Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በዱባይ የተሽከርካሪ ዘይት ማምረቻ ድርጅት የገዙ ባለሀብት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የነዳጅና የተሽከርካሪ ቅባቶችን በማቅረብ ንግድ ሥራ ላይ መሰማራት ለአገሬው ተወላጅ የተከለከለና ለዓመታትም በዚሁ አግባብ ሲመራ ቆይቶ ነበር፡፡ በመሆኑም የውጭ ኩባንያዎች ብቻ ለአገር ውስጥ የሚውለውን የነዳጅ ፍጆታ በማከፋፈልና በመቸርቸር ተሰማርተውበት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ይሁን እንጂ አገር በቀል ኩባንያዎችና ግለሰቦችም በነዳጅና በነዳጅ ውጤቶች ማከፋፈል ሥራ ላይ መሳተፍ እንዲችሉ ከተፈቀደ 15 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት በተገኘው መረጃ መሠረት በዘርፉ 26 ኩባንያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 21 ያህሉ አገር በቀል ኩባንያዎችና ግለሰቦች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያውያን ከተቋቋሙ የነዳጅ ኩባንያዎች አንዱ ጄአር ፔትሮሊየም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ይጠቀሳል፡፡

ጄአር ፔትሮሊየም ሥራ የጀመረበት ሦስተኛ ዓመት ላይ ይገኛል፡፡ ምሥረታውን በማስታወስ፣ ከኩባንያው ጋር ከሚሠሩ አከፋፋዮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ባለፈው ቅዳሜ፣ መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በነዳጅ ዘርፍ ኩባንየው ስለሚጫወተው ሚና ብሎም የዘርፉን የግብይት ሥርዓት ለማዘመን እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ የኩባንያው የግብይት ባለሙያዎችም አብረው የሚሠሩ ቸርቻሪና አከፋፋዮች ጋር ዘመናዊ የንግድ አሠራር ሥርዓትን እንዲከተሉ የሚያስችሉ ዘዴዎችን በመቅረፅ እየተገበሩ ነው፡፡

በዱባይ የተሽከርካሪ ዘይት ማምረቻ ድርጅት የገዙ ባለሀብት

የኩባንያው መሥራችና ባለቤት ወይዘሪት ደስታ ካሴ፣ ይህንኑ የኩባንያቸውን ራዕይ በመድረኩ ያብራሩ ሲሆን፣ ከኩባንያው ጋር አብረው የሚሠሩ አካላት ላነሷቸው ጥያቄዎችም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ጄአር ፔትሮሊየም በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባና በሌሎችም ከተሞች 22 የነዳጅ ማደያዎችን ገንብቷል፡፡ የገበያ ተደራሽነቱን እያስፋፋ መምጣቱን የገለጹት የድርጅቱ ባለቤት፣ አሁን ለተደረሰበት ደረጃ ለመብቃት በርካታ ውጣ ውረድ ማለፍ እንዳስፈለገ ገልጸዋል፡፡ አብረውት የሚሠሩ ድርጅቶችና አከፋፋዮች የነዳጅ እጥረት እያጋጠማቸው እንደሚገኝ ጠይቀው ነበር፡፡ የአቅርቦት እጥረቱ ጄአር ከሚደርሰው የነዳጅ ኮታ ምክንያት እንደሚከሰት ጠቅሰዋል፡፡

አብረዋቸው በሥራ ከሚሳተፉ አካላት ‹‹ብርቱዋ›› የተባሉት ወይዘሪት ደስታ፣ ወደ ሥራው እንዴት እንደገቡ፣ ውስብሰብ ችግሮችን አልፈው አሁን ለሚገኙበት ደረጃ መብቃታቸው የጥረታቸውንና አይበገሬነታቸውን ያሳየ ስኬት ተብሎላቸዋል፡፡ ወይዘሪት ደስታ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ወደዚህ ንግድ ሥራ ገብቶ ውጤታማ መሆን ፈተና ቢኖረውም በሒደት ፈተናውን ሁሉ ለመወጣት ችለዋል፡፡ ስለአጀማመራቸው ሲገልጹም፣ ከአሥር ዓመታት በላይ በአሜሪካ ኑሯቸው ያፈሩትን ጥሪት ቋጥረው ወደ አገር ቤት በመመለስ በትውልድ ሥፍራቸው በጎንደር ነበር ሥራ የጀመሩት፡፡ የወላጆቻቸውን ነዳጅ ማደያ በመረከብ ሥራውን ተቀላቀሉ፡፡ ቀስ በቀስም እንደ ኦይል ሊቢያ ካሉ የነዳጅ ድርቶች ጋር በመሆን የነዳጅ ማደያ ሥራውን ወደ ባህር ዳርም በማዳረስ ንግዱን ማስፋፋት ተያያዙት፡፡ በአዲስ አበባና በሞጆ ተጨማሪ ማደያዎችን ገንብተው ለአራት ዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ባለሦስት ኮከብ ሆቴል በጎንደር መገንባታቸውንም ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ ትኩረታቸው የነዳጁ ሥራው ላይ ስለነበር፣ የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን በመግዛት ቢዝነሱን ይበልጥ አጠናከሩት፡፡ የነዳጅ ማመላለስ ሥራውን የጀመሩት በአንድ ተሽከርካሪ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ላይ 40 ተሽከርካሪዎች እንዳሏቸው ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመትም የተሽከርካሪዎቹ ብዛት ወደ 50 ከፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በዚህ ያልተገደቡት ወይዘሪት ደስታ፣ የራሳቸውን የነዳጅ ድርጅት ማቋቋም እንዳለባቸውን በመወሰን መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡

ሆኖም የራሳቸውን የነዳጅ ማከፋፈያ ድርጅት ለማቋቋም በተነሱ ጊዜ፣ የመጀመርያው ፈተና መሬት ማግኘት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በሚፈልጉት አካባቢ መሥሪያ ቦታ ማግኘት ባይችሉም፣ በአፋር ክልል የነዳጅ ማከማቻ ዴፖ ለመገንባት የሚያስችላቸውን ቦታ አገኙ፡፡ በዚህም ህልማቸውን ዕውን የሚሆንበት መንገድ ከፈተ፡፡ እንዲህ ባለው ቢዝነስ ላይ ለመሰማራት የነዳጅ ማከማቻ ዴፖ መገንባት ከመሥፈርቶቹ አንዱ ስለነበር ከባቲ ከተማ 12 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ቡርቃ በተባለች የአፋር ክልል ከተማ ውስጥ 40 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ በማግኘታቸው፣ በዚሁ ቦታ ላይ ዴፖ ገንብተው ሁለት የነዳጅ ማደያዎችን በማቋቋም ሥራውን ጀመሩ፡፡ ብዙ ወጪና ድካም እንዳስከተለባቸው፣ መብራትና ውኃ አለመኖሩም ሥራውን ፈታኝ እንዳደረገባቸው ገልጸዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግንባታዎቹን በተቀመጠው መሥፈርት መሠረት አጠናቀው የብቃት ማረጋገጫ በማግኘት በሁለቱ ማደያዎች ሥራውን ለመጀመር በቅተዋል፡፡

 ኩባንያቸው በ100 ሚሊዮን ብር ካፒታል ሥራ ቢጀምርም፣ የዴፖና የማደያ ግንባታው ከዚህም በላይ ወጪ ጠይቋል ይላሉ፡፡ ሌሎችም ወጪ የሚጠይቁ ሥራዎች በማጋጠማቸውና ኩባንያቸውን ለማስፋት በመነሳታቸው፣ ከአቢሲኒያ ባንክ 110 ሚሊዮን ብር ብድር ጠይቀው አቅማቸውን እንዳጠናከሩ ወይዘሪት ደስታ ጠቅሰዋል፡፡  

በጎንደር በአንድ የነዳጅ ማደያ የተጀመረው ሥራ አሁን ላይ 22 ማደያዎችን አስከትሏል፡፡ ጎን ለጎን የተሽከርካሪ ዘይት ምርቶችን ወደማቅረቡ በመሸጋገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ገበያው መግባትና ተቀባነት ያገኘ ምርት ማስመጣት እንደተቻለ የሚገልጹት ወይዘሪት ደስታ፣ ሽያጩን ለማስፋፋት ሲፈለግ ግን አሁንም እንቅፋቶች አጋጥመዋል ይላሉ፡፡ ዘይት የሚያቀርው ድርጅት እየዘገየ የገበያውን ፍላጎት እንደሚጠበቀው ልክ ማሟላት ባለማስቻሉ ነበር፡፡ ይህንን ለመቀየር ወይዘሪት ደስታ ባሳለፉት ውሳኔ የኩባንያቸውን የወደፊት አቅጣጫ ይበልጥ አቃንተዋል፡፡

ወደ ዱባይ በማቅናት ዘይቱን ሲያቀርብላቸው ከነበረው ሚዛን ኦይል ከተሰኘ ኩባንያ ጋር ተደራድረው በዚያው በዱባይ የሚገኘውን የዘይት ማምረቻ ድርጅት መግዛት ችለዋል፡፡ በወቅቱ ሚዛን ኦይልን ለመግዛት ከፍተኛ ገንዘብ ሊጠይቃቸው እንደሚችል ቢገምቱም፣ የአጋጣሚ ሆነና የኩባንያው ባለንብረት ቀድመው ለሽያጭ ካቀረቡት ዋጋ ቀንሰው ለመሸጥ በመስማማታቸው፣ ጄአር ፔትሮሊየም በዱባይ የራሱን የዘይት ማምረቻ ተቋም ዕውን አደረገ፡፡ ከወይዘሪት ደስታ ለመረዳት እንደተቻለው  ለሚዛን ኦይል ግዥ ሰባት ሚሊዮን ድርሃም ወይም ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል፡፡

ይህ ግዥ ከተፈጸመ መንፈቅ ቢያልፍም፣ ሕጋዊ የባለቤትነት ዝውውሩን ለመጨረስ ሦስት ወራት ከወሰደ ሒደት በኋላ ጄአር በአሁኑ ወቅት የተሽከርካሪ ዘይቶችን በተለያየ መጠን በራሱ አምርቶና አሽጎ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት የሚችልበትን አቅም ፈጥሮለታል፡፡ ወይዘሪት ደስታ እንደሚሉት፣ የዘይት ማምረቻው ለኢትዮጵያ ገበያ ብቻም ሳይሆን፣ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ምርቶቹን ለማዳረስ አስችሎታል፡፡ ከፋብሪካው ባሻገር በዱባይ የዘይት መሸጫ መደብር በመክፈት ጭምር ጄአር እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ ቀድሞም ቢሆን የዘይት ማምረቻውን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመትከል ሐሳብ የነበራቸው ወይዘሪት ደስታ፣ ይህንን ሐሳባቸውን ለማሳካት በይችሉም በዱባይ የዘይት ማምረቻ መግዛት መቻላቸው ግን ጥቅሙ ይበልጥ እንዳየለ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ የመጀመርያው ጠቀሜታ ለዘይት ማምረቻ የሚውለው ሙሉ ጥሬ ዕቃ እዚያው መገኘቱ ነው፡፡ የዚህ ሥራ ወጪ አሁንም በርካታ መሆኑ አልቀረም፡፡ በዶላር የሚከፈላቸው ሠራተኞች ያሉት በመሆኑና በዱባዩ ኩባንያ ሥር ለሚተዳደሩ ሠራተኞች የሚውለው የወር ደመወዝ 100 ሺሕ ዶላር እንደሚጠጋ፣ ይህ ዓይነቱ አሠራር ወጪውን እንዳናረው በምሳሌነት ተጠቅሷል፡፡ ይህም ይባል እንጂ በዓመት ከ20 እስከ 25 ሚሊዮን ዶላር ሽያጭ ያስመዘግባል፡፡

‹‹ፋብሪካው የራሳችንን ምርት የምናስመጣበት ነው፡፡ በጣም ያምራል፡፡ የራስህን ምርት አስመጥተህ እዚህ ለቤትህ ስትሸጠው እንዴት ደስ ይላል፤›› በማለት ይገልጹታል፡፡ በነዳጅ አቅርቦትም ሆነ በተሽከርካሪ ዘይት ምርት ረገድ ጄአር የተሻለ ገበያ እንዲኖረው ተጠቃዎችም ይበልጥ እንዲጠቀሙ ዕድሉን ከፍተናል ይላሉ፡፡

የወይዘሪት ደስታ ራዕይና እንቅስቃሴ በዚህ አልተወሰነም፡፡ ኩባንያው በዚህ አሁን ከደረሰበት በላይ እንዲደርስ ለማድረግ ትኩታቸውን በኢትዮጵያ አራቱም አቅጣጫዎች የተከፈቱትን ማደያዎች ብዛት በአሥረኛ ዓመቱ ላይ 200 የማድረስ ዕቅድ ሰንቀዋል፡፡ ከሁሉ በላይ ጥራቱን የጠበቀ ዘይት ምርት ለኢትዮጵያ ገበያ ማቅረብ መቻላቸውን ይመኩበታል፡፡ ነዳጅ መሸጥ ቀላል ነገር ነው የሚሉት ወይዘሪት ደስታ፣ 200 ማደያዎችን መክፈትና ዴፖዎችን በየቦታው መገንባት እንደሚቻል አስታውቀው፣ ትልቁ ጉዳይ ጥራት ያለው ዘይት ማቅረብ እንደሆነ ያሰምሩበታል፡፡ ‹‹እኛ ዕድሉን ስላገኘን በዚህ ዘርፍ ብዙ እንሠራን፤›› ይላሉ፡፡

ኩባንያቸው ከኢትዮጵያ ባሻገር ኤርትራ፣ ጂቡቲና ሶማሌን ማዳረስ እንዳለበትና በኢትዮጵያ ላይ ብቻ እንዳይወሰን እንደሚፈልጉ ይናገራሉ፡፡ የኩባንያው በአገር ውስጥ ብቻ የተወሰነ የነዳጅ ማደል ሥራ በምሥራቅ አፍሪካ እንዲስፋፋ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ ኩባንያው በአሁኑ ወቅት 267 ሠራተኞችን ሲኖሩት፣ የሠራተኞቹ ቁጥር እንዲጨምር ስለሚያግዝ ወደ ውጭ የመስፋፋቱ ሥራ ላይ ሳይታክቱ እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል፡፡  

የቢዝነስ ሥራቸው በቅብብሎሽ ሊዘልቅ የሚችል ኩባንያን የማፍራት አካሄድ መከተል እንዳለበት የሚያምኑት ወይዘሪት ደስታ፣ ለዚህም የልጆቻቸውን ስም ፊደላት በመጠቀም ጄአር የሚለውን የኩባንያውን መጠሪያ በዋቢነት አንስተዋል፡፡ ጄአር ከሁለት ልጆቻቸው ስም የመጀመርያ ፊደል ተወስዶ ለኩባንያቸው የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ ሥራው ለመጪው ትውልድ መተላለፍ አለበት ከሚል ዕሳቤ ያደረጉት እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ ‹‹እኔ ለእነሱ እሰጣለሁ፡፡ እነሱም ለልጅ ልጆቻቸው እንዲሰጡት እፈልጋለሁ፡፡ ይህንን ሁሌ እናገራለሁ፡፡ ጠንካራ እንዲሆኑ፣ እንዲበረታቱ ለማድረግ ከልጆቼ ስም ፊደሎችን በማቀናጀት ስያሜውን ሰጥቼዋለሁ፤›› ብለዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች