Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአዲሱ የቋንቋ ፖሊሲ እንዲሳካ ከተፈለገ ሙያዊ ጉዳዮች ለባለሙያ እንዲተው ጥሪ ቀረበ

አዲሱ የቋንቋ ፖሊሲ እንዲሳካ ከተፈለገ ሙያዊ ጉዳዮች ለባለሙያ እንዲተው ጥሪ ቀረበ

ቀን:

በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክረ ቤት ፀድቆ ተግባራዊ እንዲሆን የተወሰነው የቋንቋዎች ፖሊሲ ትርጉም ባለው መንገድ እንዲሳካ ከተፈለገ፣ የሙያውን ጉዳይ ለባለሙያዎች መተው ያስፈልጋል ሲሉ የዘርፉ ተመራማሪዎች ጥሪ አቀረቡ፡፡

ከአማርኛ በተጨማሪ ኦሮሚኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማሊኛና አፋርኛን የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ያደረገውን የአገሪቱ የመጀመርያ የቋንቋ ፖሊሲ አስመልክቶ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ዙፋን ቤት ተብሎ በሚጠራው ሕንፃ አዳራሽ ሰኞ የካቲት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በተደረገ ውይይት ላይ ሐሳባቸውን ያቀረቡት ባለሙያዎች፣ ፖሊሲው የታለመለትን ግብ እንዲመታ ከተፈለገ ባለሙያውን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ለባለሙያው መተው የሚሉና ሌሎች ምክረ ሐሳቦችን ለግሰዋል፡፡

የቋንቋ ተመራማሪውና የፖሊሲው ዝግጅት ተሳታፊ የነበሩት ታዬ አሰፋ (ዶ/ር) በፖሊሲው ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ተሳትፎ ያላቸው አስፈጻሚ አካላት ተለይተው መቀመጥ እንዳለባቸው በመጠቆም፣ የፖሊሲው ሕጋዊ አስፈጻሚ ከሆነው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በተጨማሪ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያሏቸው ድርሻዎች ተለይተው እንዲቀመጡ ጠይቀዋል፡፡

ከ2003 ዓ.ም. ቀደም ብሎ ሥራው ለተጀመረው የቋንቋዎች ፖሊሲ ለማስፈጸም ያስፈልጋሉ ያሏቸውን ሦስት አዳዲስ ተቋማትም እንዲመሠረቱ ታዬ (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡

የመጀመርያው የቋንቋ ጉዳዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ይኼ ምክር ቤት ከሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ከክልሎች፣ ከስታትስቲክስ ኤጀንሲ፣ ከካርታ ሥራዎች፣ ከቋንቋ ጥናት ተቋማትና ከሌሎችም አባላት ያሉት እንደሆነም ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ የዚህ ምክር ቤት ውሳኔዎች በአስገዳጅ ተፈጻሚነት ይኖራቸው ዘንድ በአዋጅ ሕጋዊ ሰውነት ኖሮት መቋቋም አለበት ብለዋል፡፡ ስለዚህም የሕግ ማዕቀፍ፣ የክትትልና ግምገማ ሥርዓቶች መዘርጋት እንደሚኖርበት አመልክተዋል፡፡

ሁለተኛውና መቋቋም አለበት ያሉት ተቋም በቋንቋ ጉዳዮች ላይ ጥናት የሚያደርግ የምርምር ማዕከል ነው፡፡ ጥናትና ምርምር ማድረግ ኃላፊነቱ የዚህ ተቋም መሆን ይኖርበታል በማለት ምክረ ሐሳባቸውን ያሰሙ ታዬ (ዶ/ር)፣ ዕቅዶች ሲወጡ በዚህ ተቋም ግኝቶች ላይ ተመሥርተው ነው መሆን ያለበት ብለዋል፡፡

ሦስተኛው የታዬ (ዶ/ር) ምክረ ሐሳብ ደግሞ አገራዊ የሆነ ሕጋዊ ሰውነት ያለው የትርጉም ተቋም ነው፡፡ ሕጎች፣ መመርያዎች፣ ደንቦች፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ሌሎች ይዘቶች ተተርጉመው በሥራ ላይ እንዲውሉና ተደራሽ እንዲሆኑ የማድረግ ኃላፊነት ይኖረዋል ብለዋል፡፡ በህንድ እንዲህ ያለ ተቋም ከእነዚህ ተግባራት በዘለለ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን የመተርጎምና የማዳረስ ሥራዎችን ያከናውናል ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

ለእነዚህ ሥራዎች መሳካት ያግዝ ዘንድም መንግሥት በጀት መመደብ እንዳለበት ያመላከቱት ታዬ (ዶ/ር)፣ በተለያዩ ምክንያቶች የገንዘብ እጥረት አለብን በሚል ሰበብ ሥራዎች፣ ጥናቶችና ምርምሮች ሳይከናወኑ እንዳይቀሩ የቋንቋ ልማት ፈንድም መቋቋም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በዚህም ተናጋሪዎች የሚገኙበት ካርታ በመሥራትና በማበልፀግ ቋንቋዎችን የዕውቀት፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ማድረግ ያሻልም ብለዋል፡፡

ፀድቆ ወደ ተግባር የገባውን ፖሊሲ ለማዘጋጀት ከኢንዶኔዥያ፣ ከሩሲያ፣ ከህንድና ከደቡብ አፍሪካ ልምድ ለመቀመር ታቅዶ ከህንድና ከደቡብ አፍሪካ ብቻ ልምዶችን ማግኘት እንደተቻለ የጠቆሙት ደግሞ፣ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋ ዘርፍ ዳይሬክተርና በፖሊሲው አተገባበር ወቅት ከመነሻው ጀምሮ የተሳተፉት አቶ አውላቸው ሹምነጋ፣ ፖሊሲው እንዲዘጋጅ ያስፈለገበት ምክንያት በሕገ መንግሥቱ ለቋንቋዎች ለተሰጠው መብት ሥርዓት ለማበጀት ሲባል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ 53 ቋንቋዎች የትምህርት ቋንቋ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ አውላቸው፣ ይኼ የሆነው ሥርዓት ተበጅቶለት ሳይሆን በሕገ መንግሥት የተቀመጠላቸውን መብት ለመጠቀም ጥረት ባደረጉ ብሔሮች ተነሳሽነት ነው ብለዋል፡፡ ስለዚህም አዲሱና ለአገሪቱ የመጀመርያው የሆነው የቋንቋዎች ፖሊሲ በአገሪቱ ልሳነ ብዙኃነትን በአግባቡ ለመጠቀም፣ የሕዝቦችን የእርስ በርስ ትስስር ለማጠናከርና  ቀጣናዊ ትስስርን ለማጎልበት ይረዳል ብለዋል፡፡

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በአገሪቱ ያሉ ቋንቋዎች አንዴ ከ80 በላይ ሌላ ጊዜ ደግሞ 76 ናቸው እንደሚባል በመጠቆም፣ ‹‹ይህ ያለንን ሀብት ቆጥረን ለማልማትና ለመጠቀም አለመዘጋጀታችን ያሳያል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አሁን የቋንቋ ፖሊሲ መዘጋጀቱ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በማሳሳብም፣ ፖሊሲው ምን ያህል ጠቃሚ እንደሚሆን የባህል ፖሊሲ በመኖሩ የተገኘውን ጥቅም ማየት ያሻል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ብዝኃ ቋንቋ ያለባት አገር ብትሆንም ብዝኃ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ ማኅበረሰብ እንደሌለ የተናገሩት ሒሩት ካሳው (ዶ/ር)፣ ‹‹ይኼም አንዱ ማኅበረሰብ ከሌላው ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያሳጥር ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ያልሆነውም የቋንቋ ፖሊሲ ባለመኖሩ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ብዝኃ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰብ ያስፈልጋታል፣ አዲሱ የቋንቋ ፖሊሲም ይኼንን ያስችላል፤›› ሲሉም ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ቋንቋዎች አገራዊ፣ ክፍለ አኅጉራዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነትን ለመፈጸም የሚያስችሉ መሆን እንዳለባቸው ያከሉት ሒሩት (ዶ/ር)፣ ይኼ የሚሆነው ደግሞ ፖሊሲ ሲኖር ነው ብለዋል፡፡

‹‹ቋንቋዎች መልማት ስላለባቸው ፖሊሲው ፀድቋል፣ ከትምህርትና ከቴክኖሎጂ ጋርም መገናኘት አለበት፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...