ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን በተሾሙት አቶ አቤ ሳኖ ምትክ፣ አቶ ተፈሪ መኮንን የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲሠሩ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ወሰነ፡፡
የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ አቶ ተፈሪ የባንኩ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲያገለግሉና ይህም ሹመት እንዲፀድቅለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡
አቶ ተፈሪ የባንኩ ፕሬዚዳንት ሆነው ከመሾማቸው ቀደም ብሎ በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ውስጥ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን፣ በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ከ21 ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው መሆኑን ባንኩ አስታውቋል፡፡
አቶ ተፈሪ ከ15 ዓመታት በላይ የሚሆነውን የአገልግሎት ዘመን ደግሞ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በወጋገን ባንክና በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ የሠሩ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡