Thursday, April 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሁለት ሳምንት ውስጥ ከ600 ሺሕ ኩንታል በላይ የግብርና ምርቶች ለሸማቾች ተከፋፍለዋል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

20 ሚሊዮን ኩንታል የምርት ጭማሪ በመገኘቱ እጥረት እንደማይኖር ተገምቷል

የፌደራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ይፋ እንዳደረገው ሰው ሠራሽ የሆኑና ያልተገቡ የዋጋ ንረቶችን ለማስተካከል ያገዙ የምርት አቅርቦትና የሥርጭት ሥራዎች በመሠራታቸው ምክንያት፣ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ 628 ሺሕ ኩንታል የግብርና ምርቶች አዲስ አበባን ጨምሮ ለክልሎች መከፋፈላቸውን ገለጸ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦስማን ስሩር ሰኞ ሚያዝያ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አዳራሽ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ በኮሮና ምክንያት በተፈጠሩ የምርት አቅርቦት፣ ፍላጎትና ሥርጭት መዛባት ሳቢያ ሊፈጠሩ የሚችሉ አሳሳቢ ችግሮችን ቀድሞ ለመከላከል በሚያስችል ደረጃ የተቀናጁ 200 የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች ምርቶችን ከአርሶ አደሮች በማሰባሰብ ከክልል ክልል ባሻገር ወደ ከተሞች፣ ዞኖችና ወረዳዎች በማሠራጨት የዋጋ መረጋጋት ብቻም ሳይሆን፣ ጥራታቸው የተጠበቁና ትክክለኛ የሚዛን መጠን ያላቸው ምርቶች ለሸማቾች መቅረባቸውን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም መሠረት በሁለት ሳምንት ውስጥ 300 ሺሕ ኩንታል በቆሎ፣ 90 ሺሕ ኩንታል ስንዴ፣ 47 ሺሕ ኩንታል ጤፍ፣ 7,000 ኩንታል ፉርኖ ዱቄትን ጨምሮ፣ ጥራ ጥሬ፣ አትክልትና ፍራፍሬ የታከለበት በድምሩ ከ628 ሺሕ ኩንታል ያላነሰ የግብርና ምርት ለሸማቾች መከፋፈሉ ተገልጿል፡፡ በዚህ ሒደት 200 የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች፣ 5,500 የግብርና ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ 35 የከተማ ኅብረት ሥራ ዩኒየኖችና 1,200 መሠረታዊ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ዩኒየኖች በምርት ሥርጭት ሥራው ወቅት መሳተፋቸውን አቶ ኦስማን ገልጸዋል፡፡

ይህ ሥራ በብሔራዊ የምርት አቅርቦትና ሥርጭት ኮሚቴ በኩል ክትትል እየተደረገበት፣ አምራቾች ከሸማቾች ጋር ቀጥተኛ ትስስር እንዲፈጥሩ በማድረግ የምርት እጥረት እንዳይፈጠር ማድረግ እንደተቻለ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ ይህም ሆኖ የበሽታው መከሰት ከተገለጸበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ሥጋት በመፈጠሩ፣ ሸማቹ ከፍጆታ አቅሙ በላይ የግብርናም ሆነ ሌሎች የንፅህና ምርቶችን በገፍ እየገዛ ሲያከማች እንደነበር ያወሱት አቶ ኦስማን፣ በተለይ በግብርና ምርቶች ላይ በተፈጠረው በቂ የአቅርቦት ሰንሰለት ሳቢያ የሸማቾች የፍጆታ ፍላጎት እየተስተካከለ ለክምችት የሚደረገው ሽሚያም እየቀነሰ እንደመጣ አብራርተዋል፡፡

የአቅርቦት እጥረትንና የዋጋ ንረትን ለማስተካከል የተደረገው ርብርብ ጥሩ ውጤት እንዳስገኘ፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራቱም ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ያስታወቁት አቶ ኦስማን፣ እስከ ወረዳ ድረስ የሚዘልቅ የዘርፍ ግብረ ኃይል ተደራጅቶ፣ ከፌዴራል እስከ ክልሎች የሚተገበር የጋራ ዕቅድ በፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ በኩል ተዘጋጅቶ በመውጣቱ ወደፊት የሚሰበሰቡ የግብርና ምርቶችም ከሰሞኑ ሲደረግ በቆየው አግባብ እንዲሠራጩ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ምርቶችን ከኅብረት ሥራ ማኅበራት ውጭ በቀጥታ መግዛት ለሚፈልጉም ማቅረብ እንደሚቻል አክለው ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ጤፍ፣ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ጥራ ጥሬ፣ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ ሌሎችንም ያካተተ የ1.9 ሚሊዮን ኩንታል የግብርና ምርቶች ተሰብስበው ለሸማቹ እንደሚሠራጩ ይጠበቃል፡፡ ይህን ሥራ ለመሥራት ማኅበራቱ ያሉባቸው የፋይናንስ ችግሮች እንዲፈቱላቸው በሁሉም የመንግሥት መዋቅር በኩል ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኙ ተብራርቷል፡፡

‹‹የግብርና ምርት እጥረት ያጋጥመናል የሚል ሥጋት የለንም፡፡ በ2011/12 የምርት ዘመን ይመረታል ተብሎ በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ከተተነበየው የ329 ሚሊዮን ኩንታል ቅድመ ምርት የእህል ሰብል ምርት አኳያ የድኅረ ምርት ትንበያው 335 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መመረቱን አሳይቷል፤›› ያሉት አቶ ኦስማን፣ ይህ በመሆኑ ከዓምናው የግብርና ምርት አኳያ የ20 ሚሊዮን ኩንታል ተጨማሪ ምርት እንደተገኘ ያሳያል ብለዋል፡፡ ይህን ያህል ምርት በመኖሩ ምክንያት የጎላ የአቅርቦት እጥረት ሊከሰት እንደማይችል እምነት ማሳደሩም ተጠቅሷል፡፡

የምርቱ ዕድገት በአንድ በኩል እንዳለ ሆኖ የሥርጭት ሒደቱ ግን የኅብረት ሥራ ማኀበራትን ርብርብ እንደሚጠይቅ አሳስበዋል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን፣ በግብርና ኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካይነት የግብርና ምርቶች ላይ የሚካሄዱ የእሴት ጭመራ ሥራዎች በአሁኑ ወቅት እንዲስፋፉ እንደሚደረግ ተብራርቷል፡፡ ከስንዴ ዱቄት የሚያመርቱ፣ ከኑግና ሰሊጥ ዘይት የሚያመርቱ ኅብረት ሥራ ማኅበራት አቅማቸውን ለማሳደግ እየሠሩ ስለመሆናቸውም ተገልጿል፡፡ በአማራና በደቡብ ክልሎች ዘይት እያመረቱ ከሚገኙ ማኅበራት መካከል ‹‹ፀሐይ ዩኒየን›› የተሰኘው ኅብረት ሥራ ማኅበር በጎንደር፣ ‹‹ቅቤ ለምኔ›› የተሰኙ የምግብ ዘይት አምራቾች የኑግ ዘይቶቻቸው በተጠቃሚው ዘንድ ትልቅ ፍላጎትና ተቀባይነት በማግኘታቸው የበለጠ እንዲያመርቱ ድጋፎች እየተደረጉላቸው እንደሚገኙ ተጠቅሷል፡፡

መንግሥት የእነዚህን ማኅበራት ችግሮች በቅርበት በመፍታት ላይ መሆኑ የምርት ሥርጭት በሰው ሠራሽ ዋጋ ምክንያት ብሎም ሆነ ተብሎ በሚፈጠር የምርት መሸሸግ ችግር እንዳይከሰት ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ፣ ሕዝቡም የምርት አቅርቦትም ሥርጭትም ችግር እንደሌለ መረጃ እየተሰጠው በመሆኑ የጎላ ችግር አልተከሰተም ያሉት አቶ ኦስማን፣ ይህ ሥራ ባይሠራ ኑሮ ‹‹ከበሽታው የከፋ ሌላ ችግር ይከሰት ነበር፡፡ የሥነ ልቦና ችግር ይፈጠር ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ይባል እንጂ የዋጋ ጭማሪ ጎልቶ የታዩባቸው አጋጣሚዎች ተስተውለዋል፡፡ በተለይም በፋሲካ በዓል ዋዜማ ሰሞን የታየው ከፍተኛ ጭማሪ ተጠቃሽ ነው፡፡ በጋዜጠኞች እንደተነሳውም የዋጋ ጭማሪ ብቻም ሳይሆን የምርት እጥረት ጎልቶ እንደተስተዋለ የሸማቾችና የሻጮችን እሮሮ በማውሳት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በአንዳንድ የመንደር ገበያዎች የዶሮ ዋጋ ከ500 ብር ሲጠራበት ታይቷል፡፡ እንቁላልም የዋጋ ጭማሪ ታይቶበታል፡፡ የበግ፣ የፍየልና የበሬ ዋጋ ላይም የጎላ ጭማሪ እንደነበር በየገበያዎቹ ሲታይ እንደነበር የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች አመላክተዋል፡፡ የፍየልና የበግ ዋጋ እስከ 10 ሺሕ ብር ድረስ ሲጠራበት የተስተዋለው የፋሲካ በዓል ገበያ ላይ እጥረት እንዳያጋጥም በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚመራ ብሔራዊ የምርት አቅርቦትና ሥርጭትን የሚቆጣጠር ግብረ ኃይል ሲከታተለውና ሲገመገም እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ከፋሲካ በዓል አኳያ የዋጋ ጭማሪም የምርት እጥረትም ሆን ተብሎ ሊፈጠርባቸው እንደሚችሉ ተገምቶ ሲሠራ እንደነበር የጠቀሱት አቶ ኦስማን፣ በቁም እንስሳት አቅርቦት ላይ በበሽታው መስፋፋት ምክንያት አቅርቦት እንዳይስተጓጎል ከዚህ ቀደም ከነበረው ሒደት የተለየ አካሄድ መተግበሩን፣ አማራጭ የገበያ ቦታዎችና አካላትም የሥርጭት ሥራ መሠራቱን አስታውቀዋል፡፡

በበዓሉ ዋዜማ ወቅት ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንቁላል በኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካይነት እንደቀረበ፣ በዋጋ ደረጃም ከገበያ ዋጋ ባነሰ፣ የ50 ሳንቲም ቅናሽ ተደርጎበት ሲሸጥ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ዶሮም እንደሚፈለገው ልክ ባይቀርብም፣ ገበያዎች የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት በየቦታው ከመበተናቸው አኳያ የመረጃ እጥረት የፈጠረው የዋጋ ጭማሪ ካልሆነ በቀር የምርት እጥረት አልነበረም ብለዋል፡፡ ከበዓሉ ማግሥት በተካሄደ ግምገማም ይህ መታየቱን፣ ሸማቹ በአብዛኛው በለመዳቸው የገበያ አካባቢዎች ሄዶ የመስተናገድ አዝማሚዎች የፈጠሩት ክፍተት ካልሆነ በቀር፣ ዋና ዋና ምርቶች ላይ በሚፈለገው መጠን አቅርቦት እንደነበር ተገልጿል፡፡

በአገሪቱ ከ21 ሚሊዮን በላይ ግለሰብ አባላት ያሏቸው የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሌላም ድርብ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡ ከ90 በመቶ በላይ የግብርና ግብዓቶችን ማለትም እንደ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ ፀረ አረምና ፀረ ተባይ ኬሚካሎችንና ሌሎችም ግብዓቶችን ለገበሬው የማከፋፈል ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሚታየው የትራንስፖርትና የሌሎችም እንቅስቃሴዎች ዕገዳ ምክንያት እነዚህን ግብዓቶች ከውጭ የማስገባት እንቅስቃሴ ፈታኝ እንደሚሆን ይታያል፡፡ ይሁን እንጂ እስከ ቅርብ ጊዜ በነበረው መረጃ አብዛኛው የማዳበሪያ ምርት፣ 70 በመቶ ገደማ ወደ አገር ውስጥ በመግባቱ፣ ወደ ገበሬው በአፋጣኝ ተከፋፍሎ እንዲቀመጥና የእርሻ ጊዜ በወቅቱ እንዲጀመር ማሳሰቢያ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ አቶ ኦስማንም ይህንኑ ገልጸዋል፡፡

የግብዓት ሥርጭት በቶሎ እንዲፋጠን ለማደረግ ከዚህ ቀደም ይደረግ እንደነበረውና እንደተለመደው የምርት ዘመን ሲቃረብ ግብዓት ከመውሰድ ይልቅ አሁን ላይ በቶሎ በመውሰድ በቤቱ እንዲያከማች ለገበሬው ጥሪ ያቀረበው የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ፣ በበልግ ዝናብ አምራች የሆኑ እንደ ደቡብ ክልል ያሉ አካባቢዎችም የግብርና ሥራዎችን እንዲያጠናክሩ፣ የመስኖ እርሻ ዝግጅቶቻቸውም ከወዲሁ እንዲስፋፋ ኤጀንሲው አሳስቧል፡፡   

ከግብርና ምርቶች ባሻገር በኢንዱስሪ ምርቶች በተለይም ከወቅቱ ችግር አኳያ አስፈላጊ የሆኑ እንደ አልኮል፣ የእጅ ማፅጃ ኬሚካል ወይም ሳኒታይዘር ያሉ ምርቶችን ለማምረት የሚውሉ ግብዓቶች አቅርቦት ችግር በሰፊው እንደሚታይ ጥያቄ ቀርቦበታል፡፡ አቶ ኦስማን የእነዚህ ምርቶች እጥረት መከሰት ከችግሩ ድንገት መሆን ጋር እንደሚያያዝ፣ እነዚህ ምርቶች ቀድሞውንም ቢሆን በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውሉት በጤናው መስክና በተወሰኑ ዘርፎች አካባቢ እንጂ በአገር አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ ስላልነበሩ የምርት ሒደቱም በዚያው ልክ አነስተኛ እንደነበር አውስተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በርብርቦሽ ዩኒቨርሲቲዎች ሳይቀር ማምረት በመጀመራቸው የአቅርቦት ችግሩ እየተቃለለ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች