Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉየኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ሊያደርስ የሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖና ሊወሰዱ...

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ሊያደርስ የሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖና ሊወሰዱ የሚገባቸው የመፍትሔ ዕርምጃዎች

ቀን:

በጋሻው የትዋለ

ኮሮና ባህር ሰርጓጅ፣ ተወንጫፊ፣ ተምዘግዛጊ የሳይቨርቴክ ጦርነት የማይመክተው የ21ኛው ክፍለ ዘመን ከሰማይ በታች በምድራችን ለሰው ልጅ ትልቁና አስደንጋጭ ታሪካዊ ክስተት ነው። ኮሮና ዘር፣ ቀለም፣ ብሔር የለውም፡፡ ሁሉንም የሰው ልጅ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያጠቃ ይገኛል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያን ከሁሉም በላይ ችግር ውስጥ የሚያስገባ ብሔራዊ አደጋ ተጋርጦባታል፡፡ ይህ ብሔራዊ አደጋ ብሔራዊ ምላሽ ያስፈልገዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለዚህ ብሔራዊ ችግር የመፍትሔ አካል መሆን ከእያንዳንችን የሚጠበቅ ብሔራዊ ግዴታችን ነው፡፡ ችግሩም በእጃችን መፍትሔውም በእጃችን ነው፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ዘር ቀለም ብሔር ሳንል በጋራ መቆም ታሪካዊ፣ ተፈጥሮአዊና እምነታዊ ግዴታችን ነው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ሊያደርስ የሚችለው የማክሮ ኢኪኖሚያዊ አሉታዊ ተፅዕኖ፣ ማኅበራዊ ቀውስ፣ የፌዴራላዊና የዴሞክራሲያዊ ችግርን በተመለከተ ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም በወፍ በረር እንደሚከተለው ለማየት ተሞክሯል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ማክሮ ኢኪኖሚ ሊያደርስ የሚችለው አሉታዊ ተፅ

- Advertisement -

 በየዘመኑ የነበሩ ማክሮ ኢኮኖሚስቶች ማለትም ጥንታዊ ማክሮ ኢኮኖስሚስቶች (Traditional Macroeconomists)፣ የመካከለኛው ዘመን ማክሮ ኢኮኖሚስቶች (Kenisan and Classical Macro Economists) እና ሞደርን ማክሮ ኢኮኖሚስቶች (Modern Macro Economists) በኢኮኖሚ ዓላማና ግቦች ላይ ያለምንም ልዩነት ይስማማሉ። በዚህም ረገድ በተለይ የአንድ አገር ኢኮኖሚ ፈጣን፣ ዘላቂነት ቀጣይነት ባለው መንገድ ማደግ አለበት፣ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ዕድል መፍጠር አለበት፣ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ መፍጠር አለበት፣ አንድን አገር ከድህነት ማውጣትና የሰዎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል አለበት፣ የኢኮኖሚው ፍታዊነት መኖር አለበት፣ የተመጣጠነና የተጣጣመ የወጪና የገቢ ሥርርት እንዲሁም የዕዳ ጫና መኖር እንደሌለበት ያለ ምንም ልዩነት ይስማማሉ፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህን የአንድ አገር ኢኮኖሚ ዓላማና ግቦች እንዴት ማሳካት ይችላል፡፡ በተለይ የመንግሥት አወቃቀር ምን መሆን እንዳለበት፣ ምን ዓይነት የኢኮኖሚ ሞዴል መከተል አንደሚቻል፣ የኢኮኖሚ የፖሊሲ ማዕቀፎች፣ የሕግ ማዕቀፎች፣ የተቋማት አወቃቀርና ደረጃጀቶች፣ እንዲሁም የፖሊሲ ማስፈጸሚያ ስትራቴጅዎች ምን መሆን እንዳለባቸው አንድም ቀን ተስማምተው አያውቁም። እንደ አጠቃላይ ሲታይ ማክሮ ኢኮኖሚስቶች በሙያ እንደሚያማክሩትና ዕድል ገጥሟቸው ወደ አመራር የመጡ እንደሚመሩት አገር ተጨባም ሁኔታ የተሳካላቸው አሉ፣ ያልተሳካላቸውም አሉ፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ አሁን በዓለም ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ባለው የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ምን ዓይነት የማክሮ ኢኮኖሚ ቀውስ ሊፈጥር እንደሚችል፣ ምን ዓይነት የኢኮኖሚ የፖሊሲና የስትራቴጅ አቅጣጫ መከተል እንዲሚያስፈልግና የመፍትሔ ሐሳቡ ምን ይሁን በሚለው ላይ የተለያዩ መላምቶችንና ችግር ፈቺ ሐሳቦችን ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም ከኢትዮጲያ ተጨባጭም ሁኔታ አንፃር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለው መሠረታዊ ችግርና ሥጋት (Critical Problem & Potential Threat)፣ ሊያደርስ የሚችለው ማኅበራዊ ቀውስና ፖሊቲካዊ ችግር እንደሚከተለው ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡

ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ችግር ሊፈጠር ይችላል

በአገር ውስጥና በውጭ አገር ይገቡ በነበሩ ምርቶች የአቅርቦት ችግር ምክንያት ከፍተኛ የዋጋ ንረት ሊፈጠር ይችላል፡፡ አንደኛ ገበሬው ወረርሽኙ  ከተማ መግባቱን ከሰማ ያመረተውን ምርት ለገበያ አያቀርብም፡፡ በሌላ በኩል ገበሬው በበሽታው ከተጠቃ ምርት ማምረት አይችልም፡፡ ያመረተውንም ወደ ገበያ አያወጣም፡፡ እንዲሁም በክልል መንግሥታት ግፊት አገር አቋራጭ የትራንስፖርት አቅርቦት ከተቋረጠ፣ በሕገወጥ ነጋዴዎች ምክንያት ሰው ሠራሽ የአቅርቦት ችግር ከተፈጠረ፣ አስመጪዎች ከውጭ ማቅረብ ካልቻሉ፣ በአጠቃላይ በአምራቾች፣ በቸርቻሪዎች በጅምላ አከፋፋዮች የግብይት ሒደት በሚፈጠረው የአቅርቦት ችግር ምክንያት ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ሊፈጠር ይችላል፡፡ የወረርሽኙ ችግር በጣም ከተስፋፋ የምርት አቅርቦት በገበያ ላይ ላይኖር ይችላል፡፡ ሒደቱ ከቀጠለም ከፍተኛ የዋጋ ንረት ሊፈጠር ይችላል፡፡ ለማስተካከልም ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡

ከፍተኛ የሆነ የሥራ እጥረት ችግር ሊፈጠር ይችላል

ቀደም ብሎ የነበረው የሥራ አጥነት ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ በወረርሽኙ ምክንያት የግል ኩባንያዎች፣ የኮንስትራክሽንና የመሠረተ ልማት ዘርፎች፣ መሠረተ ሰፊ የሆኑ ኢንዱስትሪዎች፣ እንዲሁም ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩት የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሥራ በማቆማቸው ምክንያትና ሠራተኛ በመቀነስ ከሁሉም በላይ ወረርሺኙ በአገር አቀፍ ደረጃ ተሠራጭቶ ጉዳት ቢያደርስ፣ ከፍተኛ የሆነ የሥራ እጥረት ችግር ሊከሰት ይችላል፡፡ በአደጉ አገሮችም ሆነ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ችግሩ የዕለት ተዕለት ክስተት ሆኗል፡፡

የግብርና የታክስ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንስ ይችላል

የአገሪቱ የኢኮኖሚ አወቃቀር ዓምድ የሆኑት ከፍተኛ የኢንዱስትሪ ዘርፎች (Broad Based and Large Scale Industrial Sector)፣ የአገልግሎት ዘርፎችና የግብርና ዘርፎች ምርታማነት መቀነስ፣ የገቢና የወጪ ምርቶች መቀነስ፣ የጥቃቅን፣ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዘርፎች ሥራ በማቆማቸው በአገር አቀፍ ደረጃ ማለትም በፌዴራል፣ በክልል መንግሥታትና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ይሰበሰብ የነበረው ገቢ በመጠንም ሆነ በዓይነት ችግር ውስጥ ይገባል፡፡ በመሆኑም ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች፣ ከመካከለኛ፣ ከአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፎች ይሰበሰብ የነበረው ገቢ ችግር ውስጥ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ በዋናነት ቀጥተኛ ካልሆነው የተጨማሪ እሴት ታከስ የሚሰበሰበው ገቢ ችግር ውስጥ ይገባል፡፡ ወረርሽኙ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ከሆነ የኢኮኖሚ ድቀት (Economic Recession) የሚፈጠር በመሆኑ የታክስ ገቢ በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ በመሆኑም በፌዴራል መንግሥት፣ በክልል መንግሥታትና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የሚሰበሰበው ገቢ እጅግ በማሽቆልቆሉ መንግሥታት በየደረጃው የመንግሥት ግዴታ የሆኑትን የመደበኛ ወጪዎች ለመሸፈን ችግር ውስጥ ይገባሉ፡፡ የደመወዝ፣ የነዳጅ፣ የመድኃኒትና የመሳሰሉትን ወጪዎች ለመሸፈን ችግር ውስጥ ይገባሉ፡፡ በተለይ ታዳጊ ክልሎችና በመንግሥት የሚደጎሙ ተቋማት የችግሩ ሰለባ ይሆናሉ፡፡ በአጠቃላይ ችግሩ ከሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች አንፃር ሊከሰት ይችላል፡፡፡ አንደኛ የኢኮኖሚ ምርታማነት መቀነስና ወይም ድቀት፣ ሁለተኛ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ ለመሰብሰብ አለመቻል፣ ሦስተኛ ከታክስ አስተዳደር ጋር በተያያዘ የአቅም ውስንነት፣ ታክስ መሰወር፣ ማጭበርበርና ሙስና ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሊፈጠር ይችላል

በአገር ውስጥ የኤክስፖርት ኢንዱስትሪው ዘርፍ፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የሆቴልና ቱሪዝም የፋይናንስና የባንክ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግር ውስጥ ስለሚገባ መሠረታዊ የሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ይፈጠራል፡፡ በሌላ በኩል ችግሩ ዓለም አቀፋዊ በመሆኑ በብዙ አገሮች የኢኮኖማ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ችግር የሚፈጥር በመሆኑ፣ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች የሚላከው የውጭ ምንዛሪ በእጅጉ ይቀንሳል፡፡

ኢንቨስትመንትና ቁጠባ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትና የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ከመቀነስ አልፎ ይቆማል፡፡ በጅምር ላይ የነበሩና በሒደት ላይ ያሉ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ፕሮጀክቶችና የልማት ውጥኖችና ፕሮግራሞች ይቋረጣሉ፡፡ ገቢ በመቀነሱ ምክንያት ቁጠባ ይቀንሳል፡፡ ሰው የቆጠበውንም እያወጣ ለዕለታዊ ፍጆታ ያውላል፡፡ የልማት ኦፕሬተሮች፣ የልማት ተዋንያን፣ ምላተ ሕዝቡ በራስ የመተማመን ጉዳይ እየተሸረሸረ ስለሚሄድ፣ አዳዲስ የኢንቨስትመንትና የፕሮጀክት ሐሳቦችንና የፈጠራ ሥራዎችን ማመንጨት የማይታሰብ ጉዳይ ይሆናል፡፡

ድህነት በእጅጉ ይስፋፋል

እንደሚታወቀው አሁን ካለው 110 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ 22 በመቶው፣ ማለትም 24 ሚሊዮን ሕዝብ ፍፁም በድህነት ወለል ውስጥ ይኖራል፡፡ በመሆኑም ወረርሾች የድህነት ቀለበት ዙርን በማክረር በአጭር ጊዜ ሊፈታ የማይቻል የድህነት ጠባሳ ፈጥሮ ሊያልፍ ይችላል፡፡

የጉልበት ዋጋ ግብይት በእጅጉ ይቀንሳል

የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሥራ በማቆሙ፣ የመሠረተ ልማት የኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲሁም የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሥራ በማቆማቸው፣ በመቀነሳቸው የጉልበት ዋጋ የዕለት ጉርስን ለመሸፈን በማያስችል ደረጃ የወረደ ይሆናል፡፡

የባንክ ኢንዱስትሪው ችግር ውስጥ ይገባል

በችግሩ ምክንያት ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ስለሚፈጠር በሥራ ላይ ያሉ የመንግሥትና የግል ባንኮች በብድር አሰጣጥ፣ በቁጠባ፣ በኢንቨስትመንት በአጠቃላይ የባንክ አፈጻጸም ሒደት ችግር ውስጥ ይገባሉ፡፡ እንዲሁም በምሥረታ ሒደት ላይ ያሉ ባንኮችም ከመወለዳቸው በፊት ይሞታሉ፡፡

ጥቁር ገበያ ይስፋፋል

ከሁሉም በላይ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በእጅጉ ሲቀንስ ጥቁር ገበያ ይስፋፋል፡፡ በአጠቃላይ የምርት አቅርቦት ሲቀንስ በሁሉም ደረጃ ሕገወጥና ጥቁር ገበያ ይስፋፋል፡፡

ከፍተኛ የሆነ የማኅበራዊ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል፡፡ የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ በአገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ከተስፋፋ በአምራች ኃይሉ በተለይ በገበሬው፣ በአገሪቱ የልማት መሐንዲሶች ምሁራን (Professional Engineers)፣ የልማት ሞተሮች (ወጣቶች) በአጠቃላይ በምዕላተ ሕዝቡ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ ሀብት ኪሳራ ሊያስከትል ይችላል፡፡ በተለይ በጤናው ዘርፍ የጤና ባለሙያዎችንም ጭምር በማጥቃት የሥነ አዕምሮና የሥነ ልቦና ችግር በመፍጠር ቀደም ብሎ የነበሩ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ፣ በሽታዎችንም በማባባስ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ የሀብት ኪሳብ ሊያስከትል ይችላሉ፡፡ በተለይ በሽታው ከዓለም ተሞክሮ እንደተረዳነው እንደኛ ባሉ ደሃ አገሮች በሽታውን ለመከለከል መሠረታዊ የሆኑ የአቅርቦት የአልጋ፣ የመድኃኒት፣ የመተንፈሻ መሣሪያዎች ችግር ሊፈጠር ስለሚችል የሚደርሰውን ሰብዓዊ ኪሳራ ለመገመት ያስቸግራል፡፡

በአገሪቱ የፌዴራላዊና የዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ማዕቀፍ ላይ ከፍተኛ ችግር ሊፈጥር ይችላል

የሕግ አውጪውን፣ የሕግ ተርጓሚውንና የሕግ አስፈጻሚውን የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓት በማዛባትና ሚዛን በማንሳት ከፍተኛ ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚያደረገውን ጥረት ይገታል፡፡ ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ የወጡ ሕጎችን፣ የማክሮ የኢኮኖሚና የሞኒታሪ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ለማስፈጸም ከፍተኛ ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡ ቀደም ብሎ የነበሩ የማንነት የወሰንና የድንበር አለመግባባቶች እንደተጠበቁ ሆነው በምርት አቅርቦትና ፍላጎት፣ በገንዘብ አቅርቦትና ፍላጎት፣ በአገልግሎት አቅርቦት ማለትም በመብራት፣ በቴሌኮም፣ በውኃና፣ በትራንስፖርት አገልግሎት አለመስማማት ሊፈጠር ይችላል፡፡ በሌላ በኩል በአገር አቀፍ ደረጃ በፌዴራል መንግሥታትና በክልል መንግሥታት መሠረታዊ የሆነ የማስፈጸም አቅም ችግር የነበረ ከመሆኑም በላይ የተቀባይነት ደረጃው በነበረውና ባለው ሥር የሰደደ የሥነ ምግባር ችግር፣ ከታችኛው እርከን ጀምሮ በየደረጃው እስከ ላይኛው መዋቅር ድረስ  የተቀባይነት ደረጃው እየተሸረሸረ የመጣ በመሆኑ ወቅታዊ የሆነውን  ችግረ ለመቋቋምና ለመመከት የሚያስችል የአመርር ብቃት፣ የአመራር ጥበብና ብስለት የለም፣ ተስፋ ማድረግም አይቻልም፡፡ በመሆኑም በአጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚፈጠረው የኢኮኖሚ ድቀት፣ የማኅበራዊ ቀውስ፣ የፌዴራልና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስተጋብር ችግር ከታችኛው የሥልጣን እርከን ጀምሮ ማለትም በወረዳ፣ በከተማ አስተዳደር፣ በክልልና በፌዴራል ደረጃ የመንግሥት ውድቀት (Failed State) ሊያጋጥም ይችላል፡፡

የኢኮኖሚ ዕድገትና ውድቀት ዑደት ሒደት

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ማክሮ ኢኪኖሚ፣ ማኅበራዊና በአገሪቱ የፌዴራላዊና የዴምክራሲያዊ የፖለቲካና ሥርዓት ላይ ሊያደርስ የሚችለው አሉታዊ ተፅኖና የውድቀት ሒደቱን  በተመለከተ፣ በአገሮቹ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዕድገትና ውድቀት ዑደት ሒደት ማዕቀፎች ላይ በማትኮር እንደሚከተለው ለማየት ተሞክሯል፡፡ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገትና ውድቀት ዑደት ሒደቶች በአራት ዋና ዋና ማዕቀፎች ይመደባሉ። የመጀመርያው የዕድገት ማዕቀፍ (Expansion Phase)፣ ሁለተኛው የዕድገት ጫፍ የመጨረሻው ደረጃ (Peak of Growth Cycle)፣ ሦስተኛው የዕድገት መቀነስ ዑደት (Recession/Contraction) እና አራተኛው የዕድገት መቀነስ ጉዳት ማዕቀፍ የመጨረሻው ደረጃ በመባል ይታወቃሉ፡፡

በመጀመርያው የዕድገት ዑደት ማዕቀፍ (Expansion  Phassel) ኢኮኖሚው ቀስ ብሎ ማደግ ይጀምርና የዕድገት ፍጥነቱ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ በሒደት የዕድገት ፍጥነቱ እየቀነሰ የመጨረሻው የዕድገት ደረጃ ይደርሳል፡፡ በዚህ ጊዜ የኢኮኖሚው ሙቀት፣ ግፊትና  ግለት እየጨመረ የመጨረሻው የዕድገት ደረጃ (Peak of Growth Cycle) ላይ ይደርሳል፡፡ የሚፈጠረው ግፊት ኢኮኖሚውን ከመጣሉ በፊት የኢኮኖሚውን ጤንነት ለመጠበቅ በምርምርና ጥናት የተደገፉ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተቀርፆ ተግባራዊ ካልሆነ፣ የዕድገት ግፊቱ በሚፈጥረው ሙቀት ኢኮኖሚው መቅለጥ ይጀምራል፡፡ በዚህ ሒደት ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ ወደ ታች መውረድና ማሽቆልቆል (Economic Recession/Contraction) ይጀምራል፡፡ በመጨረሻም የመጨረሻው የውድቀት ጫፍ ይደረሳል፡፡ ከዚህ ውጪ የዕድገት ዑደቱ በሰው ሠራሽ አደጋ፣ በጦርነት፣ በተፈጥሮ አደጋና በጤና ወረርሽኝ በሚፈጠር አደጋ የዓለም ኢኮኖሚና ወይም የአንድ አገር ኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ወይም ዜሮና ከዜሮ በታች ኔጌቲቭ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ በመሆኑ ውድቀት ያጋጥመዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ደረጃ ውድቀቱን ለመከላከል የሚያስችል የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ የማኅበራዊ ፖሊሲና የፖለቲካ  አመራር ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል፡፡ 

በመሆኑም በዓለም አቀፍ ደረጃ በአፍሪካና በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ በሚኖረው ተፅዕኖ ዓለም አቀፍ፣ አኅጉር አቀፍና አገር አቀፍ የኢኮኖሚ ውድቀት ያጋጥማል፡፡ እያጋጠመ እንደሆነም ዓለም አቀፍ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ ረገድ የኢኮኖሚ ዕድገትና ውድቀት ዑደት ሒደትን ማዕከል በማድረግ፣ የኮሮና ወረርሽኝ ሒደትን በተመለከተ አራት ዋና ዋና የሚሆን ሴናሪዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝ ሒደትን በተመለከተ አራቱ ዋና ዋና የቢሆን ሴናሪዮዎች

የመጀመርያው የቢሆን ሴናሪዮ ወረርሽኙ በአዲስ አበባና አዋሳኝ ከተሞች ከተስፋፋ

የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና ከ65 በመቶ በላይ የአገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ማዕከል በሆነችው አዲስ አበባና አዋሳኝ ከተሞች በሽታው ከተስፋፋ የዓለም አቀፍና የአገር አቀፍ የአዲስ አበባ ግንኙነት ከተቋረጠ፣ የምርት አገልግሎትና ፍላጎት የጥቃቅን አነስተኛ መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችና ከፍተኛ የኢኮኖሚ የኢንዱስትሪ ዘርፎች መስተጋብር ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ በመፍጠር፣ በተለይም በአጭር ጊዜ ካልተገታ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ መቀዝቀዝና የኢኮኖሚ ዕድገቱ ወደ ታች የመመለስ የመጀመርያው የመነሻ ምልክት ይሆናል፡፡

ሁለተኛው የቢሆን ሴናሪዮ ከችግሩ በፍጥነት አለመውጣት

የኮሮናን ወረርሽኝ በአጭር ጊዜ ውስጥ መቆጣጠርና ከችግሩ በፍጥነት መውጣት ካልተቻለ እንዲሁም ችግሩ በጣም ተባብሶ የዕድገት ከርቩ ከ ‹‹U ቅርፅ በፍጥነት ወደ V›› ቅርፅ ካልተመለሰ፣ ለመመለስም ጊዜ ከወሰደበት የኢኮኖሚ ዕድገት ማሽቆልቆል ይጀምራል፡፡ ሒደቱም በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ይሄዳል፡፡

ሦስተኛ የቢሆን ሴናሪዮ

ወረርሽኙ በክልል መንግሥታት ዋና ዋና ከተሞችና የኢኮኖሚ ማዕከላት ከተስፋፋ መጠናት ያለባት ቢሆንም፣ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖማ ማሽቆልቆል ቀውስ በመፍጠር ምናልባትም የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ዜሮ የሚያወርድ ይሆናል፡፡

አራተኛው የቢሆን ሴናሪዮ ወረርሾች በአገሪቱ በሁሉም አከባቢ ከተስፋፋ ከሆነ

 ወረርሽኙ በአገር አቀፍ ደረጃ ከተስፋፋና በተለይም ቀደም ብለው የተጠቀሱትን የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮች በማባባስና ከፍተኛ የሰብዓዊ ሀብት ኪሳራ በማድረስ፣ በአገሪቱ የፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ማናጋት በማስከተል በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ዜሮና ከዜሮ በታች ኔጌቲቭ በማድረግ ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል፡፡ የመንግሥት ውድቀትንም በየደረጃ ሊያስከትል ይችላል፡፡ በአጠቃላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደታየው በሽታው ዓለም አቀፍ ሆኖ ከቀጠለና በአጭር ጊዜ መመለስ ካልተቻለ በኢትዮጵያም ሆነ  በአፍሪካ የአገር መበተንና መንግሥትን እስከ ማሳጣት ድረስ ከፍተኛ ዋጋ ሊያሰከፍል ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ በኢትዮጵያ የሚያጋጥመውን ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ችግር ለማቋቋም የሚያስችሉ የፖሊሲ፣ የሕግና የስትራቴጁ ማዕቀፎች በመፍትሔነት እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ  በኢትዮጵያ ሁሉ አቀፍ በሆነ መንገድ ሊያደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተፅኖ ለመከላከል የቀረቡ የመፍትሔ ሐሳቦች

የኮሮና ቫይረስ  ወረርሽኝ  በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ ሊያደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተፅኖ ለመከላከል የአጭር ጊዜ ፖሊሲ፣ የሕግና የስትራቴጂ ማሻሻያና ተግባራዊ ማድረግ አስፍላጊና ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ በሒደት ግን ወደፊት በጥናት በስፋት መታየት ያለባቸው ቢሆንም ሦስት እርከን ያላቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያ መንገዶች ፍኖተ ካርታ (Road Map/Platform) ቀርበዋል፡፡ አንዱ የኢኖሚውን መሠረት ማገንባተ፣ ሁለተኛው ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ያላትን አገር መገንባትና ሦስትኛው  የኢኖሚ ልማትና ወይም የብልፅግና ማረጋገጥ ናቸው፡፡

ሁሉ አቀፍ የአጭር ጊዜ የፖሊሲ፣ የሕግና የስትራቴጂ ማሻሻያ ማድረግ

ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ልምድን በዋናነት የቻይናን በመቀመር በሽታውን ለመከለላከልና ለመመከት ዋና ዋና አገር አቀፍ ተግባራትን በማዘጋጀት ሁሉ አቀፍ የሆነ የሕዝብ ንቅናቄ የፖሊሲ ፓኬጅ በማዘጋጀት፣ የድርጊት መርሐ ግብር በማውጣት፣ የተጠያቂነት ሥርዓት በአገር አቀፍ ደረጃ በመንደፍና በመተግበር ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ የመንግሥት ኃላፊዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አመራር አካላት በቻይና ሁቤ ግዛት እንደተደረገው ዕርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ሕዝብ ጤናውን እንዲጠብቅ የሚያስችል የጤና የማኅበራዊ ፖሊሲና ሕግ በማውጣትና ያለውን በማሻሻል መተግበር ያስፈልጋል፡፡ የመድኃኒት በዋናነት ቬንትሌሽን ችግር መሠረታዊ መሆኑን በመገንዘብ በቂ ዝግጅት ማድረግ ‹‹ምርመራ፣ ምርመራ፣ ምርመራ›› መርህን በመተግበር በሽታውን ከቁጥጥር እንደይወጣ ብሔራዊ ትግል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በሽታው ረዘም ላለ ጊዜ መቆየት ስለሚችል በር መዝጋትና ሥራ ማቆም ዋጋ ስለሚያስከፍል፣ የዓለም አቀፍ ተሞክሮን በመውሰድ ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ የመሳሰሉትን በመጠቀም ችግሩን ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን መታገል ያስፈልጋል፡፡

ጉልበት ተኮር (Labous Intensive) የሆኑ የጥቃቅንና አነስተኛ የኢኮኖሚ ዘርፎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ በመሆኑ፣ ዘርፎችን ለመደገፍና ለማበረታታት የሚያስችሉ የጥንቃቅንና አነስተኛ የኢኮኖሚ ዘርፎች የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ መደገፍና ማበረታታት፣ የአዲስ አበባን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ፣ በዚህ ረገድ የተጀመረውን የአዲስ አበባ የዳቦ ማምረቻ ሥራ ማስጀመር ሌሎችንም የግል ዳቦ ቤቶችንም ማበረታታት፣ የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር ለምግብ አቅርቦት ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን በአለ በጅምላ በኩል ማከማቸትና የምግብ ባንክ ማቋቋም፡፡ በግል ካምፓኒዎች የተጀመሩ የዘይት ማምረቻዎች በአስቸኳይ ሥራ እንዲጀምሩ ድጋፍና ክትትል ማድረግ፣ በዳያስፖራው በኩል እንዲገቡ የሚደረጉ ዘይትና ስንዴ የመሳሰሉ ምርቶች በተገቢው ፍጥነት እንዲገቡ ማድረግ ዘይት ለማምረት መሬት ወስደው አጥረው ያስቀመጡ ባለሀብቶች ለምሳሌ (ሰሚት) በአስቸኳይ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ፡፡ የግብርና ሚኒስቴር ቀደም ብሎ ከነበረው በተለያ ሁኔታ ገበሬው የበልግ ዝናብን፣ የመስኖ ውኃን ውኃ ማቆርን፣ የመሳሰሉትን በመጠቀም በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ሰብሎችን ማምረት እንዲቻል የአጭር ጊዜ የግብርና ልማት ፖሊሲ ማዘጋጀትና መተግበር ይጠበቅበታል፡፡ በቅድመ ንቃት (Proactive Leadership) በመንቀሳቀስ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በወቅቱ ከውጭ አገር ማስገባት ይጠበቅበታል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር የካፒታልና የመደበኛ በጀትን እንደ ገና በመፈተሽና ጊዜ የሚሰጡ የካፒታል ፕሮጀክቶችን በማቋረጥ የሚያስችል ምክረ ሐሳብ በማቅረብ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበጀት ቀመሩ መሠረት ክልሎች ድርሻቸውን እንዲያገኙና ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ የአስቸኳይ ጊዜ በጀት እንዲያፀድቅ በማድረግ የሰብዓዊ ሀብት ኪሳራን፣ የሕዝብ ዕልቂትን ብሔራዊ አጀንዳ በማድረግ ታሪካዊ ግዴታን መወጣትና ከተጠያቂነት ነፃ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ወደፊት ከሚፈጠረው የችግር ስፋት አንፃር አዲስ አበባ በፌዴራል መንግሥት የሚመደብ የተለየ በጀት ያስፈልጋታል፡፡ በአጠቃላይ በጤናና በኢኮኖሚ ልማት ላይ የሚያተኩር የብሔራዊ ንቅናቄ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያስፈልጋል፡፡ ከአበዳሪዎች፣ ከለጋሾችና ከሕዝቡ ገንዘብ በመሰብሰብ፣ እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም የብልፅግና ፓርቲ ያሰባሰበውን 1,5 ቢሊዮን ብር ለዚህ አደጋ እንዲውል በማድረግ የሕዝብ የቁርጥ ቀን ደራሽ መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡ የገቢዎች ሚኒስቴር የቅድመ ንቃት አመራር ጥበብን በመከተል የአጭር ጊዜ ጥናት በማካሄድ፣ የታክስ የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግና ለመንግሥት በማቅረብ የግብር ምጣኔን የመቀነስ፣ የዕፎይታ ጊዜ መስጠትና ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በከፍተኛ ግብር ከፋዮች ላይ በማተኮር ግብሩን በአግባቡ መሰብሰብ፣ ጥቃቅንና አነስተኛውን የሥራ ዘርፍ ሊያበረታታ የሚያስችል የግብር ማሻሻያ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ብሔራዊ ባንክ የአጭር ጊዜ ጥናት በማካሄድ ባንኮች የብድር ጊዜ እንዲያራዝሙ በማድረግ፣ የወለድና የቁጠባ ምጣኔ የሚሻሻልበትን የፖሊሲ ማሻሻ ማቅረብና እንዲተገብር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ የየውጭ ምንዛሪ የጥቁር ገበያ ችግርን በተመለከተ ጉዳዩ ከሚመለከተው አካላት ጋር በመቀናጀት እሳት የማጥፋት ጉዳይ ሳይሆን፣ በኢኮኖሚ ኢንተለጀንስ ላይ ያተኮረ በቋሚነት ችግሩ የሚፈታበትን የፖሊሲና የስትራቴጂ ማዕቀፍ በማዘጋጀት መተግበር ይጠበቅበታል፡፡ የፕላን ኮሚሽን አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን እንደ ገና በመመልከት ወረርሽኙ በአገር አቀፍ ደረጃ ሊደርስ የሚችለውን የኢኮኖሚ ድቀት በመገንዘብ፣ አማራጭ የፖሊሲ ሐሳብ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ የመብራት፣ የቴሌኮም፣ የኢንተርኔት ከሁሉም በላይ ውኃ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ሦስቱ የኢኖሚ የዕድገት እርከኖች

ወደፊት በጥናት በስፋት መታየት ያለባቸው ቢሆንም፣ ሦስት እርከን ያላቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያ መንገዶች ፍኖተ ካርታ (Road Map/Platform) ቀርበዋል፡፡ አንዱ የኢኖሚውን መሠረት መገንባት፣ ሁለተኛው ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ያላትን አገር ራዕይ ዕውን ማድረግና ሦስተኛው የኢኖሚ ልማትና ወይም ብልፅግና ማምጣት የሚያስችሉ ማዕቀፍ ምዕራፎች ናቸው፡፡

የኢኖሚ የዕድገት መሠረት መጣል መደላድሉን ማስፋት

 በዚህ የዕድገት ሒደት አውድ ሰፊ ትኩረት የሚሰጠው የጥቃቅንና አነስተኛ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ በማተኮር የኢኮኖሚ የዕድገት መሠረት መጣል፣ የኢኮኖሚውን መደላድል ማስፋት፣ መሬት መርገጥ፣ በማናቸውም መንገድ ራስን መቻል ይሆናል፡፡ ትልቁ ቁምነገር በልቶ የማደር ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ጉልበት ተኮር (Labous Intensive) የሆኑ የጥቃቅንና አነስተኛ የኢኮኖሚ ዘርፎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ በመሆኑ፣ ዘርፎችን ለመደገፍና ለማበረታታት የሚያስችሉ የጥንቃቅንና አነስተኛ የኢኮኖሚ ዘርፎች የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ መደገፍና ማበረታታት፣ በዋናነት በአገር አቀፍ ደረጃ የግብርና የልማት አብዮትን በማቀጣጠል በምግብ ሰብል ራስን መቻል፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ለሚሰማው መንግሥት ቁጥር አንድ አጀንዳ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ ለም መሬት፣ ዓመቱን በሙሉ የሚፈሱ ወንዞችና ከ70 በመቶ በላይ በወጣት ኃይል የተገነባች አገር ናት፡፡ በመሆኑም የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት ማድረግ ይቻላል፡፡

ከሁሉም በላይ የጥቃቅንና አነስተኛ የኢኮኖሚ ዘርፎን አወቃቀርና የኢኮኖሚ የዕድገት መደለደሉን የሚመጥን በፌዴራል፣ በክልል መንግሥታትና በከተማ አስተዳደሮች ከዘር፣ ከቀለምና ከፖለቲካዊ ተፅዕኖ የፀዳ ዕውቀትን፣ ልምድንና ችሎታን መሠረት ያደረገ በግለሶቦች ሳምባ የማይተነፍስ የሲቪል ሰርቪስ ተቋምና የሰው ኃይል መገንባት ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም ትውልድ ተሻጋሪ ተቋም በመገንባትና የጥቃቅንና አነስተኛውን የኢኮኖሚ አወቃቀ የሚመጥንና ለመተግበር የሚያስችል የሲቪል ሰርቪስ ፖሊሲና ስትራቴጂ ማዘጋጀት መተግበር ያስፈልጋል፡፡ ሌላው መሠረታዊ ነጥብ ይህንን የመጀመርያ የኢኮኖሚ መደላደል እርከን የሚመጥን ለመተግበር የሚያስችል ሁሉን አቀፍ የሆነ መሠረተ ልማት መገንባት ያስፈልጋል፡፡

የኢኮኖሚ የዕድገት ማዕቀፍ/ምዕራፍ

በዚህ የዕድገት ሒደት ዓውድ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው በመካከለኛ የኢኮኖሚ ዘርፎች አወቃቀር ላይ በማተኮር የኢኖሚ ዕድገት ማምጣት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከፍተኛና መሠረተ ሰፊ በሆኑ መካከለኛ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ በማተኮር ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላትን አገር ለመገንባት የሚያስችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ የሕግና የስትራቴጂ ማሻሻያ በማድረግ የአገሪቱን ራዕይ ማሳካትና ማረጋገጥ ነው፡፡ በአንደኛው የዕድገት ማዕቀፍ በጥቃቅንና አነስተኛ የኢኮኖሚ ዘርፍ ኢንተርፕራይዞች ያለቁና ያላለቁ ምርቶችን በግበዓትነት የሚጠቀም ከፍተኛና መሠረተ ሰፊ በሆኑ የመካከለኛ ኢንዱስትሪ ዘርፎች አብዮት በማቀጣጠል፣ በሁሉም ዘርፍ ስፔሻላይዝድና ዳይቨርሲፋይድ በማድረግ በተለይ በግብርና ኢንዱስትሪ፣ በሜዲካል ኢንዱስትሪ፣ በመዝናኛ ኢንዱስትሪዎች ማለትም/የቱሪዝም ኢንዱስትሪ፣ የፊልም ኢንዱስትሪ፣ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ፣ የስፖርት ኢንዱስትሪና በአጠቃላይ በመሠረተ ልማት፣ በቤቶች ልማት ላይ በማተኮር የኢኮኖሚ ዕድገትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

 በመሆኑም መንግሥት መካከለኛውን የኢኮኖሚ ዘርፍ አወቃቀር የሚመጥን የማይክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ (Expantonary Economic Policy)፣ በተለይ የባንክ ኢንዱስትሪውን የወለድ ምጣኔ በመቀነስ፣ የታክስ ምጣኔ በመቀነስ፣ የግብር ዕፎይታ በመስጠት፣ የገንዘብ አቅርቦት በመጨመር፣ የመሬትና የመሠረተ ልማትን አቅርቦት በማመቻቸት የኢኮኖሚ ዕድገቱን የማሽቆልቆል ጉዞውን መግታት ይቻላል፡፡ በሚፈጠረውም የኮሮና ችግር ምክንያት ኢኮኖሚውን እንደ ገና እንዲያገግም ማድረግ የሚቻለው፣ ዕድገት ተኮር የሆነ ተስፈኛ የኢኮኖሚ ሞዴልና ፖሊሲ በመንደፍና በመተግበር ብቻ ይሆናል፡፡

የኢኮኖሚ ልማትና ወይም የብልፅግና ማዕቀፍ/ምዕራፍ

በዚህ የዕድገት ሒደት ዓውድ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው በከፍተኛ የኢኮኖሚ ዘርፎች አወቃቀር ላይ በማተኮር፣ የኢኮኖሚ ልማትና ብልፅግና ማምጣት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከፍተኛና መሠረተ ሰፊ የሆኑ ከፍተኛ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ለመገንባት የሚያስችል የማይክሮ ፖሊሲ፣ የሕግ ማሻሻልና ስትራቴጂ በማዘጋጀት የአገሪቱን የልማት ወይም የብልፅግና (Economic Development and Prosperity/Welfare) ማረጋገጥ ነው፡፡ በመሆኑም በተለይ አገሪቱን ወደ ብልፅግና ጎዳና ሊወስዱ የሚችሉ ነዳጅን ጨምሮ የማዕድን ልማት ኢንዱስትሪ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ፣ የሳይቨርቴክ ኢንዱስትሪ፣ የአቪዬንሽን ኢንዱስትሪ በአጠቃላይ የዲጅታል ኢኮኖሚ መገንባት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ማዕቀፍ በተለይ የመንግሥት ሚና የሬጉላቶሪ ሥራ ማካሄድ ሲሆን፣ በነፃ ገበያ መርህ ላይ የተመሠረተ የግል ዘርፍ በኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት የመወዳደሪያ ሜዳውን ነፃና ገለልተኛ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በሒደትም በተለይ የባንክ ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለነፃ ገበያው ክፍት መሆን ይጠበቅበታል፡፡                  ማጠቃለያ

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ችግር ዓለም አቀፋዊ በመሆኑ በዓለም የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ መሠረታዊ ችግር በመፍጠር ወደ ውድቀት፣ ቀውስና ድቀት (Global Macroeconomic Recession and Crisis) በከፍተኛ ፍጥነት እያነደረደረው ይገኛል፡፡  በዚህ ረገድ ችግሩ በኢትዮጵያም ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ ማኅበራዊ ቀውስ፣ የፌዴራዊና የዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ማዕቀፍ ችግር ሊፈጥር ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡ ችግሩ አገር አቀፍ (National Pandemic) ከሆነም ከቀበሌ ጀምሮ በየደረጃው በወረዳ፣ በክልል መንግሥታት፣ በከተማ አስተዳደርና በፌዴራል መንግሥት ውድቀት ሊያስከትል ይችላል፡፡ በአጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ሊፈጥር የሚችለው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ተደምሮ ፖለቲካዊ ቀውስ በመፍጠር፣ በየደረጃው የመንግሥት ውድቀትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በመሆኑም ከችግሩ ለመውጣት የአራት የቢሆን ሴናሪዎች ተለይተዋል፡፡ የመጀመርያው ወረርሽኙ በአዲስ አበባና በአከባቢው ቢስፋፋና ለአጭር ጊዜ ቢቆይ፣ የኢኮኖሚ መቀዝቀዝ ችግር ሊፈጠር ይችላል፡፡ ሁለተኛው የሚቢሆን ሴናሪዮ በአዲስ አበባ ደረጃ  ከችግሩ ፈጥኖ መውጣት ካልተቻለ፣ የኢኮኖሚ የቁልቁለት ጉዞ የውድቀት ምልክት የሚጀምርበት የመጀመርያው መጀመርያ ይሆናል፡፡

ሦስተኛው የቢሆን ሴናሪዮ ችግሩ በክልል መንግሥታት ዋና ዋና ከተሞችና የኢኮኖሚ ማዕከላት ከተስፋፋ የኢኮኖማ ውድቀትና ድቀት (Macroeconomic Recession & Crisis) ይፈጠራል፡፡ ውድቀቱም በፍጥነት እየጨመረ ይሄዳል፡፡ አራተኛው የቢሆን ሴናሪዮ በሽታው በአገር አቀፍ ደረጃ (National Pandemic) ሆኖ ከተስፋፋ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ዜሮና ከዜሮ በታች ኔጌቲቭ ሊገባ ይችላል፡፡ በመሆኑም በየደረጃው የተፈጠረውን ችግር ለመፍታትና ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል የፖሊሲ፣ የሕግና የስትራቴጂ ማሻሻያ ያስፈልጋል፡፡

በዚህ ደረጃ ሦስት ዕርከን/ማዕቀፍ ያለው አማራጭ ምክረ ሐሳብ ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አወቃቀር በአራት ዋና ዋና ማዕቀፎች መመደብ ያስፈልጋል፡፡ የጥቃቅን የኢኮኖሚ አወቃቀር ማዕቀፍ፣ አነስተኛ የኢኮኖሚ አወቃቀር ማዕቀፍ፣ የመካከለኛ የኢኮኖሚ አወቃቀር ማዕቀፍና የከፍተኛ የኢኮኖሚ አወቃቀር ማዕቀፍ ይሆናል፡፡ አንደኛው ማዕቀፍ የዕድገት ሒደት ዓውድ ሰፊ ትኩረት የሚሰጠው የጥቃቅንና የአነስተኛ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ በማተኮር የኢኮኖሚ የዕድገት መሠረት መጣል፣ የኢኮኖሚውን መደላድል ማስፋት፣ መሬት መርገጥ፣ በማናቸውም መንገድ ራስን መቻል ይሆናል፡፡ ትልቁ ቁምነገር በልቶ የማደር ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው፡፡

በሁለተኛው ማዕቀፍ የዕድገት ሒደት ዓውድ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው በመካከለኛ የኢኮኖሚ ዘርፎች አወቃቀር ላይ በማተኮር የኢኖሚ ዕድገት ማምጣት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከፍተኛና መሠረተ ሰፊ በሆኑ መካከለኛ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ በማተኮር ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ያላትን አገር ለመገንባት የሚያስችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ የሕግና የስትራቴጂ ማሻሻያ በማድረግ የአገሪቱን ራዕይን ማሳካትና ማረጋገጥ ነው፡፡ በአንደኛው የዕድገት ማዕቀፍ በጥቃቅንና አነስተኛ የኢኮኖሚ ዘርፍ ኢንተርፕራይዞች ያለቁና ያላለቁ ምርቶችን በግብዓትነት በመጠቀም፣ ከፍተኛና መሠረተ ሰፊ የሆኑ የመካከለኛ ኢንዱስትሪ ዘርፎች አብዮት በማቀጣጠልና በሁሉም ዘርፍ ስፔሻላይዝድና ዳይቨርሲፋይድ በማድረግ ያስፈልጋል፡፡

 (ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ እንደ መሆኗ የሰው ዘር መዳኛም ትሆናለች) ምርምርና ጥናቱ መቀጠል አለበት፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው gashawy05@yahoo.co.uk ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...