Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ የሚያገኙ አገልግሎት ሰጪዎች በርካታ ቋንቋዎችን እንዲጠቀሙ የሚያስገድድ መመርያ ተረቀቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አዲስ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን በኢትዮጵያ ፈቃድ አግኝተው የሚንቀሳቀሱ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪዎች ከአማርኛና ከእንግሊዝኛ ቋንቋዎች በተጨማሪ፣ አገልግሎታቸው በሚሰጥበት አካባቢ ላለው ማኅበረሰብ ተደራሽ በሆኑ ቋንቋዎች የአገልግሎት መረጃ መስጠት እንደሚገባቸው የሚያስገድድ ድንጋጌ የያዘ መመርያ አርቅቆ ለውይይት አቀረበ፡፡

ባለሥልጣኑ ባወጣው ‹‹የተጠቃሚዎች መብትና ጥበቃ መመርያ›› መሠረት፣ ከባለሥልጣኑ የቴሌኮም ፈቃድ የሚያገኝ ማንኛውም የተፈጥሮ ሰው ወይም ሕጋዊ ሰውነት ያለው አገልግሎት ሰጪ ስለሚሰጠው አገልግሎት ተጠቃሚዎች በሚገኙበት ቋንቋ የማሳወቅ ግዴታ ይኖርበታል፡፡ ይኼም መረጃ በኅትመትና በኤሌክትሮኒክ ይዘት ከክፍያ ነፃ መቅረብ እንዳለበትም ተመላክቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የአገልግሎቱን ተጠቃሚዎች መብት የሚደነግግ የሥነ ምግባር መርህ መዘጋጀት እንዳለበት የሚያመለክተው መመርያው አገልግሎት ሰጪዎች ደንበኞቻቸው ቅሬታ ሲኖራቸው እንዴት፣ መቼ፣ የትና ለማን ማቅረብ እንዳለባቸው ረቂቁ ይደነግጋል፡፡ አገልግሎት ሰጪው ፈቃድ ካገኘ በ90 ቀናት ለባለሥልጣኑ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ መቅረብ እንዳለበት ረቂቁ ያስረዳል፡፡

አገልግሎት ሰጪው ለተጠቃሚዎች የክፍያ መጠንና ሁኔታን የሚያስረዳ መረጃ ሳያወላዳ መሰጠት እንዳለበት በመደንገግ፣ የተጠቃሚዎች የክፍያ ታሪክ ቢያንስ ለ18 ወራት ተመዝግቦ እንዲቆይ ያስገድዳል፡፡

በተጨማሪም ከደንበኞች የሚሰበሰቡ መረጃዎች ምንነትና ለምን ጥቅም እንደሚውሉ፣ እንዲሁም ከየትኛው ሦስተኛ ወገን ጋር ልውውጦች እንደሚደረጉ የሚገዛ የደንበኛ ጥበቃ መመርያ ለደንበኞች የመረጃ አጠቃቀም የፈቃደኝነት መብት የሚያጎናፅፍ መሆን እንዳለበት የሚያመላክተው ረቂቁ፣ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃድ ያገኙ ድርጅቶች እንዲህ ያሉ መረጃዎችን ለሦስተኛ ወገን መሸጥ ወይም ማጋራት እንደሌለባቸውና ይኼንንም ለመጠበቅ ሲባል ስትራቴጂ መንደፍ እንደሚኖርባቸው ያመለክታል፡፡

ይሁንና በተለያዩ ምክንያቶች የባለፈቃድ አገልግሎት ሰጪ መረጃዎች ለጥቃት ወይም ለዝርክርክነት ከተጋለጡ ወዲያውኑ ለባለሥልጣኑና ለደንበኞች መገለጽ እንዳለበት፣ አፋጣኝ ዕርምጃ ተወስዶ ደንበኞችን ከጉዳት መከላከል እንደሚገባ ረቂቅ መመርያው ያስገነዝባል፡፡

ከዚህ የደንበኞች መብትና ጥበቃ መመርያ በተጨማሪ ባለሥልጣኑ የቅሬታ አፈታትና የአገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥ መመርያዎችን በማርቀቅ ለውይይት ክፍት ያደረገ ሲሆን፣ በአገልግሎቱ ሰጪዎች መካከልም ሆነ ከደንበኞች ጋር የሚፈጠር ቅሬታ ሲኖር ባለሥልጣኑ ራሱ ብቸኛ የቅሬታ ሰሚና ውሳኔ ሰጪ እንደሆነም ደንግጓል፡፡ ባለሥልጣኑም የተለያዩ ቅራኔዎች ተመሳሳይነት ካላቸው ወይም ፍላጎታቸው የሚገናኝ ከሆነ በጣምራ ሊመለከታቸው እንደሚችልም አስታውቋል፡፡

በሚስጥራዊነታቸው ምክንያት ጉዳዩ ለሕዝብ ተገልጾ በዝግ ካልተካሄደ በስተቀር የባለሥልጣኑ የቅሬታ ክርክሮች ለሕዝብ ክፍት እንደሚሆኑም ረቂቁ ያመላከተ ሲሆን፣ በውሳኔው ያልተደሰተ ሰው በ15 ቀናት ውሰጥ ይግባኝ ማለት ይችላል ይላል፡፡ ይሁንና ፍርድ ቤቶች የሚኖራቸውን ሚናና ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤቶች ሊሄድ የሚችልበትን ዕድል አላስቀመጠም፡፡

ለሚነሱ የትኞቹም ቅራኔዎች የተሰጡ ውሳኔዎች በባለሥልጣኑ ድረ ገጽ፣ ወይም በሌላ መንገድ የሚታተሙ እንደሆነም በመመርያው ተመላክቷል፡፡

ባለሥልጣኑ በአዋጅ ቁጥር 1148/2011 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የሚሰጣቸው ፈቃዶች የግለሰብ ፈቃድ፣ የዘርፍ (Class) ፈቃድ፣ የሬዲዮ ፍሪኩዌንሲ ስፔክትረም ፈቃድ፣ እንዲሁም አስፈላጊ ናቸው የተባሉ ሌሎች ፈቃዶች እንደሆኑ ሌላው መመርያ ያስረዳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች