ለ21ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ለሦስተኛ የምድብ ጨዋታ በባህር ዳር ዝግጅቱን ይጀምራል፡፡ ከማዳጋስካር፣ ኒጀርና አይቮሪ ኮስት ጋር የተደለደለው ቡድኑ ለ24 ተጫዋቾች ጥሪ አድርጓል፡፡
ለተጫዋቾች ጥሪ ያደረጉት አሠልጣኝ አብርሃም መብራህቱ ከ13 ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች 23 ተጫዋቾችን እንዲሁም በግብፅ አል መካስ ክለብ የሚጫወተውን ሽመልስ በቀለን ብቸኛው ከውጭ ጥሪ አድርገውለታል፡፡ የተመረጡት ተጫዋቾች ቅዳሜ መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ተገኝተው ሪፖርት እንዲያደርጉ ተገልጿል፡፡
በምርጫቸው በርካታ ለውጥን ያደረጉት አሠልጣኙ ስምንት ተጫዋቾች ላይ ለውጥ አድርገዋል፡፡ ከስምንቱ ተጫዋቾች አዳዲስና ከረዥም ጊዜ በኋላ ጥሪ የተደረገላቸውም ይገኙበታል፡፡ ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች ውስጥ የተወሰኑት ወይም በፕሪሚየር ሊጉ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረጉ የሚገኙ ተጫዋቾች አልተካተቱም የሚሉ ቅሬታዎችም እየተነሱ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል የፋሲል ከነማ አጥቂ የሆነውና የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ሙጂብ ቃሲም በምርጫው ውስጥ አለመካተቱ ጥያቄ አስነስቷል፡፡
ከዚህም ባሻገር አሠልጣኝ አብርሃም ከዚህ ቀደም በነበሩት የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ተሠልፈው የነበሩ በውጭ ሊግ ላይ እየተጫወቱ የሚገኘውን ጋቶች ፓኖም፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ ምንተስኖት አሎ እና አቤል ማሞ ከምርጫው ውጪ አድርገዋቸዋል፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ መጋቢት 19 ከኒጀር አቻው ጋር የሚያደርገውን የሦስተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ ከማድረጉ ቀደም ብሎ ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ በባህር ዳር ዝግጅቱን ያደርጋል፡፡
ለ21ኛው አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጥሪ የተደረገላቸው የተጫዋቾች ስም ዝርዝር
ግብ ጠባቂዎች፣ ተክለማርያም ሻንቆ (ኢትዮጵያ ቡና)፣ ይድነቃቸው ኪዳኔ (ወልቂጤ ከተማ)፣ ሰዒድ ሀብታሙ (ጅማ አባ ጅፋር) ተከላካዮች፣ ፈቱ ዲን ጀማል (ኢትዮጵያ ቡና)፣ አህመድ ረሺድ (ኢትዮጵያ ቡና) አስቻለው ታመነ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ደስታ ዳሙ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ አንተነህ ተስፋዬ (ሰበታ ከተማ)፣ ረመዳን ዩሱፍ (ስሑል ሽረ)፣ ዮናታን ፍሥሐ (ሲዳማ ቡና) አማካዮች፣ ታፈሰ ሰለሞን (ኢትዮጵያ ቡና)፣ ሃይደር ሸረፋ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ታደለ መንገሻ (ሰበታ ከተማ)፣ ግርማ ዲሳሳ (ባህር ዳር)፣ ይሁን እንዳሻው (ሀድያ ሆሳዕና)፣ ከነዓን ማርክነህ (አዳማ ከተማ)፣ ሱራፌል ዳኛቸው (ፋሲል ከነማ) ሽመልስ በቀለ (አል መካስ)፣ አጥቂዎች፣ አማኑኤል ገብረ ሚካኤል (መቐለ ከተማ) መስፍን ታፈሰ (ሐዋሳ ከተማ)፣ አዲስ ግደይ (ሲዳማ ቡና)፣ አቤል ያለው (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ሚኪያስ መኮንን (ኢትዮጵያ ቡና)፣ አቡበከር ናስር (ኢትዮጵያ ቡና)፡፡