በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚሰናዳው የአምስት ኪሎ ሜትር የሴቶች የጎዳና ላይ ሩጫ እሑድ መጋቢት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ይከናወናል፡፡
ለ17ተኛ ጊዜ የሚካሄደው የጎዳና ላይ ሩጫ በመዲናው ከሚኖሩት ተሳታፊዎች ባሻገር 200 አትሌቶች ከፍተኛ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ መነሻና መድረሻውን አትላስ የሚያደርገው ውድድሩ በዘንድሮ አካል ጉዳተኞችንም ያካተተ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በጎዳና ላይ ውድድሩ 15,000 ተሳታፊዎች መመዝገባቸውን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡
የታላቁ ሩጫ ዓመታዊ ፕሮግራም አንዱ የሆነ የአምስት ኪሎ ሜትር ውድድሩን ላሸነፉ 70,000 ብር ሽልማት አዘጋጅቷል፡፡ ዝግጅቱ ለአዲስ አትሌቶች ዕድል ከመፍጠሩም ባሻገር የተለያዩ በጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ድጋፍ በማድረግ ይታወቃል፡፡ ‹‹በተሟላ ሥርዓተ ምግብ ምኞቷ ይሳካል›› በሚል መሪ ቃል የሚከናወነው ውድድር ለተቸገሩ እንስቶች የሚውል የንፅህና መጠበቂያ ከሁሉም ተሳታፊዎች ለመሰብሰብ ዓላማን አንግቧል፡፡
የተሰበሰበውም የንፅህና መጠበቂያ ከሴቶች፣ ሕፃነናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን ከአዲስ አበባ ውጪ ለሚገኙና ለተቸገሩ አካባቢዎች ይከፋፈላል ተብሏል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ወደ ውድድሩ የሚያመጣቸው አምባሳደር የሚሆኑ ታዋቂ ሰዎች ለተሳታፊዎች መነቃቃትን በመፍጠር ይታወቃሉ፡፡
ዓለም አቀፉ የማራቶንና የረጅም ርቀት ማኅበር የሆነው ኤአይኤምኤስ መሠረት ደፋርን ምርጥ የአነቃቂ ሽልማትን አበርክቶላታል፡፡ አትሌቷ ለሽልማቱ የታጨችው ለበርካታ ሴት ኢትዮጵያውያን ምሳሌ መሆንዋ ታሳቢ ተደርጎ ነው፡፡ በ17ተኛው የሴቶች አምስት ኪሎ ሜትር ውድድር ላይ ተጋባዥ በመሆን ለአሸናፊዎች ሽልማት ታበረክታለች ተብሏል፡፡