Wednesday, June 7, 2023

አዲሱ የቋንቋ ፖሊሲ ለዘመናት ጥያቄ ምላሽ ይዞ ይሆን?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ለዓመታት ኢትዮጵያን የመሩ መንግሥታት የተጻፈና በግልጽ የተመለከተ የቋንቋ ፖሊሲ ባይኖራቸውም፣ በአንድም በሌላም መንገድ የሚጠቀሙትን ቋንቋ ሲያበለፅጉና ለተለያዩ ዓላማቸው ማሳኪያ ሲጠቀሙ ቆይተዋል፡፡ በዚህ ረገድ አማርኛ ቋንቋ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን፣ በተለይ አፄ ቴዎድሮስ አማርኛን የመጻፊያ ቋንቋ ማድረጋቸውን ለቋንቋው ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ሲሉ አጥኚዎች ያስረዳሉ፡፡ ከእሳቸው ቀጥሎ የነበሩት የአፄ ዮሐንስና የአፄ ምኒልክ አስተዳደሮች ተመሳሳይ መንገድ በመከተላቸው የአማርኛ ቋንቋ እንዲበለፅግ ሆኗልም ይላሉ፡፡

ሆኖም ከእነዚህ ቀደምት ያልተጻፉ የቋንቋ ምርጫዎች በተለየ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥተ ተሻሽሎ በተዘጋጀው ሕገ መንግሥት አማርኛ ብሔራዊ ቋንቋ እንደሆነ ታውጇል ሲሉ፣ እ.ኤ.አ. በ2006 ጥናት ያቀረቡት ጌታቸው አንተነህና ደርብ አዶ ያስረዳሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ አማርኛ የማስተማርያ ቋንቋ ሆኖ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲያገለግል ተደርጓል፡፡ አማርኛ በተደረገለት የማበልፀግ ድጋፍ የተነሳም የመገናኛ ብዙኃን ቋንቋ ሲሆን፣ ሌላ የአገሪቱን ቋንቋዎችን ለማበልፀግ ግን ምንም የታየ ጥረት እንዳልነበረና ይኼም በወቅቱ በነበረው አንድ ቋንቋ አገራዊ ኅብረት ያግዛል በሚለው አስተሳሰብ የተመራና ወዳልሆነ አቅጣጫ የተወሰደ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ንጉሠ ነገሥቱ በመጨረሻው የሥልጣናቸው ዘመን ለሁሉም ብሔሮች ቋንቋቸውን የማበልፀግ መብት የለገሰ ሕገ መንግሥት አርቅቀው እንደነበር አጥኚዎቹ አውስተዋል፡፡

የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በወታደራዊ መንግሥት ሲተካ ለሁለም ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋቸውን የማሳደግ፣ የመጠቀምና የማቆየት መብት በመስጠት የተመረጡ አሥራ አምስት ቋንቋዎች ደግሞ በመሠረተ ትምህርት ማይምነትን ማጥፊያ ይሆኑ ዘንድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ፣ የደርግ መንግሥት አድርጓል፡፡ እነዚህም ቋንቋዎች አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ወላይታ፣ ሶማሊ፣ ሐዲያ፣ ከምባታ፣ ትግርኛ፣ ትግረ (ኤርትራ)፣ ሲዳማ፣ ጌዴኦ፣ አፋር፣ ካፋና ሞቻ (ካፋና ሸካ)፣ ሳሆ፣ ኩናማና ስልጤ እንደሆኑ ጌታቸውና ደርብ ይዘረዝራሉ፡፡

ይሁንና የደርግ አካሄድ ሁሉም ቋንቋዎች የአማርኛን ፊደል (የግዕዝ ፊደላት) እንዲጠቀሙ በማድረጉና ይኼም በሁሉም ቋንቋዎች የሚገኙ ድምፆችን ለመወከል ከባድ መሆኑ፣ እንዲሁም ሁሉም ለማለት በሚያስችል ደረጃ የመሠረተ ትምህርት መምህራን አማርኛ ተናጋሪ በመሆናቸው ድክመቶች እንደነበረበት በመጠቆም፣ በአነስተኛ ልዩነት የቀደመውን ዓይነት አካሄድ የተከተለ ነበርም ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ከዓመታት የትጥቅ ትግል በኋላ የደርግን መንግሥት በኃይል ገርስሶ ሥልጣን የያዘው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መንግሥት፣ በሕገ መንግሥቱ አማርኛ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንደሆነ ከመደንገግ ባለፈ፣ እያንዳንዱ ክልል የራሱን የሥራ ቋንቋ የመምረጥ ሥልጣን እንዳለው ይፋ አድርጓል፡፡ ይሁንና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ምክረ ሐሳብ መሠረት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት በአፍ መፍቻ ቋንቋ እንዲሰጥ መወሰኑ፣ ከሁሉ የላቀና መሠረታዊ ለውጥ ያመጣ እንደሆነ በርካቶችን ያስማማል፡፡

ነገር ግን በትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲው የተቀመጠው ይኼ የቋንቋዎች መብትና አጠቃቀም ወደ ትግበራ ገብቶ ከፍተኛ የተመዘገቡበትና ለተቀሩት የአፍሪካ አገሮች በአፍ መፍቻ ቋንቋ ማስተማር ያለውን ጠቀሜታ ለማሳየት የሚቀመር ልምድ ተደርጎ ቢጠቀስም እንዴት? መቼ? በማን? በምን ሁኔታና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በመመለስ ሕገ መንግሥታዊ ሆኑ የፖሊሲ አንቀጾች የሚተገበሩበት የቋንቋ ፖሊሲ ሳይኖር የተገኙ ውጤቶች ናቸው ይባላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ተዘጋጅቶ የካቲት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው የኢትዮጵያ የቋንቋ ልማትና አጠቃቀም ፖሊሲ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ያስችላል የተባለለት ሲሆን፣ ከፖሊሲው ቀድሞ የነበረውን አሠራር በጥሞና ለመምራት የሚያስችል እንደሆነም በፖሊሲው ላይ የካቲት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በነበረው መድረክ ላይ ተጠቁሟል፡፡

በዚህ መድረክ ላይ የፖሊሲ አለመኖር ከአሁን ቀደም የፈጠረውን ክፍተት በተመለከተ በመክፈቻ ንግግራቸው ያካተቱት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር)፣ ‹‹ቋንቋችን አንዴ ከ80 በላይ ነው እንላለን፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ 76 ነው እንላለን፡፡ ይኼ የሚያሳየውም ያለንን ሀብት ቆጥረን ለማልማት አለመዘጋጀታችንን ያሳያል፤›› ያሉ ሲሆን፣ የባህል ፖሊሲ ኖሮ በተሠራው ሥራና በተገኘው ውጤት የቋንቋ ፖሊሲ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እናያለን ብለዋል፡፡

አራት አቅራቢዎችና 19 ተሳታፊዎች በታደሙበት በዚህ የፖሊሲ ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የቋንቋ ፖሊስ ስላልነበራት የጎደለባት ነገር እንደነበር የጠቆሙት ሒሩት (ዶ/ር)፣ ‹‹ኢትዮጵያ ብዝኃ ቋንቋ ያለባት አካባቢ ናት፡፡ ግን ብዝኃ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰብ የለንም፡፡ ይኼም አንዱ ማኅበረሰብ ከሌላው ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያሳጥር ነው፡፡ ይኼ ያልሆነውም የቋንቋ ፖሊሲ ስላልነበረን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ብዝኃ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰብ ያስፈልጋል አዲሱ የቋንቋ ፖሊሲም ይኼን ያስችላል፤›› ብለዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ቋንቋዎች መልማት ስላለባቸው ፖሊሲው እንደፀደቀ ጠቁመው፣ ከትምህርትና ከቴክኖሎጂ ጋርም መተሳሰር አለባቸው ሲሉ አክለዋል፡፡

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋዎችና የባህላዊ እሴቶች ልማት ዳይሬክተር አቶ አውላቸው ሹምነጋ የፖሊሲው አስፈላጊነት ሲያስረዱ፣ በሕገ መንግሥቱ መብት መሠረትና በቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰቦች ጥረት ቋንቋዎች ማደጋቸውንና 53 ቋንቋዎች የትምህርት ቋንቋ መሆናቸውን በማስገንዘብ፣ ‹‹ነገር ግን ይኼ የሆነው ሥርዓት ተበጅቶለት ሳይሆን ሰዎች ባላቸው ተነሳሽነት ነው፡፡ ስለዚህ ልሳነ ብዙኃንነትን በአግባቡ ለመጠቀም፣ የሕዝቦችን የእርስ በርስ ትስስር ለማጠንከርና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጎልበት ፖሊሲው ይረዳል፤›› ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት ጥያቄ ሆኖ ሲነሳ የነበረና የፖለቲካ ክርክሮች አንደኛውና ዋነኛው ጉዳይ የነበረው ከአማርኛ በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎችን የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ማድረግ ሲሆን አዲሱ ፖሊሲ አማርኛን፣ አፋን ኦሮሞን፣ ትግርኛን፣ አፋርኛንና ሶማሊኛን የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ ያትታል፡፡

ይኼንን አስመልክተው የተናገሩት የቋንቋ ተመራማሪው ሞገስ ይገዙ (ዶ/ር)  በበኩላቸው እስከ ዛሬ፣ ‹‹የቋንቋ አጠቃቀማችን የሚታየው ከመብት አንፃር ብቻ ነው እንጂ፣ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ከመፍጠር ሕገ መንግሥታዊ ራዕይና ቀጣናዊ ትስስርን ከመፍጠር አኳያ አልታየም፤›› ሲሉ በመገምገም፣ የአዲሱ ፖሊሱ ዕይታ በዚህ የተቃኘ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

ፖሊሲው በቀጣይ የመገናኛ ብዙኃንና የመዝናኛ ኢንዱስትሪ የቋንቋ አጠቃቀምን፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪዎች ከአፍ መፍቻው በተጨማሪ አንድ የፌዴራል የሥራ ቋንቋን አክለው እንዲማሩና ብዝኃ ቋንቋነት እንዲፈጠር እንዲሁም በሒደት የእንግሊዝኛ የማስተማሪያ ቋንቋነት እየቀረ ወደ አገር በቀል ቋንቋ እንዲደረግ አቅጣጫ ማስቀመጡን ሞገስ (ዶ/ር) አክለዋል፡፡

የቋንቋ ፖሊሲው ይሳካ ዘንድ ሙያዊ ጉዳዮች ለባለሙያ መተው አለባቸው በማለት በመድረኩ ጥሪ ያቀረቡት ደግሞ ታዬ አሰፋ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ የፖሊሲው አስፈጻሚና ተባባሪ አካላት ተለይተውና ሚናቸው ታውቆ መቀመጥ አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ለስኬቱ ሲባልም ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ አባላት ያሉት የቋንቋዎች ምክር ቤት በአዋጅ እንዲቋቋም፣ የቋንቋ ጉዳዮች ጥናትና ምርምር ማዕከል እንዲቋቋምና በግኝቶች ላይ የተመሠረቱ ፖሊሲዎች እንዲዘጋጁ፣ እንዲሁም ሕጋዊ ሰውነት ያለው የትርጉም ተቋም እንዲኖር በማለት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት በጀት መመደብ፣ የቋንቋ ጥናት ፈንድ ለማቋቋም ጥናቶች በገንዘብ እጥረት እንዳይስተጓጎሉ ማድረግ፣ ፖሊሲው የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር ማዘጋጀትና መሥራት፣ ተናጋሪዎች የሚገኙባቸውን ካርታ መሥራት፣ እንዲሁም ቋንቋዎችን የዕውቀት፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

‹‹76 ወይም ከሰማንያ በላይ ቋንቋዎች አሉ ቢባልም የትኛው ነው ቋንቋ? የትኛው ነው ዘዬ? አንድ ቋንቋ ስንት ዘዬዎች አሉት? የሚለው መለየት አለበት፡፡ ይኼ በስሜት ሳይሆን በባለሙያ ነው መሠራት ያለበት፤›› ሲሉም ምክር ለግሰዋል፡፡

ከአሥር እስከ 15 ዓመታት ለትግበራ ይፈጃል በማለት የተጠቆመው ይኼ ፖሊሲ፣ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያም እንደሚያስፈልገው ተነግሯል፡፡ ስለዚህም ሕገ መንግሥቱ ሲሻሻል የፌዴራል የሥራ ቋንቋ የሚሆኑ ቋንቋዎች ዝርዝር ውስጥ ተጠቅሰው ይደነገጋሉም ተብሏል፡፡

በቀጣይ ሌሎች ቋንቋዎች ከፌዴራል የሥራ ቋንቋዎች አንፃር ሲታዩ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የቋንቋዎች እኩልነት ድንጋጌ አይጻረርም ወይ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ታዬ (ዶ/ር)፣ ቋንቋዎች ከደረሱበት ደረጃ፣ ከተናጋሪዎች ብዛትና ቋንቋዎቹ ሊፈጽሙት ከሚችሉት አገልግሎት አኳያ እየታየ ሌሎች ቋንቋዎችም በተመሳሳይ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ሊሆኑ እንደሚችሉ በማለት፣ ይኼ ከማበላለጥ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ሲሉም ተከራክረዋል፡፡

የዚህ የቋንቋ ፖሊሲ መፅደቅ ከአሁን ቀደም በትምህርት ፍኖተ ካርታ ዝግጅት፣ ወቅት የተፈጠረውን ዓይነት ውዝግብ ሊያስቀር እንደሚችልም ታዛቢዎች ይጠቁማሉ፡፡ የቋንቋ ፖሊሲ በሌለበት አገር በትምህርት ፍኖተ ካርታ የተመለከተውን ዓይነት ከአፍ መፍቻ ቋንቋ ውጪ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ በአንድ የትምህርት ዓይነት ይሰጥ መባሉ ትርጉሙ ምን ማለት ነው በማለት በወቅቱ ጥያቄ የሰነዘሩ ሲኖሩ፣ የቋንቋ ፖሊሲው በዚህ ረገድ መልስ የሚሰጥ እንደሆነም የሚገልጹ አሉ፡፡

በእነዚህ ጉዳዮች ሳቢያም አዲሱ የቋንቋ ፖሊሲ ለረዥም ዓመታት የተንከባለሉ ጥያቄዎችን ለመመለስና ወደ ሌላ ጉዳይ ለማተኮር ያግዛል ሲሉም የሚከራከሩም አልጠፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -