ጥሩ የአመራርነት ሚናዋን እየተወጣች ነው፡፡ ከሱዳን፣ ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከኤርትራ ጋር ጥሩ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በኢኮኖሚ ጠንካራ በመሆን ጭምር ጥሩ መሪ አገር ለመሆን መጣር ያስፈልጋል፡፡ አንዳንድ ጎረቤት አገሮች ቀላል የማይባል ኪራይ ሰብሳቢነት ተጣብቷቸዋል፡፡ ጂቡቲ ብትሄድ ገበያ ወዳመጣለት ዞር ይላል፡፡ ጠንካራ አገር ከሆንክ ግን እንደ አመላቸው ለማስተናገድ የምትችልበት አቅም ይኖርሃል፡፡ ወደ አንድ ዓላማ ታመጣቸዋለህ፡፡ በእኛ በኩል እንዲህ ያለ አቅም አለመፍጠራችን ተጋላጭ አድርጎናል፡፡ ለምሳሌ አንበጣን የመቋቋም አቅም ሲታሰብ ከአሥር ወይም ከአሥራ አምስት በላይ አውሮፕላኖች ሊኖሩን በተገባ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ጄቶች ገዝታና ፓይለቶች አሠልጥና መዋጋት ከቻለች፣ ታንክን የመሰለ የጦር መሣሪያ መገጣጠምና መሥራት ከቻለች፣ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ (ሜቴክ) የመሰለ የቴክኖሎጂ፣ የባዙቃ፣ የጥይት ምርት ማምረት የሚችል ተቋም መመሥረት ከቻልን፣ አንበጣ ለመከላከል የሚችል አቅም ማጣት አልነበረብንም፡፡ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ የሚያስፈልገንን አቅም መገንባቱ ላይ ትኩረት አልሰጠንም፡፡ አሁንም ይህንን አቅም በመገንባት ችግሮችን ማቃለል ያስፈልጋል፡፡ በአንዴ ሳይሆን ቀስ በቀስ ነው አቅም የሚገነባው፡፡ ስትራቴጂካዊ በሆኑ ዘርፎች ላይ አቅም ለመገንባት ቅድሚያ መስጠት ያስፈልገናል፡፡ ኢትዮጵያ በምግብ እህል ራሷን ለመቻል የሚሳናት አይደለችም፡፡ በቂ ውኃና መሬት አላት፡፡ ነገር ግን የመሥራትና የመፈጸም አቅም ወሳኝ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በእነዚህ መስኮች ላይ አቅሟን አዳብራ ራሷን ችላ ብትገኝ ሌሎች በዙሪያዋ የሚገኙ አገሮችም ይከተሏታል፡፡ ኢትዮጵያም በለጋስነት መደገፍ ብትችል ትልቅ ለውጥ ይመጣል፡፡ ለምሳሌ ለጂቡቲ በለጋስነት ውኃና ኤሌክትሪክ ልትሰጣት ትችላለች፡፡ ይህ ሲሆን አብሮ ማደግና መለወጥ በማምጣት ቀጣናውን የተሻለ ማድረግ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- የከተማ ሴፍቲኔትና የዕለት ደራሽ ዕርዳታ አይቀሬ እየሆነ እንደሚመጣ እየታየ ነው፡፡ አብዛኛው አነስተኛ ነጋዴ ከሥራ ውጪ እየሆነ ነውና በከተማ አካባቢ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ተገኘወርቅ ጌጡ (ዶ/ር)፡- እንደ እኔ ከሆነ ባለው ላይ መገንባት ነው ተመራጩ አካሄድ፡፡ በአገራችን ዘንድሮ ያመረትነውን ሳይሆን ዓምና ያገኘነውን ነው ዘንድሮ ለፍጆታና ለመብል የምናውለው፡፡ ይህ በሆነበት ዓምና ያመረትነው ለዘንድሮ ከዋለ፣ የዘንድሮው ለመጪው ጊዜ እንዲውል ሲታሰብ፣ ሊጎድል የሚችለውንና መስተካከል ያለበት ከወዲሁ አመቻችቶና አቅዶ ለመጪው ጊዜ መጠባበቅ ይገባ ነበር፡፡ ተጋላጭ የሆነው የሕዝብ ቁጥር ወይም ከድህነት ወለል በታች በሆነ መንገድ የሚኖረው ሕዝብ 24 ሚሊዮን ያህል ነው፡፡ ከዚያ ውስጥ ስምንት ሚሊዮን በሴፍቲኔት የሚደገፍ ነው፡፡ ስድስት ሚሊዮን በተረጂነት መዝገብ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ስለዚህ 14 ሚሊዮን ሕዝብ በዕርዳታ ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኝ ነው ማለት ነው፡፡ የተቀረው አሥር ሚሊዮን ሕዝብ ነው፡፡ ይህ ከ30 እስከ 40 ሚሊዮን ኩንታል እህል እንደሚፈልግ ከግብርና ሚኒስቴር ሰዎች ተረድቻለሁ፡፡ ይህ ከሌሎች አስፈላጊ የምግብ ግብዓቶች ጋር ተዳምሮ ለአንድ ዓመት ፍጆታ የሚውል መጠን ነው፡፡ መንግሥት ፖሊሲ ቀርጿል፡፡ ሰፋፊ የመስኖ እርሻዎች ጀምሯል፡፡ ይህ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ገበሬው በደንብ እንዲያርስ መደገፍና ማበርታት ያስፈልጋል፡፡ በተቻለ መጠን ገበሬውን መጠበቅና በበሽታው እንዳይጠቃ መከላከል ያስፈልጋል፡፡ ከከተማ የሚሄደው በሽታ ይዞበት እንዳይሄድ የሚያስችል ሥራ ማከናወን ጠቃሚ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሬት ጦም እንዳያድር አውጇል፡፡ ባንክ በዕዳ ማስያዣነት የያዘው መሬት ቢኖረው፣ በአዋጁ መሠረት መሬቱ እንዳይታረስ ማድረግ አይችልም፡፡ የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ የእርሻ መሣሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መፍቀዱ፣ ያላቸውን መሬት ማረስ የማይችሉም ለሌሎች ማከራየት እንደሚችሉ ሕግ ወጥቷል፡፡ እንዲህ ያሉ ለውጦች እንዲተገበሩና እንዲሳኩ መረባረብ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ መንገድ የ30 እና የ40 ሚሊዮን ዜጎችንም ፍላጎት ማሟላት እንደሚቻል አምናለሁ፡፡ በዕርዳታ ላይ ጥገኛ ከመሆን መውጣት መቻል አለብን፡፡

 ነገር ግን ይህ እስኪሳካ በየከተማውና በየቀበሌው ከውጭ የሚገባውን ስንዴና ሌላውንም ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ተጎጂዎች በቶሎ ማዳረስ ተገቢ ይሆናል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግብርና ሚኒስቴር ከመስከረም ጀምሮ ለእርሻ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ሲያስገባ ቆይቷል፡፡ ማዳበሪያ ሲገባ ቆይቷል፡፡ አሁን በቂ ማዳበሪያ አለ፡፡ በመጪዎቹ ሁለት ወራት ውስጥ የተቀረው ሲገባ የማዳበሪያ ጉዳይ ለገበሬው ጥያቄ አይሆንም፡፡ ነገር ግን ሥርጭት ላይ ነው ጥያቄ ሊኖር የሚችለው፡፡ እዚህ ላይ በዘመቻ በመሥራት ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ብዙ ጉዳታችንን በማሳነስ ከመጣብን አስከፊ ችግር መዳን እንችላለን፡፡ በአጠቃላይ ግን በጀታችንን፣ የፊስካልና የሞኒታሪ ፖሊሲያችንን በገጠመን ቀውስ ምክንያት መለከስ ያለብን ይመስለኛል፡፡ በአገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ፕሮግራም ውስጥ የተቀመጡ የስኬት ግቦችን በዚህ ወቅት ማሳከት ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንት ይቀንሳል፣ ሐዋላ ይቀንሳል፣ የወጪ ንግድ ገቢ ይቀንሳል፡፡ የአገር ፍጆታና ወጪ ይጨምራል፣ ቁጠባ እየቀነሰ ይመጣል፣ የዋጋ ግሽበት ዛሬም ወይም ነገ መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ ብዙ ገንዘብ ወደ ገበያ ወይም ወደ ኢኮኖሚው እንዲገባ እየተደረገ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው የተፈጠረውን ችግር ለማለፍ የመንግሥት የፖሊሲ ክለሳ እንድናደርግ የሚያስገድዱን ይመስለኛል፡፡ እንደ መፍትሔ የጤናው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ዋናው ጉዳይ ሆኖ፣ ከገበሬው ጀምሮ የሠራተኞች ድጋፍ ትኩረት የሚሻ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የንግድ ተቋማት ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡ ለግሉ ዘርፍ ድጋፍ እየሰጠኸው በተራው የግሉ ዘርፍም ሊደግፍ ይገባል፡፡ የግሉ ዘርፍ ደጋፊ መሆን ካልቻለ ኢኮኖሚው ሲጎዳ አብሮ መሞቱ አይቀሬ ነው፡፡ ትልቅ የሲሚንቶ ፋብሪካ ያለው ኩባንያ ወይም ሌላ ድርጅት ሠራተኛውን ይዞ በማቆየት ካልደገፈ፣ ከመንግሥት ብቻ ድጎማ በመጠየቅ ከችግሩ አያመልጥም፡፡ እንዲህ በማድረግ ችግራችንን በጋራ መወጣት አለብን፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...