Monday, June 24, 2024

የኢትዮጵያና የግብፅ የቃላት ጦርነት በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የግብፅ መንግሥት የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ግድቡ ወደ ግብፅ የሚፈሰውን የውኃ መጠን በመቀነስ፣ የታችኞቹ የተፋሰስ አገሮች ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ያሳድራል ስትል በተደጋጋሚ አቤቱታ ያሰማል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም የሚቀርቡበት ትችቶች በጥናት የተመለሱ፣ ሁሉንም በሚያግባባ መንገድ ግኝቶቹ መሰራጨታቸውን በመጥቀስ ሲያጣጥል ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ለናይል ወንዝ 85 በመቶ ውኃ በሚያበረክተው የዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባውና 74 ቢሊዮን ሜትር ኩዩብ ውኃ የመያዝ አቅም ያለው ግድብ፣ በታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች ላይ የሚያሳድረው ጉልህ ተፅዕኖ የለም የሚለውን አቋሙን የተጠኑ ግኝቶችንና የመከራከሪያ ሐሳቦችን በመያዝ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ድርድር ከተቀመጠ እነሆ ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

በእነዚህ ስምንት ዓመታት በተካሄዱ ውይይቶች የተገኘና ለስምምነት የበቃ ጠብ የሚል ውጤት አልተገኘም የሚሉ ወገኖች፣ ድርድሩ ጊዜ ከማባከን የዘለለ ሚና የለውም በማለት ይተቻሉ፡፡ ነገር ግን ድርድሩ ከሚጠበቀው በላይ የሆነ ውጤት አስገኝቷል የሚሉም አልጠፉም፡፡ ይኼም ውጤት ግብፅ የዓባይን ውኃ አትጠቀሙና የህዳሴ ግድቡን አትገንቡ ከማለት መለስ ብላ፣ የኢትዮጵያን የመጠቀም መብት በማክበር የውኃ ፍሰት ላይ ለመደራደር መሆኑ ነው ይላሉ፡፡

ይኼ የተሻለ ውጤት ቢሆንም ቅሉ የድርድሩ ዋና ዓላማ በሆነውና የህዳሴ ግድብን የውኃ ሙሌትና አለቃቅ የተመለከተ ስምምነት ማድረግ፣ የሰማይ ያህል ሩቅ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ድርድሮቹ በተካሄዱባቸው ስምንት ዓመታት ከስምምነት ሊደረስባቸው በሚችሉ ጊዜያት ሁሉ፣ የግብፅ ተደራዳሪዎች በተጠናና ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ ጥቅማቸውን በሚያስጠብቅ መንገድ ድርድሩን ጥለው እንደሚወጡ እየተነገረ ሲተቹ ቆይተዋል፡፡ ድርድሮቹም ይቀጥሉ ዘንድ በመሪዎች ደረጃ በሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶች የተቋቋሙት የቴክኒክና የሚኒስትሮች ኮሚቴዎች፣ ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ውኃ ቢወቅጡት (…) ዓይነት ንትርኮች ውስጥ ቆይተዋል፡፡

ድርድሮቹ ተቋርጠው በቀጠሉ ቁጥር በቂ ዝግጅት እያደረጉና አዳዲስ ሐሳቦችን ይዘው የሚመጡት የግብፅ የውጭ ጉዳይና የውኃ ሚኒስትሮች፣ በስተመጨረሻ ከህዳሴ ግድቡ የሚለቀቀውን ውኃ ከ40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ እንዳያንስ፣ በግብፅ የሚገኘው ትልቁ የአስዋን ግድብ የውኃ መጠን ከባህር ወለል በታች 165 ሜትር ከወረደ በአፋጣኝ ውኃ ከህዳሴ ግድቡ እንዲለቀቅለት፣ የህዳሴ ግድብ ከ12 እስከ 20 ዓመታት ባላነሰ ጊዜያት እንዲሞላ፣ እንዲሁም የግድቡ ሙሌትና የውኃ አለቃቀቅ በየዓመቱ በሚኖረው የድርቅና የአየር ንብረት ሁኔታ ላይ የተመረኮዘ እንዲሆን የሚሉ ምክረ ሐሳቦችን ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም፡፡

ከመጀመርያው የግድቡ ግንባታ አንስቶ የውኃ አሞላሉን ዕቅድ በማውጣት ወደ ግድቡ የሚገባና የሚወጣ የውኃ መጠን በመቀመር ስትከራከር የቆየችው ኢትዮጵያ፣ ይኼንን ምክረ ሐሳብ አልቀበልም በማለቷ ድርድሩ በመስተጓጎሉ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጣልቃ ገብተው ለጉዳዩ ዕልባት እንዲያበጁ ጥሪ አስተላለፉ፡፡ በዚህም መሠረት የአሜሪካ የግምጃ ቤት ሚኒስትር ስቲቨን ምኑሽንና የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስ፣ የኢትዮጵያን የውኃና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከግብፅ አቻዎቻቸው ጋር አስቀምጠው በዋሽንግተን ዲሲ ‹‹በታዛቢነት›› ሲያሸማግሏቸው ቆዩ፡፡

ከዋሽንግተንና ከዓለም ባንክ ጣልቃ ገብነት በኋላ የተደረጉ ተከታታይ ውይይቶች በግድቡ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተው ከስምምነት ተደርሶ ፊርማ ይደረጋል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም፣ ይኼ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ የአሜሪካ የግምጃ ቤት ሚኒስትሩም አዘጋጅተው ያቀረቡት የስምምነት ሰነድ ለፊርማ ቢቀርብም፣ ኢትዮጵያ ለመፈረም ፈቃደኛ ሳትሆን በመቅረቷ ውይይቱ ሳይቋጭ ቀርቷል፡፡ በተመሳሳይ ሱዳንም ፊርማዋን ከወረቀት ሳታኖር ቀርታለች፡፡

የመጨረሻውና የስምምነት ፊርማ ይደረጋል ተብሎ በተጠበቀው እ.ኤ.አ. ከፌብሩዋሪ 27 እስከ 28 ቀን 2020 በዋሽንግተን ዲሲ በተደረገው ስብሰባ፣ ኢትዮጵያ በተዘጋጀው ሰነድ ላይ በአገር ውስጥ ካሉ ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርጌ አልጨረስኩም በማለት ያልተሳተፈች ሲሆን፣ ግብፅ በሰነዱ ላይ ለመፈረም በዝግጁነት ተገኝታለች፡፡ ሱዳን ብትገኝም ሳትፈርም ተመልሳለች፡፡

ይኼንን የመጨረሻና ኢትዮጵያ ያልተገኝበትን ውይይት ተከትሎ በአሜሪካ የግምጃ ቤት ሚኒስትር ስቲቨን ምኑሽን የወጣው መግለጫ፣ ግብፅን በስምምነቱ ላይ ፊርማዋን ለማኖር ላሳየችው ፈቃደኝነት ያመሠገነ ሲሆን፣ የግድቡን ደኅንነት በተመለከተ የታችኛው የተፋሰስ አገሮች (በተለይ ግብፅና ሱዳን) ሥጋት ስለገባቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያ በአፋጣኝ የምታደርገውን የውስጥ ምክክር አጠናቅቃ ወደ ውይይት እንደምትመለስ ተስፋ እያደረግን፣ ከስምምነት ሳይደረስ ግድቡ እንዳይሞላ፤›› ሲል ይደመድማል፡፡

ይኼንን መግለጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በጋራ ባወጡት መግለጫ የአሜሪካ መግለጫ እጅግ እንዳሳዘናቸው በማተት፣ ኢትዮጵያ እንድትፈርምበት የተጠየቀችው ሰነድ ከውይይቱ የመነጨ ሳይሆን ከግብፅ የመጣ ነው በማለት ድርድሩ ስላበቃ ፈርሙ መባሉ ልክ አይደለም በማለት ተችተዋል፡፡

የግድቡን የግንባታ ሒደት በመከተልም የውኃ ሙሌት ሥራ እንደሚጀመርና የኢትዮጵያን የግድቡ ባለቤትነት በመጥቀስ የሚከራከረው ይኼ መግለጫ፣ በመርህ መግለጫ ስምምነቱ መሠረት ፍትሐዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነትን በማገናዘብ ጉልህ ተፅዕኖ (ጉዳት) በማያስከትል መንገድ ይቀጥላል ሲል ያስረዳል፡፡

በውይይቶች መቋጫ ያላገኙና መፈታት ያለባቸው ያላለቁ ጉዳዮች አሉ በማለትም፣ ከግብፅና ከሱዳን ጋር በቀጣይነት በመወያየትና ጉዳዮችን በመፍታት የመጨረሻውን የግድቡን ውኃ አሞላልና አስተዳደር የተመለከቱ ስምምነቶችን ለመፈጸም ኢትዮጵያ ዝግጁ ናት በማለት ያጠቃልላል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ መግለጫ ግድቡ የእኔ ነውና ውኃ መሙላቴን ማንም ሊከለክል አይችልም ስትል ያሳየችውን ጠንካራ አቋም በመቃወም ለአገራቸው መገናኛ ብዙኃን የተናገሩት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ግድቡን በምንም ዓይነት ሁኔታ መሙላት የለባትም፤›› ሲሉ የተደመጡ ሲሆን፣ ‹‹ድንበር አቋራጭ ወንዞችን በተመለከተ ማንም ለብቻው ውሳኔ መስጠት እንደማይችል ዓለም አቀፍ ሕጎች የደነገጉ ሲሆን፣ የመርህ ስምምነቱም ይኼንን ነው ያስቀመጠው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የግብፅ የተለያዩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የግብፅ ፓርላማ ምክትል አፈ ጉባዔና ፕሬዚዳንት አልሲሲን ጨምሮ ግብፅ በዓባይ ላይ ያላትን ታሪካዊ መብት ለማስጠበቅ የትኛውንም ዓይነት አማራጭ መጠቀም እንደምትችልና እንዳለባት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ የግብፅ ፕሬዚዳንት በግድቡ ላይ ከመከላከያ ሠራዊት አባላትና ከፍተኛ አመራሮች ጋር ስብሰባዎችን ሲያደርጉ በማሳየት፣ ለኢትዮጵያ መልዕክት ሲያስተላልፉም ነበር፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት አቋሙ በግድቡ ላይ ለሚኖሩ የትኛውም ዓይነት ልዩነት መፍትሔው መወያየትና መግባባት እንደሆነ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ከውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ጋር በመሆን ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ያስታወቁ ሲሆን፣ ከዚህ ውጪ ያለ ዛቻና ማስፈራሪያ ከንቱ ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ ‹‹የሚያጋጭና ወደ ሌላ ነገር የሚያስገባ ነገር የለም፡፡ ይህ ዕርባና ቢስ አመለካከት ነው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚታሰብ አይደለም፡፡ ሌላ ምክንያት ከሌለ በስተቀር፤›› ሲሉም አቶ ገዱ የሚጎሰመውን የጦርነት ነጋሪት አጣጥለዋል፡፡

በተመሳሳይ ከወራት በፊት ይኼንኑ የግድቡን ጉዳይ በተመለከተ በፓርላማ ተጠይቀው ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ጦርነት ከሆነ ሚሊዮኖችን ማሰባሰብ ይቻላል በማለት የግብፅን ዛቻ ያጣጣሉ ሲሆን፣ ጉዳዩ ግን ጦርነት ላይ ሳይደርስ መፍትሔ ያገኛል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ የግብፅ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ከመከላከያ አመራሮች ጋር ላደረጉትና በኢንተርኔትና በሌሎች መገናኛ ብዙኃን ለተላለፈው ውይይት ምላሽ እንዲሆን በሚመስል፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም ከመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አባላት ጋር በግድቡና በሌሎች የፀጥታና የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ውይይት እንዳደረጉ ከሚናገር መግለጫ ጋር በዩኒፎርም የሚታዩ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ያሉበት ምሥል ተለቅቋል፡፡

ነገር ግን የሁለቱ አገሮች የቃላት ጦርነት፣ የመከላከያና የዲፕሎማሲ ጡንቻ መለካካት በዚህ ያበቃና የሚበቃ አይመስልም፡፡ በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ መቀመጫውን ያደረገውን የዓረብ ሊግ በመሰብሰብ ግድቡንና የኢትዮጵያን አቋም እንዲያወግዙ ያደረጉት ፕሬዚዳንት አልሲሲ፣ ለምን የሚል ጥያቄ ከአባላቱ አልቀረበላቸውም ነበር፡፡ ሱዳን አልፈርምም ብላ በተቃውሞ ከመውጣቷ በቀር፡፡

ሱዳን ግድቡ የውኃ መጠን የመቀነስም ሆነ ሌላ ጉዳት በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ ያስከትላል የሚል እምነት እንደሌላት በመግለጽ፣ የኢትዮጵያን ልማት እንደምትደግፍ አስታውቃለች፡፡

ይኼንን የዓረብ ሊግ ውሳኔ ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የካቲት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የዓረብ ሊግን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ እንደማይቀበለው በማስታወቅ፣ አባላቱ የግድቡን እውነታ ሳይረዱ ለግብፅ ጭፍን ድጋፍ መስጠታቸው ያሳዝናል ብሏል፡፡ ነገር ግን ሱዳን የያዘችውን አቋም አድንቋል፡፡ በዚህ ውሳኔው ሳቢያም የዓረብ ሊግ ሉዓላዊ እየሆነ በመጣ ዓለም ውስጥ ሰላምን፣ መረጋጋትንና ትብብርን ለማምጣት ያለው ብቃትና ታማኝነት ከጥያቄ ውስጥ ገብቷል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያን መግለጫ የተመለከተው የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን ጉዳዩን በዝምታ አላለፈውም፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ መግለጫ ትክክል ያልሆነና ዲፕሎማሲያዊነት የጎደለው ነው፤›› በማለት አጣጥሎታል፡፡

የግብፅ መንግሥት እንዲህ ፊት ለፊት ከሚያደርገው እሰጥ አገባ በተጨማሪ ሰፋፊ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን የሚያከናውን ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት ልዑካኖችን ተፅዕኖ ሊያሳድሩ ወደሚችሉ አገሮች በመላክ ድምፅ ለማሰማት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በተመሳሳይ የሚደርገው ነገር እንዳለና ወደ ሌሎች አገሮች እውነታን ለማስረዳት ጥረት እንደሚያደርግ ቢነገርም፣ መንግሥት ግን በግልጽ የተናገረው ነገር የለም፡፡ አቶ ገዱ በመግለጫቸው እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ባላት እውነታ እንጂ፣ እገሌ ኃያል አገር ስለሆነ ከእኔ ጎን ይሠለፋል ስትል እየተደራደረች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህ ግን ኢትዮጵያን ብዙ ጊዜ የጎዳት አስተሳሰብ በመሆኑ፣ በተቻለ መጠን እውነትን ይዞ በዲፕሎማሲው መስክ ጠንክሮ በመገኘት የማግባባት ሥራውን ማቀላጠፍ እንደሚገባ የብዙዎች እምነት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -