Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየለንደን ግማሽ ማራቶንን ክብረ ወሰን የሰበረው ቀነኒሳ በለንደን ማራቶን ይጠበቃል

የለንደን ግማሽ ማራቶንን ክብረ ወሰን የሰበረው ቀነኒሳ በለንደን ማራቶን ይጠበቃል

ቀን:

ውድድሩ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሊሰረዝ ይችላል ተብሏል

የሦስት ጊዜ የኦሊምፒክ ሻምፒዮኑ ቀነኒሳ በቀለ በለንደን ግማሽ ማራቶን 1፡00፡22 በማጠናቀቅ በሞ ፋራህ ተይዞ የነበረውን የቦትውን ክብረ ወሰን ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ‹‹ቫይታሊቲ ቢግ›› በሚል የሚታወቀው የለንደን ግማሽ ማራቶን የርቀት ክብረ ወሰን ባለፈው ዓመት እንግሊዛዊው ሞ ፋራህ 1፡01፡40 ተይዞ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ሞ ፋራ በዚህ ውድድር ላይ እንደሚሳተፍ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም በጤና ምክንያት ሳይወዳደር መቅረቱ ተገልጿል፡፡

ባለፈው እሑድ የካቲት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በለንደን ቫይታሊቲ ቢግ ግማሽ ማራቶን ድል የተቀዳጀው ቀነኒሳ፣ በሚያዝያ ወር ለሚያደርገው የለንደን ማራቶን ውድድር ከወዲሁ ከፍተኛ ግምት እንዲቸረው አስችሎታል፡፡

ምንም እንኳን ውድድሩ የጎዳና ላይ ፈርጥ በሆነው ኤሊዩድ ኪፕቾጌ ጋር ከፍተኛ ፉክክር ቢጠብቀውም፣ ቀነኒሳ ግን በቂ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ መናገሩ ፉክክሩን ተጠባቂ አድርጎታል፡፡

የዓለማችን ፈጣን አትሌቶች መካከል የሚደረገው የለንደን ማራቶን ፍጥጫ የበርካታ ሚዲያዎችን ቀልብ መሳቡ እየተነገረ ይገኛል፡፡ በተለይ ኬንያዊ ኤሊዩድ ኪፕቾጌ በአወዛጋቢው የናይኪ ጫማ 42 ኪሎ ሜትርን ከሁለት ሰዓት በታች (ምንም እንኳ በዓለም አቀፉ ደረጃ ባይመዘገብም) ከገባ በኋላ የዓለም ትኩረትን መሳብ ችሏል፡፡

በአንፃሩም ቀነኒሳ በቀለም በበርሊን ማራቶን 2፡01፡41 ያጠናቀቀበት ሰዓት በቀጣይ የሚደረገውን የለንደን ማራቶን ውድድር ተጠባቂ ያደርገዋል፡፡ በረዥም ርቀት በርካታ ድሎችን ማሳካት የቻለው ቀነኒሳ በቀለ፣ በመም (ትራክ) ላይ የነበረውን አይበገሬነት ወዲያውኑ በጎዳና ላይ ለማስቀጠል በጤና ምክንያት ተገድቦ ቆይቷል፡፡ ቀነኒሳ ለዓመታት ከውድድሮች ርቆ የነበረ ቢሆንም፣ ከጊዜ በኋላ ግን ከአገሩ ልጆች ጋር ልምምድ ማድረግ መጀመሩንና ይታወቃል፡፡ በአሠልጣኝ ሐጂ አብዴሎ ከፍተኛ ዕርዳታ እየተደረገለት ስለመሆኑም ተደምጧል፡፡

ኬኒያዊው ኪፕቾጌም ምንም እንኳ በመም ውድድሮች የቀነኒሳን ያህል ገዝፎ መውጣት የቻለ ገድል ባይኖረውም፣ ካደረጋቸው ዘጠኝ ማራቶኖች በስምንቱ ወርቅ ማምጣት መቻሉ ትልቅ ግምት እንዲሰጠው ማድረጉ አልቀረም፡፡ ከእነዚህም ድሎች ውስጥ አራቱን ማለትም እ.ኤ.አ. በ2015፣ 2016፣ 2018 እና 2019 የለንደን ማራቶንን በበላይነት አጠናቋል፡፡ ቀነኒሳ በአንፃሩ በ2016 በነበረው ተሳትፎ የነሐስ ሜዳሊያ እንዲሁም በ2017 የብር ሜዳሊያ ማስመዝገብ ችሏል፡፡

ሁለቱ ከዋክብት በለንደን ማራቶን የናይኪ ቬፕር ፍላይ ጫማን ተጫምተው እንደሚወዳደሩ ይጠበቃል፡፡

በጫማው ላይ የተነሳውን ውዝግብ የሁለቱ አትሌቶች የወራት ዝግጅትና የጎዳና ላይ የበላይነት ፍጥጫ በሁሉም ስፖርት አፍሪቃውያን ዘንድ የሚጠበቅ ነው፡፡ ዳሩ ግን የ2020 የለንደን ማራቶን ላይከናወን ይችላል የሚሉ ዜናዎች መደመጥ ጀምሯል፡፡ በበርካታ አውሮፓ አገሮች እየተስፋፉ የመጣው የኮሮና ቫይረስ ለውድድሩ መሰረዝ ምክንያት ሊሆን ይችላል እየተባለ ነው፡፡

የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ማክሰኞ የካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የተወሰኑ የአገሪቷ ዜጎች ላይ ምልክቱ መታየቱንና ሕዝቡም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ያደርግ ዘንድ ጠበቅ ያለ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተመልካች እንዳለው የሚነገርለት የለንደን ማራቶን መንግሥት መሰረዝ እንዳለበት የሕክምና ባለሙያ የሆነው ማት ሃንኮክ በተለይ ለቢቢሲ ብሬክፋስት አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ይኼ መረጃ እስከተጠናቀቀበት ድረስ በአገሪቱ 51 ሰዎች ላይ የቫይረሱ ምልክቱ መታየቱ ተዘግቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...