Saturday, June 22, 2024

ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው

[ክቡር ሚኒስትሩ ለአንድ ካድሬ ስልክ ይደውላሉ]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሰላም ይንሳህ፡፡
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው ስትል ትንሽ አታፍርም ደግሞ?
 • የሰው ወሬ ሰምተው እንዳይሆን ክቡር ሚኒስትር?
 • ራሴ አረጋግጫለሁ፡፡
 • እውነት ክቡር ሚኒስትር እኔ ከብልፅግና ጋር ለዘለዓለም ነው የተፈራረምኩት፡፡
 • እንዳንተ ዓይነቱማ የብልፅግና ሳይሆን የብልግና ፓርቲ ካድሬ ነው መሆን ያለበት፡፡
 • ምን አጠፋሁ ክቡር ሚኒስትር?
 • ለመሆኑ የት ነው የምትኖረው?
 • ለምን ግራ ያጋቡኛል ክቡር ሚኒስትር?
 • ለነገሩ ግራ ባትጋባማ ኖሮ እንዲህ አታደርግም ነበር፡፡
 • ምን አደረግኩ ክቡር ሚኒስትር?
 • መንግሥት የሰጠውን መግለጫ አልሰማህም?
 • ስለምን?
 • ስለኮሮና ቫይረስ ነዋ፡፡
 • ሰምቻለሁ ምነው?
 • ታዲያ የምን ሥልጠና ነው የምታካሂዱት?
 • የብልፅግና ነዋ፡፡
 • ስብሰባ እኮ ተከልክሏል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ምን ነካዎት?
 • ምነው?
 • በዚህማ ቀልድ አናውቅም፡፡
 • በምኑ?
 • በብልፅግና ነዋ፡፡
 • እሱ ጥሩ ነው ግን ወረርሽኝ ገብቷል እኮ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ብልፅግና የተወለደው እኮ ወረርሽኝን ለመከላከል ነው፡፡
 • የቱን ወረርሽኝ?
 • የድህነትን ወረርሽኝ ነዋ፡፡
 • የተነከርክ ካድሬ ነህ ልበል?
 • እኔ በብልፅግና ቀልድ አላውቅም፡፡
 • ለማንኛውም ወረርሽኙ ከባድ ነው፡፡
 • አያስቡ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • ይኼንን ወረርሽኝ እንመክተዋለን፡፡
 • በምን?
 • እኛ ራሳችን ሥልጠናውን ከመጀመራችን በፊት አሰምተናል፡፡
 • ምንድነው ያሰማችሁት?
 • መፈክር ነዋ፡፡
 • እና በመፈክር ወረርሽኙ ይጠፋል ያለህ ማን ነው?
 • ያው ለሁሉም ነገር መፈክር ያስፈልጋል ብዬ ነው፡፡
 • እ…
 • ያውም እጅ ለእጅ ተያይዘን ነው መፈክሩን ያሰማነው፡፡
 • ወይ ድንቁርና፡፡
 • ምነው?
 • ሰውዬ ወረርሽኙን የምንመክተው በመፈክር ሳይሆን በመጠንቀቅ ነው፡፡
 • ወረርሽኙ ግን የሚያጠቃው በዕድሜ የገፉትንና ታማሚዎችን ነው ሲባል ሰምቻለሁ እኮ?
 • ሌላ በጣም የሚያጠቃቸው ሰዎች አሉ፡፡
 • እነ ማንን?
 • ነፃ የሆኑ ሰዎችን፡፡
 • ከምን?
 • ከዕውቀት!

[ክቡር ሚኒስትሩ ምሳ ለመብላት ቤት ሄደው ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • መጀመርያ ይኼን ብላ፡፡
 • ምንድነው?
 • መድኃኒት ነዋ፡፡
 • የምን መድኃኒት ነው?
 • የኮሮና፡፡
 • እየቀለድሽ ነው ሴትዮ?
 • በኮሮና ቀልድ የለም፡፡
 • ይኼ ምንድነው?
 • ነጭ ሽንኩርትና ፌጦ ነዋ፡፡
 • ኮሮና እኮ መድኃኒት አልተገኘለትም፡፡
 • ፈረንጆቹ ነዋ ያላገኙለት፡፡
 • ምን እያልሽ ነው?
 • እኛ አግኝተንለታል፡፡
 • ምንድነው መድኃኒቱ?
 • ነጭ ሽንኩርትና ፌጦ አልኩህ፡፡
 • እ…
 • ምነው?
 • አንቺ ፊደል ቆጥረሻል አይደል እንዴ?
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • እንዲህ ዓይነት ወሬ ስታወሪ አሳዝነሽኝ ነዋ፡፡
 • የእኛ አባቶች አዋቂዎች ናቸው፡፡
 • ማለት?
 • የባህላዊ ሕክምና አባቶቻችን ለብዙ በሽታዎች መድኃኒት አግኝተዋል፡፡
 • ስሚ እኔ የባህል መድኃኒትን እየናቅኩ አይደለም፡፡
 • ታዲያ ምን እያልከኝ ነው?
 • አሁን እንደምታደርጊው ዓይነት ቂልነት ግን ችግር ውስጥ ይከተናል፡፡
 • ማለት?
 • ነጭ ሽንኩርትና ፌጦ መውሰድሽ ጥሩ ነው ግን ወረርሽኙን ይከላከለዋል የሚለውን ተረት ተረት አቁሚ፡፡
 • ለምን?
 • በሳይንሳዊ መንገድ ስላልተረጋገጠ ነዋ፡፡
 • አሁን ሳይንስ እንደማያዋጣን ያረጋገጥንበት ወቅት ነው እኮ፡፡
 • ታዲያ ምንድነው የሚያዋጣው?
 • እምነት ነዋ፡፡
 • እምነትማ ሁሌም አስፈላጊ ነው፡፡
 • ይኸው እኔም ነገ ንግሥ ልሄድ ነው፡፡
 • አብደሽ መሆን አለብሽ፡፡
 • ምን?
 • ለራስሽ ባታስቢ እንዴት ለእኛ ለቤተሰቦችሽ አታስቢም?
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • ሕዝብ የሚበዛበት ቦታ ሰው እንዳይሄድ ተከልክሏል እኮ፡፡
 • በዚህማ ቀልድ የለም፡፡
 • አንቺም በሰው ሕይወት አትቀልጂ፡፡
 • ልፀልይ እኮ ነው የምሄደው፡፡
 • ፀሎቱንማ ማን ከለከለሽ?
 • ታዲያ ለምን አትሂጂ ትለኛለህ?
 • መጠንቀቅ ስለሚያስፈልግሽ ነዋ፡፡፡
 • በእምነቴ ቀልድ የለም፡፡
 • እምነት እኮ በመሄድ አይደለም ያለው፡፡
 • ታዲያ የት ነው ያለው?
 • በልብ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጋር ተገናኙ]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እዚያው በሩቁ፡፡
 • ልጨብጥዎት እኮ አይደለም፡፡
 • በሽታው ከመጨባበጥም ባለፈ ርቀትን መጠበቅ ይጠይቃል፡፡
 • ግን ምን ያደርጋል ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት?
 • እየፈራሁ ነው፡፡
 • ለምን?
 • በሽታው ብዙ ጥፋት እንዳያደርስ ነዋ፡፡
 • መቼም እናንተ ሁሌ ሟርት ነው የምታወሩት፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የእውነቴን እኮ ነው፡፡
 • ማለት?
 • ወሬያችሁና ተግባራችሁ ለየቅል ስለሆኑ ነዋ፡፡
 • ይኸው በየሰዓቱ ታጠቡ እያልን አይደል እንዴ?
 • እሱ ለእኔ ቀልድ ነው፡፡
 • የምን ቀልድ ነው?
 • በእንባችን ነው እንዴ የምንታጠበው?
 • አልገባኝም?
 • ውኃ ከየት ይምጣ?
 • እ…
 • ውኃውን ሳትለቁት በምን እንታጠብ?
 • የአገራችንን ችግር እያወቅከው?
 • ለነገሩ ከትንሽ ጊዜ በኋላ በእንባችን እንታጠባለን፡፡
 • ለምን?
 • እነ ጣሊያንን ያየ የእኛ አገር ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብደውም ብዬ ነው፡፡
 • እናንተ ሁሌ ሟርት ብቻ ነው የምታወሩት በቃ?
 • ክቡር ሚኒስትር ይኸው ሥራም እያስቆማችሁ ነው፡፡
 • ወረርሽኙ እንዳይዛመት እኮ ነው?
 • ኢኮኖሚው ላይ ሌላ ወረርሽኝ ልትቀሰቅሱበት ነዋ፡፡
 • ሕዝቡ ላይ ክፉ ከሚደርስ ኢኮኖሚው ቢጎዳ አይሻልም?
 • ነጋዴዎች እኮ ከአሁኑ ዋጋቸውን ማናር ጀምረዋል፡፡
 • እነሱንም ዋጋቸውን እንሰጣቸዋለን፡፡
 • ምን ልታደርጓቸው?
 • እንዘለዝላቸዋለና፡፡
 • እንዴት?
 • በዚህ ጊዜ ሕዝብ ላይ የሚቆምር ነጋዴን እኛም እንቆምርበታለን፡፡
 • በምኑ?
 • በሕይወቱ ነዋ፡፡
 • ይኼ እንኳን ትንሽ ያስፈራል፡፡
 • በዚህ ጊዜ የማንንም ብልግና የምናስተናግድበት ትዕግሥት የለንም፡፡
 • እኛም አለቀልን በሉኛ፡፡
 • አርፋችሁ ካልተቀመጣችሁ መቼ ይቀርላችኋል?
 • ለማንኛውም እኛ የመንግሥትን አካሄድ አልወደድነውም፡፡
 • በምን ጉዳይ?
 • በኮሮና ጉዳይ ነዋ፡፡
 • ታዲያ እንደለመዳችሁት በኮሮና ላይም ለምን አታዘጋጁም?
 • ምን?
 • የተቃውሞ ሠልፍ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]

 • ተከበናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይህችን አባባል የት ነበር የማውቃት?
 • ከእሷ ጋር እኛ ግንኙነት የለንም፡፡
 • ማን ነው የከበባችሁ?
 • ቫይረሱ ነዋ፡፡
 • እንዴት?
 • ኤርትራ መግባቱን ሰምተን ነዋ፡፡
 • ማለት?
 • ያው እናንተም ጋ ከገባ ሰነባበተ ብለን ነዋ፡፡
 • የራሳችሁ አገር እንዳላችሁ ነው እንዴ የምታስቡት?
 • ዓለም ከእኛ መማር ነበረበት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • እኛ ቫይረሱ ከመምጣቱ በፊት ነዋ ራሳችንን አጥረን ያስቀመጥነው፡፡
 • እ…
 • እኛ ጋ በምን አባቱ ይገባል ብለው ነው?
 • እኔም እንዳይገባ ነው የምፀልየው፡፡
 • ለምን?
 • ቫይረሱ እንደ እናንተ ዓይነቱን ዕድሜ ጠገብ ነዋ የሚያጠቃው፡፡
 • እ…
 • በሕግ ስለምንፈልጋችሁ ኮሮና እንዳይቀድመን ነዋ፡፡
 • ለማንኛውም ክቡር ሚኒስትር እኛ ኮሮናን አንፈራውም፡፡
 • ማንን ነው ታዲያ የምትፈሩት?
 • ፌዴራል መንግሥትን!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት ሐዘን ለመድረስ ጎረቤት ተገኝተው ለቀስተኛው በሙሉ የሚያወራው ነገር አልገባ ብሏቸው ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ባለቤታቸውን ስለጉዳዩ እየጠየቁ ነው] 

ጎረቤታችን ሐዘን ለመድረስ ብሄድ ለቀስተኛው በሙሉ በሹክሹክታ ያወራል። ግን የሚያወሩት ነገር ሊገባኝ አልቻለም። ምንድነው የሚያወሩት? እኔ ምን አውቄ? እንዴት? የሚያወሩትን ምንም አልተሰማሽም? እኔ እንድሰማ የፈለጉ አይመስልም ግን ... ግን...

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት የሚታወጁ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ማለቴ ነው። ምን ታወጀ? አንዴ ከዕዳ ወደ ምንዳ አላችሁ፡፡ እሺ? የእሱን ውጤት እየጠበቅን ሳለ ደግሞ... እ...? ኢትዮጵያ ታምርት...

[ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን በተጀመረው አገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ስለተላለፉ መልዕክቶች በተመለከተ ከባለቤታቸው ጋር እያወጉ ነው] 

እኔ ምልህ? እ... አንቺ የምትይው? አለቃህ በምክክር መድረኩ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት አደመጥክ? አዎ፡፡ የሚገርም እኮ ነው አልተገረምክም? ምኑ ነው የሚያስገርመው? ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ምከሩና አምጡ ብለው የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ...