አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን የተሾሙት፣ የዛሬ አንድ ዓመት ገደማ በሚያዝያ ወር 2011 ዓ.ም. ነበር፡፡ ከዚህ ሹመት አስቀድሞ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት በመሆን ለረዥም ዓመታት ያገለገሉት አቶ ገዱ፣ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመጡት ከወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) መልቀቅ በኋላ ለወራት ክፍት ሆኖ ቆየውን ኃላፊነት በመረከብ ነበር፡፡ አቶ ገዱ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመጡበት ጊዜ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ለውጦች የተስተዋሉበት በመሆኑ የተነሳ፣ በርካታ ሥራዎች ይጠብቋቸው ነበር፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በዋናነት ከግብፅና ከሱዳን ጋር የሚደረጉትና እየተጧጧፉ የመጡት የህዳሴ ግድብ ድርድሮችና የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላም ስምምነቶች ሲሆኑ፣ ሁለቱም ጉዳዮች ከፊት ሆኖ የሚመራና ውጤት የሚጠበቅበት አመራር ይጠይቁ ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ አቶ ገዱ የመጡበት ጊዜ ፈታኝ እንደሆነ በርካቶች ይስማማሉ፡፡ እሳቸው ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከመጡ በኋላ በህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ የሚደረጉ ውይይቶች እየጦፉ ነው፡፡ በተለይ የአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ በታዛቢነት በህዳሴ ግድቡ ድርድር መሳተፍ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የግድቡ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ገጽታን እየተላበሰ የመጣ ሲሆን፣ የአሜሪካ መንግሥት የግምጃ ቤት ኃላፊ ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበትን የመጨረሻ ውይይት አስመልክቶ ላወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ምላሽ ስትሰጥ፣ ግብፅ ደግሞ በበኩሏ ኢትዮጵያን መውቀስ ጀምራለች፡፡ ይኼም በተደጋጋሚ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል የቃላት ጦርነት እንዲታይ አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያ አሜሪካ ሳትገኝበት ከቀረችው የውይይት መድረክ በኋላ በአገሮቹ መካከል በጉዳዩ ላይ የተደረገ ውይይት ባለመኖሩ፣ የዚህ ውዝግብ ጉዳይ መጨረሻ ምን ሊሆን ይችላል ሲሉም ብዙዎች ይጠይቃሉ፡፡ የህዳሴ ግድቡ ድርድር ቀጣይ ዕጣ ፈንታ፣ የግብፅ ተፅዕኖ፣ የአሜሪካ ለግብፅ ማድላት፣ በዓረብ ሊግ ውሳኔ የጂቡቲና የሶማሊያ አቋም፣ እንዲሁም የኢትዮ ኤርትራ ዕርቅን የተመለከቱ ጉዳዮችን በማንሳት ብሩክ አብዱ ከአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡– በህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ በኢትዮጰያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል ሲደረግ የቆየው ድርድር ስምንት ዓመታትን ቢዘልቅም በአገሮቹ መካከል ለዚሁ ጉዳይ ገዥ ሊሆን የሚችል ሕግ ላይ ስምምነት ተደርሶ ሊፈረም አልቻለም፡፡ በስተመጨረሻም የአሜሪካ መንግሥት ከዓለም ባንክ ጋር በመሆን ድርድሩን በታዛቢነት አስኬዳለሁ በማለት የተሳተፈ ሲሆን፣ አሜሪካና የዓለም ባንክ ከሚናቸው ውጪ በመሄድ ስምምነት አርቅቀን እናቀርባለን በማለታቸው የኢትዮጵያ መንግሥት በሁለቱ ታዛቢነት ከሚደረገው የመጨረሻ ድርድር ራሱን አግልሏል፡፡ ይኼንን ተከትሎ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ያወጣውን መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት አሳዝኖኛል በማለት ለግብፅ ያደላ እንደሆነ በማስታወቅ አጣጥሎታል፡፡ ነገር ግን የአሜሪካና የዓለም ባንክ የሚታዘቡት ድርድር ላይ ከመገኘታችሁ አስቀድሞ፣ በተለይ አሜሪካ ለግብፅ ልታደላ እንደምትችል መገምገም አልተቻለም ነበር?
አቶ ገዱ፡– የህዳሴ ግድብ ድርድር ወደ አሜሪካ ሲሄድ አሁን ወደ መጨረሻ አካባቢ የታየው አዝማሚያ እንደሚኖር አልተገመተም ወይ ለሚለው፣ የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ ሐሳቦች ነበሯቸው፡፡ ምን ማለት ነው? በተለይ ግብፆች የሚያሳዩት ባህርይ ስለነበረና አሜሪካን ለምነው ስለሆነ ወደዚያ የሄዱት የእነሱም ባህርይ እንዲታረቅ፣ እንደገና ደግሞ አሜሪካ የሁለቱም አገሮች ወዳጅ ስለሆነች ልዩነቱ የሚቀራረብበትን መንገድ ይፈልጋሉ፣ ያግዛሉ በሚል ነው፡፡ ዋናው የቴክኒክ ጉዳይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ዞሮ ዞሮ አማካሪዎቹ ይኼ ይሁን፣ ያ አይሁን ብለው ይመጣሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ይፈታል ብለው ተስፋ ያደረጉ ሰዎች ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አሜሪካኖች ጉዳዩን በጥልቀት ስለማይገነዘቡት፣ እንዲሁም በጉዳዩ እየገቡ ያሉት በግብፅ ግፊት ስለሆነ ኢትዮጵያን እንጉዳ ብለው ቢያስቡ እንኳን ከዕውቀትም ማነስ፣ ወይም ደግሞ ግብፆች የበለጠ እንደተበደሉ አድርገው በመገንዘብ ያልሆነ አቅጣጫ እንዲይዝ ሊያደርጉት ይችላሉ በማለት፣ ጉዳዩ አሜሪካ መሄዱ ለኢትዮጵያ ላይጠቅማት ይችላል የሚሉም ነበሩ፡፡ ስለዚህ ሁለቱም ወገኖች የየራሳቸው ግምት ነበራቸው ማለት ነው፡፡ በመንግሥት በኩል ግን እርግጠኛ የምንሆነው በአንድ ነገር ነበር፡፡ አሜሪካኖች እናግዛችሁና ችግራችሁን እናንተው ፍቱ፣ እኛ እናቀላጥፍላችሁና ይህንን ጉዳይ አቃልላችሁ በሌላ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጉ፣ ይኼ ቀጣና ለትብብርና ለሰላም እንጂ ሌላ ግጭት እንዲፈጠርበት አንፈልግም ብለው ሲጋብዙን አንገኝም ማለት ከድርድር እንደ መራቅ ይቆጠራልና ለዲፕሎማሲያችንም ጥሩ አይሆንም፡፡ ነገር ግን እርግጠኛ መሆን ያለብን የምናካሂደው ድርድር አሜሪካም፣ ካይሮም፣ ካርቱምም ሆነ አዲስ አበባ ተካሄደ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ መስጠት የማይቻል መሆኑን እርግጠኛ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት እርግጠኛ የነበረው በተያዘው አቋም ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር እስከሆነ ድረስ ድርድር ነውና ድሮውንም ቢሆን የታችኞቹን አገሮች መጉዳት ፍላጎታችን ስላልነበረ፣ በድርድሩ አንዳንድ ነገሮችን ሰጥተን በሰጥቶ መቀበል ችግሩ የሚቃለል ከሆነ ምንም ችግር የለውም ብለን ነው የገባንበት፡፡
ሪፖርተር፡– ማመላከቻዎቹን ባለማየታችሁ መጨረሻ ላይ የተከሰተው ጉዳይ ያልተጠበቀ ነበር ማለት ይቻላል?
አቶ ገዱ፡– በዚህ ድርድር ሰው የሚመለከተው የመጨረሻውን ነው፡፡ አሜሪካኖች በዚህ ድርድር በመሳተፋቸው ከግብፅ ጋር ብዙ የተራራቅንባቸው ጉዳዮች ላይ እንድንቀራረብ አግዞናል፡፡ እውነቱን ለመናገር በብዙ ነገሮች ተቀራርበናል፡፡ ከሁለትና ከሦስት ጉዳዮች በዘለለ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ተስማምተናል፡፡ ለምሳሌ ከሞላ ጎደል ከሙሌት ጋር ተያይዞ በብዙ ነገሮች ተቀራርበናል፡፡ የሚቀሩ ጉዳዮች ግን ይኖራሉ፡፡ የውኃ አለቃቀቁን በተመለከተም እኛ መሠረታዊ ያልናቸውና ያልተግባባንባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም፣ በብዙ ነገሮች የተግባባንባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ስለዚህ አሜሪካኖች በታዛቢነትም ሆነ በአመቻችነት በመሳተፋቸው በብዙ መንገድ ኢትዮጵያን የጠቀመበት ገጽታ አለው፡፡ አንደኛው አሜሪካኖቹ ራሳቸው ጉዳዩ ውስብስብ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ተደርጓል ብለን እናምናለን፡፡ ሌላው ደግሞ ግብፅ ሁሉን ነገር ኢትዮጵያ አግዳ ይዛ ለውኃ ጥምና ለረሃብ ልታጋልጠን ነው በሚል ከፍተኛ ዘመቻ ከፍታ ስለነበር፣ ይኼንን ሁኔታ በትክክል እንዲገነዘቡ አስችሏል፡፡ በልኩ መሥጋታቸውን እንደ ትክክለኛ ጉዳይ ወስደው፣ ነገር ግን የሚያጮኹት በዚያ ልክ እንዳልሆነ ለማሳወቅ ዕድል ሰጥቶናል፡፡
ነገር ግን መጨረሻ ላይ እንደታየው አሜሪካኖቹ የሚፈልጉት ቶሎ ብሎ ይኼ ጉዳይ እንዲቋጭ ነው፡፡ እነሱ የዓባይን ጉዳይ በዓለም ላይ ካሉ ትልልቅ ጉዳዮች አንፃር ነው የሚመለከቱት፡፡ ከኢራንና ከአሜሪካ፣ ከእስራኤልና ከፍልስጤም፣ ከሰሜን ኮሪያና ከአሜሪካ ግንኙነት፣ እንዲሁም ከቻይናና ከአሜሪካ የንግድ ግንኙነትና ከመሳሰሉ ጉዳዮች ተርታ ነው ይኼንን ጉዳይ የሚመለከቱት፡፡ ስለዚህ ይኼን ቶሎ ብሎ መጨረስ ለራሳቸው ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ለመፍጠርም የራሱ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለውም ሊሆን ይችላል፡፡ ጉዳዩ ቶሎ እንዲቋጭ ይፈልጋሉ፡፡ በእኛ በኩል ደግሞ ያልተስማማንባቸውን ጉዳዮች ጊዜ ወስደን፣ ከሥር መሠረታቸው አጥርተን ነው መሄድ ያለብን የሚል እምነት አለ፡፡ በጉዳዩ ላይ አለመስማማት ብቻ ሳይሆን ስንስማማ እንኳን፣ የህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ መንግሥትና በኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ የሚሠራ በመሆኑ ባለቤቱ ብዙ ነው፡፡ ባለቤቱ ብዙ ከመሆኑ አኳያ ምክክር ያስፈልጋል፡፡ ምን ምን ላይ እየተመካከርን እንደሆነ ማኅበረሰቡ ማወቅ አለበት፡፡ ስለዚህ ያልተግባባንባቸውን ጉዳዮች ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በጋራ በመሆን መፈጸም ይኖርብናል ነው አቋማችን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በተስማማንባቸው ነገሮች ጭምር እኛ ከኅብረተሰባችን ጋር መነጋገር ይጠበቅብናል፡፡ እንደገና የዚህ ግድብ ስምምነት አብዛኛውን ግዴታ የሚጥለው በኢትዮጵያ ላይ ነው፡፡ በሱዳንና በግብፅ ላይ የሚጥለው ግዴታ የለም፡፡ ግዴታዎቹ ከውኃ አሞላል፣ አለቃቀቅ፣ ከአካባቢ ተፅዕኖና ከአስተዳደር አኳያ በኢትዮጵያ ላይ የሚጣሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ትልቅ ጉዳይ ከማኅበረሰቡና ከባለሙያ ጋር በመመካከር መብሰል አለበት ነው ያልነው፡፡
ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ በተመለከተ እንዲህ ዓይነት ገዥነት (Compreneshive) ያለው ስምምነት ስታደርግ የመጀመርያዋ ነው፡፡ ምንም እንኳን ከግድቡ አሞላልና አለቃቀቅ ጋር ብቻ የተገናኘ ቢሆንም፣ አሁን የምናደርገው ድርድር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከውኃ ክፍፍል ጋር የሚነካካበት ሁኔታ አለ፡፡ እነዚህ በጥንቃቄ መታየት አለባቸው፡፡ ከአሁን ቀደም በሱዳንና በግብፅ የተደረጉ የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ኢትዮጵያን ያገለሉ ናቸው፡፡ ከምንም ነገር በላይ ግን ኢፍትሐዊ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከእነዚያ ጋር በማይተሳሰርና የእነዚያን ውርስ (Legacy) በማይጠብቅ መንገድ በጥንቃቄ መታየት አለበት፡፡ ከዚያ አኳያ ነው አሜሪካኖች በጥድፊያ እንዲፈጸም፣ እኛ ደግሞ ቀስ ብሎ መፈጸም አለባቸው በማለት የተለያየነው፡፡ ስለዚህ ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ በተፅዕኖና ጥሩ ባልሆነ ሁኔታ ነው የቀጠለው የሚል እምነት የለኝም፡፡ የጠቀመን ብዙ ነገር አለ፡፡ ነገር ግን መጨረሻ ላይ በግምጃ ቤቱ ኃላፊ የወጣው መግለጫ በምንም መንገድ ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ ተቀባይነት የለውም ስንል የአሜሪካ መንግሥት የግምጃ ቤት ኃላፊ ይኼንን መግለጫ የሚያወጡበት ምንም ዓይነት ሥልጣን የላቸውም፡፡ ከሚናቸው ውጪ የሄደ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በመግለጫው የተጠቀሰው በተለይ ግድቡን ከስምምነት ሳትደርሱ አትሞሉም የሚለው አገላለጽ ግብፆች እንኳን ያልጠየቁት ነው፡፡ እናም ኢፍትሐዊና የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጋፋ አቋም ነው፡፡ ይኼም በምንም ሁኔታ ልንቀበለው የማንችለው አቋም ነው፡፡ እኛ ተደራድረን መቋጨት ያሉብን ጉዳዮች እያሉ እነዚያ ሳያልቁ በዚህ ተስማሙ ብሎ ሰነድ ማምጣት ስህተት ነው፡፡ እኛ ተደራድረን መጨረስ ያለብን ጉዳዮች አሉ፡፡ ድርድሩ አላለቀም ማለት ነው፡፡ ድርድሩ ሳያልቅ ነው እነሱ እንዳለቀ አስመስለው፣ ‹‹እናንተ ስላልተስማማችሁ በመሀል ሁለታችሁን የሚያስማማ ሰነድ እኛ አዘጋጅተናልና ተቀበሉ›› ማለታቸው ያለ ሥራቸው ነው፡፡ ሁለተኛ እኛ መጨረሻ ላይ አካሄዱ ልክ አይደለም፣ ስብሰባው በሌላ ጊዜ ይዛወርና ነው የምንገኘው፣ አሁን በጥድፊያ አይሆንም ስንላቸው አትሞሉም ብሎ መግለጫ ማውጣት አድሎዓዊ ነው፡፡ በዚህ በዚህ ብለን ልንሸፍነው የምንችለው ጉዳይ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡– በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ለምን ያህል ጊዜ ነበር በአገር ውስጥ የሚደረገው ምክክር እስከሚጠናቀቅ ስትል የመጨረሻው ድርድር እንዲራዘምላት የጠየቀችው?
አቶ ገዱ፡– ኢትዮጵያ ሁለት ነገሮችን ነው ያቀረበችው፡፡ አንደኛው በተለይ እ.ኤ.አ. ከጃንዋሪ 28 እስከ 31 ቀን 2020 ባደረግነው ውይይት ድርቅና የተራዘመ ድርቅ፣ ደረቅና የተራዘሙ ደረቃማ ዓመታት የሚያስከትሉትን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችል ሐሳብ ቀርቦ ነበር፡፡ የተራዘመ ድርቅና የድርቅ ዓመታት፣ እንዲሁም የተራዘሙ ደረቃማና ደረቃማ ዓመታት በማለት በወንዙ ፍሰት ላይ የተራዘመ አነስተኛ ፍሰት በሚኖርበት ጊዜ፣ የታችኞቹ የተፋሰስ አገሮች ግድቦች የውኃ ይዘቶች ስለሚቀንሱ ኢትዮጵያ ደግሞ ውኃ ስለምትይዝ የሚያደርሰውን ጉዳት መቀነስ ያስፈልጋል በሚል ከህዳሴ ግድብ ውኃ እንዲለቀቅ የሚል ሐሳብ ቀርቦ አልተስማማንም፡፡ ያልተስማማንባቸው ጉዳዮች እያሉ ያኔ ተነጥሎ ወጥቶ በዚህች ጉዳይ ብቻ ላይ ፈርሙ ተባለ፡፡ እኛ ሙሉ ሰነዱ ካለቀ በኋላ ነው እንጂ አሁን አንፈርምም አልን፡፡ ቀጠሉና እ.ኤ.አ. ፌብሩዋሪ 12 እና 13 ቀን 2020 ውይይት ሲካሄድ ፈርሙ አሉ፡፡ አይሆንም እንደገና መነጋገር አለብን አልን፡፡ እነሱም ‹ያ ያለቀና የተዘጋ ነገር ስለሆነ አንከፍትም› በማለት በቀጣዮቹ ጉዳዮች ላይ ተደራደሩና ጨርሱ አሉን፡፡ ያ ስብሰባ ሲጠናቀቅ እናንተ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ተነጋግራችሁ አልተስማማችሁም፣ እኛ ረቂቅ የስስምነት ሰነድ አዘጋጅተን እንልካለን አሉ፡፡ እዚያ ያሉ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ይኼ ልክ አይደለም በማለት መግለጫ ሲወጣ በእኛ ስም እንደተስማማን ተደርጎ መውጠት የለበትም ብለው አቋም ሲይዙ፣ በመግለጫው የግምጃ ቤት ኃላፊው ከዓለም ባንክ ጋር በመደጋገፍ ለተደራዳሪዎች ረቂቅ ሰነድ አዘጋጅተን እናቀርባለን የሚል በትዕምርተ ጥቅስ ሆኖ ተጠቀሰ፡፡ ተደራዳሪዎቻችን ከተመለሱ በኋላ ‹ይኼ ሰነድ እንልካለን የምትሉት ትክክል አይደለም እንዳትልኩ› ብለው እ.ኤ.አ. ፌብሩዋሪ 20 ቀን 2020 ደብዳቤ ልከንላቸዋል፡፡ ይኼንን ብለን ሳለ የስብሰባ ጥሪ እ.ኤ.አ. ለፌብሩዋሪ 27 ቀን 2020 ላኩ፡፡ እኛ ለጻፍነው ደብዳቤ ደግሞ ‹የዓባይ ግድብ ጉዳይ ለኢትዮጵያ እጅግ ወሳኝ ቢሆንም፣ ለሱዳንና ለግብፅም የዚያኑ ያህል ጠቃሚ ነውና ይኼንን ሊያግባባ የሚችል ሰነድ አዘጋጅተን እንልካለን› ብለው መለሱ፡፡ ይኼንን መልስ ከሰጡ በኋላ ልዩነቶችን ሳናስታርቅ ስብሰባ መገኘት አልነበረብንም፡፡ ስለዚህ አንደኛ ሰነድ አርቅቆ የመላክ ሚና የላችሁም በታዛቢነታችሁ እንድትቆዩ ስንል፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ይኼንን ስብሰባ እኛ ልንሳተፍ አንችልም ብለን ቀን አልቆረጥንም ግን ከተመካከርን በኋላ ውይይቱ ይቀጥላል በሚል በደብዳቤ ጠየቅናቸው፡፡ ጥያቄዎቻችንን ለሱዳንም ለግብፅም አሳውቀናል፡፡
ሪፖርተር፡– ቀን አልቆረጣችሁም?
አቶ ገዱ፡– ቀን አልተቆረጠም፡፡ ተመካክረን ነው ቀን መቁረጥ ያለብን በማለት ነው ያንን ያደረግነው፡፡ እነርሱ ስብሰባውን ቀጠሉበት፡፡ በእርግጥ ስብሰባው የተካሄደው በጋራ ሳይሆን በተናጠል ነበር፡፡ ከዚያም ይኼንን የመጨረሻውን የአሜሪካ ግምጃ ቤት መግለጫ አወጡ፡፡ ይኼንን መግለጫ ሲያወጡ፣ የአሜሪካ መንግሥት የሄደበት መንገድ የተሳሳተ መሆኑንና በፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገለጽንላቸው፡፡
ሪፖርተር፡– አንዳንድ ታዛቢዎችና ተንታኞች አሜሪካ ለግብፅ ልታደላ የቻለችበትን ጉዳዮች ሲያስረዱ፣ ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ በምሥራቅ አፍሪካ ወሳኝ የአሜሪካ አጋር መሆኗ እየቀነሰና ሥፍራዋ እየተዳከመ እንደሆነ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር የነበራት ጥብቅ ግንኙነት በመቀዛቀዙ ነው ሲሉ ያስቀምጣሉ፡፡ ዕውን የኢትዮጵያና የአሜሪካ አጋርነት በሚባለው ደረጃ ነው? ይኼ ግንኙነትስ ምን ያህል ለጉዳዩ አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ?
አቶ ገዱ፡– በእኔ እምነት ሽብርተኝነት በዓለም ደረጃ የተዘጋ አጀንዳ አይደለም፡፡ ምናልባትም የተለያዩ ገምጋሚዎች በተለያዩ መንገዶች ሊመለከቱት ይችላሉ፡፡ አሁንም ሰፊ አድማስ እንደያዘ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ በምሥራቅ አፍሪካ ብንመለከተው ቀደም ብሎ የነበረው አልሸባብ በተወሰነ ደረጃ መዳከም ቢያሳይም፣ አሁንም በጎረቤታችን ኬንያ ምን ያህል ጥቃት እያደረሰ እንደሆነ፣ ምናልባትም ቀደም ብሎ ሲያደርሰው ከነበረው በላይ ጥቃት እየፈጸመ እንደሆነ እንመለከታለን፡፡ ይኼንን የሚያደርገውም በአሜሪካ ወታደሮች ላይ ጭምር ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ የተለያዩ አሸባሪ ኃይሎች የተለያየ ስም እያወጡ መንቀሳቀሳቸው አሁንም እንዳለ ነው፡፡ እንዲሁም በምዕራብ አፍሪካ ቦኮ ሐራምን ጨምሮ የተለያዩ ቡድኖች በተለያዩ ሥፍራዎች ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ከሽብርተኝነትን አንፃር ከወሰድነው የኢትዮጵያና የአሜሪካ አጋርነት ይበልጥ መጠናከር ያለበት ነው እንጂ፣ እየቀነሰ ነው የሚል መረጃ የለም፡፡ በተጨባጭም ስንመለከተው ትብብራችን በዚህ ረገድ ጥሩ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ በአሜሪካ የኢትዮጵያን ተፈላጊነት ካነሳን ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ትልቅ ጂኦግራፊያዊ ሥፍራን የያዘች፣ በአፍሪካ ሁለተኛዋ ብዙ የሕዝብ ቁጥር ያላት አገር፣ ብሎም በአፍሪካ እንደ አኅጉር ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደር የምትችል አገር ናት፡፡ እንዲሁም ደግሞ የምሥራቁን ዓለም ከአፍሪካና ከተቀረው ዓለም ጋር ለማገናኘት እንደ ድልድይ ሆና የምታገለግል አገር ናት፡፡ አሁን ደግሞ አሜሪካ በአፍሪካ ልትከተለው ካሰበችው ፖሊሲ አኳያ ኢትዮጵያ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው አገሮች ተርታ ትገኛለች፡፡ ስለዚህ በአሜሪካ የኢትዮጵያን ተፈላጊነት ስንመለከተው እየጨመረ የሚሄድ ሁኔታ እንጂ ይቀንሳል ብለን አናስብም፡፡ ይኼ ከሆነ ታዲያ ለምንድነው ለግብፅ ያደላ አካሄድ የተከተሉት ስንል፣ ጉዳዩ በራሱ የአሜሪካ መንግሥት አቋም ነው ወይ የሚለውን መመልከት ይኖርብናል፡፡ ሌላው ቀርቶ ስቴት ዲፓርትመንት የሚባለውና የውጭ ግንኙነትን የሚያንቀሳቅሰው መሥሪያ ቤት በዚህ ጉዳይ ብዙም ተሳታፊ አይደለም፣ በአመራርም በሙያተኛም ደረጃ፡፡ ስለዚህ ይኼንን ሙሉ በሙሉ የአሜሪካ መንግሥት አቋም አድርገን ልንወስደው አንችልም፡፡ ፕሬዚዳንቱ ለግምጃ ቤት ኃላፊው ነውና ሥራውን የሰጡት ጉዳያችን በእሳቸው ክፍል ነው የተያዘው፡፡ በቅርብ ጊዜ እየተመለከትን እንዳለነውም የአሜሪካ ምክር ቤት (ኮንግረስ) አባላት ጉዳዩን ጠንከር አድርገው እየተቃወሙት ይገኛሉ፡፡ በቀጣይም ይኼ ሁኔታ እየተጠናከረ ይሄዳል ብለን ነው የምናስበው፡፡ ከዚህ አንፃር ሙሉ ለሙሉ የአሜሪካ መንግሥት ለግብፅ አድልቷል ብለን ልንወስድ አንችልም፡፡ ጉዳዩ በቶሎ እንዲያልቅ ስለፈለጉ እኛ እንድንፈርም ተፅዕኖ ማድረግን እንደ አንድ መንገድ የወሰዱት እንደሆነ ነው የምንገነዘበው፡፡ እነርሱም ያውቁታል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚጋፋ ውሳኔ ልትወስን እንደማትችል እያወቁ፣ ይኼንን በተወሰነ ደረጃ ጫና ለማሳደር የወሰዱት ዕርምጃ እንደሆነ አድርገን ነው የምንመለከተው፡፡ እንደ መንግሥት አቋም አድርገን አንወስደውም፡፡
ሪፖርተር፡– የህዳሴ ግድቡን ግንባታ ለማስቆም እንዲሁም ተገንብቶ ጥቅም ላይ እንዳይውል፣ ግብፆች የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊና ሌሎች ጫናዎችን ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ በቅርቡ ደግሞ በፓርላማቸው በግድቡ የሚሳተፉ ተቋራጮች ምንም ዓይነት ሥራ በግብፅ እንዳይሠሩ ለማድረግ ሕግ በማውጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይኼ ድርጊት በግድቡ ግንባታ ላይና በተቋራጮች ላይ የሚያሳድረው ሥጋት ይኖር ይሆን?
አቶ ገዱ፡– ግብፆች የህዳሴ ግድቡን በተመለተ ግንባታው ከተጀመረ ጀምሮ ለማናቀፍ የሚከተሏቸው መንገዶች አሉ፡፡ በዓባይ ላይ ምንም ዓይነት ግድብ እንዳይሠራ ፍላጎት አላቸው፡፡ ይኼ ማንም የሚያመዛዝንና ፍትሐዊ ዕይታ ያለው ኃይል ሊወስደው የማይገባ አቋም ነው፡፡ ምንም ዓይነት ግድብም ይሁን የመስኖ ሥራ፣ ሌላው ቀርቶ ለመጠጥ ውኃ እንኳን ከፍ ያሉ ፕሮጀክቶች እንዲከናወኑ ፍላጎት የላቸውም፡፡ ከዚህ ፍላጎታቸው በመነሳት መጀመርያ የግድቡ ግንባታ ሲጀመር እንዳይገነባ ነበር ትግላቸው የነበረው፡፡ ግድቡ እንዳይገነባ ያላደረጉት ጥረት የለም፡፡ ኋላ ይኼ እንደማይሳካ ሲያውቁት ግድቡ ከፍታው በሚፈለገው መጠን እንዳይሆን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ ይኼም የማይሆን መሆኑን ሲነገዘቡ ደግሞ የግድቡ ውኃ የመያዝ አቅም እንዲቀንስ ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል፡፡ ይኼም የማይሆን መሆኑን ሲያውቁ የግድቡ አሞላል እስከ 20 ዓመታት ሊወስድ በሚችል የተራዘመ ጊዜ እንዲሆን ሐሳብ አቅርበው ክርክር ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ይኼም እንደማይሆን ሲያውቁ አስዋን ግድብና የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ እንዲተሳሰሩ በማድረግ የአስዋን ግድብ ውኃ ሲቀንስ፣ የህዳሴ ግድብ ውኃ ወደ ታች እንዲመግብ ግዴታ ጋር ውስጥ የሚያስገባ ሐሳብ አቅርበው ነበር፡፡ ሌላው ከኢትዮጵያ ይኼንን ያህል ውኃ መፍሰስ አለበት በማለት የዓባይን ፍሰት ዋስትና እንድንሰጣቸው ፈልገዋል፡፡
እንግዲህ ውኃውን የሚሰጠን ፈጣሪ ነው፡፡ ፈጣሪ በሚሰጠው ውኃ ላይ እኛ ዋስትና እንድንሰጥ ድረስ ጠይቀዋል፡፡ ስለዚህ ግብፆች አሁንም ቢሆን ሰሞኑን እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ ከእነዚህ ከማይሳኩ ጥረቶች ውስጥ የሚመደብ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይኼንን የምልበትም ምክንያት ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብት ነው ያላት፡፡ ማንም እንዲፈቅድላት የምትጠይቀበት ምክንያት የለም፡፡ ተፈጥራዊ መብት ነው ሲባል 86 በመቶ የዓባይ ውኃ የሚመነጨው ከኢትዮጵያ ነው፡፡ ይኼ ውኃ ከኢትዮጵያ መመንጨቱ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይኼንን ውኃ መጠቀም የግድ የሚለው ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ይኼንን ውኃ ካልተጠቀመ እስከ ህልውና መፈታተን ደረጃ የሚደርስ ሁኔታ ይኖራል ማለት ነው፡፡ እንግዲህ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን ወደ 110 ሚሊዮን ያህል ደርሷል፡፡ ከዚህ ሕዝብ ውስጥ ወደ 65 ሚሊዮን የሚደርሰው ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት የለውም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሕዝቡ ኃይል የማግኘት ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፡፡ እነዚህን እንዴት አድርገን ነው የምናስታርቃቸው? ያለንን ሀብት መጠቀም የግድ ይላል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ማዕከል እየሆነች ነው፡፡ ኢንዱስትሪ ደግሞ የኃይል ፍላጎቱ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ኃይል ማመንጨት አለብን ማለት ነው፡፡ ሦስተኛ ኢትዮጵያ ለቱሪዝም የተመቸ ተፈጥሮ የሰጣት ፀጋ፣ በርካታ ለቱሪዝም መስህቦች የሆኑ ሰው ሠራሽ ሀብቶችም ያሉባት አገር ናት፡፡ እነዚህ መዳረሻ የሆኑ አካባቢዎች ደግሞ የተለያዩ የመሠረ ልማት አቅርቦቶችን ይጠይቃሉ፡፡ ከመሠረተ ልማት አቅርቦት መካከል ደግሞ አንዱ መብራት ነው፡፡ ስለዚህ ከኃይል አቅርቦት ብቻ ስንመለከት ከሌሎቹ ምንጮች ይልቅ በቀላሉ ኢትዮጵያ ማልማት የምትችለው ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ስለሆነ፣ ወንዟቿን ማልማት ይኖርባታል ማለት ነው፡፡ ከእነዚህ ወንዞች መካከል ደግሞ ዓባይ አንዱ ነው፡፡ ስለዚህ ኃይልን ለማማንጨት ዓባይን መጠቀም የግድ የሚልበት ዘመን ላይ ነው ያለነው፡፡
በተጨማሪ ኢትዮጵያ መስኖን ካላስፋፋች ይኼንን መቶ ሚሊዮን ሕዝብ በምን ትቀልባለች? በእርግጥ የእኛ መሬት ከሱዳን ጋር ሲነፃፀር ለመስኖ የሚያመቸው በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ግን ያለችንን በመስኖ ማልማት ይኖርብናል፡፡ መስኖን ለማልማት ደግሞ ወንዞቻችንን መጠቀም ይኖርብናል፡፡ ከወንዞቻችን መካከል ደግሞ አብዛኞቹ ወደ ዓባይ የሚፈሱ ናቸው፡፡ ተከዜ፣ ዓባይ፣ ባሮና አከቦን የመሳሰሉ ትልልቅ ወንዞችን ብንመለከት የናይል ገባሮች ናቸው፡፡ የእኛ የሕዝብ ቁጥር ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የሚሄድ ነው፡፡ ይኼንን ሕዝብ ለመመገብ ወንዞቻችንን፣ ውኃችንን መጠቀም ይኖርብናል፡፡ ይኼው እያደገ ያለ ሕዝብ የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ይፈልጋል፡፡ በግድብም መልክ ሆነ በተለያየ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የንፁህ መጠጥ ውኃ ለሕዝቦቻችን ማቅረብ ይኖርብናል፡፡ ለዚህም ወንዞቻችንን መጠቀም አለብን፡፡ ስለዚህ የፈለገውን ያህል ግብፆች ዓለም አቀፍ ዘመቻ ቢያካሄዱ፣ ሰፊ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ቢሠሩና የፈለጉትን አቋም ቢወስዱ ኢትዮጵያን በወንዟ ከመጠቀም፣ በውኃ ሀብቷ ከመጠቀም ሊያግዱ መብትም የላቸውም፡፡ የሞራል ብቃትም የላቸውም፡፡ ስለዚህ ከእኛ የሚጠበቀው ኢትዮጵያ ይኼንን ውኃ ስትጠቀም የሌሎቹን ድርሻ መንካትና የታችኞቹን አገሮች መጉዳት የለባትም፡፡ የራሷን ድርሻ ግን መጠቀም አለባት፡፡ ከግብፆች የሚጠበቀው ደግሞ ኢትዮጵያ የራሷን ድርሻ እንድትጠቀም አምኖ መቀበል ነው፡፡ ኢትዮጵያ የራሷን ድርሻ ለመጠቀም ያላትን መብት ለማደናቀፍ የሚያደርጉት ማንኛውም ጥረት የሚሳካ አይደለም፡፡ አሁንም አይሳካም፣ በመጪው ትውልድም አይሳካም፡፡ ይልቁንም ሌላ እልህ እንዲጨመር ነው የሚያደርጉት፡፡ የሚጠቅመን መግባባት ነው፡፡ እነሱም መጎዳት የለባቸውም፣ እኛም ሙጥጥ አድርገን የእነሱን ድርሻ ልንወስድ እንችልም፡፡ ኢትዮጵያ ይህ ዓይነት ፍላጎት የላትም፡፡ እስካሁን ድረስ በነበሩ መንግሥታትም ሆነ በአሁኑ መንግሥት ኢትዮጵያ የታችኞቹን አገሮች የመጉዳት ፍላጎት የላትም፡፡ ዋናው እየተጠየቀ ያለው ተባብረን በጋራ እንጠቀም የሚለው ነው፡፡ ጥያቄው ፍትሐዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የዓባይን ውኃ መጠቀም ነው፡፡ ስለዚህ ሰሞኑን የሚያካሂዱትና በግድቡ ግንባታ ላይ በተሰማሩ ድርጅቶች ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር የሚያደርጉት ጥረት፣ አሁንም ያለፉት የተሳተቱ መንገዶች ተቀጥላ የሆነ ተጨማሪ ስህተት ነው፡፡
ሪፖርተር፡– እርስዎ አሁን እንደገለጹት ሆነ ካሁን ቀደም ሲነገር እንደነበረው የኢትዮጵያ አቋም መደራደርና መግባባት ነው፡፡ ሆኖም ግን በሦስቱ አገሮች መካከል የሚደረገው ድርድር አሁን ቆሟል፡፡ ድርድሩ መቼ ሊቀጥል ይችላል? በውይይቱ መፍትሔ ማምጣትና መግባባት ላይ መድረስ ካልተቻለ ጉዳዩ ወዴት ሊያመራ ይችላል? በርካቶች ወደ ጦርነት ሊያመራ ይችላል የሚል ፍርኃትና ሥጋት አላቸውና፡፡
አቶ ገዱ፡– በእኛ ወገን ድርድሩ አልቆመም፣ አንድ ስብሰባ ነው የተቋረጠው ብለን ነው የምናስበው፡፡ ምክክር አድርገንና በጉዳዩ ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጡ ባለሙያዎች እንዲመክሩበት በማድረግ ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማጥራት ነው ያለብን አሁን፡፡ ይኼንን ሐሳብ ለሕዝቡ ግልጽ ማድርግና ምክክሩን መቋጨት ከእኛ በኩል ይጠበቃል፡፡ ይኼ እየተካሄደ ስለሆነ ሲገባደድ በግልጽ የምናሳውቅ ይሆናል፡፡ በግብፆች ወገን ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር የሚያካሂዱት ዘመቻና ከሕግም ከሞራልም አኳያ ተቀባይነት የሌለው ፊርማ እንድንፈርም የሚያደርጉትን ዘመቻ ትተው፣ በቀሩ ጉዳዮች ላይ ተደራድረን እንቋጨው የሚል ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ ወደ ድርድሩ እንመለሳለን፡፡
ኢትዮጵያና ግብፅ ናቸው አሁን ዋነኞቹ ባለቤቶቹ፡፡ ሱዳን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ኢትዮጵያ የምታነሳውን ጉዳይ ከግምት ያስገባ አካሄድ እየተከተለች ነው፡፡ በሱዳን በኩል ሚዛናዊና ፍትሐዊ ስምምነት እንዲካሄድ ፍላጎት አለ፡፡ ይኼ የእነሱ አቋም በእኛም በኩል የሚደገፍ ነው፡፡ ግብፆች ወደ ሱዳንና ወደ ኢትዮጵያ አቋም መምጣት አለባቸው ብለን ነው የምናስበው፣ ጉዳዩን በአግባቡ ለመቋጨት፡፡ ዞሮ ዞሮ በመጨረሻው መስማማታችን አይቀርም፡፡ የማያስማማ ነገር ብዙ የለም፡፡ ከወደ ግብፆች በኩል አንድ የሚጠበቅ ነገር ስላለ ነው፡፡ በቅን ልቦና ኢትዮጵያ በውኃ ሀብቷ መጠቀም የተከበረ ነው የሚለውን እምነት ይዘው፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ ስትጠቀም እነሱም እንዳይጎዱ ሰጥቶ መቀበልን መሠረት ያደረገ ሚዛናዊና ፍትሐዊ ስምምነት እንዲደረስ አቋም ከያዙ፣ አሜሪካም ሳያስፈልግ ሌላ ኃይልም ከመካከላችን ሳይገባ ሦስታችን ተመካክረን መቋጨት እንችላለን፡፡ ግን ከበስተኋላ ያለው ፖለቲካዊ ፈቃደኝነት ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያን በራሷ የውኃ ሀብት የመጠቀም መብት ከልብ አምኖ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ይኼ ስለጎደለ ማቃለል ከቻሉ መስማማት እንችላለን፡፡ ይኼንን አልፎ ለጦርነት የሚያደርስ ጉዳይ አለ ብዬ አላምንም፡፡ ጦርነት የሚካሄድም ከሆነ ማንም ተጠቃሚ ሳይሆን ተጎጂ ነው የሚሆነው፡፡ በጦርነት የተፈታ ችግር የለም፡፡ አሁንም ይኼ በጦርነት የሚፈታ ችግር አድርገው የሚመለከቱ ካሉ ተሳስተዋል፡፡ የማያዋጣ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ይኼንን ግብፆቹም ይገነዘባሉ ብዬ አምናለሁ፡፡
ሪፖርተር፡– በዓባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ የምትገነባው ግደብ ኢትዮጵያ እንደምትለው ጉዳት እንደማያደርስባቸው፣ ይልቁንም ጥቅም እንደሚያስገኝላቸው ግብፆች ይረዳሉ የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡ ሆኖም ግብፆች ጉዳዩን ለውስጣዊ የፖለቲካ ፍጆታ እየተጠቀሙበት ነው የሚሉ ስላሉ፣ የህዳሴ ግድቡን በግብፅ ለፖለቲካዊ ፍጆቻ የመዋል ዕድልን እንዴት ያዩታል?
አቶ ገዱ፡– የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ከዓባይ ውኃ መጠቀም ካለባት አኳያ ካየነው በጣም ትንሽ ነው፡፡ ከድርሻዋ አኳያ ከተመለከትነው ኢምንት ነው፡፡ ምክንያቱም ግድቡ ውኃውን ወስዶ የሚያስቀር ሳይሆን፣ ለተወሰነ ጊዜ ውኃ ይዞና ኃይል አመንጭቶ ለታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች የሚለቀቅ ነው፡፡ ወደፊት መስኖ ስናስፋፋ የተወሰነ ውኃ እንጠቀማለን፡፡ ይኼ የግብፅ ዓባይን ለዘለዓለም ተቆጣጥሮ የመኖር ፍላጎት ለ20ኛው ክፍል ዘመን ሠርቶ ሊሆን ቢችልም በ21ኛው ክፍል ዘመን ግን አይሠራም፡፡ ናይል የሚባለው ወንዝ ከዘጠኝ በላይ አገሮች ውኃ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበት ወንዝ ነው፡፡ እነዚህ አገሮች በሙሉ በውኃው የመጠቀም ፍላጎት አላቸው፡፡ ይኼ ፍላጎታቸው እያደገ ስለመጣ አንዱ ሲጠቀም ሌላውን እንዳይጎዳ፣ ተመካክሮ ፍትሐዊና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የምንጠቀምበትን ሥርዓት ነው መዘርጋት ያለበን፡፡ በርካታ የተፋሰሱ አገሮች የፈረሙበትና ያፀደቁት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) ተግባራዊ አድርጎ ካልሆነ በስተቀር፣ በተናጠል ከልክሎ የሚሆን ነገር አይደለም፡፡ ጠቡ የሚሆነው ከብዙ አገሮች ጋር ነው፡፡ ስለዚህ ፍትሐዊ አጠቃቀምን የሚያሰፍን ሥርዓት መዘርጋት ነው የሚያወጣው፡፡ ከዚያ አልፎ ግብፆች ለብዙ ዘመናት በሕዝባቸው ውስጥ ያሰረፁት አንድ የተሳሳተ ነገር አለ፡፡ እሱም ናይል የግብፅ የተፈጥሮ ፀጋና ብቸኛ ባለቤቶች እንደሆኑ በኅብረተሰባቸው ውስጥ አስርፀዋል፡፡ ናይል ከሌለ የግብፅ ሕዝብ የለም በማለት በሕዝባቸው ውስጥ ለዘመናት ሲያሰርፁት የኖረ አስተሳሰብ አለ፡፡ ናይል የፈጣሪ ስጦታ መሆኑን ማንም የሚክደው አይደለም፣ ይኼ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን ናይል የግብፅ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪ ለኢትዮጵያ፣ ለሱዳን እንዲሁም ለሌሎቹ የተፋሰሱ አገሮች የሰጠውም ሀብት ነው፡፡
የናይል ውኃ የግብፅ ብቸኛ ሀብት ስለሆነ ማንም ሊነካው አይችልም ብለው የከፈቱት ዘመቻ ትክክል አይደለም፡፡ ሁሉም አገር ለመጠቀም ይፈልጋል፡፡ ይኼንን እውነታ ክደው በተሳሳተ መንገድ ሕዝባቸውን የሚያስገነዝቡበት ሁኔታ አለ፡፡ ይኼ ግንዛቤና የቆየ አመለካከት በኅብረተሰቡ ዘንድ የሰረፀ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ግብፅ ውስጥ የሆነ ፖለቲካዊ ሁኔታ ሲነሳ ናይልን ለሕዝባቸው እንደ ማስፈራሪያ ይጠቀማሉ፡፡ ኢትዮጵያ ግድብ ሠርታ የግብፅን ሕዝብ ልትጎዳ ነው፣ በውኃ ጥም ልታጠፋ ነው እያሉ፡፡ እውነታው ግን ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ ላስቀር ብትል እንኳን አትችልም፡፡ የህዳሴ ግድቡ የመጨረሻ ውኃ የመያዝ አቅሙን ብንመለከት 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነው፡፡ የዓባይ ውኃ ዓመታዊ ፍሰቱ ደግሞ 49 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ኃይል እያመነጨች ያንን ውኃ ወደ ታች ካልላከች በስተቀር አግጄ ላስቀምጥ ብትልም አትችልም፡፡ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ነውና፡፡ ይኼንን የመሰለ ቀላል አረዳድ መፍጠር ስላልፈለጉ፣ የኢትዮጵያ ግድብ ውኃውን እንደሚያስቀር አድርገው ነው ለሕዝባቸው የሚያስረዱት፡፡ ይኼንን ግዙፍ ወንዝ እንዴት አድርገን ነው ገድበን የምናስቀረው?
ሌላው የህዳሴ ግድብ ከሱዳን ድንበር 20 ኪሎ ሜትር ገባ ብሎ ነው የሚገነባው፡፡ ኃይል በማመንጨት ወደ ታች ነው የሚሄደውና ለግብፅም ለሱዳንም ጠቃሚ ነው የሚሆነው፡፡ እንዲያውም ሌላ ማጠራቀሚያ ነው የሚሆንላቸው፡፡ ችግር በሆነ ጊዜ ተጨማሪ ውኃ እንዲያገኙ ያግዛቸዋል፡፡ ግድቡ ኃይል ካመነጨ በኋላ ወንዙ ተፈጥሯዊ ፍሰቱን ይቀጥላል፡፡ በተወሰነ ደረጀ የሚያዝ ውኃ አለ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ መጠቀም ካለባት አንፃር ሲታይ ኢምንት ናት ማለት ይቻላል፡፡ የግብፅን ሕዝብ በማስጨነቅ፣ በማስፈራራት ላይ ተመሥርቶ የፖለቲካ ተቀባይነትን ለማግኘት የሚደረግ ጥረት የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የሚያዋጣ አይሆንም፡፡ ጊዜው የመረጃ ዘመን ነው፡፡ እንደ ድሮው መንግሥት ብቻ የመረጃ ባለቤት ሆኖ ሕዝብን የሚያታልልበት ዘመን አይደለም፡፡ ስለዚህ የግብፅ ሕዝብም መንቃቱ አይቀርም ነው፡፡
ሪፖርተር፡– ኢትዮጵያ ካልተሳተፈችበት የአሜሪካ ድርድር በኋላ ግብፅ የዓረብ ሊግ አገሮችን በካይሮ ስብሰባ አንድ የውሳኔ ሐሳብ እንዲፀድቅ አድርጋለች፡፡ በዚህ ኢትዮጵያን በሚኮንን የውሳኔ ሐሳብ ለግብፅ ድጋፋቸውን ካቀረቡ አገሮች መካከል ሶማሊያና ጂቡቲ ይገኙበታል፡፡ ሶማሊያ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ መዳረሻ ከሆኑ የመጀመርያ አሥር አገሮች የምትሠለፍ ከመሆኗ አንፃር፣ እንዲሁም ጂቡቲ የኢትዮጵያ 90 በመቶ የገቢ ንግድ የሚደረግባት በር ከመሆኗ አኳያ ይኼንን አቋም መያዛቸው በኢትዮጵያ ወገን መሠራት የነበረበት ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ደካማ ስለሆነ ነው ተብሎ ይተቻል፡፡ ይኼንን የመሰለ ግንኙነት ከኢትዮጵያ ጋር ኖሯቸው ሳለ ከግብፅ ጎን መሠለፋቸው ድክመቱን አያሳይም?
አቶ ገዱ፡– ኢትዮጵያ ግድቡን ለምን ፈለገችው? 65 ሚሊዮን ሕዝባችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ እንዲሆን ብለን ነው፡፡ ኃይል አመንጭተን ኢትዮጵያ የጀመረችውን የልማት እንቅስቃሴ ለማጠናከርና ከድህነት ለመውጣት ነው፡፡ እንዲህ ብለን ሁሉንም ነገር እየነገርናቸው ነው፡፡ ይኼንን ደግሞ ግድቡ ሲጀመር ጀምሮ ዲዛይኑን ጭምር እንዲያውቁት ተደርጓል፡፡ ሁሉም ነገር በኢትዮጵያ ወገን መርህን በተከተለና ግልጽነትን በተላበሰ መንገድ ነው እየተካሄደ ነው ያለው፡፡ ሱዳኖች ይኼንን ተገንዝበው የዚህ ግድብ ደጋፊ ናቸው፡፡ ግብፆች በዘመቻና በኢትዮጵያ ላይ የማነሳሳቱን ሥራ ነው የያዙት፡፡ ግብፆች በዲፕሎማሲም ሆነ በሚዲያዎቻቸው በተለያየ መንገድ ሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለማጠናከር የተለያዩ መሣሪያዎችን ይጠቀማሉ፣ ከእነዚህም አንዱ የዓረብ ሊግ ነው፡፡ የዓረብ ሊግ 22 የሚሆኑ የዓረብ አገሮችን አባል ያደረገ ማኅበር ነው፡፡ ይኼ ማኅበር በአሁኑ ዘመን ግብፅ የምታወጣውን የጦርነትና ሌላ ቅስቀሳ መደገፍ ሳይሆን የነበረበት፣ እኔ ድጋፍ አድርጌ ችግሩ እንዲፈታ የራሴን ጥረት አደርጋለሁ ብሎ ተደራዳሪዎቹን ማበረታትት ነበረበት፡፡ ይኼንን የምልበት ምክንያት ጦርነት፣ ግጭትና አለመግባባት ምን ያህል አገሮችን እያፈረሰ እንዳለ ከዓረብ ሊግ የተሻለ የሚረዳ ተቋም አለ ብዬ አላስብም፡፡ እውነት ህልውና ያለው ተቋም ከሆነ በዓለም ላይ በቀውስ ውስጥ ያሉ አገሮች በብዛት የሚገኙት የዓረብ ሊግ ውስጥ መሆኑን ይገነዘባል፡፡ የዓረብ ሊግ አባል አገሮች እየፈረሱ ነው እኮ፡፡ እንቁጠር፡፡ የመን ፈርሳ ሕዝቡ ምን ያህል ለችግር እንደተጋለጠ እናውቃለን፡፡ ኢራቅ ምን ላይ እንዳለች እንገነዘባለን፡፡ ሶሪያ፣ ምን የመሰለች አገር ፈርሳ አሁን ሕዝቧ ምን ያህል ሥቃይ ውስጥ እንዳለ እንገነዘባለን፡፡ ሊቢያ የቀውስ መናኸሪያ ናት፡፡ ሶማሊያ ወደ ነበረችበት ለመመለስ በበርካታ ጥረቶችና መሻሻሎች ቢኖሩም እንኳን፣ አሁንም በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ያለችና የሽብርተኛ ኃይሎች መናኸሪያ እንደሆነች እንገነዘባለን፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ባለቡት ሁኔታ ለሰላም መቆም፣ ሰላምን መስበክና ስለሰላም ማስተማር የሚጠበቅበት ማኅበር ግጭትንና አለመግባባትን የሚያባብስ መግለጫ ማውጣቱ እውነትም በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ሳይሆን፣ ለግብፅ ተጨማሪ ማቆያ ሆኖ የሚያገለግል ተቋም እንደሆነ ያሳያል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ጂቡቲንም ሶማሊያንም ጠይቀናቸዋል፡፡ በደንብ ተመክሮበት፣ ተዘክሮበትና ሁሉም ከስምምነት ደርሶበት አይደለም የዓረብ ሊግ መግለጫ የወጣው፡፡ ግብፆች በአጀንዳ ከተያዙ ጉዳዮች ውስጥ ‹ሌሎች› በሚል ዘርፍ ነው አጀንዳ ያስያዙት፡፡ ጎረቤቶቻችን ጂቡቲም፣ ሶማሊያም ‹ይኼ ነገር አይጠቅምም፣ ነገሩን ከማባባስ የዘለለ የሚያመጣው ነገር የለም፣ እንዲያውም እንድትግባቡ እኛ እናሸማግል› እያሉ ነው ፀድቋል በማለት መግለጫ እንዲወጣ የተደረገው፡፡ በዓረብ ሊግ ተልዕኮ ላይ ያለው የሶማሊያ ልዑክ ያወጣው መግለጫ አለ፡፡ ጂቡቲ ደግሞ በደብዳቤ አሳውቀውናል፡፡ ከራሳቸው በውስጥ ካላቸው ጉዳይ ተነስተው በግልጽ ላለመቃወም ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን በጻፉልን ደብዳቤ የዓረብ ሊግ ያወጣው መግለጫ ችግሩን ማባባስ ካልሆነ በስተቀር፣ ችግሩን የሚፈታ አይደለም የሚል አቋም እንዳላቸው እናውቃለን፣ ገልጸውልናል፡፡ ችግሩን በዚያ መንገድ መፍታት አይቻልም የሚል አቋም አላቸው፡፡ መፍትሔ የሚሆነው ሦስቱ አገሮች በጥሞና፣ እንዲሁም በተረጋጋ መንገድ ተወያይተው መፍታት ነው ለአገሮቹም የሚጠቅመው የሚል አቋም ነው ያላቸው፡፡ እነዚህ አገሮች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎቹም የዓረብ አገሮች ይኼንኑ አቅጣጫ ይይዛሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡
ሪፖርተር፡– በህዳሴ ግድብ ላይ ያለንን ቆይታ ለጊዜው በዚህ እናቆይና ኢትዮጵያ ከአዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ፣ ወዳየችው የዲፕሎማሲያዊ ጉልህ ጉዳይ እንሻገር፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላም ስምምነት በሁለቱ አገሮች መካከል የቆየውን ጠላትነት አስቀርቶ ድንበሮች እንዲከፈቱ፣ የአየርና የስልክ ግንኙነት እንዲቀጥል፣ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓለም አቀፍ ሽልማት አግኝተዋል፡፡ ነገር ግን ትንሽ ሳይቆይ ድንበሮች ተዘግተዋል፡፡ ግንኙነቱም ተቋማዊ ሳይሆን ሁለት ዓመታት ሊያስቆጥር ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ካሁን ቀደም ወደ ጦርነት እንዲያመራ እንዳደረገው ዓይነት የሁለት ሰዎች ግንኙነት ተደርጎ ስህተት እየተፈጸመ፣ አሁንም ግንኙነቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ግንኙነት ነው ሲሉ የሚተቹ አሉ፡፡ ግንኙነቱን ተቋማዊ አድርጎ ሕጋዊ የሰዎች ዝውውርና የድንበር ግንኙነት መፍጠር እንዳይችል ያደረገው እንቅፋት ምንድነው? ለምንስ ይኼንን ያህል ቆየ?
አቶ ገዱ፡– የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ላለፉት 20 ዓመታት አካባቢ ጦርነትም ሰላምም የሌለበት፣ በጣም ከፍተኛ የወታደር ክምችት በሁለቱም ወገን የነበረበት አስፈሪ ቀጣና ነበር፡፡ ጠቅላይ ማኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ይኼ አስፈሪ የነበረ ድባብ ከመሠረቱ ተቀይሯል፡፡ አሁን ኤርትራ ኢትዮጵያን ትወራለች፣ ኢትዮጵያም ኤርትራን ትወራለች ብሎ የሚሠጋ በሁለቱም በኩል የለም፡፡ አንድ መሠረታዊ ነገር መፋጠጡ ተፈትቷል ማለት ነው፡፡ ይኼ ትልቅ ዕፎይታ ያመጣ ፍፃሜ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ እነዚህ አገሮች ምንም ዓይነት ግንኙነት አልነበራቸውም ነበር፡፡ የአየር፣ የስልክና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ተቋርጦ ነበር፡፡ አሁን የስልክ ግንኙነት ተከፍቷል፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ የአየር ግንኙነት በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ ሁለቱም አገሮች የዲፕሎማሲ ሥራቸውን ቀጥለው ተቋማዊ በሆነ መንገድ የኤርትራ ኤምባሲ አዲስ አበባ ውስጥ ተከፍቷል፣ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስመራ ውስጥ ተከፍቷል፡፡ ስለዚህ ዲፕሎማሲው እንደገና ቀጥሏል ማለት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ኤርትራና ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ በሚገናኙበት ወቅት ንትርክ ነበር፡፡ አንዱ ሌላኛውን በጥርጣሬ ይመልከት ነበር፡፡ አሁን እነዚህ ግንኙነቶች ተወግደው ሰላማዊ ግንኙነት ተፈጥሯል፡፡ እነዚህ እኔ የምቆጥራቸው ትልቅ ድሎች ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ እንዳሉ ሆነው የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ ከዚህ የተሻለ ነገር ነው የሚጠብቀው፡፡
ሕዝቡ መንገዶች እንዲከፈቱ፣ የወደቦች አገልግሎት ወደ ሥራ እንዲገባና የበለጠ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ ትስስሩ እንዲጠናከር ይፈልጋል፡፡ እነዚህ በሚፈለገው መንገድ አልሄዱም፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ ተጓትተዋል፡፡ ለዚህ ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አንደኛ መንገዶቹ ጥገና ያስፈልጋቸዋል፡፡ ወደቡም በተመሳሳይ በርካታ ሥራዎችን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ የእነዚህን አገሮች ግንኙነት ከላይ እስከ ታች እንዲወርድ በዋነኛነት እየተነሳ ያለው ጉዳይ ጊዜ ነው ማለት ነው፡፡ በተረጋጋ መንገድ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ እንደገና ደግሞ በሁለቱም በኩል ከጥርጣሬ በፀዳ መንገድ ግንኙነቶቹን ለማሳለጥና እያዳበሩ ለመሄድ በቀጣይ መከናወን ያለባቸው ሥራዎች አሉ፡፡ እነዚያ ሥራዎች የተጓተቱ ቢሆንም ለወደፊቱ መሠራት ያለባቸው ናቸው፡፡
እንግዲህ አሁን ያለው ግንኙነት ከሰላም አኳያ ትልቅ ውጤት የተገኘበት ነው፡፡ በዲፕሎማሲ መስኩ የተሻለ ሁኔታ እየተፈጠረ መጥቷል፡፡ የየብስ ግንኙነት ገና ቢሆንም የአየር ግንኙነት በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ በስልክም ሆነ በመሬት ያለውን ግንኙነት ለማሳለጥ ገና መሠራት ያለባቸውና ከድንበሩ ጋርም ተያይዞ ያላለቁ ጉዳዮች አሉ፡፡ ገና ከጅምሩ ለግጭቱ ምክንያት የሆነው ጉዳይ ተፈትቶ አላለቀም፡፡ በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት በተፈለገው መንገድና የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ በሚጠብቀው ልክ ሄዷል ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የበለጠ መተማመንንና ግልጽነትን ለመፍጠር እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች፣ ግንኙነቱን መሠረት አስይዞ ለማጠናከርና ለመቀጠል የተመቸ ሁኔታ ይፈጥራሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ካሁን ቀደም በግለሰቦች መካከል ተቋማዊ ሳይሆን እንደነበረው ዓይነት ግንኙነት እንዲሆን አይደለም ፍላጎቱ፡፡ በኤርትራም በኩል፣ በኢትዮጵያም በኩል ያለው ፍላጎት ግንኙነቱ ግልጽ ሆኖ ሥርዓት ባለውና ተቋማዊ በሆነ መንገድ እንዲፈጸም ነው ነገር ግን ተቋማዊ አድርጎ ሁሉንም ነገር መከፋፈት ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡ የፍላጎት ሳይሆን የጊዜ ጉዳይ ነው ያለው፡፡ ሌላው ግልጽ መሆን ያለበት ደግሞ በከፍተኛ ጦርነት ውስጥ የቆዩ አገሮች ናቸው፡፡ በብዙ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ያለፈበት ግጭት ነው የነበረው፡፡ እናም ነገሮች ወደዚያ በማይመልስና ሌላ ቁርሾ እንደገና በማይቀስቅስ መንገድ በጥንቃቄ ታይተው መፈጸም ያለባቸው ስለሆነ፣ እነዚህን ጥንቃቄዎች ለመውሰድ ሲባል ጉዳዩ የተጓተተ ቢመስልም መሠረት ይዞ ወደፊት ሊቋጭ ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡