Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክበግድብ ውኃ አሞላል አመካኝቶ ዓባይን ለመብላት አንጉቶ

በግድብ ውኃ አሞላል አመካኝቶ ዓባይን ለመብላት አንጉቶ

ቀን:

ውብሸት ሙላት

በዚህ ጽሑፍ፣ ጥቁርና ነጭ ዓባይን በአንድነት “ናይል”፣ ባሮ አኮቦ፣ ዓባይና ተከዜን በጥቅሉ “ጥቁር ዓባይ” በሚል እንጠራለን፡፡ ዓባይ ስንል በህዳሴው ግድብ ገብቶ ወደ ሱዳን የሚፈሰውን የተለያዩ ገባር ወንዞች ተሰባስበው የፈጠሩትን ወንዝ ነው፡፡ በዚህ መልኩ መጥራት የተፈለገበት ዓላማ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተነሱት ጭብጦችን የተሻለ ግልጽ ለማድረግ እንዲረዳ ብቻ ነው፡፡

የህዳሴውን ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቅ በተመለከተ ግብፅና ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በድርድር ላይ ናቸው፡፡ ድርድሩ እየተደረገ የነበረው ደግሞ በዓለም ባንክና በአሜሪካ ፊት ነው፡፡ በታዛቢነትም ይሁን በአደራዳሪነት ብቻ ግልጽ ባልሆነ አቋም ተሳትፈዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ስለ ዓባይ ውኃ የዓለም ባንክ ሁልጊዜም ቢሆን ከግብፅ ባለነሰ ሊባል በሚችል መልኩ ወገንተኛ እንደሆነ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ አሜሪካም ብትሆን ግብፅ ከፍ ያለ ጂኦ ፖለቲካዊ ጥቅምና ፋይዳ ስላላት ከኢትዮጵያ ይልቅ ለእሷ ማዘንበሏ አይቀሬ ነው፡፡

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2015 ስለ ግድቡ ካርቱም ላይ ከተስማሙት ባፈነገጠ አካሄድ ግብፅ ብቻዋን አደራዳሪ መርጣ እንወያይ ስትል ኢትዮጵያም ምንም ሳታቅማማም የካርቱሙን ስምምነትም በመዘንጋት አሜን ብላ ተቀብላለች፡፡ ከዚያ ያለምንም ፋታ በሳምንታት ልዩነት እየተመላለሱ፣ ለጥናትም ሆነ ለማሰላሰልና ለመምከር ጊዜ ሳያገኙ ድርድሩ ቀጠለ፡፡ ምንም እንኳን ያለቀ ስምምነት ባይኖርም በረቂቅ ደረጃ እንዳሉ የተነገሩ መረጃዎች አሉ፡፡ በእርግጥ ዘግይቶም ቢሆን፣ ዋሽንግተን ላይ በሚደረገው ድርድር ኢትዮጵያ መሳተፍ እንደምታቆም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር) ይፋ አድርገዋል፡፡

ድርድሩ ዋሽንግተን ላይ ይቀጥልም አይቀጥለም የህዳሴው ግድብን የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ በሚመለከት የቀረበው ረቂቅ ሐሳብ አሁን ባሉበት ደረጃ የተወሰኑ ነጥቦችን በመውሰድ ሊያስከትሉ የሚችሉትን አንድምታ እንቃኛለን፡፡ ከእነዚህ መረጃዎች በጥቅሉና በግርድፉ መረዳት የሚቻለው ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ “ርትዓዊና ሚዛናዊ መርህ”ን (Equitable and Reasonable Utilization Principle) ከመከተል ይልቅ “ዓብይ (ጉልህ) ጉዳት ያለማድረስ መርህ”ን (No Significant Harm Principle) ወደ መቀበል እየተንደረደረች ይመስላል፡፡ በአንድ በኩል የህዳሴው ግድብ ውኃ የሚሞላበትን ወቅት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአየር ንብረትን መሠረት ያደረገ የውኃ አሞላልና አለቃቅን የሙጥኝ ተብሏል፡፡

በረቂቅነት የቀረበው ስምምነት፣ ከወቅት አንፃር ግድቡ የሚሞላው በክረምት እንዲሆን፣ እንዲሁም የሚሞላበትን የጊዜ ርዝማኔ ማራዘምን ይጠይቃል፡፡ ከአየር ንብረት ለውጥ አንፃር ደግሞ በኢትዮጵያ ድርቅ በሚከሠትበት ጊዜ የዓባይ ውኃ ስለሚቀንስ በግድቡ ከሚገባው የውኃ መጠን ምን ያህል መልቀቅ እንዳለባት የስምምነቱ አካል እንዲሆን ተፈልጓል፡፡ በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ ድርቅ ተከስቶ ወደ ሱዳንና ግብፅ የሚያልፈው ውኃ ስለሚቀንስ ወደ ግድቡ ከሚገባውም ቀድሞ በግድቡ ከተከማቸውም መልቀቅን ግዴታ የሚደርግ ድንጋጌ የስምምነቱ አካል እንዲሆን ተፈልጓል፡፡

ድርቅን ብያኔ ለመስጠት የተሞከረው፣ ወደ ግድቡ የሚገባው ዓመታዊ የውኃ መጠን 37 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ሲደርስ እንደሆነ፣ ከባድ ድርቅ ደግሞ አሁንም ወደ ግድቡ የሚገባው ውኃ 31 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር  ሲሆን እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የድርቁ ወቅት ከተራዘመም እንዲሁ ተጨማሪ ግዴታን በኢትዮጵያ መጣል ሌላው ዳርዳርታ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ወደ ግድቡ የሚገባውን 37 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር  ውኃ ምንም ሳታስቀር ከማሳለፍ ጀምሮ ድርቁ ከቀጠለ በግድቡ ካከማቸችው 40 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር  እንድትለቅም የስምምነቱ አካል እንዲሆን ተፈልጓል፡፡

አሁን ባለው መደበኛ የውኃ ፍሰት መጠን ወደ ግድቡ የሚገባው አማካይ የውኃ መጠን 49.5 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር  ሆኖ ሳለ፣ ከዚህ መጠን ላይ የድርቅ ማሳያ መስፈርቱ 37 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር  እንዲሆን ነው በአቦሰጥ የተመረጠው፡፡ 12 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ገደማ የሚሆን ውኃ በሙቀት መጨመር፣ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ጥቅም ላይ በማዋል ሊቀንስ ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ከግምት ሳይገቡ 37 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር  ውኃን እንደ የድርቅ መለኪያ አድርጎ ወደ ግድቡ የሚገባውን ውኃ ምንም ሳታስቀር እንድታሳልፍ መስማማት በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ ዓበይት/ጉልህ ድርሻ አለማድረስ ብቻ ሳይሆን “የራሷ አሮባት የሰው ታማስል ዓይነት” መርህን  መሆኑ ነው፡፡

በ1997 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ የፀደቀው “ከመጓጓዣ በስተቀር ዓለም አቀፍ የውኃ ተጋሪዎች ስምምነት”ም (The Convention on the Law of Non-Navigational Uses of International Watercourses) በአንቀጽ ስድስት ላይ ርትዓዊና ሚዛናዊ መርህ ተጨባጭ ለማድረግ አመላካቾችን በማስቀመጥ አገሮች ዓለም አቀፍ የውኃ ተፋሰስን በግዛታቸው ውስጥ እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው፣ እንዲሁም ሲጠቀሙም፣ ሲያለሙትም ሆነ ጥበቃ ሲያደርጉ በእዚህ መርህ መሠረት መሆን እንዳለበት በማሳሰብ ዘርዝሯል፡፡

እነዚህ አመላካቾች ከፍርድ ቤት ፊት ሲቀርቡ፣ በሕግ ሚዛን ላይ ሲቀመጡ ግርታን የሚፈጥሩ፣ አፍን ሞልቶ ትርጉማቸው እንዲህ ነው ለማለት አዳጋች መሆናቸውን የተለያዩ የዓለም አቀፍ ሕግ ምሑራን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ በአጭር ባጭሩ ለማቅረብ የተሞከረው፣ ድንበር ዘለል ወንዝን በጋራ በርትዓዊና ሚዛናዊ ሁኔታ ለመገልገል የተሻሉ አመላካቾች ስለሆኑ፣ ኢትዮጵያም የህዳሴው ግድብን የውኃ አሞላልና አለቃቅ በሚመለከት ከግብፅና ሱዳን ጋር በምትደራደርበት ጊዜ ድርድሩ ውጤት ወደ ስምምነት ከመቀየሩ በፊት ብሔራዊ ጥቅም፣ አሁን ባይሆን እንኳን መጭውን ትውልድ የሚጎዱ እንዳይሆኑ ማስታወስ ያሉብንን ነጥቦች በወፍ በረርና የ1997ን ዓለም አቀፍ ስምምነት እንዲሁም የሔልስንኪ ደንብን ምርኩዝ በማድረግ ብልጭታ ማሳየት ነው፡፡ በመሆኑም ጠቅለል ብለው በሰባት ተከፍለው ቀርበዋል፡፡

አንድ

ከአመላካቾቹ የመጀመሪያው የመልክዓ ምድር፣ ሃይድሮግራፊ፣ የውኃው መጠንን (ሃይድሮሎጂ) የሚመለከት ነው፡፡ የውኃው ምንጭ፣ መጠንና የመሳሰሉትን ታሳቢ ስለሚያደርግ 86  ከመቶ ውኃ የምታዋጣው ኢትዮጵያ ስለሆነች ውኃ በማዋጣት ምንም አስተዋጽኦ የሌላቸው ግብፅም ትሁን ሱዳን ከኢትዮጵያ ያነሰ ነጥብ ነው የሚያገኙት፡፡ ለኢትዮጵያ የተሻለ አመላካች ነው ማለት ይቻላል፡፡

መልክዓ ምድራዊ ሽፋኑን ከግምት ሲገባ፣ በዓባይ ተፋሰስ ጋር ትስስር ያለው የደቡብ ሱዳንና ሱዳን መሬት በስፋት ከኢትዮጵያም ከግብፅም ይልቃል፡፡ በተለይ በምታዋጣው የውኃ መጠን ኢትዮጵያ ርትዓዊና ሚዛናዊ የሆነ ግልጋሎት በማገኘት ረገድ ከሁሉም የናይል ተፋሰስ አገሮች ተደምረው ከሚኖራቸው ድርሻ ከፍ እንደሚል ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የባሮ አኮቦና የተከዜን ውኃ ሳይጨምር 37 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር  እንደዝቅተኛ መለኪያ በመውሰድ ይህን ያህል ውኃ ህዳሴው ግድብ ውስጥ ማቆር ይቅርና ሰተት ብሎ እንዲያልፍ መስማማት በተዘዋዋሪ የ1929ኙንም ሆነ የ1959ኙን የግብፅና ሱዳን የውኃ ክፍፍል ውል ዕውቅና መስጠትም ማጽናትና ማጽደቅም ነው የሚሆነው፡፡

 ከባሮ አኮቦ 14 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር፣ ከተከዜ 10 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር  ውኃ ለዓባይ ስለሚገበር የእነዚህ ግማሽ እንኳን ይህ 37 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር  ላይ ከተደመሩ 49 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር  ውኃ እንዳለ ማሳለፍ ግድ ይሆናል፡፡ ለዚያውም ከጥቁር ዓባይ ውኃ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ለሱዳንና ለግብፅ እንዳለ መለገስን ወዶና ፈቅዶ መስማማት እንደማለት መሆኑ ነው፡፡

ይሄ መቼም በርትዓዊና ሚዛናዊ ግልጋሎት መለኪያ ይቅርና ዓበይት ጉዳት ያለማድረስ መርህንም አልፎ፣ ልሙጡን ጉዳት ያለማድረስ መርህን (No Harm Rule) ወደ መቀበል የተቃረበ ነው፡፡

ለዚያውም በድርቅ ወቅት በሚሆንበት ጊዜ ይህን ያህል ውኃ ለመልቀቅ መስማማት “የራሷ አሮባት የሰው ታማስል” እንዲሉ በድርቅ ምክንያት ወደ ግድቡ የሚደርሰውን እንጥፍጣፊም ሳታስቀር ውኃ ለመስጠት፣ ከዚህ መጠን በሚያንስበት ጊዜ ደግሞ ቀድማ በግድቡ ያቆረችውን እንድትሰጥ ውል ማድረግ ነው ትርፉ፡፡       

የአየር ጠባይና የአካባቢው ሌሎች ተፈጥሯዊ ሁኔታዎችን ከግምት አስገብቶ በውኃው መገልገል ሌላኛው አመላካች ነው፡፡ በናይል ተፋሰስ ከሚተሳሰሩ አገሮች መካከል በርሃማና የገጸ ምድር ውኃ ባለመኖር ቀዳሚዋ ግብፅ ስትሆን፣ ድርቅን ጨምሮ የሕዝብ ህልውናን ከሚፈታተኑ ክስተቶች አንፃር ኢትዮጵያም የዓባይን ውኃ መጠቀም አማራጭ የለውም፡፡

ምናልባት የታላላቅ ሐይቆች አገሮች ከግብፅና ከኢትዮጵያ አኳያ የተሻለ ተስማሚ የአየር ጠባይና የተፈጥሮ ሁኔታዎች አላቸው፡፡ በመሆኑም ሁለቱም አገሮች በከፍተኛ ሁኔታ ከናይል የመጠቀም ቅድምና ይኖራቸዋል ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ግን በድርቅ ወቅት ሳይቀር በዚህ መጠን ግብፅ ዓባይን መበዝበዝ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ የበይ ተመልካች እንድትሆን እንዳያደርግ መጠንቀቅ ያሻል፡፡ 

ሁለት

በወንዙ ተፋሰስ አገሮች የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ፍላጎቶች ያሉበት ሁኔታ ሁለተኛው መለኪያ ነው፡፡ አንድ ሰንበት ያለ የዓለም ምግብ ድርጅት (FAO) ጥናት እንደሚያሳየው ለግብፅ በዓመት ቢያንስ 57.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር፣ ለሱዳን (ደቡብ ሱዳንንም ጨምሮ) 38.5 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር  ውኃ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ አገሮች ዋናው የውኃ ምንጫቸው ናይል በመሆኑ፣ በዚህ ድርጀት ጥናት መሠረት ከሙሉው የናይል ውኃ በላይ ይፈልጋሉ ማለት ነው፡፡

የሌሎቹ ተፋሰሶች ግን 30 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር እንኳን እንደማይደርስ በዚህ ድርጅት ጥናት ይገልጻል፡፡ የጥናቱን አስተማማኝነትና ተገቢነት የሚያጠያይቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዚህ ጥናት መሠረት ካየነው ሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ካላቸው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፍላጎቶች አንፃር የናይልን ውኃ ሙሉ በሙሉ ያህል ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡

ይሁን እንጂ፣ የታችኛውና የላይኛው ተፋሰስ አገሮችም፣ በተለይ ኢትዮጵያ፣ አሁን ያሉበት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታ ናይልን ሳይጠቀሙ እንደ አገር መቀጠል አዳጋች ስለሆነ፣ ምንም እንኳን በዚህ መሥፈርት ሁለቱ አገሮች የተሻለ ነጥብ ሊያገኙ ይችሉ ካልሆነ በስተቀር የዓለም የምግብ ድርጅት ያጠናውን ያህል ውኃ ከናይል ማግኘት ከህልም አልፎ ቅዠት ነው፡፡ ግብፅ የህዳሴው ግድብን በድርቅ ወቅት ውኃ የሚለቀቅበትን ሁኔታ አስታክካ ይህን ፍላጎቷን ለማሳካት እየጣረች ይመስላል፡፡

ሦስት

የወንዙን ሀብት በመጠቀም የሚተዳደረው የሕዝብ ብዛት ድግሞ ሌላኛው አመላካች ነው፡፡ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የግብፅ ሕዝብ ሕልውናው በናይል ውኃ ላይ ሙጥኝ ያለ ነው፡፡ በእርግጥ የተፋሰሱ አገሮች ሕዝብም ፐርሰንቱ ይለያይ እንጂ በወንዙ ተፋሰስ ውስጥ የሚኖረው የሕዝብ ብዛት ቀላል አይደለም፡፡ በዓባይ ወንዝ ጠገግ የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጠቅላላው 45 በመቶ ገደማ ነው፡፡ የግብፅ ሕዝብ እንደሚጨምረው ሁሉ የኢትዮጵያም ስለሚጨምር መስኖና ሌሎች ዘዴዎችን መጠቀም ካልተቻለ ዝናብ እየጠበቁ ብቻ በሚደረግ እርሻ መወሰን፣ ሕዝብን ለርሃብና ድርቅ ስጦታ ማበርከት ነው ትርፉ፡፡ ወደ ህዳሴው ግድብ ከሚገባው ብቻ ከ37 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር  ውኃ ድርሻ ለማጽናት መፈለግም ሆነ መስማማት በመጭው ትውልድ ላይ መፍረድ ነው የሚሆነው፡፡ በዓባይ ተፋሰስ የሚኖረው ኢትዮጵያዊም ውኃውን የመገልገል ዕድሉን በዚህ ደረጃ ማጣበብ ያስከትላል፡፡

አራት

በአንዱ አገር የሚከናወነው በሌላው አገር ላይ የሚያስከትለው ውጤትና ተፅዕኖ መጠንን መሠረት በማድረግ ሲታይ፣ በላይኛው ተፋሰስ አገሮች የሚከናወኑ የመስኖና ሌሎች የውኃውን መጠን የሚቀንሱ ፕሮጀክቶች በታችኛው ተፋሰስ ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ወደ ግዛታቸው የሚደርሰውን ውኃ ሙሉ በሙሉ የሚጠቀሙ ከሆነ ነው፡፡ የኃይል ማመንጨት ሥራ ውኃን በቋሚነት እምብዛም ስለማይቀንስ ተፅዕኖው ያነሰ ነው፡፡ ግድብ ለመሙላትና በድርቅ ወቅት ግድቡ ስለሚጎድል አልፎ የሚሄደው መጠን መቀነሱ ግን አይቀርም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በታችኛው ተፋሰስ አገሮችም ተግባር ተመልሶ የላይኞቹን የሚጎዳበት አጋጣሚም አለ፡፡ ለምሳሌ ግብፅ የገነባችው የአስዋን ግድብ ግዙፍ በመሆኑና በርሃ ላይ በመሆኑ በትነት የሚባክነው የውኃ መጠን ከ10 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ይበልጣል፡፡ ልትጠቀምበት ከምትችለው ውስጥ ይህን ያህል እያባከነች ነው፡፡ የላይኞቹ ተፋሰስ አገሮችም እንዳይጠቀሙበት እንቅፋት በመሆን ተፅዕኖ መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡

በመሆኑም በላይኛውም ይሁን በታችኛው ተፋሰስ የሚሠሩት የሚያሳድሩት የፊትና የኋሊዮሽ ተፅዕኖ ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ግብፅና ሱዳን ግድቦቻቸውንም ይሁን ግዙፍ የመስኖ ፕሮጀክቶቻቸውን ሲያከናውኑ ይቅርና፣ ውል ሲያደርጉ እንኳን ለብቻቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ በምታከናውናቸው ፕሮጀክቶች ግን ድርድርን ይሻሉ፡፡ ርትዓዊና ሚዛናዊ ግልጋሎት ላይ የሚደረሰው በጋራ በመሥራትና በትብብር እንጂ በግብፅና በሱዳን መንገድ ሊሆን አይችል፡፡

አምስት

በወቅቱም ሆነ ለወደፊት ሊፈጸሙ የታቀዱ ግልጋሎቶችና ፕሮጀክቶችም በመለኪያነት ይወሰዳሉ፡፡ ናይልን በመጠቀም ረገድ ግብፅ ወደር የላትም፡፡ ከግብፅ የምትቀጥለው ሱዳን ናት፡፡ ኢትዮጵያ ጥቁር ዓባይን በዘመናዊ መንገድ ለመጠቀም ማቀድ ከጀመረች ወደ 100 ዓመት ሊጠጋት ነው፡፡ እንግሊዝ ከኢትዮጵያ ጋር በመስማማት በጣና ሐይቅ ጎን ትልቅ የውኃ ማጠራቀሚያ በመገንባት ሱዳንና ግብፅ ውስጥ በስፋት ጥጥ ለማምረት ባቀደችበት ወቅት ነው፡፡ ከሚሠራው ግድብ የሚወጣውን ውኃ የምትጠቀመው እንግሊዝ ስትሆን ኢትዮጵያ ዓመታዊ ኪራይና ሌሎች ክፍያዎችን በማግኘት ውኃ ለመሸጥ ነበር ድርድሩ፡፡ በበርካታ ምክንያቶች ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል፡፡

ሁለተኛውና ከፍተኛ ጥቅም ሊያስገኝ ይችል የነበረው ጥናት እ.አ.አ. ከ1958 ጀምሮ ለስድስት ዓመታት ያህል በአሜሪካው የእርሻ መሬት ማልሚያ ቢሮ (Bureau of Reclamation) መሪነት የተከናወነው ጥናት መሠረት “የጥቁር ዓባይ የውኃ ሀብትና መሬት” (Land and Water Resources of the Blue Nile) በሚል ርዕስ የያዘው ባለ 314 ገጽ ሰነድ ላይ የቀረበው ነው፡፡ በቀዝቃዛው ጦርነት ምክንያት አሜሪካ ከግብፅ ይልቅ ኢትዮጵያ በተሻለ ሁኔታ ወዳጅ ነበረችና ትብብሯንም አለነፈገችም ነበር፡፡ በዚህ ጥናት መሠረት አራት ዋና ዋና ግድቦችን ጨምሮ ሌሎች 29 የመስኖና ኤሌክትሪክ ማመንጫዎች እንዲሠሩ ታቅዶ ነበር፡፡ ይሁንና በእዚህ ዕቅድ መሠረት በወቅቱ ሊገነባ የቻለው የፊንጫ የኃይል ማመንጫ ብቻ ነው፡፡

በደርግም ዘመን ይሁን ከእዚያ በኋላ በቁጥር ሲታዩ ዝቅተኛ የማይባል ግድቦችን ለመስኖና ለኤሌክትሪክ ማመንጫ ለመገንባት ዕቅዶች እንደነበሩ ይፋ ተደርጎ ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ኢትዮጵያ ጥቁር ዓባይን በመጠቀም ልታለማና ልትገለገልበት ከምትችለው መጠን አንፃር እየተገለገለችበት ያለው ከአንድ ከመቶ የማይዘል ነው፡፡ የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ ከፍ የሚል ቢሆንም፡፡ በመሆኑም ወቅታዊውን ግልጋሎት ከግምት ማስገባቱ ቅድምና የሚሰጠው ከሆነ መሥፈርቱ ግብፅና ሱዳንን የበለጠ መጥቀሙ ግልጽ ነው፡፡

ከወቅታዊው ግልጋሎት ባለፈ፣ ወደፊት ሊፈጸሙ የታቀዱ ፕሮጀክቶችን አብሮ መመልከቱ ተገቢነት ስላለው ወቅታዊውንም የወደፊቱንም በአንድነት ጎን ለጎን በመሥፈርትነትም በመደራደሪያነትም ማቅረብ አስፈላጊ ነው፡፡

ስድስት

የወንዙን ውኃ ለመጠበቅና ለመንከባከብ የሚያስከትለው ወጭን ከግምት ሊገባ እንደሚችል ተገልጿል፡፡ የሁለቱም ዓባዮች ውኃ መጠኑ እንዳይቀንስ ወይም እንዲሻሻል ለማድረግ የተለያዩ የእንክብካቤ ሥራዎች የሚያስፈልጉት በላይኛው ተፋሰስ አገሮች ዘንድ ነው፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የውኃው መጠን እንዳያንስ ማድረግ ግድ ነው፡፡ በዚህ አንፃር የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ሚና ያነሰ ስለሚሆን በናይል ላይ ለሚደረጉ በርትዓዊና ሚዛናዊ ግልጋሎት መነጽር የሚደረጉ ስምምነቶች ይህ መለኪያ ለኢትዮጵያ የተሻለ ይጠቅማል፡፡  

 

ሰባት

ሌላኛው ጠቋሚ፣ ወንዙ የሚሰጠውን ግልጋሎት በሌላ አማራጭ ሊተካ የሚችል መሆኑ የሚለው ነው፡፡

ከናይል ተጋሪ አገሮች መካከል የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ተጨማሪ ወንዞች ስላሏቸውና የዝናብ ውኃ ስለሚያገኙ አማራጭነት የውኃ ሀብት እንዳላቸው ይታያሉ፡፡ ግብፅና ሱዳን ደግሞ እነዚህ አማራጮች የሏቸውም፡፡ ይሁን እንጂ፣ አማራጭ ሲባል ወንዝና ዝናብ መኖር ብቻ ሊሆን አይችልም፡፡ ግብፅ የከርሰ ምድር ውኃን፣ ከሜድትራኒያንና ከቀይ ባህር ውኃ መጠቀምን በአማራጭነት ሊወሰድ ይችላል፡፡ ጨውን በማስወገድ ለመስኖና ለሌሎች ግልጋሎቶች ማዋል፣ እንዲሁም ከናይል ውኃ ከእጥፍ በላይ የሚበልጥና ለአትላንቲክ ውቅያኖስ ቀለብ የሚሆኑ ወንዞች ካሏቸው እንደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ኒጀር የመሳሰሉ አገሮች ውኃን በመግዛት መጠቀምን በአማራጭነት ሊያዩት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ የላይኛው ተፋሰስ አገሮችም በመደራደሪያነት ሊያቀርቡትም ይገባል፡፡ በአጭሩ፣ አማራጭ ውኃ ምንጭ የሚለው በጠባቡ ብቻ መታየት የለበትም፡፡

ምን ያህል ውኃ ለማን?

ከናይል ተጋሪ አገሮች ሳያካትት፣ አብዛኛዎቹ በድንበር ዘለል ወንዞች የተሳሰሩ አገሮች ውኃን በጋራ ለማስተዳደርና ለመገልገል ስምምነት አድርገዋል፡፡ ውኃውንም እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው የሚያስተዳድር የጋራ ተቋም ያላቸውም አሉ፡፡ ናይልን በሚመለከት ግን ግብፅና ሱዳን ለብቻቸው መጠቀምን እንጂ መጋራትንና መተባበርን ባለመሻታቸው ስምምነትም ተቋምም ሊኖር አልቻለም፡፡ እርግጥ ነው የተለያዩ ጥረቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡

 የናይል ውኃ ለብቻቸው ለመካፈል ስምምነት ሲያደርጉ የኖሩት ሁለቱ አገሮች ብቻ ቢሆኑም በተለይ ጥቁር ዓባይን በሚመለከት ማለትም ባሮ-አኮቦን ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳንና ግብፅ፣ ዓባይን ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ፣ ተከዜ አትባራን ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንና ግብፅ በጋራ የሚጠቀሙበትን ማዕቀፍ ማዘጋጀትና ለዚህም መተባበር አማራጭ የለውም፡፡

በህዳሴው ግድብ አልፎ የሚሄደውን ውኃ፣ ዓመታዊ መጠኑ 37 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር  ከሆነ ኢትዮጵያ በቀጥታ እንድታሳልፍ ስምምነት ማድረግ፣ ለሱዳንና ለግብፅ ዝቅተኛው ድርሻቸው ቢያንስ ይኼን ያህል እንደሆነ ዕውቅና መስጠት ነው፡፡ ይኼ የውኃ መጠን ዓመታዊ መጠናቸው 14 እና 10 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር  ገደማ የሆኑትን የባሮ አኮቦና የተከዜን ውኃ ሳይጨምር መሆኑ ነው፡፡ ወደ ህዳሴው ግድብ የሚገባው የውኃ መጠን በአማካይ 49 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር  ገደማ ነው፡፡ 37 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር  ወደ ግድቡ ከሚገባው የዓባይ ውኃ ለሁለት ሦስተኛው በላይ ነው፡፡ ለዚያውም ሱዳንና የግብፅ ድርሻ ይህ እንዲሆን ሳይሆን በድርቅ ወቅት የሚፈልጉት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ስምምነት ማድረግ፣ ድርቅ በማይሆንበት ጊዜ ከእዚህ በላይ ድርሻ እንዳላቸው ዕውቅና መስጠት ሆኖ መቆጠሩ አይቀርም፡፡

የህዳሴው ግድብን መሙላት አንድ ነገር ነው፡፡ አንድ ጊዜ ከሞላ በኋላ በሌላ ጊዜ መለቀቅ ያለበትን ውኃ ለመወሰን መስማማት፣ እግረ መንገዱንና በግልጽ ባይጻፍም ቢያንስ የኢትዮጵያን በአንድ በኩል፣ የሱዳንና የግብፅን በሌላ በኩል የውኃ ድርሻ የሚያመላከት ነው፡፡

ከጥቁር ዓባይ ላይ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን (ደቡብ ሱዳንንም ጨምሮ) እና ግብፅ ምን ያህል ውኃ ያግኙ የሚለውን ምክረ ሐሳብ ያቀረቡ ባሉሙያዎች አሉ፡፡ ዊቲንግተንና ማክከሌላንድ የተባሉ ምሑራን የግብፅንና የሱዳንን (ደቡብ ሱዳንንም ጨምረው) መልክአ ምድራዊና የአየር ንብረት ሁኔታ፣ በናይል ላይ የተንጠለጠሉ መሆናቸውን፣ አማራጭ የላቸውም በሚሉና በሌሎች ምክንያቶች መነሻነት ሦስቱ አገሮች ከጥቁር ዓባይ ውኃ ግብፅ 65 በመቶ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ እያንዳንዳቸው 17.5 በመቶ እንድያገኙ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

ኢሊየን ዳርቢ የሚባሉ ሌላ ምሑር በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለናይል 86 ከመቶ ውኃ ማዋጣቷንና የኢትዮጵያዊያንን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት፣ ሱዳንና ግብፅም ያለ ናይል መኖር አዳጋች (እንደውም እንደማይቻላቸው) በማተት፣ የኢትዮጵያ ድርሻ 44 ከመቶ፣ የግብፅ 29 ከመቶና ሱዳን (ሁለቱም) 27 በመቶ እንዲሆን “የናይል ወንዝ ተፋሰስ” (Nile River Basin) በሚል እ.አ.አ. በ2005 ባሳተሙት መጽሐፍ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

ጴጥሮስ ጄ.ገበቶ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ምሑር በበኩላቸው፣ “No More Thirst: The Citizens of the Nile” በሚል ርዕስ እ.አ.አ. በ2010 አቆጣጠር ባሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ በርካታ ምክንያቶችን በማስቀመጥ እንደገለጹት ኢትዮጵያና ግብፅ እያንዳንዳቸው 40 በመቶ፣ ሱዳን (ሁለቱም) ደግሞ 20 በመቶ እንዲሆን ነው፡፡

ከላይ የቀረቡት የጥቁር ዓባይን ውኃ ማከፋፈያ ቀመር እንዳለ ሆኖ፣ ናይልን በብቸኝነት መጠቀም የሚታሰብ ባለመሆኑና የተሻለው መፍትሔ ርትዓዊና ሚዛናዊ የውኃ ግልጋሎት መርህን መከተል ነው፡፡ ስለሆነም፣ በሔልንስኪ ደንብ እና በ1997ቱ ዓለም አቀፍ ስምምነት ላይ የተዘረዘሩትና ሌሎች አመላካቾችንም ከግምት በማስገባት በናይል ውኃ ለመጠቀም መስማማት ነው፡፡ ለመስማማት ደግሞ በቅንነት መተባበር ከናይል ተጋሪ አገሮች የሚጠበቅ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡

ሱዳንና ግብፅ በ1929ኙ እና በ1959ኙ የሁለትዮሽ ስምምነታቸው ላይ በተምኔት ተንጠልጥለው፣ እነዚህ ላይ የሙጥኝ ብለው የሚመጣ ስምምነት አይኖርም፡፡ በተለይ ግብፅ የጋራ ተቋም ለመፍጠር የሚያስችል የመተባበሪያ የስምምነት ማዕቀፉን (Cooperative Framework Agreement) ባለመፈረም አሻፈረኝ በማለት በቀጠለችበት ሁኔታ፣ ካርቱም ላይ እ.አ.አ. በ2015 የተደረገውን ስምምነት ወደ ጎን በመተው ግብፅ በዓለም ባንክና በአሜሪካ ፊት እንደራደር የሚል ጥሪ ለኢትዮጵያ ስታቀርብ ሰተት ብሎ በመግባት አሁን የተፈጠረው ዓይነት ቅርቃር ውስጥ ከቶናል፡፡ ድርድሩ የትና በማን ፊት ይቀጥል፣ ዋሽንግተን ላይ የቀረበው የህዳሴው ግድብ ውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ረቂቅ ስምምነት ከቴክኒካዊ ጉዳዮች ባለፈ ወደፊት የሚጎትተውን ሕጋዊ መዘዝ በጥልቀት ማጤን ግድ ነው፡፡

አዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው wuobishett@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...