Wednesday, June 7, 2023

አገራዊ ምርጫው በወቅቱ ሊካሄድ ባለመቻሉ አደባባይ ያወጣቸው ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

እንደ ቀደሙት አምስት አገራዊ ምርጫዎች ሁሉ በግንቦት ወር 2012 ዓ.ም. መደረግ የነበረበት መጪው ምርጫ በተለያዩ ምክንያቶች ተገፍቶ በነሐሴ ወር 2012 ዓ.ም. እንደሚደረግ ቀን ተቆርጦለት የነበረ ቢሆንም፣ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በሆነው የኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ይኼ ቀን ምርጫ እንደማይደረግበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ምርጫ ቦርድ በቫይረሱ ምክንያት የዘገዩ ሥራዎችን፣ እንዲሁም አማራጭ የምርጫ ቀናትን የጠቆመበትን የዳሰሳ ጥናት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. አስረክቧል፡፡ በዚህ የዳሰሳ ጥናትም ወረርሽኙን ለመግታት የተወሰዱ ዕርምጃዎች በኢትዮጵያ አየር መንገድ መጋዘን የሚገኙ የምርጫ ቁሳቁሶችን የማሸግ ሥራ መዘግየት፣ የኅትመት ውጤቶች ግዥ መዘግየት፣ የአሠልጣኞችና የምርጫ አስፈጻሚዎች ሥልጠና አለመከናወን፣ የታቀዱ የምክክር መድረኮች መስተጓጎላቸው፣ የኮሮና ቫይረስ የጥንቃቄ መልዕክቶች የመራጮች ትምህርትና ቅስቀሳዎችን እንዲዋጡ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ከግንዛቤ መግባቱ፣ እንዲሁም በመከላከያ ሠራዊት ዕገዛ መከናወን የነበረበት የቁሳቁሶች ሥርጭት መንግሥት ወረርሽኙን ለመከላከል ከመከላከያ ጋር ስለሚሠራ ተግዳሮት መፍጠሩ የምርጫ ሰሌዳውን ሊተገበር እንዳይቻል ምክንያት እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በዚህ ሳቢያ ቦርዱ ለፓርላማው በላከው የዳሰሳ ጥናት የወረርሽኙ መከላከል ዕርምጃዎች ለአራት ሳምንታት (አንድ ወር) ብቻ ከዘለቁ፣ ምርጫውን የተለያዩ ታሳቢዎች እንዳሉት ሆነው ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ማድረግ እንደሚቻል ያስረዳል፡፡

ይሁንና በዚህ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ምርጫውን ለማካሄድ በማያስችል ደረጃ የኮሮና ቫይረስ በሽታ መከላከል ዕርምጃዎች በአራት ሳምንታት ውስጥ ካልተጠናቀቁ አገራዊ ምርጫው በኅዳር መጨረሻ ወይም በታኅሳስ ወር 2013 ዓ.ም. መጀመርያ ይደረግ የሚል ምክረ ሐሳብ ያቀርባል፡፡ ይሁንና ለቫይረሱ መከላከል ሲባል የተጣሉ ገደቦች ከክረምት ወራት በኋላ የሚነሱ ከሆነ፣ ምርጫው በየካቲት ወር 2012 ዓ.ም. ይካሄድ የሚል ምክረ ሐሳብ አክሏል፡፡

ምርጫ ቦርድ አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫ ማከናወን ባለመቻሉ ምክር ቤቱ (ፓርላማው) መፍትሔ ይስጠኝ የሚለው ጥያቄው፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 መሠረት መንግሥት የሚመሠርቱ የሕዝብ ተወካዮች በአየምስት ዓመቱ እንደሚመረጡ የሚደነግገው ድንጋጌ ተግባራዊ እንደማይሆን፣ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ሥልጣኑ የሚያበቃው ፓርላማ ተተኪ እንደማይመረጥ ስለሚያመላከት ክፍተቱ እንዴት ሊታለፍ ይችላል የሚሉ ጥያቄዎች መደመጣቸው አልቀረም፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 56 መንግሥት የሚመሠረተው በሕዝብ ድምፅ አብላጫ ድምፅ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅቶች እንደሚሆኑ ስለሚደነግግም፣ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ዕጣ ፈንታስ ምን ሊሆን ይችላል የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡

ከዚህ ባለፈም ከአሁን ቀደም በአዳራሽ ብቻ ይደመጡ የነበሩ ጥያቄዎች ወደ አደባባይ መምጣታቸው አልቀረም፡፡ ለአብነት ያህልም በሥራ ላይ ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣን በሰኔ ወር በ30ኛው ቀን ሲያበቃ፣ አዲስ የሚመረጠው ምክር ቤት የሥልጣን ጊዜውን እስከሚጀምርበት የመስከረም ወር መጨረሻ ሳምንት ድረስ ያለው የሦስት ወራት ክፍተት ላይም የሚደረጉ ውይይቶች መደመጥ ጀምረዋል፡፡ ለምን? እንዴት? ለማን? ሲባል የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል፡፡

ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ የተባለው የጥናትና የምርምር ተቋም ባወጣው የኢትዮጵያ ምርጫና የኮሮና ወረርሽኝ ሁኔታን የሚተነትን ጽሑፍ ምንም እንኳን የተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገሪቱ ቫይረሱን በመከላከል ረገድ የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንደሚያበረታቱና አጋር እንደሆኑ ቢገልጹም፣ ምርጫ በማይደረግበት ሁኔታ በገዥው ፓርቲ ወረርሽኙን ምክንያት በማድረግ ከተቀመጠለት ጊዜ በላይ ሥልጣኑን ሊያራዝም  ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ጠቁሟል፡፡ ስለዚህም አሁን ያለው መንግሥት የሥልጣን ጊዜው ሰኔ 30 ቀን ሲያበቃ ወዲያውኑ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ይቋቋም የሚል ጥያቄ እንዳለም ያመላክታል፡፡

ከዚህ በዘለለ እንደ ኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የመሳሰሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ መንግሥት ወረርሽኙን ለመከላከል ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሽታውን ከመከላከል ባለፈ ለፖለቲካ ግብ እንዳይውል አሳስበዋል ሲል ክራይሲስ ግሩፕ አሥፍሯል፡፡

ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ይኼንን የወሳኝ ወቅት ችግር የሚፈቱበትን መንገድ ኢትዮጵያ ለምትገኝበት ነውጠኛ ሽግግር መሳካት ወሳኝ ሚና ይጫወታል በማለት፣ ‹‹ቦርዱ አሁን የምርጫ ደንቦችን ለማጠናቀቅና የምርጫ ጣቢያ ሠራተኞችን ለመመልመል ተጨማሪ ጊዜ ቢያገኝም፣ መንግሥት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የሚያስተዳድርበት ሁኔታና መሀል የሚመሠረተው ጊዜያዊ መንግሥት ሊኖረው የሚገባው ቅርፅ ላይ መግባባት እንዲኖር የማድረግ ችሎታው እጀግ በጣም ወሳኝ ይሆናል፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትና ተቃዋሚዎች የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ባይችሉና ምርጫው በመጪዎቹ ወራት እንዴት መደረግ እንዳለበት መግባባት ባይችሉ፣ ኢትዮጵያን ወደ ሌላ ብጥብጥ ውስጥ ሊከታት ይችላል፤›› በማለት ክራይስስ ግሩፕ ይደመድማል፡፡

ክራይሲስ ግሩፕ ያወጣው ሪፖርት ውስጥ የተጠቀሰው ‹‹ጊዜያዊ መንግሥት›› በተለያዩ ጊዜያት የተነሳ ጉዳይ ሲሆን፣ ቫይረሱ ከመከሰቱ አስቀድሞ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ምርጫ ማድረግ አትችልም በሚሉ ፖለቲከኞች ሲስተጋባ የቆየ ጉዳይ ነው፡፡

ለአብነት ያህል የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ብሔራዊ ምክር ቤት አባል አቶ ልደቱ አያሌው በተደጋጋሚ ሲሉት እንደነበረው በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም. በጽሑፍ እንዳሠፈሩት፣ የዕርቅና የአንድነት የሽግግር መንግሥት መቋቋም እንደሚያስፈልግ በመከራከር የለውጥ መንግሥት የሆነው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት ለብቻው አሻጋሪ ነኝ ማለቱን፣ እንዲሁም ሰላምና መረጋጋትን ማምጣት አለመቻሉን በመግለጽ ምርጫው በታቀደለት ጊዜ መደረግ እንደሌለበት ጠቅሰው ተከራክረዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ምርጫው ይደረግ ከተባለ አገሪቱ መመለሻ ወደሌለው ብጥብጥ እንደምትገባ፣ ይኼንን ለማስቆምም መንግሥት አምባገነን እንደሚሆንና ከዚህ ካለፈም አገር ሊበታተን እንደሚችል በመጥቀስ ሞግተዋል፡፡

ነገር ግን ይኼ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም እንደማይሆን በመጥቀስ የሚከራከሩ ፖለቲከኞች የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አስተዳዳር ሌላ አማራጭ እንዳሉት ያስቀምጣሉ፡፡ የመጀመርያው አማራጭ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 60 መሠረት ፓርላማውን በመበተን ለምርጫ የሚሆን ስድስት ወራት መግዛት ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 60 መሠረት ‹‹የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሄድ በምክር ቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱ እንዲበተን ለማድረግ ይቻላል፡፡›› በዚህ አንቀጽ መሠረት ምክር ቤቱ ከተበተነ አዲስ ምርጫ ከስድስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ መደረግ እንዳለበት በዚያው አንቀጽ ተደንግጓል፡፡

በእነዚህ ስድስት ወራት በሥልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የፓርቲዎች ጥምረት የዕለት ተዕለት የመንግሥት ሥራ ከማከናወን በዘለለ፣ ሕግ ማውጣትም ሆነ መሻር አይችልም ሲል ሕገ መንግሥቱ ደንግጓል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሕግ ባለሙያው አቶ አንተነህ ሙሉጌታ የሽግግር መንግሥት መጠየቅ ሞኝነት እንደሆነ በመከራከር፣ አንዱ በምርጫ አለመደረግ የሚመጣውን ክፍተት ለመድፈን ሊደረግ የሚችለው ለውጥ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል እንደሆነ ያሰምራሉ፡፡ በዚህም በአምስት ዓመታት የታሰረውን የሥልጣን ጊዜ በዓመት ወይም በሌላ ማራዘምና ምርጫውን ከዚያ በኋላ ማድረግ እንደሚቻል ያስገነዝባሉ፡፡ ለዚህም የፓርላማው ሁለት ሦስተኛ ድምፅና ከዘጠኙ ክልሎች የሁለት – ሦስተኛ (ስድስት) ድምፅ ማግኘት እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ፡፡ በዚህም ለፓርላማው የሥልጣን ቆይታ ጊዜ ማራዘሚያ ሥልጣን መስጠት እንደሚቻል ይጠቁማሉ፡፡

ይሁንና ሕገ መንግሥቱ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረጉ ድንጋጌዎችን የያዘ ባለመሆኑ ክፍተቶች እንደሚታዩበት የሚያስገነዝቡት የሕግ ባለሙያዎች፣ ከምርጫ በኋላም ሆነ በምንም ሁኔታ የሚደረግ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ማገዝ እንደሚችል ያሳስባሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -