Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግድ ባንክ የቀድሞ ፕሬዚዳንቱ ዳግም ተሹመውለታል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ላይ የተለያዩ የለውጥ ዕርምጃዎች እንደሚተገበሩ ሲገለጽና ይህንኑ ለመተግበር ከአንድ ዓመት ተኩል ጀምሮ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል፡፡

 ሪፎርሙ ይመለከታቸዋል ከተባሉ የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት አንዱ  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ በዚህ ተቋም ውስጥ የሪፎርም ጅማሬ የተደረገው የባንኩን አመራሮች በአዲስ በመተካት ሲሆን፣ በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥም የባንኩ ማኔጅመንት አባላት በአዲስ አመራሮች ተተክተዋል፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንትም በሌሎች ተተክተዋል፡፡ የቦርድ አባላትም ተለውጠዋል፡፡  

 ንግድ ባንክ እንዲህ ባለው መንገድ የጀመረው ሪፎርም የታሰበውን ያህል ለውጥ አልመጣም የሚሉ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል፡፡ ከጥቂት ወራት ወዲህም በባንኩ ውስጥ አዳዲስ ለውጦችን ለማድረግ እንቅስቃሴዎች መታየት ጀምረዋል፡፡ የቦርድ አባላትን ከመለወጥ ጀምሮ ወደ ማኔጅመንቱ የደረሱ ዕርምጃዎች ታይተዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመት ውስጥ ሦስት የቦርድ ሰብሳቢዎች ተፈራርቀውበታል፡፡ አዲስ ቦርድ አባላትም ተካተውበታል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊትም የቀድሞ የብሔራዊ ባንክ ገዥ፣ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ የንግድ ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው መሰየማቸው ተጠቃሽ ነው፡፡ ቦርዱን ዓመት ላልሞላ ጊዜ ሲመሩ የቆዩት የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ወደ ቦርድ አባልነት ዝቅ ተደርገው፣ ለአቶ ተክለ ወልድ ቦታቸውን አስረክበዋል፡፡ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ቦርዱን ሲመሩ የነበሩት የቀድሞው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው ነበሩ፡፡ እሳቸውም ቢሆኑ በቦርድ ሰብሳቢነት የሠሩት ዓመት ላልሞላ ጊዜ ነበር፡፡

ባለፉት ጥቂት ወራት ከተደረጉ ለውጦች መካከል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) የንግድ ባንክ ቦርድ አባል ሆነው መቀላቀላቸው ነው፡፡ ሌሎች አዳዲስ የቦርድ አባላት ተካተውበታል፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በንግድ ባንክ ቦርድ አባልነት እያገለገሉ ከሚገኙ የመንግሥት ሹማምንት መካከል፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሯ ወ/ሮ ደምቢቱ ሐምቢሳ፣ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንቱ አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አድማሱ ነበበ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪና የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ተደራዳሪው አቶ ማሞ እስምላለም፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገብረ መስቀል፣ የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ጉዳዮች አማካሪው አቶ ነብዩ ሳሙኤል ሲካተቱ፣ ከዘርፉ ጋር ባላቸው ግንኙነትና ተሞክሮ ማክሮ ኢኮኖሚስቱ እዮብ ተስፋዬ (ዶ/ር) በቦርድ አባልነት ንግድ ባንክን ሲመሩ የቆዩ ናቸው፡፡  

እንዲህ ያሉ ለውጦች ከተደረጉ በኋላ የባንኩ አካሄድ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ለማስቀመጥ የንግድ ባንክን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በመፈተሽ ለውሳኔ ማቅረብ ሌላኛው አካሄድ ነበር፡፡

ይህ ከተደረገ በኋላም ንግድ ባንክን በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የቆዩት አቶ ባጫ ጊና ኃላፊነታቸውን እንደሚለቁና በምትካቸው አዲስ ፕሬዚዳንት ለመሰየም መታሰቡን የሚጠቁሙ ፍንጮች መደመጥ ጀመሩ፡፡  

ብዙም ሳይቆይ አቶ ባጫ ተነስተው በምትካቸው አዲስ ፕሬዚዳንት ይሰየማል የሚለው ፍንጭ ጋሃድ ወጥቶ ስንብታቸው ይፋ ተደርጓል፡፡ ለአቶ ባጫ ስንብት ምክንያቱ ምን እንደሆነ በግልጽ ማወቅ ቢያዳግትም፣ በአምባሳደርነት መሾማቸው ተገልጿል፡፡ አቶ ባጫን ተክቶ የሚሠራ ኃላፊ የማፈላለጉ ሥራም ግን ውስጥ ውስጡን ሲካሄድ ቆይቷል፡፡፡

የካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. አቶ ባጫ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ በሴቶች ሠራተኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጠውን ሁለተኛ ቅርንጫፍ ለማስመረቅ በተገኙበት ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ቢያደርጉም፣ በዚሁ ዕለት ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ቢሮ የወጣው መግለጫ ግን የአቶ ባጫን የንግድ ባንክ ቆይታ ስንብት ያመላከተና ንግግራቸውም የመጨረሻው እንደነበር አመላክቷል፡፡ ከፕሬዚዳንቷ ቢሮ የወጣው መግለጫ ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎችን ጨምሮ በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነት ላይ የነበሩ 15 ባለሥልጣናት በአምባሳደርነት ስለመሾማቸው የሚገልጽ ነበር፡፡

የአምባሳደርነት ሹመት ከተሰጣቸው 15 ባለሥልጣናት አንዱ አቶ ባጫ በአምባሳደርነት መሾማቸው በሌላ አነጋገር ከኃላፊነት መልቀቃቸውን የሚያመለክት ነበር፡፡ ይህ ከተሰማ በኋላ የአገሪቱን ግዙፍ ባንክ የመምራት ኃላፊነት የሚረከበው ማነው? የሚለው ጥያቄ ሲብላላ ሰንብቷል፡፡ ለቦታው የሚሾሙት የባንኩ የውስጥ ሠራተኞች ስመሆናቸው አለያም ከውጭ የሚመጡ ይሆኑ እንደሆነ ለማወቅ ሲመሞከር፣ ብዙም ሳይቆይ በማግሥቱ ለቦታው የሚመደቡት ኃላፊ ከባንኩ ውጪ እንደሚመጡ ያመላከተ ነበር፡፡

ይህ ደግሞ የአቶ ባጫ ስንብት የድንገቴ እንዳልነበርና ነገሩ ቀድሞውንም ታስቦበት ዝግጅት ሲደረግበት የቆየ እንደነበር አመላክቷል፡፡ አዲሱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ማን እንደሚሆን ለማሳወቅ ብዙ ጊዜ አላስፈለገም፡፡ በአቶ ባጫ እግር የተተኩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ናቸው፡፡

የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ11 ዓመታት በላይ በፕሬዚዳንትነት ሲመሩት የቆዩት አቶ አቤ፣ ከየካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን ከአቶ ባጫ ኃላፊነቱን ተረክበዋል፡፡ ተሰናባችና ተተኪው ፕሬዚዳንቶች በጋራ ኬክ ቆርሰዋል፡፡ ከንግድ ባንክ ማኔጅመንት አባላትም ጋር የትውውቅ ጊዜ ነበራቸው፡፡

አቶ አቤ ከወጣትነታቸው ጀምሮ የተቀላቀሉትና በወጣትነት ዕድሜያቸውም የመሩትን ባንክ ዳግም የተቀላቀሉት የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማበርከት በመፈለግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ወደ ባንኩ በድጋሚ የመምጣታቸው ምክንያትም የባንኩን ሠራተኞች ከልብ በመውደዳቸውና ሠራተኛውም ለእሳቸው የነበረውን አክብሮትና ፍቅር በማስታወስ ጭምር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡  

አቶ አቤ የንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው መሰየማቸው በብዙዎች ዘንድ ያልተጠበቀ እንደሆነባቸው የሚጠቅሱ አካላት ከ12 ዓመታት በፊት ንግድ ባንክን ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩ በመሆናቸውና መልሰው ወደ ቀድሞ ቢሯቸው ይመጣሉ የሚለው በብዙዎች ዘንድ ከግምት ባለመግባቱ ነበር፡፡ ንግድ ባንክን በፈቃዳቸው ተሰናብተው ከወጡ በኋላ ወዲያውኑ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ የአቶ አቤ ሹመት ያልጠበቁት ለመሆኑ የሚያነሱ ሌሎች ደግሞ ምልከታቸውን በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከግል ባንክ ወደ መንግሥት ባንክ ከመሄድ ይልቅ ከመንግሥት ባንክ ወደ ግል ባንኮች መሄድ የተለመደው ክስተት ሆኖ በመቆየቱ ነው ይላሉ፡፡ በተለይም የመንግሥት ባንኮች የደመወዝ መጠን ከግሎች አኳያ ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑ ሌላው ተጠቃሽ ምክንያት ነበር፡፡ የመንግሥት ባንኮች ከግሎቹ አኳያ ከሁለት እስከ ሦስት እጥፍ ያነሰ እንደሚከፍሉ ይነገራል፡፡ አቶ አቤ ከምሥረታው ጀምሮ አሁን ለሚገኝበት ደረጃ ያበቁትን የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ተሰናብተው ንግድ ባንክን በድጋሚ ሊመሩ እየተዘጋጁ ነው፡፡ ይህ ዜና ለኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ማኅበረሰብም ያልተጠበቀ ሆኗል፡፡ አቶ አቤ ግን ወደ ቀደሞው ቢሯቸው ተመልሰዋል፡፡  

እንደ አቶ አቤ ሁሉ ተሰናባቹ አቶ ባጫም ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ወደ ንግድ ባንክ ሳይመጡ ይሠሩ የነበረው በኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ውስጥ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በወቅቱ የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ ቀደም ሲልም የአዋሽ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜም የአዋሽ ኢንሹራንስ ቦርድ አባል ነበሩ፡፡

አቶ አቤ ከግሉ ዘርፍ ወደ መንግሥታዊው ባንክ በመምጣት ፕሬዚዳንት በመሆን ሁለተኛው ሰው መሆናቸውን አሳይቷል፡፡ የአቶ አቤ ወደዚህ ኃላፊነት መምጣት አብሮነት የሚያያዝ ዓላማ ያለው ሲሆን፣ ባንኩ ያሉበትን ችግሮች የማስተካከል አቅም እንዳላቸው ታምኖባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ትልቅ ሥራ እንደሚጠብቃቸው ይታመናል፡፡ ባንኩን ሪፎርም የማድረግ ኃላፊነት እንደሚሰጣቸው ይጠበቃል፡፡ ከ20 ዓመታት በላይ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው በአብዛኛው በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በመሥራት የሚታወቁት አቶ አቤ፣ በኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ ውስጥ ቦርድ አባል ናቸው፡፡

አቶ አቤ ከባንክ ፕሬዚዳንትነታቸው በተጨማሪ 18ቱንም ባንኮች በአባልነት የያዘው የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ አሁን ከሚኖርባቸው ኃላፊነት አንፃር ይህንን ኃላፊነታቸው ሊያስረክቡ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡

 በንግድ ባንክ ላለፉት 25 ዓመታት ባንኩን በፕሬዚዳንትነት ከመሩት ውስጥ አቶ ጥላሁን ዓባይ፣ አቶ ዓባይነህ ገዛኸኝ፣ አቶ አቤ ሳኖ፣ አቶ በቃሉ ዘለቀ ይጠቀሳሉ፡፡ ባንኩን በቦርድ ሊቀመንበርነት ካገለገሉት ውስጥ ደግሞ አቶ መኮንን ማንያዘዋል፣ አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ አቶ በረከት ስምዖን፣ ይነገር ዶሴ (ዶ/ር)፣ አቶ አህመድ አብተው፣ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ይጠቀሳሉ፡፡ አሁን ደግሞ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ 77 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁኑ ወቅት ከ34 ሺሕ በላይ ሠራተኞች አሉት፡፡ እስከ 2012 የሒሳብ ዓመት አጋማሽ ድረስ ከታክስ በፊት 9.33 ቢሊዮን ብር ማትረፉ ይታወቃል፡፡ ባንኩ ከ23 ሚሊዮን በላይ አስቀማጮች አሉት፡፡ በመላ አገሪቱ ያለው የቅርንጫፎች ቁጥርም ከ1,560 በላይ ደርሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች