Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክምርጫው እንዴት ይራዘማል?

ምርጫው እንዴት ይራዘማል?

ቀን:

በውብሸት ሙላት

የክልሎችና የፌዴራል መንግሥታቱ ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን በመጪው ዓመት መስከረም ወር ይጠናቀቃል፡፡ ከመጠናቀቁ ቢያንስ አንድ ወር ቀደም ብሎ ምርጫ መደረግ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዕቅዱ መሠረት ሥራውን ለማከናወን የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትና ወረርሽኝ እንቅፋት ስለሆነበትና ምርጫ ለማከናወንም አስቸጋሪ በመሆኑ ነሐሴ ወር ላይ ለማከናወን እንደማይቻል ይፋ አድርጓል፡፡

ይህንንም ተከትሎ እየተነሳ ያለ በሥሩ በርካታ ንዑስ ጥያቄዎችን የያዘ አንድ ጥያቄ አለ፡፡ ጥያቄውም ‹ምርጫው እንዴት ይራዘም?› የሚል ነው፡፡ ይህ ጹሑፍም የሚሽከረከረው በዚሁ ጥያቄ ላይ ተንጠልጥሎ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ያለወትሮው በነሐሴ

ለወትሮው ምርጫ ሲደረግ የነበረው በግንቦት ነው፡፡ በዚህ ዓመት ግን ያለልማዱ በነሐሴ እንዲሆን ታቀደ፡፡ የፌዴራሉም ይሁን የክልሎቹ ሕገ መንግሥታት የደነገጉት በሥራ ላይ የሚገኙት ሕግ አውጭ ምክር ቤቶች የሥራ ዘመናቸው ከመጠናቀቁ ከአንድ ወር ቀደም ብሎ ሌላ ምርጫ መደረግ እንዳለበት እንጂ መስከረም ላይ ለሚያልቀው ጊዜያቸው በነሐሴ ወይም በሐምሌ ወዘተ. ይሁን በማለት አይደለም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ግን አንድ ወር ቀደም ብሎ መከናወን ግድ መሆኑን ደንግገዋል፡፡

ከዚህ አንፃር የፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥራውን የሚጀምረው በመስከረም ወር የመጨረሻው ሰኞ በመሆኑ፣ የቀድሞው ምክር ቤት የሥራ ጊዜው የሚያልቀው በዋዜማው እሑድ ነው ማለት ነው፡፡ እሑድ ስንት ሰዓት ላይ የሚለው ግልጽ ባይሆንም ቅሉ፡፡ ማለትም፣ ከምሽቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ወይስ ሰኞ ጧት አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ የሚለው ነው ግልጽነት የሚጎድለው፡፡ የአንድ ቀን ሃያ አራት ሰዓት ከየት ጀምሮ የት ላይ ያልቃል? (ከጠዋት እስከ ጠዋት ወይስ ከማታ እስከ ማታ ወይስ ከእኩለ ሌሊት እስከ እኩለ ሌሊት?)

በነሐሴ ውስጥ ምርጫ ማድረግን ሕገ መንግሥቱ ቢፈቅድም የአየር ፀባዩ ግን እንቅፋት ሆኖ በተግባር ሊከለክል ይችላል፡፡ በጋ ከክረምት በየቀበሌው በተሽከርካሪ የሚያስኬዱ መንገዶች በሌሉበት ሁኔታ በወርሐ ነሐሴ ምርጫ ለማድረግ ማቀድ አማራጭ የማጣት ብቻ ነው መሆን ያለበት፡፡ አማራጭ ሳይጠፋ በዚህ ወር ለማድረግ ማቀድ ከቅንነት የሚመነጭ ሐሳብ ነው ማለት ያስቸግራል፡፡ በደርግ ዘመን በነበረው የሦስተኛ ክፍል የአማርኛ መማርያ መጽሐፍ ላይ የዓመቱ ወራት በሚለው ግጥም  ነሐሴን ሲገልጸው፡

 ‹‹ነሐሴ ተተካ ኃይለኛው ክረምት

 ያወርደው ጀመር የዝናብ መዓት›› በሚል ነበር፡፡

የዝናብ መዓት ካለ የጎርፍ መዓት ስለሚኖር መንገድ ቢዘጋ፣ የምርጫ ኮሮጆን ጎርፍ ቢወስደው ቢያንስ እንዲህ ዓይነት ችግር ተከሰተ በተባለባቸው አካባቢዎች (የምርጫ ጣቢያዎች) የምርጫ ቀን መራዘሙ አይቀሬ ይሆናል፡፡

የምርጫ ጊዜ ከሚራዘምባቸው የታወቁ ምክንያቶች በምርጫው ዕለት ወይም በምርጫው ሰሞን የተፈጠሩ ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ሰደድ እሳት፣ የጎርፍና ማዕበል አደጋዎች፣ የሽብር ጥቃት ወዘተ፡፡

እንዲህ ዓይነትና መሰል ችግሮች ከተፈጠሩም ቢያንስ ችግሮቹ በተፈጠሩባቸው አካባቢዎች ይራዘማል፡፡ በርካታ አገሮችም ታይቷል፡፡ ሆኗልም፡፡ በአንድ አካባቢ ብቻ ሳይወሰንም በጠቅላላው እንዲራዘም የሚያስገድዱ ምክንያቶችም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ጦርነት፣ የሽብር ጥቃት፣ እንደ ኮቪድ ዓይነት ወረርሽኝ በሚያጋጥምበት ጊዜም ምርጫ ይራዘማል፡፡  ያም ሆነ ይህ፣ በክረምት የሚደረግ ምርጫም በጎርፍ ምክንያት ሊራዘምባቸው የሚችሉ ጣቢያዎች የመኖር ዕድሉ ከፍ ያለ ነው፡፡ በግንቦት ሲደረግ የኖረው ከጎርፍ ሽሽትም ይመስላል፡፡ የዓመቱ ወራት የሚለው ከላይ የተጠቀሰው ግጥም ግንቦትን ሲገልጸው፡

‹‹ግንቦት ደረቅ ወር ነው ፀሐይዋ ከረረች

አቧራው ቦነነ ምድር ተራቆተች›› በሚል ነው፡፡

በግንቦት ምርጫ ማድረግ በጎርፍና በዝናብ ሊመጣ የሚችለው ሥጋቱ ዝቅ ያለ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ግን በጎርፍ ምክንያት የሚፈጠረው ሥጋት ወደ ጎን ቢባል የኮሮና ቫይረስ በወረርሽኘት በመዛመቱ፣ ‹‹እዬዬም ሲደላ ነው›› እንዲሉ፤ ከወረርሽኙ አንፃር ምርጫ ‹‹ቅንጦት›› መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ምርጫውን በወቅቱ ማድረግ ካልተቻለ የሚከተለው ምንድን ነው?

ምርጫ ካልተደረገ

ምርጫው በዚህ ዓመት ካልተደረገ የክልልና የፌዴራል ምክር ቤቶች የሥራ ዘመናቸው ያከትማል፡፡ እርግጥ ነው የሥራ ጊዜያቸው አክትሞና አልቆ አሁንም በሥራ ላይ ያሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ምክር ቤቶች አሉን፡፡ እነሱም የቀበሌ፣ የወረዳና የልዩ ዞን ምክር ቤቶች ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ብቻ በግልጽና በአዋጅ ሲራዘም፣ በየክልሎቹ ያሉት የአካባቢ ምክር ቤቶች ዕድሜያቸው ካለቀ ሁለት ዓመታት ሆነው፡፡

 2005 ዓ.ም. ነው የአካባቢ ምርጫ የተደረገው፡፡ በ2010 ዓ.ም. አበቃ፡፡ እነሱ ግን ቀጠሉ፡፡ እንዴት እንደቀጠሉ ሕዝባዊ አጀንዳ አልሆነም፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ17 ሺሕ በላይ ቀበሌዎች፣ ከሰባት መቶ በላይ ወረዳዎች ስላሉ የእነዚህ ሁሉ ምክር ቤቶች የሥራ ዘመናቸው አልፎና አልቆ እነሱ ግን አሉ፡፡ 

ለሕዝቡም ይሁን ለፖለቲካ ፓርቲዎቻችን፣ ምክር ቤት ማለት የፌዴራሉና የክልሉ ብቻ የሆኑ ይመስላል፡፡ ምርጫ እንዴት ይራዘማል? የሚለው እልባት ማግኘት የነበረበት በ2010 ዓ.ም. ነበር፡፡ ምክንያቱም በዚያን ዓመት መፈጸም የነበረበት የአካባቢ ምርጫ ስላልተካሄደ፡፡  በዚህ ዓመት ምርጫ ካልተካሄደ የፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮችና የክልሎቹ ምክር ቤቶች ዕድሜያቸው በዚሁ ስለሚቋጭ የሕግ አስፈጻሚውም አብሮ ይቋጫል፡፡ ስለሆነም ምርጫውን ማረዘም የሚቻልበትን ሕጋዊ ሥርዓት መፈለግ ግድ ይላል፡፡

ምርጫ ማራዘሚያው ሥርዓት

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና ሕግ፣ ምርጫ እንዴት ይራዘማል? ማን ነው የማራዘም ሥልጣን ያለው? ለምን ያህል ጊዜ ነው የሚራዘመው? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት ወሳኝ ነው፡፡ ለጥያቄዎቹ በቀጥታና በግልጽ የተቀመጡ መልሶች አናገኝም፡፡ ከዚህ የተነሳ የተለያዩ አማራጮች ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ በተለያዩ ሚዲያዎችም እየቀረቡ ነው፡፡ ምክር ቤቶቹን በመበተን ወይም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማዋጅ ማራዘም ይቻላል የሚሉት ጎላ ብለው እየተሰሙ ነው፡፡ 

ምክር ቤት በመበተን ማራዘም

የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 60 እንደገለጸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስት ዓመቱ የሥራ ጊዜው ከማለቁ በፊት በሁለት ምክንያቶች ሊበተን ይችላል፡፡ የመጀመርያው በንዑስ ቁጥር አንድ ባለው መሠረት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሸነት ነው፡፡ የሥራ ጊዜው ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ማድረግ ካስፈለገና የምክር ቤቱ አባላት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሐሳብ ተቀብሎ ከተስማማ ራሱን ይበትናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርላማውን ለመበተን መሟላት ያለባቸውን ምክንያቶች ሕገ መንግሥቱ አልዘረዘረም፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የፌዴራሉ መንግሥት የተመሠረተው በተለያዩ ፓርቲዎች ጥምረት ሆኖ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የመፍረስ አጋጣሚ ሲደርስበትና አብላጫ መቀመጫ ያለው ፓርቲ በምክር ቤቱ ሲጠፋ ነው፡፡ በዚህ ጊዜም ምክር ቤቱ ሊበተን ይችላል፡፡ በሁለቱም ሁኔታዎች ምክር ቤቱ ከተበተነ፣ በስድስት ወራት ውስጥ አዲስ ምርጫ መደረግ አለበት፡፡ ከዚያም ምርጫው በተደረገ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ መንግሥት መመሥረት አለበት፡፡ ምርጫውን ለማራዘም ያስችላል በሚል የሚነሳው የመጀመርያው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህን አማራጭ መከተል ቢያንስ አራት መዘዞችን/ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል፡፡

አንደኛው ችግር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መንገድ ፓርላማውን ቢበተኑ ምርጫውን በጣም ቢበዛ ለስድስት ወራት ማረዘም ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ምርጫውን ለማራዘም ምክንያት የሆነው የኮሮና ወረርሽን ምክር ቤቱ ከተበተነ ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ ሥጋትነቱ ወይም እንቅፋት መሆኑን ማስቀረት ካልተቻለ ወይም ድጋሚ ቢከሰት ይህ አማራጭ ሌላ ጣጣ ያስከትላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ምርጫው በስድስት ወር እንዲደረግ ጊዜውን ገድቦታል፡፡ ፓርላማው ፈርሷል፡፡ ሕግ የሚያወጣ አካል አይኖርም፡፡ በዚህ ሁኔታ ስድስቱ ወሩ ቢያልቅ ሌላና የባሰ ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ ያስከትላል፡፡

ሁለተኛው ችግር ፓርላማው ከተበተነ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ምርጫ ተደርጎ ዓመታዊ ሥራን ለመጀመር ሕገ መንግሥቱን አስቀድሞ ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዓመታዊ ሥራውን የሚጀምረው በመስከረም ወር በመጨረሻው ሰኞ መሆን እንዳለበት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58 (2) ስለተደነገገ ለዚህ አንቀጽ መፍትሔ መስጠትን ይጠይቃል፡፡ ይህ ሳይሆን ምክር ቤቱ ቢበተን ዓመታዊ ሥራውን ለመጀመር እስከ መስከረም እንዳይጠብቅ፣ ምርጫ በተደረገ በአንድ ወር ሥራ መጀመር እንዳለበት በአንቀጽ 60 (4) ተወስኗል፡፡ ዓመታዊ ሥራው መጀመር ያለበት ደግሞ በመስከረም በመጨረሻው ሰኞ መሆን አለበት ስለሚል ሕገ መንግሥታዊ አጣብቂኝ ውስጥ ይከተዋል፡፡ ሦስተኛው ችግር የፌዴራሉን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከላይ በተገለጸው ሁኔታ ቢበተን የክልል ምክር ቤቶች ዕጣ ፋንታስ ምን ይሁን የሚለው ነው? ከደቡብ ክልል ሕገ መንግሥት በስተቀር የክልል ምክር ቤቶች ሊበተኑ የሚችሉበትን አሠራር በሕገ መንግሥታቸው የለም፡፡ በመሆኑም የፌዴራሉን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መበተን ብቻውን ምርጫውን ለማራዘም አይበቃም፡፡ የክልል ምክር ቤቶች ምርጫም ጭምር ስለሆነ መራዘም ያለበት፡፡

አራተኛው ችግር አገራችን አሁን ያለችበት የፀጥታ ሁኔታ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ የፀጥታ ሁኔታው አስተማማኝ ባልሆነበት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተበተነ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ግድ የሚሉ ሁኔታዎች ቢከሰቱ ምን ሊደረግ እንደሚቻል ሕገ መንግሥቱ አይመልስም፡፡ ሕገ መንግሥቱን ለማፅደቅ በተደረገው ውይይት ላይ ይህ ሁኔታ ተነስቶ ነበር፡፡ ማለትም፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተበተነበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የሚጠይቁ ችግሮች ቢፈጠሩ እንዴት ይስተናገዱ? የሚለው ምክር ቤቱ በሚበተንበት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማወጅ ሥልጣን ለፕሬዚዳንቱ መሰጠት እንዳለበት ተነስቶ ይህ ሁኔታ መንግሥት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰበብ ሥልጣኑን ሊያራዝም ይችላል በሚል ምክንያትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢበተን እንኳን የክልል ምክር ቤቶች ስለሚኖሩ የተፈጥሮ አደጋና ወረርሽኝ ቢከሰት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ስለሚችሉ አሳሳቢ እንዳልሆነ ተገልጾ ጥያቄው ውድቅ ሆኗል፡፡ የክልሎቹ ምክር ቤትም ከፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በተመሳሳይ ጊዜ ቢበተን የሚለውንም ጭምር የዘነጋ መፍትሔ ነው፡፡ 

ከላይ ከቀረቡት አራት ችግሮች አኳያ ሲታይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በመበተን ምርጫው ለማራዘም በመፍትሔነት መጠቀም ተጨማሪ ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ ሊያስከትል ከመቻሉም በተጨማሪ፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያና ለክልል ምክር ቤቶቸ ሌላ መፍትሔ እስካልተገኘ ድረስ በቂ አለመሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማራዘም

ምርጫውን ለማራዘም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅን እንደ አማራጭ ሲቀርብም ይስተዋላል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጅባቸው ምክንያቶች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 ተገልጸዋል፡፡ እነዚህም የውጭ ወረራ፣ የተለመደውን የሕግ ማስከበር ሥርዓት በመጠቀም ሊቀለበስ ሳይቻል ቀርቶ የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ውስጥ የጣለ ሁኔታ ሲከሰት፣ የተፈጥሮ አደጋና  የሕዝብን ጤና አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ መከሰት የሚሉት ናቸው፡፡ የመጨረሻዎቹ ሁለቱ የተከሰቱት በአንድ ክልል ብቻ ከሆነ አደጋዎቹ የተፈጠሩባቸው ክልል መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማወጅ በፌዴራሉም በክልሎቹም ሕገ መንግሥት አማካይነት ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡

ከላይ ከተዘረዘሩት ውስጥ ቢያንስ ከአንድ ክልል በላይ ብቻ ሳይሆን በመላ አገሪቱ ሊዛመት የሚችል ወረርሽኝ ስለተከሰተ የፌዴራሉ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጅ ይችላል፡፡ ዓላማው፣ እነዚህን ችግሮች መቅረፍ መሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ እነዚህ ችግሮች መፈጠር የተነሳ ምርጫ ማድረግ አለመቻሉ ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አማካይነት ምርጫን ማራዘምም የሚያስከትላቸው ችግሮች አሉ፡፡ የመጀመርያው፣ ዓላማውን በመሳት መጥፎ ልማድ መትከሉ ነው፡፡ ምርጫን ለማራዘም የፀጥታ ችግርን መፍጠር ወይም ሌላ ሰው ሠራሽ አደጋን ማስከተል እንደ ታክቲክ መውሰድ ለወደፊትም ሊመጣ ይችላል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ቅቡልነትም ጥያቄ ውስጥ መጣሉ አይቀርም፡፡ ታሪክ እንደሚመሰክረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በማወጅ ነው ብዙ አምባገነኖች ሥልጣን ይዘው የኖሩት፡፡

ሁለተኛው ችግር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ምክንያት የሆነው ጉዳይ ለምሳሌ ከነሐሴ በፊት ቢቆምና ሥጋት መሆኑ ቢቀር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መፍትሔ አይሆንም ማለት ነው፡፡ ካልሆነ ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል የሚደረገው ትግል ላይ ዳተኝነት ሊያስከትል ይችላል፡፡ በዚህ ብቻ ሳይቆም፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታወጀበት ምክንያት ከአዋጁ በኋላ በአጭር ጊዜ ቢቀረፍ የምርጫ ፕሮግራም ወጥቶ እስከሚጠናቀቅ ድረስ አዋጁን ማስቀጠል ተገቢነትም ተቀባይነትም አይኖረውም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት ያህል ፀንቶ ሊቆይ ቢችልም፣ ችግሩ ከተቀረፈ የግድ ስድስት ወራት ይቆይ ሊባል አይችልም፡፡ ይህ የጊዜ እርዝማኔ ጉዳይ ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ ተነስቶ ነበር፡፡ አፅዳቂዎቹ የተስማሙት ከላይ እንደተገለጸው ነው፡፡

ሦስተኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅም ሲነሳም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መኖር አለበት፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ሥልጣን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማራዘም ሌላው አስቸጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ ምክር ቤቱ አዋጁን ለማንሳት ዳተኛ ሆኖ ሊቀጥል ይችል ይሆናል የሚለውን ብንተወው እንኳን፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አማካይነት ሕገ መንግሥቱን የማሻሻል ውጤት የሚኖራቸውን ተግባር መፈጸም ይቻላል ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የሥራ ዘመን ማራዘም እንዲህ ዓይነት ውጤት አለው፡፡ ለምሳሌ ያህል መሬት ሊሸጥ እንደማይችል ሕገ መንግሥቱ ደንግጓል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ መሬትን መሸጥ አይቻልም፡፡ ሕገ መንግሥቱን የማሻሻል ውጤት ስላለው ልክ እንደዚህ ሁሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥትን መተርጎም አይችልም፡፡ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣናቸው ተነጥቋል ማለት አይቻልም፡፡ ስለሆነም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ማለት በአንቀጽ 93 በማናቸውም ሁኔታ ሊታገዱ አይችልም ከሚላቸው ውጭ ያሉት የሕገ መንግሥቱ ድጋጌዎች ወዲያውኑ ቀሪ ሆነዋል ማለት አይደለም፡፡ አዋጁ ስለወጣ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን አምስት ነው የሚለው ቀርቷል ማለት አሳማኝ ሊሆን አይችልም፡፡

አራተኛ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አገር እየተመራች ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ ምርጫ ማድረግ ይቻላልን? የሚለው ብዙ መብቶች ሊታገዱ የሚችሉበት ሁኔታ ስለሚጨምር የምርጫው ተቀባይነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖው ከፍ ማለቱ አይቀርም፡፡

አምስተኛው ችግር የፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከላይ በተገለጸው አኳኋን ሥልጣኑን ቢያራዝም፣ የክልል ምክር ቤቶቹ ጉዳይ አሁንም ሌላ መፍትሔ ይፈልጋል፡፡ የክልል ምክር ቤቶችን የሥራ ጊዜ የማራዘም ሕጋዊ  ሥልጣን የለውም፡፡ ይኼ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ከማይታገዱት ጋርም ይያያዛል፡፡ ከማይታገዱት አንዱ፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ አንድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሪፐብሊክ መሆኗን የሚመለከት ነው፡፡ ፌዴራላዊ ሆነን ማገድ ካልተቻለ፣ ክልልነታቸውን ቀሪ የሚያደርግ ውሳኔ ማሳለፍ አይቻልም፡፡ በአጭሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የምርጫ ጊዜን ማራዘም ከዓላማውም፣ ከሚያስተላልፈውም መጥፎ ልማድና ትምህርት በተጨማሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን የማራዘም ውጤት ይኖረዋል ማለት ሌሎች ሕገ መንግሥታዊ ምስቅልቅሎችን ሊያስከትል ይችላል፡፡

ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል ወይም በመተርጎም ማራዘም

ሌላው አማራጭ ምርጫ ማከናወን የማይቻልበት ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ምን መደረግ እንዳለበት፣ የሥራ ዘመናቸው የሚያበቃው ምክር ቤቶች የሚኖራቸውን ሚና የሚወስን ወይም የሚገልጽ ማሻሻያ ማድረግ ወይም ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም መስጠት ነው፡፡ ምርጫ ማከናወን በማይቻልበት ጊዜ ምን መደረግ እንዳለበት ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ በማድረግ ካልሆነም ሕገ መንግሥቱን መተርጎም ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ጠበቅ ያለ ሁኔታዎች መሟላትን ቢጠይቅም፣ ከዘጠኙ ክልሎች የስድስቱ በአብላጫ ድምፅና የፌዴሬሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች በጋራ ስብሰባ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ከደገፉት ማሻሻል ማድረግ ይቻላል፡፡

የክልል ምክር ቤቶችም በዚሁ መንገድ በራሳቸው ማሻሻያ ማድረግ ይችላሉ፡፡ የእነሱም ቢሆን ከክልል ምክር ቤት በተጨማሪ የወረዳ ምክር ቤቶች ማሻሻያውን ማፅድቅ ይጠይቃል፡፡ በተወሰኑ ክልሎች የብሔረሰቦች ዞን ምክር ቤትም በተመሳሳይ መልኩ ማሻሻያውን መደገፍ አለባቸው፡፡ እዚህ ላይ የሚነሳው ችግር፣ እነዚህ የወረዳና የብሔረሰብ ዞን ምክር ቤቶች የሥራ ዘመናቸው ስላለቀ ሕጋዊ ሥልጣን ያለመኖር ጉዳይ ነው፡፡

ማሻሻያ በማድረግ ምትክ ወይም እንደ አማራጭ ሊቀርብ የሚችለው ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም መስጠት ነው፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ተከስቶ ምርጫ ማድረግ በማይቻልበት ጊዜ የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ዕጣ ፋንታ ምን ይሆናል? የሚለውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ትርጉም እንዲሰጥ ማድረግ ሌላው አማራጭ ነው፡፡ ክልሎችም ቢሆኑ ምን ሊያደርጉ እንደሚገባ አንድም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ካልሆነም በራሳቸው የሕገ መንግሥት ተርጓሚ ኮሚሲዮን መፍትሔ መስጠት ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው wuobishett@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...