በህዳሴ ግድቡ ላይ ለተነሳው ውዝግብ መፍትሔው ከመደራደርና ከመስማማት ውጪ አማራጭ እንደሌለ መንግሥት አስታወቀ፡፡ መንግሥት ይኼንን ያስታወቀው በህዳሴ ግድቡ የድርድር ሒደት ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁንና ከረታ ዓለሙ (አምባሳደር) ጋር በመሆን ማክሰኞ የካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በአሜሪካና በዓለም ባንክ ‹‹ታዛቢነት›› ሲካሄድ ከቆየው ከሱዳንና ከግብፅ ጋር የሚደረገው የህዳሴ ግድብ ውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ድርድር ራሷን ማግለሏን አስመልክቶ ምላሽ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹መፍትሔው መደራደርና መስማማት ነው፡፡ ከግብፅ የሚሰጠው መግለጫ ለእነሱም ለእኛም አይጠቅምም፡፡ ዛቻ ምንም ጥቅም የለውም፤›› ብለው፣ ‹‹በራሳችን ንብረት በሌላ ግፊት የሚሆን ነገር የለም፤›› ሲሉ የመንግሥትን አቋም አስታውቀዋል፡፡
የዓባይ ግድብ ምንም እንኳን በራስ ድንበርና በራስ ሀብት እየተገነባ ያለ ፕሮጀክት ቢሆንም፣ ድንበር አቋራጭ ወንዝ ላይ የሚገነባ ከመሆኑና ከግድቡ ግዝፈት የተነሳ ግብፅና ሱዳን በገባቸው ሥጋት ሳቢያ ወደ ድርድር መገባቱን የጠቆሙት አቶ ገዱ፣ ይኼንን ሥጋት ለማስቀረት ድርድር ማድረግ ወሳኝ ስለነበር አሁንም እየተካሄደ ያለው ድርድር በዚህ መንፈስ ነው ብለዋል፡፡
የሱዳን አቋም አሁንም ድረስ ግድቡ ይጠቅመናል የሚል እንደሆነና የሱዳን አቋም እንደተለሳለሰ ተደርጎ የሚቀርበው ልክ አይደለም ያሉት አቶ ገዱ፣ ሱዳን ያላት ሥጋት የግድቡ ደኅንነትና የውኃ አለቃቀቅ ብቻ ስለሆነ ይኼንን ደግሞ ተረጋግጦላቸዋል ብለዋል፡፡
‹‹ሱዳን የዓባይን ውኃ የመቆጣጠር ፍላጎት የላትም፣ የዓባይን ውኃ የመቆጣጠር ግልጽ ፍላጎት ያላት ግብፅ ናት፤›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ስለዚህም በግብፅና በ‹‹ታዛቢነት›› የገባቸው አሜሪካ ዘንድ ድርድሩን በጥድፊያ የመቋጨት ፍላጎትና ‹‹የማጣደፍ ሁኔታ›› መኖሩን የተረዳው የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን፣ በጉዳዩ ላይ ከሚነሱ ጥያቄዎች ክብደት አኳያ መታየት ስላለበት ኢትዮጵያ ልዩነት እንዳላትና ይኼንንም አሳውቃ ከድርድሩ እንደወጣች ተናግረዋል፡፡ በድርድሩ ልዩነቶችን ለማቀራረብ የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትርና የዓለም ባንክ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር ያስረዱት አቶ ገዱ፣ ‹‹ነገር ግን ሕግ አዘጋጅቶ የማቅረብ ፍላጎት ስላየን ልክ አይደለም ብለናል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹የዓባይን የውኃ ሀብት የመጠቀም መብታችን ሉዓላዊ መብት ነው፤›› ያሉት ደግሞ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ‹‹ያንን ማንም ሊጋፋ አይችልም፤›› ብለዋል፡፡
በዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው የህዳሴ ግድብ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ የሚመራ ስለሆነ የደኅንነት ሥጋትም የለበትም ያሉት ስለሺ (ዶ/ር)፣ ግድቡን በተመለከተ በሚደረጉ ድርድሮች ወደፊት የኢትጵያን የመጠቀም መብት የሚጎዱ የሕግ ማዕቀፎች እንዲኖሩ አይፈለግም ብለዋል፡፡ ነገር ግን በግብፅ እ.ኤ.አ. በነሐሴ 2019 የቀረበው ሐሳብ ይኼንን ያመለክታል ብለው፣ ‹‹ድርድሩ የውኃ ክፍፍል እንዳይሆን ጥንቃቄ እያደረግን ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በግድቡ ድርድር ‹‹በታዛቢነት›› የገባችውን አሜሪካ አቋም የሚያስወስዳት ምንም ነገር የለም ያሉት ሚኒስትሩ፣ ሦስቱ አገሮች ሊፈቱት ይችላሉ ብለዋል፡፡ ‹‹የሚያጋጭና ወደ ሌላ ነገር የሚያስገባ ነገር የለም፡፡ ይኼ እርባና ቢስ አመክንዮ ነው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚታሰብ አይደለም ሌላ ምክንያት ከሌለ በስተቀር፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
ከስምምነት ሳይደረስ ግድቡ ውኃ መሞላት የለበትም ተብሎ በአሜሪካ የወጣው መግለጫ ዲፕሎማሲያዊ አይደለም በማለት የተቹት አቶ ገዱ በበኩላቸው፣ ‹‹ትክክል ነው ብለን አናምንም፡፡ ይኼንን አገለላጽ ራሳቸው ያስተካክላሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡
አሜሪካ በራሷ የውኃ ሀብት ላይ ያላደረገችውን ኢትዮጵያ እንድታደርግ መግፋት ትክክል አይደለም ካሉ በኋላ፣ በመጨረሻው የአሜሪካ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ያልተገኙት የአሜሪካ የሚና መዛነፍ እንዳለ ስላጤኑ መሆኑን አክለዋል፡፡
ለህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልና አለቃቀል መመርያና ደንብ ላይ ድርድር የሚደረግ መሆኑን ያስታወሱት ረታ (አምባሳደር) በበኩላቸው፣ አሁን ከስምምነት ያልተደረሰባቸውና ድርድር እየተደረገባቸው ያሉ ጉዳዮች አምስት ናቸው ሲሉ ዘርዝረዋል፡፡
አንደኛው የአፈጻጸም ወሰን ሲሆን፣ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባውን የህዳሴ ግድብን ብቻ የተመለከተ ድርድር እንደሆነና የውኃ ክፍፍልንም ሆነ ካሁን ቀደም ያሉ የስምምነት ሰነዶችን የማይመለከት መሆኑ እንዲካተት ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሁለተኛው አሞላልና አለቃቀቁን የሚመለከት ሲሆን፣ መቼና ምን ያህል ውኃ ይለቀቃል የሚለውን የሚገዛ ነጥብ ነው፡፡ ሦስተኛው ነጥብ የመረጃ ልውውጥ እንደሆነና ምን፣ መቼ፣ ለማንና በምን አግባብ የሚሉ ጉዳዮችን ያቀፈ ነው፡፡
አራተኛው ነጥብ የክርክር አፈታትን የሚመለከት እንደሆነ ያመለከቱት ረታ (አምባሳደር)፣ ኢትዮጵያ በተለመደ የዲፕሎማሲያዊ መስመር ይፈታ ስትል ግብፅ የተለየ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥ የግልግል ተቋም ይቋቋም የሚለውን አቋሟን ለማስታረቅ የሚደረግ የውይይት ነጥብ ነው ብለዋል፡፡
አምስተኛው ስምምነቱ በተፈጻሚነት የሚቆይበትን ጊዜ የሚዳኝ መሆኑን፣ ኢትዮጵያ ሦስት ዓመት እንዲሆን ወይም ከአሥር ዓመት ሳይበልጥ በየጊዜው የሚሻሻል እንደሆነም ሐሳብ አቅርባለች ሲሉ አምባሳደሩ አስረድተዋል፡፡