ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የብድር ወለድ ማስከፈያ ምጣኔው ላይ በርካታ ማሻሻያ ለማድረግ ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታውቆ፣ ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በሚውል ብድር ላይ እስከ 4.5 በመቶ የወለድ ቅናሽ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
ባንኩ በአሁኑ ወቅት በሁሉም የንግድ መስኮች ላይ ለሚሰጣቸው ብድሮች የወለድ ምጣኔውን ለመቀነስ የሚችልበትን ጥናት እያጠናቀቀ ሲሆን፣ ቅድሚያ በተሰጠው በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ብድር ላይ የሚያስከፍለውን የወለድ ምጣኔ ላይ ቅናሹን ይፋ አድርጓል፡፡ በሌሎች ዘርፎች ላይ ስላደረጋቸው የብድር ወለድ ቅናሾች ይፋ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡
ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ቅድሚያ በመስጠት የወለድ ማሻሻያ የተደረገው ግን ሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ አስገኚ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ሲሆን፣ ዘርፉን በማጎልበት የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ከፍ ለማድረግ በመታሰቡ የወለድ ቅናሹ ለዚህ ዘርፍ ቅድሚያውን እንደሰጠ ባንኩ አስታውቋል፡፡
በግል ባንኮች ላይ በአስገዳጅነት ሲተገበር የቆየው የ27 በመቶ የቦንድ ግዥ መመርያ እንዲነሳ በመደረጉ፣ ባንኮችም የለወድ ማስከፊያቸው ላይ ቅናሾችን እንዳደረጉ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ እስካሁን ተመሳሳይ ዕርምጃ መውሰዳቸውን በይፋ ካደረጉ ባንኮች መካከል አዋሽ ባንክ፣ ሕብረት ባንክና ዓባይ ባንክ ይጠቀሳሉ፡፡
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በ2011 ዓ.ም. ያስመዘገበው የብድር ክምችት 19.4 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በ2012 ግማሽ ዓመት ግን ከ23.3 ቢሊዮን ብር በላይ አስመዝግቧል፡፡ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑም ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ በዚሁ ወቅት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ከ750.2 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡ ባንኩ በአሁኑ ወቅት የደረሰበት አጠቃላይ የሀብት መጠን ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ይገመታል፡፡