Thursday, June 20, 2024

ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር ወደ ቢሮ እየሄዱ እያወሩ ነው]

 • ደህና አደሩ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ደኅንነት አለ ብለህ ነው?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴ? እንዴ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምንድነው ድምፅህ?
 • ጉሮሮዬን አሞኝ ነው፡፡
 • ኡኡ. . .  ብዬ ሳላሲዚህ አውርደኝ፡፡
 • ሰላም ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ በዚህ ቀልድ አላውቅም አልኩህ፡፡
 • በምን ክቡር ሚኒስትር?
 • በኮሮና ነዋ፡፡
 • ኮሮናማ በሕይወታችን እየቀለደ ነው፡፡
 • አሁን ጨዋታውን አትቀይረው፡፡
 • ማለት?
 • ጉሮሮህ ምን ሆኖ ነው?
 • አሞኝ እኮ አልኩዎት፡፡
 • ሰውዬ አደጋ እንዳይደርስብህ፡፡
 • ምን እያሉ ነው?
 • የበሽታው አንደኛው ምልክት እኮ እየታየብህ ነው፡፡
 • ተረጋጉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነው የምረጋጋው?
 • ትናንት ጮኼበት ነው፡፡
 • እ. . .
 • ትናንትና ብዙ ጮኼ ነው ጉሮሮዬ የተዘጋው፡፡
 • ምን ሆነህ ነው የጮኽከው?
 • ያጠፋዋል ተብሎ ነዋ፡፡
 • ምኑን ነው የሚያጠፋው?
 • በሽታውን ነዋ፡፡
 • ምኑ?
 • ጩኸት አሉ፡፡
 • ቂል ሆንክ ልበል?
 • እውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማን ነው ያለህ?
 • ገጠር ያሉ ቤተሰቦቼ ናቸዋ፡፡
 • ይኼ ሕዝብ ምን ይሻለዋል ግን?
 • እንዳይሳሳቱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • እናንተው አይደል እንዴ ዜናውን የሠራችሁት?
 • የምን ዜና?
 • መድኃኒቱ ተገኘ ብላችሁ ነዋ፡፡
 • እሱማ ልክ ነህ፡፡
 • በዚያ ላይ ደግሞ ከባህላዊ መድኃኒት ነው የሚቀመመው አሉ፡፡
 • አዎ ምነው?
 • ስለዚህ ከዚህ በኋላ የባህላዊውን ዕውቀት ማጣጣል ተገቢ አይደለም፡፡
 • ማን አጣጣለ ታዲያ?
 • ይኸው ጩኸቱን አልቀበልም እያሉ አይደል እንዴ?
 • ስማ ይኼ መጃጃል ነው የሚባለው፡፡
 • እኔ ግን በሽታውን የምመክትበት ምንም አቅም ስለሌለኝ የተባልኩትን አደርጋለሁ፡፡
 • ታዲያ ጩኸት ምንም አያደርገውም እኮ?
 • አያዘናጉኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማለት?
 • እንዲያውም ማታ ማታ ብቻ መጮኼን ትቼ በየሰዓቱ አደርገዋለሁ፡፡
 • ለምን?
 • ለማባረር ነዋ፡፡
 • ማንን?
 • ኮሮናን!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ምሣ ለመብላት ሲመለሱ ሚስታቸውን አገኟቸው]

 • ምን ሆነሃል?
 • ምን ሆንኩ?
 • የተጨነቅክ ትመስላለህ፡፡
 • ለምን አልጨነቅ?
 • አትስመኝም እንዴ?
 • ሴትዮ ሥርዓት ያዢ፡፡
 • ምነው?
 • ቢሮ ብዙ ነገር ሳነብ ነበር፡፡
 • ስለምን?
 • ስለበሽታው ነዋ፡፡
 • ስለዚህ?
 • እንዲያውም መለየት አለብን፡፡
 • ምንድነው የምንለየው?
 • መኝታ ነዋ፡፡
 • ለምን ሲባል?
 • በበሽታው ምክንያት ነዋ፡፡
 • ጤነኛ ነህ ግን?
 • ሳልመረመር እሱ እንዴት ይረጋገጣል?
 • ለነገሩ ምርመራ በደንብ ያስፈልገሃል፡፡
 • ምልክቶቹ ይታዩብኛል እንዴ?
 • የምኑ?
 • የበሽታው ነዋ፡፡
 • ኧረ ተረጋጋ ሰውዬ፡፡
 • ስሚ ስንት በሽታ እንዳለብኝ ታውቂያለሽ አይደል?
 • ምን ይጠበስ ታዲያ?
 • ታዲያ አሁን ኮሮና ከያዘኝ ያበቃልኛል እኮ፡፡
 • ተጠንቀቃ፡፡
 • ከስንቱ ልጠንቀቅ?
 • ከምትችለው ነዋ፡፡
 • ደግሞ ታዋቂ ሰዎችን እያደነ ነው የሚይዘው አሉ፡፡
 • እና እኔም ታዋቂ ነኝ እያልክ ነው?
 • ምን ያንሰኛል እባክሽ?
 • ለማንኛውም ብዙ አትፍራ፡፡
 • ርቀትሽን ጠብቂ ሴትዮ፡፡
 • ወይ ጣጣ?
 • ምነው?
 • ለመሆኑ ቢሮ እንዴት ነው የምትሠራው?
 • ዛሬ እኮ ለሠራተኞቹ መልዕክት አስተላለፍኩ፡፡
 • ምን ብለህ?
 • ቢሮ እንዳትመጡ ብዬ ነዋ፡፡
 • ስለበሽታው ግን ተገቢ ግንዛቤ አለህ?
 • አሁንማ ከሳይንቲስቶቹ በላይ የማውቀው እየመሰለኝ ነው፡፡
 • ለማንኛውም በሰዎች ላይ ሽብር እየነዛህ ነው፡፡
 • ማን እኔ?
 • ምን ጥያቄ አለው?
 • እንዳይመስልሽ፡፡
 • ስማ አንድ ነገር ግን አስፈርቶኛል?
 • ምን?
 • መንግሥት እንዳይከስህ ነዋ፡፡
 • በምን?
 • በሽብር!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሀብት ስልክ ደወለላቸው]

 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • በተደጋጋሚ ስልክ ስደውልልዎት አያነሱም፡፡
 • ስልኩንም ፈርቼ እኮ ነው፡፡
 • ለምን?
 • ምናልባት በእሱስ ቢተላለፍ ብዬ ነዋ?
 • ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • አሁን ምንም ነገር ማመን አያስፈልግም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በሽታው የሚተላለፍበት መንገድ እኮ ይታወቃል፡፡
 • ራስህ ተመራምረህ ካልደረስክበት በስተቀር እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡
 • እና እየተመራመሩ ነው?
 • ምን ጥያቄ አለው?
 • አለቅን በሉኛ?
 • እንዴት?
 • ሰሞኑን በሽታው እዚሁ መድኃኒት ተገኘለት የሚል ወሬ ሰምቼ ነበር፡፡
 • ልክ ነህ፡፡
 • ያገኙት እርስዎ እንዳይሆኑ ብዬ ነዋ፡፡
 • ቀልደህ ሞተሃል፡፡
 • ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር?
 • በዚህ ወቅት ይቀለዳል?
 • ያለበለዚያማ ፍርኃትና ጭንቀቱን እንዴት እንችለዋለን?
 • አሁን ቀልድ አያዋጣንም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ምንም ሳይረጋገጥ ግን መድኃኒቱ ተገኘ ተብሎ መነገሩ አሳዝኖኛል፡፡
 • እ. . .
 • ሕዝቡ ክፉኛ ተዘናግቶ ወረርሽኙ ጉዳት እንዳያስከትል ጥንቃቄ መደረግ ነበረበት፡፡
 • ለመሆኑ አዋጥተሃል?
 • ምንድነው የማዋጣው?
 • ገንዘብ ነዋ፡፡
 • ለምን?
 • ወረርሽኙን ለመዋጋት ነዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሥራ እኮ አቁሜያለሁ፡፡
 • ለምን?
 • እንቅስቃሴ ስለተገታ ነዋ፡፡
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • ሠራተኞቼን ላሰናብት ነው፡፡
 • እ. . .
 • ፋብሪካዬንም ልዘጋ ነው፡፡
 • ላለማዋጣት ነው ይኼን የምትነግረኝ፡፡
 • የደወልኩትም አንድ ነገር እንዲደረግልኝ ነው፡፡
 • ምን?
 • ለእኔም እንዲዋጣልኝ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]

 • ቁጥሩ እየጨመረ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የምኑ?
 • የበሽታው ተጠቂዎች ነዋ፡፡
 • ኧረ እንዲያውም ጥሩ ነው ያለነው፡፡
 • ለነገሩ እስካሁን ምንም ሞት አልተመዘገበም፡፡
 • እሱንማ እናንተ አፈረሳችሁ፡፡
 • እንዴት?
 • በበሽታው ምክንያት የመጀመርያ ሞት ተመዘገበ አይደል እንዴ?
 • እያሟረቱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን አሟርታለሁ?
 • ታዲያ ምንድነው የሚሉት?
 • ባለፈው መጠጥ ቤት የተገደለውስ?
 • እ. . .
 • ከኮሮና ጋር በተገናኘ አይደል እንዴ የተገደለው?
 • አሽሙር መሆኑ ነው?
 • ኧረ እኔ ከልቤ ነው፡፡
 • ለማንኛውም እኛ በበኩላችን ብቃታችንን አሁን እናስመሰክራለን፡፡
 • የምን ብቃት?
 • የአመራር ብቃታችንን ነዋ፡፡
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • በሽታው እኛ ጋ አይገባም፡፡
 • ደስ ይለኝ ነበር፡፡
 • እናሳይዎታለን ስልዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በሽታው እንደማይመርጥ ግን ታውቃለህ አይደል?
 • ምን?
 • ዘር!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት ሐዘን ለመድረስ ጎረቤት ተገኝተው ለቀስተኛው በሙሉ የሚያወራው ነገር አልገባ ብሏቸው ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ባለቤታቸውን ስለጉዳዩ እየጠየቁ ነው] 

ጎረቤታችን ሐዘን ለመድረስ ብሄድ ለቀስተኛው በሙሉ በሹክሹክታ ያወራል። ግን የሚያወሩት ነገር ሊገባኝ አልቻለም። ምንድነው የሚያወሩት? እኔ ምን አውቄ? እንዴት? የሚያወሩትን ምንም አልተሰማሽም? እኔ እንድሰማ የፈለጉ አይመስልም ግን ... ግን...

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት የሚታወጁ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ማለቴ ነው። ምን ታወጀ? አንዴ ከዕዳ ወደ ምንዳ አላችሁ፡፡ እሺ? የእሱን ውጤት እየጠበቅን ሳለ ደግሞ... እ...? ኢትዮጵያ ታምርት...

[ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን በተጀመረው አገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ስለተላለፉ መልዕክቶች በተመለከተ ከባለቤታቸው ጋር እያወጉ ነው] 

እኔ ምልህ? እ... አንቺ የምትይው? አለቃህ በምክክር መድረኩ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት አደመጥክ? አዎ፡፡ የሚገርም እኮ ነው አልተገረምክም? ምኑ ነው የሚያስገርመው? ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ምከሩና አምጡ ብለው የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ...