በምሥረታ ላይ የሚገኘውን የአማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር ባለፉት ስምንት ወራት አክሲዮኖች የገዙ ባለአክሲዮኖች ቁጥር ከ145 ሺሕ በላይ ሲደርስ፣ የተከፈለ ካፒታል ደግሞ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡
የባንኩ መሥራች ኮሚቴ አባላት ሰኞ የካቲት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ የተፈረመ ካፒታሉን 5.3 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻላቸውን አስታውቀዋል፡፡ የባንኩ የአክሲዮን ሽያጭ ለሦስተኛ ጊዜ እንደተራዘመ ያስታወቁት የባንኩ አደራጆች፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን የአክሲዮን ባለቤት ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የባንኩን አክሲዮኖች የገዙ ባለአክሲዮኖች ቁጥር ከ145 ሺሕ በላይ መድረሱ፣ በባንክም ሆነ በሌሎች የንግድ ዘርፎች ከፍተኛ የሆነ ባለአክሲዮኖችን ያሰባሰበ ብቸኛ ተቋም አድርጎታል፡፡
ይሁን እንጂ ከየትኛውም ዘርፍ በተለየ ቁጥጥር ይደረግበታል በሚባለው የፋይናንስ ዘርፍ፣ ይህንን ያህል ቁጥር ያላቸውን ባለአክሲዮኖች እንዴት ማስተዳደር ይቻላል የሚለው ጥያቄ አሳሳቢ መሆኑ አልቀረም፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት የፋይናንስ ተቋማት፣ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ማካሄድና በውጭ ኦዲተሮች የተረጋገጠ ሪፖርት ማቅረብ ግዴታቸው ነው፡፡ አማራ ባንክ ከ145 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖችን በአንዴ ለመሰብሰብ እንኳን አዳራሽ ስታዲየም አይበቃውም፡፡
የመሥራች ጠቅላላ ምልዓተ ጉባዔ ባለአክሲዮኖች መጠን 50+1 በመቶ ስለሚሆን፣ አሁን ባለው የባለአክሲዮኖች ብዛት ከ70 ሺሕ በላይ ተሳታፊዎች መገኘትን የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የዚህን ያህል ቁጥር በአንድ ቦታ ለማሰባሰብ ይቻላል ወይ የሚለው ያሳስባል፡፡ በአገሪቱ እስካሁን ከ20 ሺሕ የዘለለ ባለአክሲዮኖች ያሏቸው ተቋማት ስለሌሉ፣ አሁን የአማራ ባንክ የደረሰበት የባለአክሲዮኖች ቁጥር ለአስተዳደርም የሚፈትን ይሆናል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡
እንዲህ ያለ ከፍ ያለ ባለአክሲዮኖች ሲኖሩ ምን መደረግ ይኖርበታል በሚለው ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ባንኩ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት ባለአክሲዮኖች እንዴት እንደሚያስተናግድና አጠቃላይ አሠራሩን በግልጽ ማስቀመጥ ይኖርበታል ይላሉ፡፡ አጋዥ ሕግ እንዲኖርም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር፣ ሊገጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ከወዲሁ መቅረፍ እንደሚገባውም ያክላሉ፡፡
በአገሪቱ የንግድ ሕግም ሆነ በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት አንድ የፋይናንስ ተቋም መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ፣ ከጠቅላላ ባለአክሲዮኖች 25+1 በመቶ ምልዓተ ጉባዔ መሟላት አለበት፡፡ አስቸኳይና ድንገተኛ መደበኛ ጉባዔ ለማካሄድ ደግሞ 50+1 በመቶ መሆኑን ባለሙያዎቹ አስታውሰው፣ 145 ሺሕ ባለአክሲዮኖችን (ከዚህ በኋላም ሊጨምር ይችላል) የያዘ ባንክ ምሥረታው ሲያካሂድ ለሁሉም ጥሪ ማድረግ አለበት፡፡ ስለዚህ 50+1 በመቶ ባለአክሲዮኖች መገኘት አለባቸው፡፡ ያለበለዚያ ምሥረታውን ለማካሄድ አይችልም ይላሉ፡፡ የፋይናንስ ዘርፍ ባለሙያዎች አሁን ባለው ቁጥር ከ70 ሺሕ እስከ 80 ሺሕ ባለአክሲዮኖች የሚይዝ ስታዲዮም በሌለበት አገር፣ የባንኩ ምሥረታ እንዴት ዕውን ይሆናል የሚለው ጉዳይም እንደሚያሳስባቸው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
በተለይ የአክሲዮን ሽያጩ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በመከናወኑ፣ ባለአክሲዮኖች ሊወከሉበት የሚችል አሠራር ካልተፈጠረ ሊያስቸግር ይችላል የሚል ሥጋትም አላቸው፡፡ አሁን ባለው አሠራር መሠረት እያንዳንዱ ባለአክሲዮን የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ቀርቦ መፈረም ያለበት ስለሆነ፣ ይህም የራሱ ተግዳሮት ሊኖረው ይችላል ብለዋል፡፡
ከ145 ሺሕ ባለአክሲዮኖች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ባለአክሲዮኖች ለማግኘት ሊኖር የሚችለው ፈተና በመጀመርያው ምሥረታ ወቅት ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያም በኋላ ባንኩ ከመደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ውጪ በሚያካሂዳቸው ድንገተኛና አስቸኳይ ጉባዔዎች ላይ ሊያስቸግር የሚችል መሆኑን በመንዘብ ከወዲሁ መዘጋጀት ተገቢ ነው ተብሏል፡፡ ለምሳሌ ባንኩ ካፒታሉን ማሳደግ ወይም መተዳደርያ ደንቡን ለመለወጥ ቢፈልግ፣ ወይም በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ የሚሹ ሌሎች አጀንዳዎች ቢኖሩ የግድ 50+1 በመቶ የባለአክሲዮኖች ድምፅ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በአንዴ 70 ሺሕ እና 80 ሺሕ ባለአክሲዮኖች ላይገኙ እንደሚችሉ፣ ቢገኙ እንኳን ይህንን ያህል ባለአክሲዮኖች የት ይስተናገዳሉ የሚለው ጥያቄ ቢያሳስብ ትክክል መሆኑን ባለሙያዎች አስረድተዋል፡፡
የአማራ ባንክ እንደ ምሳሌ ቀረበ እንጂ ወደፊት ተመሳሳይ ሁኔታዎች ቢፈጠሩ እንዴት ይስተናገዳል የሚለው ነገር መታሰብ እንዳለበት፣ ለመፍትሔም ብሔራዊ ባንክ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የፋይናንስ ተቋማትን የጠቅላላ ጉባዔ አጠራርና መሥፈርቶች የሚመለከቱ ሕግጋት መከለስ እንዳለበት፣ ምክንያቱም በርካታ ባለአክሲዮኖች ያሉዋቸው ባንኮችም አሁን እየተቸገሩ መሆኑን ያወሳሉ፡፡
ሌላው የውክልና አሠራር እንዴት ተግባራዊ ይደረግ የሚለው ጉዳይ ላይም፣ ተቆጣጣሪው ብሔራዊ ባንክ ጥናት ማድረግና ሕግጋቱን ጊዜው ከሚጠይቀው ሁኔታ ጋር ማጣጣም አለበት ሲሉም ያክላሉ፡፡ አንዳንድ ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች መደበኛ ጉባዔያቸውን ለማድረግ የሚፈለገውን 25+1 በመቶ የባለአክሲዮን ቁጥር በማግኘት ምልዓተ ጉባዔ ተሟልቶ ስብሰባ ያደርጋሉ፡፡ ሆኖም በዚያው ስብሰባ ላይ ድንገተኛ ወይም አስቸኳይ ጉባዔ ካለ ጉባዔ ለማካሄድ 50+1 የሚሆን ምልዓተ ጉባዔ ባለማግኘት የካፒታል ማሳደግና ሌሎች ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ ያልቻሉባቸው አጋጣሚዎች ስለሚታዩ፣ ብሔራዊ ባንክ እንዲህ እያጋጠሙ ያሉ ጉዳዮችን በቶሎ ሊያስተካክል እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎች ያሳስባሉ፡፡ አንዳንድ ባንኮች የባለአክሲዮኖቻቸው ቁጥር እየጨመሩ መሄዱን ታሳቢ በማድረግ አሠራሩን ማስተካከል የግድ ነው ይላሉ፡፡
እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ላይ ሰኞ ዕለት በተሰጠው መግለጫ ላይ የተብራራ ነገር ባይቀርብም የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መላኩ ፈንታ፣ ‹‹ባንኩ በአክሲዮን አሠራርና አፈጻጸም መሠረት የሚሄድ ስለሆነ ወደኋላ አይመለስም፤›› ብለዋል፡፡ በባንኩ ላይ የሚነሱ አግባብ ያልሆኑ አስተያየቶችንም ተችተዋል፡፡ ‹‹እንደ አማራ ባንክ ብዙ የአክሲዮን ባለቤቶች አሉ፡፡ ባንካችን የሕዝብ ባንክ ነው፡፡ ስለዚህ የሕዝብ ባንክ በተለያዩ አሉባልታዎች፣ በተለያዩ ትርጉም በማይሰጡና አንሰው ሊያሳንሱ በሚያስቡ ሰዎች ምክንያት ወደኋላ የማይልበት ደረጃ የደረሰ ነው፡፡ ስለዚህ የሕዝብ ባንክ ነው፡፡ ሕዝብ ይጠብቀዋል፡፡ መንግሥትም ይጠብቀዋል፤›› ብለዋል፡፡
የአማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር አደራጅ ኮሚቴ እንዳስታወቀው፣ የአክሲዮን ሽያጩን እስከ ሚያዝያ 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ እንዲራዘም መወሰኑ ለተሻለ ነገር ታምኖበት ነው፡፡ የአክሲዮን ሽያጩ ለሦስተኛ ጊዜ ነው የተራዘመው፡፡ የአክሲዮን ሽያጩ ለሦስተኛ ጊዜ እንዲራዘም የተደረገበት ዋነኛ ምክንያት፣ ውጭ ላሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዕድል ለመስጠት ነው፡፡ ከሙስሊሙ ኅብረተሰብ በተነሳ ጥያቄ መሠረት ለእነሱም ዕድል መስጠት በማስፈለጉ መሆኑንም አቶ መላኩ አስረድተዋል፡፡
ትውልደ ኢትዮጵያውያን በፋይናንስ ዘርፍ እንዲሳተፉ አዋጅ መውጣቱን ያስታወሱት አቶ መላኩ፣ ‹‹ነገር ግን አዋጁን ተከትሎ ሊወጣ የሚገባው መመርያ በመጠየቅ ላይ ስለነበርን የአክሲዮን ሽያጩ እንዲራዘም አድርገናል፡፡ መመርያው የወጣው የካቲት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው፡፡ ስለዚህ ዳያስፖራውን የአክሲዮን ባለቤት ለማድረግም በተለያዩ ባንኮች ዝግ አካውንቶች ከፍቶ አክሲዮን እንዲገዛ ለማድረግ የነበረው ጊዜ አጭር ጊዜ ስለነበር ማራዘሙ አስፈልጓል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም በቀሪዎቹ ሳምንታት ዳያስፖራዎች በዚህ ዕድል እንዲጠቀሙ በባንኩ ጥሪ ተላልፏል፡፡ የሙስሊም ኅብረተሰብም ይህንኑ ተጨማሪ ጊዜ በመጠቀም የአክሲዮን ግዥውን ይፈጽማል ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ ይኼ ዕድል ለዳያስፖራውና ለሙስሊሙ ኅብረተሰብ በስፋት የተከፈተ ስለሆነ ይህንን ዕድል ባለችው ጊዜ ተጠቅመው አክሲዮን እንዲገዙ አቶ መላኩ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡