Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ማራቶን ሞተርስ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ የ200 ሚሊዮን ብር የሽያጭ ገቢ ሊያጣ እንደሚችል ተገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኮሮና ቫይረስ ወይም ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የኢኮኖሚ ቀውስ ከሚያጋጥማቸው ዘርፎች አንዱ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ሲሆን፣ ከፍተኛ ኪሣራ ሊገጥመው እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

ይህ ወረርሽኝ በተለይ በተሽከርካሪ ሽያጭና በመገጣጠም ምርት ሥራ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎችን አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ በዓመት 10,000 ተሽከርካሪዎችን በአገር ውስጥ ገጣጥሞ ለገበያ የማቅረብ ውጥን ይዞ ሥራ የጀመረው ማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ፣ የ200 ሚሊዮን ብር የሽያጭ ገቢ ሊያጣ እንደሚችል የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መልካሙ አሰፋ ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡

የኮቪድ ወረርሽኝ በሰው ልጆች ህልውና ላይ የመጣ እንደመሆኑ፣ ዓለም አቀፉ ሃይንዳይ ኩባንያ ከ100 ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎችን ማምረት እንዳላስቻለው ሥራ አስኪያጁ ይናገራሉ፡፡

 የሃይንዳይ ወኪል የሆነው ማራቶን ሞተርስ በወረርሽኙ ምክንያት ለጊዜው መለዋወጫ በማቅረብና የተለያዩ አገልግሎቶችን ለደንበኞቹ በመስጠት ላይ እንደተወሰነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ቀደም ብሎ ከወደብ የገቡ የተሽከርካሪ አካላትን በመጠቀም አዳዲስ መኪናዎችን እየገጣጠመ እንደሚገኝ ዋና ሥራ አስኪያጁ አስታውሰዋል፡፡

በአንፃሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ መኪኖች ወደብ ላይ መቅረታቸውና ከኮሪያ የሚነሱና ከህንድ የሚጫኑ ቢኖሩም፣ በርካታ የዓለም ከተሞች ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴ በማቆማቸው የተጫኑት መኪኖች ባሉበት እንዲቆሙ መገደዳቸውን አቶ መልካሙ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ወደብ ላይ የሚጫኑ ኮንቴይነሮች መጥፋታቸውን ተከትሎ ዕቃውን በተፈለገው መጠን ማጓጓዝ አልተቻለም፤›› በማለት ስለችግሩ ገልጸዋል፡፡

ወደብ ላይ የተራገፉ ዕቃዎችን ወደ ከተማ በተሽከርካሪዎች ማንቀሳቀስ እንዳልተቻለም ጠቁመዋል፡፡ ከጉዕዝ ዕቃው ባሻገር የዶክሜንትና የባንክ ሒደቶችን መከወን እንዳልተቻለና የባንኮች ዝግ መሆን እንቅስቃሴውን ቀርፋፋ አድርጎታል ይላሉ፡፡

በአገር ውስጥ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዝግ በመሆናቸውና መንገድ ትራንስፖርትም ለተወሰነ ጊዜ ታርጋ መስጠት ማቆሙን ተከትሎ መኪኖቹ ለገበያ እንኳ ቢቀርቡ፣ ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ለደንበኛ ማቅረብ አለመቻሉም ተጠቅሷል፡፡

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የዓለም ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ኪሣራና ዝቅጠት እያጋጠመ ነው፡፡ በበርካታ አገሮች የሥራ አጥነት ቁጥር እየጨመረ ይገኛል፡፡ በአሜሪካ ብቻ እስካለፈው ሐሙስ፣ ሚያዝያ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ከ16 ሚሊዮን በላይ ሥራ አጦች ለድጋፍ ፍለጋ መመዝገባቸውን ዘገባዎች አሳይተዋል፡፡ የተለያዩ አገሮችም ችግሩን ለመፍታት የቢዝነስ ዘርፎችን በመለየት የድጎማ ገንዘብ እየበጀቱ ይገኛሉ፡፡

በወረርሽኙ የተነሳ በማኑፋክቸሪንግ፣ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች በከፍተኛ ኢኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ ከ750‚00 እስከ 1.5 ሚሊዮን በሚደርሱ ሠራተኞች ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

እንደ ጥናቱ ከሆነም፣ የቫይረሱ ሥርጭት ሁኔታና ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ መንገደኞች ላይ ገደብ መጣሉን ተከትሎ የሆቴል፣ የመጠጥና የምግብ አቅርቦት የሚሰጡ የንግድ ተቋማት ገበያ ማግኘት እንዳልቻሉ ሲገለጽ፣ በተለይ ሆቴሎች ባዶ በመቅረታቸው ሠራተኞቻቸውን በማሰናበት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

ሌላኛው ተጋላጭነቱ ሰፊ እንደሆነ የሚጠቀሰው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሲሆን፣ ግብዓት ከውጭ ማምጣት ካልተቻለ በርካታ ኩባንያዎች ከወደቁበት ላይነሱ እንደሚችሉ በርካቶች ሥጋታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ ከዚህ አኳያ መንግሥት የተጎዱ ዘርፎችን በመለየትና በመደጎም ከቀውሱ ሊታደጋቸው እንደሚገባ አቶ መልካሙ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹መንግሥት የትኛው ዘርፍ ምን ያህል እንደተገፋ መለየት ይኖርበታል፤›› ብለዋል፡፡

ከወራት በፊት ማራቶን ሞተርስ በአገር ውስጥ የተገጣጠሙ ሦስት አዳዲስ የሃይንዳይ ሞዴል ተሽከርካሪዎችን ለገበያ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ታኅሳስ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ገላን አካባቢ በሚገኘው መገጣጠሚያው አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን ያስተዋወቀው ማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ፣ በኤሌክትሪክ የምትንቀሳቀስና አዮኒክ (Ionic) የተሰኘች አውቶሞቢል በአገር ውስጥ ገጣጥሞ ለማቅረብ ማቀዱን ገልጾ ነበር፡፡ መጋቢት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. መኪናዋን ለማስተዋወቅ ቢያቅድም፣ በወረርሽኙ ሳቢያ ላልተወሰነ ጊዜ ማራዘሙን አስረድተዋል፡፡

በ130 ኪሎ ዋት ኃይል መጓዝ የምትችለው የኤሌክትሪክ መኪናው 220 ቮልት ኃይል በቤት ውስጥ ለስድስት ሰዓታት ቻርጅ ተደርጋ እስከ 300 ኪሎ ሜትር የመጓዝ አቅም ያላትን መኪና በአገር ውስጥ ሙሉ በሙሉ ገጣጥሞ ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች