Sunday, June 4, 2023

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ገጽታ በያዘው የህዳሴ ግድብ ድርድር አሸናፊ ሆና ለመውጣት ምን አማራጮች አሏት?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያ ከመጋቢት 2003 ዓ.ም. ጀምሮ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ባለችው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ምክንያት፣ ግድቡ በታችኛው የተፋሰስ አገሮች ላይ ሊኖረው የሚችለውን ጉልህ ተፅዕኖ ለመቀነስ ያስችላል የተባሉ ውይይቶችን ከግብፅና ከሱዳን ጋር ስታደርግ ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ለስምንት ዓመታት የግድቡን የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ የተመለከቱ ውይይቶች በተለያዩ ደረጃዎች ሲካሄዱ የቆዩ ቢሆንም፣ እነዚህ ውይይቶች እዚህ ግባ የሚባል ውጤት አምጥዋል ለማለት እንደሚያዳግት በርካቶችን ያስማማል፡፡ ድርድርና ውይይቱ ከግብ ሊደርስ ሲል ግብፅ በተደጋጋሚ ራሷን በማግለል ይኼን ያህል ጊዜ እንዲወስድና ፍሬ አልባ ምልልስ ብቻ እንዲሆን የበኩሏን ድርሻ እንደተጫወተች በተደጋጋሚ ስትወቅስ የቆየች ሲሆን፣ የግድቡ ድርድር በውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ብቻ ሳይታጠር ወደ ውኃ ክፍፍል የዘለቀ እንዲሆን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ እንደቆየችም ሲነገር ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በተደራዳሪዎቹ አማካይነት ሲገልጽ የቆየው፣ ለናይል ከ85 በመቶ በላይ አስተዋጽኦ የሚያደርገው የዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ግድብ በታችኛው የተፋሰስ አገሮች ላይ ጉልህ ተፅዕኖ እንደማያስከትል ነበር፡፡ በእኩልና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርሆዎች የተመራ ድርድር እንዲኖር እንደሚሠራ ሲያስታውቅም ቆይቷል፡፡ ግብፅም ይኼንን የኢትዮጵያን አቋም በቆይታ የተጋራች ይመስላል በማለት አስተያየት የሚሰጡ የመሰሉ ታዛቢዎችና ተንታኞች፣ ግድቡ መገንባት የለበትም ከሚለው የቀደመው አቋሟ በመለወጥ በውኃ መጠን ላይ ለመነጋገር መዘጋጀቷም የዚህ ማመላከቻ ነው ይላሉ፡፡

ይሁንና ግድቡ ከ12 እስከ 21 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ መያዝ የሚችለውን 74 ኪዩቢክ ሜትር ውኃ እንዲሞላ፣ እንዲሁም ከግድቡ በየዓመቱ 41 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ እንዲለቀቅልኝ ስትል ግብፅ ያቀረበችውን ጥያቄ የኢትዮጵያ መንግሥት አልተቀበለውም፡፡ ግድቡ ከአራት እስከ ሰባት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲሞላ፣ እንዲሁም ከግድቡ የሚለቀቀው ውኃም በዓመት ከ31 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር እንደማይበልጥ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ምክረ ሐሳብ በሁለቱ አገሮች መካከል አለመግባባት ፈጥሯል፡፡ ሱዳን በበኩሏ ግድቡ እንደሚጠቅማት በተደጋጋሚ ስትናገር የቆየች ቢሆንም፣ ሥጋቷ የግድቡ ጥንካሬ እንደሆነና ለዚህም ሥጋት እንዳይገባት በኢትዮጵያ መንግሥት ሳይንሳዊ ማረጋገጫ እንደተሰጣት ይታወቃል፡፡ በዚህም ሳቢያ በድርድሮቹ ወቅትም ሆነ በሌሎች መድረኮች ያላት አቋም ብሔራዊ ጥቅሟን ባገናዘበ መንገድ ከኢትዮጵያ ጋር የተጣጣመ እንደሆነ ሲገለጽም ቆይቷል፡፡

በግድቡ ግንባታ ወቅታዊ ሁኔታ፣ እንዲሁም በግድቡ ላይ እየተካሄደ ያለውን ድርድር በማስመልከት ከውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ጋር በመሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባለፈው ሳምንት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ‹‹ሱዳኖች ያላቸው አቋም አሁንም ግድቡ ይጠቅመናል የሚል ጠንካራ አቋም ነው፡፡ ነገር ግን ከራሳቸው ጉዳዮች ተነስተው የሚያነሷቸው ጥያቄዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ግድቡ በእነሱ ድንበር አቅራቢያ ስለተገነባ አንድ ነገር ቢሆን ቀድመው የሚጎዱት እነሱ ናቸውና የደኅንነት ጥያቄ አላቸው፡፡ ከውኃ አለቃቀም ጋርም በተያያዘ እንዲሁ፡፡ ነገር ግን ሱዳን የዓባይን ውኃ የመቆጣጠር ፍላጎት የላትም፡፡ የዓባይን ውኃ የመቆጣጠር ፍላጎት ያላት ግብፅ ናት፤›› ሱሉ ተናግረዋል፡፡

ስለሺ (ዶ/ር) ግን ግድቡ የሚሠራበት ቴክኖሎጂ የደኅንነት ሥጋት የሌለበትና ይኼም በጥናት የተረጋገጠ ስለሆነ፣ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ምንም ሥጋት ሊገባቸው እንደማይገባ ጠቁመዋል፡፡

ይሁንና ይኼ የግድብ ድርድር ያለ ስምምነት ስምንት ዓመታት አስቆጥሮ መጨረሻው ቅርብ አልመስል እያለ በሄደበት ወቅት፣ የግድቡ ድርድር የሦስቱ አገሮች ወይም የተፋሰሱ፣ ወይም የአፍሪካ ጉዳይ ብቻ ከመሆን አልፎ ዓለም አቀፍ ገጽታ እየያዘ መጥቷል፡፡ ይኼ እንዲሆን ያደረገው ክስተት ግድቡን በተመለከተ ሥጋት ገብቶኛል በማለት ግብፅ ለአሜሪካ ባቀረበችው የአደራድሩኝ ጥያቄ ጣልቃ የገቡት የአሜሪካ የግምጃ ቤት (ትሬዥሪ) ኃላፊ ስቲቨን ሞኑሽንና የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስ በታዛቢነት መሳተፋቸው ሲሆን፣ የታዛቢነት ሚናቸው ምን እንደሆነ በግልጽ ሳይታወቅ የሚና መለዋወጥ ሲታይም ነበር፡፡

በዚህም ሳቢያ ሥጋት የገባቸው ወገኖች አሜሪካ ለምን ጣልቃ ገባች? ይኼስ እ.ኤ.አ. በ2015 ከተፈረመው የመሮሆዎች መግለጫ (Declaration of Principles)  ያፈነገጠ አይደለም ወይ? ከሆነስ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንጂ ለእንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ዕውቀት የሌለው የግምጃ ቤት ኃላፊ ለምን ታዛቢ ተደረገ? በማለት ሲጠይቁ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በመጀመርያው ስብሰባ ከመሳተፉ አስቀድሞ፣ ይኼንን ጥያቄ በደብዳቤ ለአሜሪካ መንግሥት ማሳወቁን በወቅቱ ተናግሮ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ የአሜሪካን ታዛቢነትም ሆነ አደራዳሪነት ያልጠየቀች መሆኗን የገለጹት አቶ ገዱ፣ በአሜሪካና በዓለም ባንክ ታዛቢነት በሚካሄደው ድርድር ለመሳተፍ የፈቀደችው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረትና አገሪቱ ከአሜሪካ ጋር ባላት ወዳጅነት ምክንያት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በአሜሪካ ታዛቢነት የተደረገው ድርድር አገሮቹ በብዙ ጉዳዮች ላይ እንዲስማሙ ማድረጉን ያስታወቁት አቶ ገዱ፣ አሁንም ግን ከቴክኒክና ከሕግ አንፃር ገና ስምምነት ያልተደረሰባቸውና ንግግር ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም የአሜሪካና የዓለም ባንክ የሚና መዛነፍ ነበር ብለዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ አሜሪካኖቹ አንዴ ታዛቢ፣ አንዴ አቀላጣፊ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ አደራዳሪ እንደሆኑ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

ሆኖም ኢትዮጵያ ከግድቡ ድርድር ራሷን ማራቋንና በአሜሪካ ለመጨረሻ ጊዜ በተካሄደው ድርድር አለመሳተፏን ተከትሎ፣ ይኼ ዓለም አቀፍ ገጽታ የያዘው የዓባይ ውኃ ግድብ ምን ዓይነት አንድምታዎች (Implications) ይኖሩታል ሲሉ የሚጠይቁ በርካቶች ናቸው፡፡ ሐሙስ የካቲት 26 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው የዓረብ ሊግ ስብሰባ በግብፅ ካይሮ የተገኙ የዓረብ አገሮች ከሱዳን በስተቀር፣ በሙሉ ኢትዮጵያን የሚኮንን ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ ይኼም የዓረቡ ዓለም በድርድሩና በግድቡ ጉዳይ ከፍተኛ ሥፍራ እየያዘ መምጣቱን ያመላክታል ሲሉ ታዛቢዎች ይገልጻሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአገር ልማት ጥናት ኮሌጅ የክፍለ አገራዊና አካባቢያዊ ልማት ጥናት ማዕከል መምህር የሺጥላ ወንድሜነህ (ዶ/ር)፣ የዚህን ጉዳይ አንድምታ  በቅጡ ለመረዳት ወደኋላ መለስ ብሎ ማየት ያስፈልጋል በማለት እ.ኤ.አ. በ2010 የተፈረመውን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (Cooperation Frame Work Agreement) እና በ2015 በግብፅ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተፈረመውን የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት ይጠቅሳሉ፡፡

የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱ ከመፈረሙ አስቀድሞ በናይል ተፋሰስ አገሮች መካከል ሁሉን አቀፍ የሆነ ስምምነት ያልነበረ መሆኑን የሚጠቁሙት የሺጥላ (ዶ/ር)፣ እ.ኤ.አ. በ2010 የተፈረመው ስምምነት ግብፅ በዓባይ ውኃ ላይ የነበራትን የበላይነት የሚገዳደር ነበር ይላሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ እ.ኤ.አ. በ1929 እና በ1959 የተፈረሙት የዓባይ ውኃ ክፍፍል የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ውስጥ ተገፍተው የነበሩ የተቀሩት የናይል ተፋሰስ አገሮች የመጡበት፣ እንዲሁም የቅኝ ግዛት ስምምነትን ጥያቄ ውስጥ የከተተ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

‹‹በዓባይ ውኃ ዙሪያ የታዩ ለውጦች ከዚህ ስምምነት ይጀምራሉ፤›› በማለት ምልከታቸውን የሚያጋሩት የሺጥላ (ዶ/ር) ግብፅ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን ምንም እንኳን የህዳሴ ግድቡን የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ የተመለከተ ቢሆንም እ.ኤ.አ. በ2015 የፈረሙት የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት የቀደመውን መልካም ስምምነት ጥያቄ ውስጥ የከተተና ሌሎቹን የተፋሰስ አገሮች ያገለለ ነበር በማለት ይተቻሉ፡፡ ይኼም ስምምነት ከፍተኛ ድጋፍና ኃይል ከሆኗት የተፋሰስ አገሮች ኢትዮጵያ እንድትነጠል ማድረጉን፣ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የነበረው የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እንዳይተገበር እንቅፋት ነበር ይላሉ፡፡

ግብፆችም ኢትዮጵያን ከሌሎች የተፋሰሱ አገሮች በመነጠል ምክንያታዊ የሆኑ የሚመስሉ ጥያቄዎችን እያነሳች ጉዳዩን መስመር ስታስቀይር መቆየቷንና ይኼም በተወሰነ ደረጃ የተሳካላት ድርጊት እንደሆነ በማመላከት፣ በዚህ ሒደት ግን ግብፆች ቢያንስ እኩል ተጠቃሚነት የሚለውን መርህ እንዲቀበሉ የሆኑበትም ነበር ይላሉ፡፡ ሆኖም የህዳሴ ግድቡ በእነሱ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ያመጣል የሚለውን ለዓለም ማሳመን ችለዋል ሲሉም የሺጥላ (ዶ/ር) ያክላሉ፡፡

ከዚህ ሊስተካከል የሚችል ሥራ በኢትዮጵያ በኩል እንዳልተሠራ፣ የግብፅ ባለሙያዎችም ሆኑ ሳይንቲስቶች በተሰማሩበት ዘርፍ በሚያወጧቸው ጽሑፎች ያንን ሲያስተጋቡ፣ የኢትዮጵያ አጥኚዎች ከዚያ ጋር ሊወዳደር የሚችልና ግድቡ ለኢትዮጵያውያን ያለውን ጥቅምና በታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ላይ የጎላ ተፅዕኖ እንደማይኖረው የሚያሳይ ሥራ አላከናወኑም በማለት ይወቅሳሉ፡፡

ስለዚህም ግብፆች ግድቡ ጉልህ ጉዳት ከማድረስ ባለፈ በመካከለኛው ምሥራቅ የደኅንነት ሥጋት እንደሚሆን ለአሜሪካ ማሳመን በመቻላቸው፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጣልቃ እንዲገቡ አድርጓቸዋልም ሲሉ መምህሩ ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለዓመታት ለዘለቀው የእስራኤልና የፍልስጤም ጦርነትን መጨረሻ ያበጅለታል በማለት ያዘጋጁት የመካከለኛው ምሥራቅ የሰላም ዕቅድ ለመተግበር ግብፅ አጋዥ እጇን ስለዘረጋች፣ ይኼንን ለመጠቀም ፕሬዚዳንቱ ይፈልጋሉ ሲሉ ይተነትናሉ፡፡

ለዚህ ደግሞ የግብፅ የዓረቡ ዓለም መሪ ተደርጋ መወሰዷና ያላት ተቀባይነት ከፍተኛ በመሆኑ ዕድል ይሆናታል ይላሉ፡፡ ማሳያውም የፍልስጤም መንግሥት በፅኑ እየተቃወመው ያለውን የአሜሪካ መንግሥት የመካከለኛው ምሥራቅ የሰላም ዕቅድ፣ ሌሎች የዓረብ አገሮች ሲቃወሙት አለመታየቱ ነው ብለው፣ ስለዚህም ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ገጽታ በመያዝ የደኅንነት ሥጋትም ተደርጎ ቀርቧል ብለዋል፡፡

የዚህ አንዱ አንድምታ ግብፅ ጉዳዩን ዓለም አቀፍ ገጽታ በማስያዝ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደር መፈለጓን ነው የሚሉት የሺጥላ (ዶ/ር)፣ ይኼም ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገሮች እንዲሁም ከዓረቦች በመነጠል ለማዳከም ያለመ ነው በማለት ያመላክታሉ፡፡

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ግንኙነት ከዓረብ አገሮች፣ በተለይም ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር መመሥረቷንና እነሱም በኢትዮጵያና በቀጣናው ፍላጎቶች የራሳቸው ያሏቸው መሆኑን በማመልከት፣ ጫና መፍጠሩና መነጠሉ የተቀናጀ እንዲሆን የማድረግ ፍላጎት አለ ሲሉ የሺጥላ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡

ስለዚህም በዚህ ሒደት አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ኢትዮጵያ በጥንቃቄ ልትከተላቸው የሚገቡ አማራጮች ስላሉ፣ እነሱን ማገናዘብ ያሻል በማለት አማራጮችን ይጠቁማሉ፡፡

የመጀመርያው አማራጭ እ.ኤ.አ. በ2010 በተፈረመው የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት፣ ከኢትዮጵያ ጎን የነበሩትን የተፋሰሱ አገሮች የዚህ ድርድር አካል እንዲሆኑ ማድረግ ነው ይላሉ፡፡ አሁን ጉዳዩ ሌሎቹን የተፋሰስ አገሮች ያገለለ፣ እንዲሁም የግብፅና የኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻ እንዲመስል በመደረጉ ሌሎቹን የተፋሰስ አገሮች ማሳተፍ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚቻል በማመን፣ ነገር ግን መከፈል ያለበት ዋጋ ተከፍሎ ይኼንን ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ግብፅ ጉዳዩን ወደ ዓረብ ሊግ እንደወሰደችው ሁሉ፣ ኢትዮጵያም የአፍሪካ ኅብረት ተሳታፊ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋታል በማለት ያሳስባሉ፡፡

ሦስተኛው አማራጭ ደግሞ በሕዝብ ዲፕሎማሲ (Public Diplomacy) ላይ በደንብ መሥራት፣ የህደሴ ግድቡ የሚባለውን ያህል ጉዳት እንደማያስከትልና ለኢትዮጵያ አስፈላጊ መሆኑን ለተቀረው ዓለም ማሳወቅ የግድ ነው ይመክራሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የአሜሪካ ሕዝብን፣ ምሁራንን፣ የትምህርት ተቋማትን፣ እንዲሁም የሕግ አውጪውን አካል ለማሳመን (Lobby) መሥራት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ነገር ግን ይኼ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ፣ ጉዳዩን አሁን የያዙት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ስለሆኑና እሳቸው ዘንድ ድረስ ተፅዕኖ ማሳደር ይቻላል ወይ ከሚሉት ጉዳዮች አንፃር መታየት አለበት ይላሉ፡፡

ነገር ግን ይኼ የግብፅ ግፊት እዚህ መድረሱ መልካም ነው በማለት በጎ ጎን እንዳለው የሚናገሩት የሺጥላ (ዶ/ር)፣ የግድቡንና የዓባይን ጉዳይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመፍታት የግብፅን እጅ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ዞር በማድረግ የአገሪቱን ትኩረት በዴሞክራሲና በልማት ላይ ለማድረግ አስተዋጽኦ ያበረክታል ይላሉ፡፡ የግብፅ የቆየና ኢትዮጵያን ከ70 ዓመታት በላይ ሲፈታተናት የነበረው እንዳትረጋጋ የማድረግ የውጭ ፖሊሲዋ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቋጫ ይበጅለታል ሲሉም ያመላክታሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች ተመልካቾች ኢትዮጵያ የኃይል ሚዛኗን ለማስጠበቅ፣ ሌሎች ኃያላን አገሮችን ከጎኗ ለማሠለፍ መሥራት እንዳለባት፣ ለዚህም ሊረዱ ስለሚችሉ በተጤነ መንገድ ሩሲያና ቻይናን ማምጣት ነው ሲሉ ያክላሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ አገሮች የራሳቸውን ፍላጎት ይዘው ስለሚመጡ ያንን ሚዛን ማስጠበቅ ራሱን የቻለ ፈተና ሊሆን ይችላልም የሚሉ አልጠፉም፡፡

የሺጥላ (ዶ/ር) ግን ምንም እንኳን የዚህን ጉዳይ መቋጫ መተንበይ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ መንግሥትም መዘግየቱን ሊፈልገው ይችል ይሆናል ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡ ምናልባት ይኼንን ጉዳይ አገራዊ ፖለቲካዊ ተቀባይነት ለማግኘት ሊጠቅመው ይችል ይሆናል በማለት፡፡

ሆኖም አሁን አሜሪካ የምርጫ ወቅት ላይ ስለምትገኝ በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን የግድብ ውዝግብ የሚጠፋ ጊዜ ስለማይኖራት ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሚያደርጉትን ተፅዕኖ ማለሳለሳቸው አይቀርምና ጉዳዩ ተመልሶ ሊረግብ ይችላል የሚሉም አሉ፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -