የተበላሸ ብድር መጠኑ ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ነው
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከሚሰጠው ብድር 85 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍንበት የነበረው የግል ባንኮች የ27 በመቶ የቦንድ ግዥ መመርያ መነሳት፣ ሌሎች የፋይናንስ አማራጮችን እንዲያፈላልግ እያስገደደው መሆኑን ገለጸ፡፡ የቀድሞ የባንኩ የብድር አሰጣጥና አስተዳደር በርካታ ችግሮች የነበሩበት እንደሆነም አስታወቀ፡፡
በወቅታዊው የባንኩ ቁመናና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሐሙስ የካቲት 19 ቀን 2012 ዓ.ም. በተሰጠው መግለጫ፣ በአሁኑ ወቅት የ27 በመቶ የቦንድ ግዥ መመርያ መቋረጡ ዋነኛ የፋይናንስ ምንጩን እንዲያጣ መደረጉ ተገልጿል፡፡ ሆኖም ይህንን ቀድሞ በመረዳት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሌሎች የፋይናንስ ምንጮችን ለመጠቀም የሚያስችለውን ጥናት አስጠንቶ፣ ለመንግሥት በማቅረብ ውሳኔ እየጠበቀ መሆኑን አስረድቷል፡፡
ከግል ባንኮች በ27 በመቶ የቦንድ ግዥ መመርያ መሠረት ተሰብስቦ በብሔራዊ ባንክ በኩል ለልማት ባንክ የተሰጠው 52 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ያስታወሱት፣ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ልማት ባንክ ሌላ የፋይናንስ አማራጭ እንዲፈልግ ተወስኗል ብለዋል፡፡ መመርያው ከዚህ በኋላ የማይቀጥል ቢሆንም፣ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ግን አሠራሩ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል፡፡ ሆኖም ከቦንድ የሚያገኘው ፋይናንስ በመቋረጡ አዳዲስ የገቢ ምንጮችን ለማግኘት ጥናት መደረጉን፣ አሁን ሥራ ላይ ባዋለው የባንኩ የአምስት ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድና አሁን እየተተገበረ ባለው ሪፎርም ውስጥ ተካትቶ እንዲሠራበት ይደረጋል ብለዋል፡፡
ፋይናንስ ለማሰባሰብ ከሚከናወኑ ሥራዎች ውስጥ አንዱ፣ ባንኩ ከሰጠው ብድር በማስመለስ ለብሔራዊ ባንክ መክፈል እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡ የተረፈውን ደግሞ በማበደር የፋይናንስ አቅሙን ከፍ ማድረግ መታሰቡን ከፕሬዚዳንቱ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ሌላው ከውጭ አጋሮች ጋር በመሥራት ፋይናንስ ለማግኘት መታቀዱንም አመልክተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በባንኩ ባለፈው ዓመት የነበረውን የ40 በመቶ የተበላሸ የብድር መጠን በ2012 ዓ.ም. ግማሽ የሒሳብ ዓመት ወደ 34 በመቶ ዝቅ እያደረገ መሆኑ ቢገለጽም፣ አሁንም በተበላሸ የብድር መጠኑ ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚደርስ ታውቋል፡፡ ባንኩ የተበላሸ ብድርን በማስመለስ ባደረገው ጥረት በ2012 ዓ.ም. የሒሳብ ዓመት የተለያዩ ሥራዎችን በማከናወን 202 ሚሊዮን ብር ማስመለስ ቢችልም፣ አሁንም የተበላሸ ብድር መጠኑ ከፍተኛ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ባንኩ ከነበረበት የብድር አሰጣጥና አስተዳደር ጋር ተያይዞ በነበረበት ችግር ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በተበላሸ ብድር ክምችት ውስጥ እንዲገባ ምክንያት መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህንን በተበላሸ ብድር ውስጥ የሚገኝ ገንዘብ ለማስመለስ ባለፉት አንድ ዓመት ተኩል ውስጥ የተለያዩ ጥረቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ባንኩን እዚህ ደረጃ ያደረሱ አካላትን ለሕግ ከማቅረብ አንፃር ተጨባጭ ሥራ አለመከናወኑ እየተነገረ ቢሆንም፣ አቶ ኃይለየሱስ ግን የባንኩን ገንዘብ ለማስመለስ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡ ዕዳ ያልከፈሉ ተበዳሪዎችን ለሕግ የማቅረብ ሲሠራ መቆየቱን፣ በአሁኑ ወቅት ተበዳሪዎች ጥለው የጠፉትን ንብረት ጭምር ማሰባሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ በዋስትና የተያዘውን ንብረት ማሰባሰብ፣ መሬትም ከሆነ ወደ ሦስተኛ ወገን እንዳይተላለፍ ከሚያስተዳድሩ የክልል የመሬት አስተዳደሮች ጋር በመነጋገር እየተሠራ እንደሆነ ከአቶ ኃይለየሱስ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ባንኩ ገንዘብ ለማስመለስ ብዙ ፈተናዎች ያሉበት ቢሆንም፣ ጥረቱን መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡ በተለይ በዝናብ ለሚለሙ የእርሻ ኢንቨስትመንቶች ብድር ከወሰዱ ተበዳሪዎች ውስጥ፣ 171 የሚሆኑት ብድር የወሰዱበትን ኢንቨስትመንታቸው ጥለው መጥፋታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
በባንኩ አሠራር አሁን ጥለው የጠፉትን መረጃ መስጠት ባይቻልም፣ በሕጉ መሠረት እነሱን እያፈላለገ መሆኑንና መረጃዎች ተሰብስበው በመጠናቀቃቸው ለሕግ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ረገድ መረጃ ማሰባሰብና የማጠናከር ሥራው ተጠናቅቋል ያሉት አቶ ኃይለየሱስ በፍትሐ ብሔር ሕግ ለመጠየቅ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት በመግለጫቸው የባንኩ የብድር አሰጣጥና አስተዳደር ከፍተኛ ችግር የነበረበት እንደነበር በተደረገ ግምገማ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የባንኩ የብድር አሰጣጥ ችግር እንደነበረበት በማስታወስ፣ ለተበላሸ የብድር አስተዋጽኦ ማድረጉን ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡
አቶ ኃይለየሱስ ከብድር አሰጣጡ ጋር የጠቀሱት ሌላው ችግር፣ ባለሥልጣናት ሳይቀሩ እጃቸውን ያስገቡ የነበረ መሆኑን ነው፡፡ በጥቅሉ ሲታይ የባንኩ ሠራተኞች፣ ተበዳሪ ግለሰቦችና ሦስተኛ አካላት በብድር አሰጣጡ ውስጥ እጃቸው የነበረ በመሆኑ ይህንን በማጣራት ዕርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡ እስካሁን በተደረገው ማጣራት ችግር የተገኘባቸው ዘጠኝ ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ መወሰዱን ገልጸው፣ ብድራቸውን ባለመክፈል የጠፉት ደግሞ ዝርዝር የምርመራ ሒደቱ በመጠናቀቁ ይኸው በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ተብሏል፡፡
ቀድሞ በነበረው አሠራር በተለይ ለውጭ ኢንቨስትመንት ይሰጥ የነበረው ማበረታቻ የተለጠጠና በርካታ ክፍተቶች እንደነበሩበት የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፣ እንዲህ ያሉ ክፍተቶች አሁን እየተስተካከሉ ነው ብለዋል፡፡ ቀድሞ በነበረው አሠራር የውጭ ኩባንያዎች አሮጌ ማሽን ጭምር እንዲያስገቡ መደረጉ፣ በርካታ የውጭ ኩባንያዎች ያለባቸውን ብድር እንዳይከፍሉና ጥለው እየጠፉ ማገዙ ተገልጿል፡፡
በተለይ እንደ ጋምቤላ ባሉ ቦታዎች ለእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰጠው ብድር ብዙ ችግር እንደነበረበት በሚመለከት፣ ‹‹አሁን ባለን መረጃና በደረስንበት አግባብ ባንኩ ተበዳሪዎችን የተመለከተ ችግር ነበረበት፤›› ብለዋል፡፡ በዘርፉ ቢሰማሩ ልምዱ አላቸው ወይ የሚለውን ከማየት ይልቅ፣ የእርሻ መሬት ይዘው የሚጠበቅባቸውን መዋጮ ስላመጡ ብቻ ከየት እንዳመጡና ምንጩ ምን እንደሆነ ባልተገመተበት ሁኔታ አብዛኛው ብድር በመፈቀዱና በመሰጠቱ፣ ከተፈቀደ በኋላም ከባንኩ ሠራተኞችና በመመሳጠር፣ ከዕቃ አቅራቢዎች ጋር በመመሳጠር ከባንኩ ብድሩ እንዲወጣ መደረጉን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም እንዲህ ያሉትን መረጃዎች በመለየትና በማጥራት በ71 ፕሮጀክቶች ላይ ልዩ ምርመራ እያካሄዱ መሆኑን፣ በዚህ መሠረት ለሕዝብ ገንዘብ ብክነት ምክንያት የሆኑና የተሳተፉ አካላት ከላይ እስከ ታች ሁሉም አስተዳደራዊና ሕጋዊ ዕርምጃ ይወሰድባቸዋል ብለዋል፡፡
እስካሁን ባንኩን ለዚህ ያበቁ አካላትን ለሕግ የማቅረቡ ሥራ ለምን ዘገየ ለሚለው ጥያቄም ፕሬዚዳንቱ በሰጡት ምላሽ ጉዳዩ ውስብስብ በመሆኑ መረጃው ተሰባስቦ ለማደራጀት ጊዜ በመውሰዱ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹አሁን ግን ይህንን ምርመራ በማጠናቀቃችን ሕዝብ እንዲያውቀው ይደረጋል፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡