Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየኮሮና ቫይረስ ሥርጭትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

ቀን:

በውብሸት ሙላት

የኮሮና ቫይረስ በወረርሽኝ መልክ በዓለም ደረጃ በመከሰቱ አገሮችን ከባድ ሥጋት ላይ ጥሏል፡፡ መንግሥታትም የቫይረሱን ሥርጭት በመግታት ሕዝባቸውን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከሚመጣ ቸነፈር ለመታደግ ደፋ ቀና እያሉ ነው፡፡ ቫይረሱ በመጀመርያ የታየባትን፣ ቻይናን፣ ጨምሮ በበርካታ አገሮች ተስፋፍቶ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡ ቫይረሱ የሚያስከትለውን አደጋ ለመቀነስ አገሮች የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ ነው፡፡ ሕዝብ የሚገናኝባቸውን ድርጅቶችና አገልግሎቶች ከመዝጋት ጀምሮ በአገር ደረጃም ሕዝብ ከቤት እንዳይወጣ ማድረግን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ፣ በኢትዮጵያም ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው እየተመለሱ ነው፡፡ የምሽት መዝናኛ ቤቶች እንዲዘጉ ተወስኗል፡፡ ፍርድ ቤቶች በከፊል ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ ተወስኗል፡፡ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አውቶብሶች በወንበር ቁጥር ልክ ብቻ ሰው እንዲጭኑ እየተደረገ ነው፡፡ በእጅ በመጨባበጥ የሚደረግ ሰላምታም እየቀረ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከላይ የተጠቀሱት መንግሥታዊ ውሳኔዎች የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት የተላለፉ ናቸው፡፡ የኅብረተሰብ ጤናን አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ተላላፊ በሽታዎች በሚከሰቱበት ወቅት አሁን መንግሥት እንዳደረገው ዓይነት ዕርምጃዎች ሊወስዱ እንደሚችሉ ግልጽ ነው፡፡ የመንግሥትም ተፈጥሯዊ ግዴታም ኃላፊነትም  ነው፡፡

ይሁን እንጂ፣ መንግሥት የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች የሰዎችን ሰብዓዊ መብት የሚያጣብብና የሚገድብ ሊሆን ስለሚችል እንዴትና ማን ይወስን የሚለው በሕግ ተደንግጓል፡፡ በሕግ ባይቀመጥም ከመንግሥት መኖር ተፈጥሯዊ ሁኔታ ጋር የተቆራኘ ስለሆነ ሕዝብን ከአደጋ መጠበቅና መከላከል አይቀሬ ግዴታ ነው፡፡

እንደ ኮሮና ቫይረስ ሁሉ፣ የኅብረተሰብን ጤና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ተላላፊ በሽታ ሊከሰት እንደሚችል ማንም ሰው የሚገምተውም በታሪክ የታወቀ ስለሆነ፣ እንዲህ ዓይነት ችግር ሲኖር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳይቀር ሊታወጅ ይችላል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛም መንግሥት እያሳለፋቸው ያሉትን አንዳንድ ውሳኔዎች በመንቀስ ሕጋዊነታቸውን ማየት ነው፡፡

የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትንና ወረርሽኝን ለመከላከል የተላለፉት ውሳኔዎች ሕጋዊ አቋማቸው (Status) ግራ ማጋባቱ አይቀርም፡፡ የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ ሲባል እየተወሰዱ ያሉት ዕርምጃዎች ተገቢ መሆናቸው አያጠያይቅም፣ በሕግ መነጽር ሲታዩ ምን ይመስላሉ የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር ሲፈጠር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊጣል እንደሚችል በማያሻማ ሁኔታ ተገልጿል፡፡

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93 ላይ እንደተቀመጠው ከአራቱ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ እንኳን ከተከሰተ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ በፌደራል መንግሥቱ ሊታወጅ ይችላል፡፡ እነዚህም የውጭ ወረራ፣ የተለመደውን የሕግ ማስከበር ሥርዓት በመጠቀም ሊቀለበስ ባለመቻሉ የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ውስጥ ሲገባ፣ የተፈጥሮ አደጋና የሕዝብን ጤና አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ መከሰት የሚሉት ናቸው፡፡ የመጨረሻዎቹ ሁለቱ የተከሰቱት በአንድ ክልል ብቻ ከሆነ ደግሞ አደጋዎቹ የተፈጠሩባቸው ክልል መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ ሊያውጁ ይችላሉ፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ የዓለም አገሮችን ለጭንቅ የዳረገ፣ የሕዝብን ጤና አደጋ ላይ የጣለ፣ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሕይወትን የሚቀጥፍ በሽታ እየተዛመተ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ፣ የሰው ሕይወት ባያልፍም ወደ አንድ ደርዘን ገደማ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡ ቻይና፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጣሊያን፣ ስፔን፣ አሜሪካና በሌሎች በርካታ አገሮች ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡

ከቫይረሱ ባህርይና መተላለፊያ መንገዶች አንፃር የሰዎችን እንቅስቃሴና ቅርርቦሽ መገደብ አስፈላጊ ነው፡፡ ጥያቄ የሚሆነው፣ እንዲህ ዓይነት ገደቦችን የሚጥለው ማን ነው? የሚለው ነው፡፡ ይሄ በተራው ይዞት የሚያስከትለው ሌላ ጥያቄ ይዞ ይመጣል፡፡ በቀረ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያስወጣ እንደሚችል የሚያጠራጥር አይደለም፡፡

ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያቶች፣ የሆኑትን ድርጊቶች መከሰታቸውን በማረጋገጥ የማወጅ ሥልጣን የተሰጠው አስፈጻሚው አካል፣ በተለይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፡፡ ነገር ግን የሕግ አውጭው አካል ዕውቅና ከነፈገው አዋጁ ውድቅ ሆኖ አስፈጻሚው አካል መደበኛውን የሕግ ሥርዓት ብቻ በመከተል ድርጊቱን ማስወገድ አለበት ማለት ነው፡፡ አዋጁ ከፀደቀ ደግሞ በመደበኛው የአገር አስተዳደር ጊዜ ይከበሩ የነበሩ መብቶች፣ አሠራሮች፣ ተቋማት ወዘተ ሊታገዱ ስለሚችሉ እነዚህ የታገዱትን መብቶች አስቀድሞ በማሳወቅ አስተዳደሩ ይቀጥላል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን በመግታት፣ የሕዝብን ጤና ከአደጋ ለመታደግ የተላለፉት ውሳኔዎችን በምንመለከትበት ጊዜ ግን ከላይ በተገለጸው ሁኔታ፣ ማለትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ፣ የተሰጡ አለመሆናቸውን ግልጽ ነው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረቱ የአገር ህልውና (Survival) ነው፡፡ አንድ አገር  እንደቀድሞው መኖሩን እንዳይቀጥል የሚያደርግ፣ ፀንቶ ያለውን የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የሚያናጋ፣ በተለመደው የሕግ አሠራርና አስከባሪ ኃይል ሊመከት የማይቻል ሁኔታ በድንገት ሊያጋጥም ይችላል፡፡  አስቸኳይ ጊዜ ሕግ  የሚታወጀው እንዲህ ዓይነት አስገዳጅ ሁኔታዎች (Necessity) ሲከሰቱ ነው፡፡ ‹‹አስገዳጅ ሁኔታ ሕግ አያውቅም፣ አያከብርምም!›› እንዲሉ ሕግ የማያውቅን ሁኔታ በሕግ መመከት ወይንም መመለስ አይቻልም፡፡

የአገር ህልውና ላይ አደጋ የሚጥል ነገር ቢከሰትና ሕጋዊ አካሄዶችን መከተል ደግሞ አደጋውን የማያስወግድ ከሆነ በተረጋጋና በአዘቦት ቀናት የተለመደውን አሠራር በመተው፣ በቀድሞው አስተዳደር ዓይን ሲለካ ሕጋዊ ያልሆነ መንገድን ተከትሎም ቢሆን አገርን ማትረፍ፣ ሕዝብን ከአደጋ ማዳንና መጠበቅ ተገቢ ነው የሚሉ አሉ፡፡ የአገርን ህልውና አደጋ ውስጥ የጣለ አስገዳጅ ሁኔታ ሲከሰት አስፈጻሚው አካል ማንኛውንም መንገድ በመከተል ከቀውስ አውጥቶ ወደ መደበኛው አመራር የመመለስ ሥልጣን ሊሰጠው ይገባል የሚሉም አሉ፡፡ የቀውስ ጊዜ አመራር ስለሆነ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ላይመራ ይችላል፡፡

ሕገ መንግሥታዊነትና የሕግ የበላይነት ሳይሆን የአስፈጻሚው አካል የበላይነት የሚሰፍንበትም የሚፈተንበትም ወቅት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ቀውስ ሲያጋጥም አገር በምን መንገድ መመራት እንዳለባት ለመወሰን የሚወጡ ሕጎች የአስቸኳይ ጊዜ ሕጎች ይባላሉ፡፡ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን በመግታት የሕዝብን ጤና በመጠበቅ የአገርን ህልውና ማዳን ያስፈልጋል፡፡ ሕዝብ ካለቀ፣ አገርም ያልቃል፡፡ ሕዝብ ከጠፋ፣ አገርም ይጠፋል፡፡ ሕዝብ የሌለው አገር አይኖርም፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያስወጣ ሁኔታ በሚያጋጥማቸው ጊዜ በርካታ አገሮችምና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ምን መደረግ እንዳለበትና እንደሌለበት የሚገልጹ ሕጎችን አሏቸው፡፡ በእርግጥ እንደ ሲዊዘርላድ የአስቸኳይ ጊዜ እንዴት መመራት እንዳለበት ሕግ አያስፈልግም፤ ፕሬዚዳንቱ ትክክል ነው ብሎ ያመነበትን ነገር በሙሉ የማድረግ ሥልጣን አለው የሚሉም አሉ፡፡

በኢትዮጵያ፣ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ፓርላማዊ ስለሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማወጅ ሥልጣኑ የፕሬዚዳንት አይደለም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩም አይደለም፣ ሊሆንም አይችልም፡፡ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ሲባል የተላለፉት ውሳኔዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅነት አቋም ያላቸው ሳይሆን መደበኛ የአስፈጻሚው የመንግሥት አካል ተግባርና ኃላፊነት እንደሆኑ ተደርገው የተላለፉ ይመስላሉ፡፡ ውሳኔዎቹ ከተላለፈባቸው መንገድና ከወሳኙ አካል በስተቀር፣ ይዘታቸው ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዓይነት ነው፡፡

የሕግ አስፈጻሚው አካል የዕለት ተዕለት መደበኛ ተግባር ለመምሰላቸው በአስረጂነት ታሪካዊ አቻዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ምርጫ 1997ትን ተከትሎ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ለአንድ ወር ያህል በአደባባይ ሠልፍና ስብሰባ ማድረግን በመከልከላቸው፣ በወቅቱ ዋነኛ ተፎካካሪ የነበረው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርጊት ሕገወጥ ነው በማለት ክስ አቅርቦ ስለነበር፣ ፍርድ ቤቱም በተራው ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሚፈልግ በመግለጽ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ልኮት ነበር፡፡

ጉባዔው ግን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ነገር በአስፈጻሚው የመንግሥት አካል የሚጠበቀውን በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት ስብሰባና ሠልፍ የመከልከል ውሳኔ ሕገ መንግሥት የሚቃረን ስላልሆነ ትርጉም እንደማያስፈልገው በመግለጽ ለፍርድ ቤቱ መልሶታል፡፡ ከሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔው ውሳኔ መረዳት የሚቻለውና ውሳኔው ትክክል ነው ከተባለ፣ አሁንም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ሲባል ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ መወሰን፣ ስብሰባዎችን እንዳይካሄዱ ማዘዝ በሥልጣናቸው ሥር ነው በሚል ለመሞገት ይህንና ሌሎች ምሳሌዎችን ጭምር ማቅረብ ይቻላል፡፡ በሕግ ሚዛን ላይ ሲቀመጡ ክብደታቸው ምን ያህል ነው? የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡

ከላይ ከተገለጸው በተለየ መልኩ፣ በጤና አጠባበቅ አዋጁ ላይ እንደተገለጸው ከሆነ፣ ወረርሽኝና መሰል በሽታዎች ተከስተው የሕዝብን ጤና አደጋ ላይ የሚጥሉ ከሆነ የጤና ሚኒስቴር ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ሕዝብ የሚሰበሰብባቸውን ድርጅቶች እንዲዘጉ፣ ትራንስፖርት እንዲቆም ሊወስን እንደሚችል ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ከዚህ አዋጅ አንፃር ሲታይ፣ በአንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አካል ውሳኔ ማሳለፍ ይችላል፡፡

የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የተላለፉት ውሳኔዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማይባሉ ናቸው ሊባል ቢችልም፣ የሚጋሩት ነገር መኖሩ ግን ግልጽ ነው፡፡ እግረ መንገዳችንን አንድ ወሳኝ ነጥብ እናንሳ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያሳልፈው አካል ስብሰባ ማድረግ የማይችል ከሆነስ? የሚል፡፡ እንደሚታወቀው፣ በአንቀጽ 93 መሠረት በማናቸውም መልኩ ሊታገዱ የማይችሉ ነገሮችን ሲዘረዝር የአገሪቱን መንግሥት ስያሜና ሦስት መብቶችን ይዟል፡፡

በመሆኑም ከመብት በተጨማሪ የመንግሥትን ስያሜ ማካተቱ ሊታገዱ የሚችሉት መብቶች ብቻ አለመሆናቸውን ያመላክታል፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ሌሎች መዋቅሮችና ተቋማት ሊታገዱ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ በእርግጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያፀድቀውና የሚያራዝመው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን ስናይ ሊታገድ የማይችል ተቋም ነው ማለት ይቻላል፡፡

እዚህ ላይ ለማንሳት የተፈለገው ዋናው ነጥብ የአስቸኳይ ጊዜ ሕግ በባህርይው አስፈጻሚውን አካል ሉዓላዊና ከሕግ በላይ በማድረግ አምባገነንነትን ስለሚያበረታታ ሌሎች ተቋማት እንደማይታገዱ በግልጽ መቀመጥ ቢኖርበትም፣ በተፈጠረው ችግር ምክንያት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሰብሰብ የማይችልበት ሁኔታ ቢፈጠር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዕጣ ፋንታ ምን ይሆናል የሚለው በራሱ አጠያያቂ ነው፡፡

 ከኢራን የፓርላማ አባላት ውስጥ ከሃያ በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተሰምቷል፡፡ ቫይረሱን ለመከላከል ስብሰባን መከልከል ያስፈልጋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ቢሆንም በቫይረሱን ምክንያት መሰብሰብ የማይችሉ ከሆነ ያው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢታወጅ እንኳን ለማስፀደቅ አይቻልም ማለት ነው፡፡

በእርግጥ ይህ ሁኔታ የሚኒስትሮች ምክር ቤትንም ሊጨምር ይችላል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአካል ተገናኝቶ ስብሰባ ማካሄድ ካልቻለ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ማሳለፍ ሊቸገር ይችላል፡፡ በስልክና በሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች ስብሰባ ማድረግ ከተቻለና በሕግ ከተፈቀደ መወሰን የሚቻል ሲሆን፣ በአካል መገኘትን ግድ የሚል ሕግ በሚኖርበት ጊዜ ግን አዳጋች መሆኑ አይቀርም፡፡ በዋናነት የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት ውሳኔ ያሳለፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሆኑ፣ ከሚኒስትሮች ጋር ስብሰባ ማድረግ አስቸግሮ ሊሆን ይችላል ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ እንዲህ ቢሆንስ የአስቸኳይ ጊዜ አካል አዋጅ ማውጣት ይችላሉ ወይ?

ይሁን እንጂ፣ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋን መሠረት ያደረጉ ችግሮች፣ የሕዝብን ጤና ለአደጋ የሚጥሉ በሽታዎች በሚከሰቱበት ጊዜ፣ የፌደራሉ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመጣል ሥልጣን እንደሚኖረው፣ ክልሎችም አላቸው፡፡ ከፌደራሉ መንግሥት ውሳኔ በተለይም ተጨማሪ ውሳኔዎችን ሊያሳልፉ ይችላሉ፡፡ የትግራይ ክልልም ይህንን ሥልጣኑን ተጠቅሞ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል፡፡ ሌሎች ክልሎች ግን እንደ ፌደራሉ መንግሥት የተለያዩ ውሳኔዎችን በክልሎቹ የሕግ አስፈጻሚው አካላት አማካይነት አስተላልፈዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሳለፏቸው ውሳኔዎች ምክንያት ክልሎች ተጨማሪ በጀት የሚያስወጣቸው ሁኔታ ቢመጣ ወጪውን ማን ይሸፍናል የሚለው ውሳኔ ያሳለፈው ማን ነው የሚለውን ተከትሎ የሚመጣ ነው፡፡ ለአብነት፣ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ክልሎቹ ለተጨማሪ ወጪ ቢዳረጉ፣ የበጀት ጥያቄ መኖሩ ስለማይቀር በዚህ መልክ መወሰኑ በሕግና ሥርዓት ብቻ የምትመራ አገር ብትሆን የሕግ ጣጣ ይዞ መምጣቱ አይቀርም ነበር፡፡ እዚህ ላይ ሳይወሳ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ ቢኖር በክልል መንግሥታት የሚተዳደሩትን ዩኒቨርሲቲዎች ጨምሮ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችና ተቋማት፣ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የሚያስተዳደረው፣ በጀቱን የሚችለው የክልል መንግሥት መሆኑን ነው፡፡  

የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የተላለፉ ውሳኔዎች አስገዳጅነት የላቸውም ማለት ይቻላል፡፡ የአስገዳጅነት ባህርይ ያልኖራቸው ከውሳኔው ይዘት የተነሳ ነው፡፡ ውሳኔውን የተላለፈ የሚከተለው ቅጣት የለም፡፡ ማመንታት የታየበት ሕዝብ እንዳይሰባሰብ በማድረግ ቫይረሱን ሥርጭት መግታት እንደሆነ ቢታወቅም፣ በየወረዳውና በየቀበሌ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎች የያዙ ስብሰባዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ስንታዘብ ነው፡፡ የውሳኔዎቹን ሕጋዊነት በማጠናከር፣ ተፈጻሚነታቸውን በማጥበቅም ጭምር ወረርሽኝ እንዳይከሰት ማድረግ ከመንግሥት የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፡፡ የሕግም የመንግሥትም መኖር ለሕዝብ ነውና!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው wuobishett@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...