የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አራት መንገዶችን በ4.8 ቢሊዮን ብር ለማስገንባት ስምምነት ፈጸመ፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት ሦስት የአገርና አንድ የቻይና ተቋራጮች ናቸው፡፡
የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. የግንባታ ስምምነት በተፈረመበት ወቅት እንደተገለጸው፣ የግንባታ ሥራቸውን ለማስጀመር ውል የተገባባቸው ፕሮጀክቶች የቆሼ ሚጦ ወራቤ፣ የጋምቤላ፣ አቦቦ፣ ጎግ፣ ዲማ ሎት 2፣ የፑኝዶ ጎግ ጊሎ ወንዝ፣ የግሸን መገንጠያና የጎንጂ ቆለላ (ቆሬ አዳስ ዓለም) መንገድ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡
ከአራቱ መንገዶች ውስጥ የሦስት ቢሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቁትን ሦስት መንገዶች ለመገንባት ጨረታውን በማሸነፋቸው ከአገር ውስጥ የተመረጡት የንኮማድ፣ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽንና የአማራ መንገድ ሥራዎች ኢንተርፕራይዝ ናቸው፡፡ አንዱን መንገድ ለመግንባት የተመረጠው ቻይና ሬልዌይ ሰቨንዝ የተባለ ኩባንያ መሆኑ ታውቋል፡፡ ከሦስቱ አገር በቀል ተቋራጮች ውስጥ ሁለቱ በመንግሥት ይዞታ ሥር ያሉ ኩባንያዎች ናቸው፡፡
ለመንገዶቹ ግንባታ የሚውለው አጠቃላይ ገንዘብ ከ4.8 ቢሊዮን ብር በላይ ሲሆን፣ የአራቱም መንገዶች ርዝመት በጠቅላላው 169 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡ የግንባታውን ሙሉ ወጪም የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚሸፍነው ተገልጿል፡፡
በስምምነት ሥነ ሥርዓቱ ወቅት እንደተገጸው፣ ከቆሼ ሜጦ ወራቤ ድረስ የሚገነባውን መንገድ ከዲዛይን ጀምሮ ግንባታውን የሚያከናውነው የንኮማድ ኮንስትራክሽን ነው፡፡ መንገዱ 72.91 ኪሎ ሜትር ርዝመት ኖሮት በአስፋልት ደረጃ ይገነባል፡፡ የመንገዱን ትከሻ ጨምሮ በገጠር በአማካይ 10 ሜትር ስፋት ሲኖረው፣ በወረዳ 21 ሜትር በዞን ከተሞች 22.5 ሜትር ስፋት ይኖረዋል ተብሏል፡፡ በተጨማሪም ግንባታው አነስተኛ፣ ከፍተኛ የፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎችና ፉካዎችን የሚያካትት እንደሚሆን ታውቋል፡፡
የንኮማድ ለመንገድ ግንባታው አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 1.85 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ተቋራጩ መንገዱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ሦስት ዓመታት ተሰጥቶታል፡፡ የቆሼ ሜጦ ወራቤ መንገድ ለዓመታት ጥያቄ ሲቀርብበት መቆየቱ ሲገለጽ፣ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ በተገኙበት ወቅትም የዚሁ መንገድ ጉዳይ ላይ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ የመንገዱ የግንባታ ውል ከሰሞኑ እንደሚፈጸም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹበት ንግግራቸው በተሰማ በአንድ ቀን ልዩነት የግንባታ ስምምነት ተፈርሟል፡፡
ሌላው በአገር በቀል ተቋራጭ የሚገነባው የመንገድ ፕሮጀክት የግሸን መገንጠያ ነው፡፡ ይህ መንገድ ጠቅላላ 14 ኪሎ ሜትር ዋና መንገድ፣ 1.56 ኪሎ ሜትር አገናኝ መንገድና 1.8 ኪሎ ሜትር ከዋናው መንገድ የሚገነጥል መንገድ (Spur Road) ርዝመት ኖሮት በአስፋልት ደረጃ የሚገነባ ሲሆን፣ በተጨማሪም መንገዱ በጠቅላላ 131,000 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው አራት የመኪና ማቆሚያ ሎቶች ወይም ሥፍራዎች ይኖሩታል፡፡ በአማካይ የመንገድ ትከሻ፣ የእግረኛ መንገድና የመኪና ማቆሚያ ጨምሮ ከ12.5 ሜትር እስከ 18 ሜትር ስፋት ያለው እንደሆነም ታውቋል፡፡ ይህንን የግሸን መገንጠያ የመንገድ ግንባታ በ1.31 ቢሊዮን ብር ለመገንባት ጨረታውን አሸንፎ የውል ስምምነቱን የፈረመው መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ነው፡፡
በዕለቱ የተፈረመውና በአገር በቀል ተቋራጭ የሚሠራው ፕሮጀክት ጎንጂ ቆለላ (ቆሬ አዲስ ዓለም) መንገድ ሥራ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ይህ መንገድ ጠቅላላ 10.74 ኪሎ ሜትር ርዝመት ኖሮት በአስፋልት ደረጃ የሚገነባ ነው፡፡ የመንገዱን ትከሻ ጨምሮ በገጠር በአማካይ 10 ሜትር ስፋት ሲኖረው በወረዳ 21.5 ሜትር ተጨማሪ ስፋት ይኖረዋል፡፡ በተጨማሪም ግንባታው አነስተኛ፣ ከፍተኛ ፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎችና ከልቨርቶች የሚያካትት እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን፣ ይህንን መንገድ ለመገንባት የተመረጠው የአማራ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ነው፡፡
ይህንን መንገድ ለመገንባት በ333.3 ሚሊዮን ብር ጨረታውን አሸንፎ ስምምነቱን የፈረመው የአማራ መንገድ ሥራዎች ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡ ከኢንተርፕራይዙ መንገዱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ የተሰጠው ጊዜ አንድ ዓመት ተኩል ነው፡፡
ቻይና ሬልዌይ ሰቨንዝ ግሩፕ እንዲገነባ የተሰጠው ጋምቤላ አቦቦ ጎግ ዲማ ሎት 2 ፑንጊዶ ጎግ ጊሎ ወንዝ ዲዛይንና ግንባታ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ መንገድ ጠቅላላ 72 ኪሎ ሜትር ርዝመት ኖሮት በአስፋልት ደረጃ የሚገነባ ሲሆን፣ የመንገዱን ትከሻ ጨምሮ በገጠር በአማካይ አሥር ሜትር ስፋት ሲኖረው በወረዳ 21 ሜትር በዞን ከተሞች 22.5 ሜትር ስፋት ይኖረዋል፡፡ ይህ ግንባታም አነስተኛ፣ ከፍተኛ ፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎችና ከልቨርቶች የሚያካትት ነው፡፡ ይህንን መንገድ የቻይናው ተቋራጭ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 1.34 ቢሊዮን ነው፡፡ በአጠቃላይ መንገዱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ሦስት ዓመት ይፈጃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን መረጃ፣ የመንገዶቹ መገንባት ለተሽከርካሪዎች ደኅንነት ከሚፈይዱት ባሻገር፣ የጉዞ ጊዜን በማሳጠር፣ በቂ የመንገድ መሠረተ ልማት የሌለባቸውን አካባቢዎች ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻልና የትራንስፖርት ችግሮችን ማቃለል የሚያስገኟቸው ጠቀሜታዎች ናቸው፡፡
እነዚህ መንገዶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳና የጥራት ደረጃ እንዲጠናቀቁ መንገዶች ባለሥልጣን ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል ተብሏል፡፡ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር) እንደገለጹት፣ ስምምነት መፈራረም ብቻ ሳይሆን፣ መንገዶቹን በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቁ ዋናው ነገር ነው፡፡ ለዚህም ተቋራጮቹና መንገዶች ባለሥልጣን ብቻም ሳይሆኑ፣ መንገዶቹ በሚገነባባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችም ትብብር ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
መንገዶቹ በሚገነቡባቸው መስመሮች ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች፣ የአስተዳደር አካላት፣ እንዲሁም የመንገዱ ተጠቃሚዎች በሙሉ የመንገዱ ግንባታ ተጀምሮ በታሰበለት ጊዜ በስኬት እንዲጠናቀቅ ትብብር እንዲያደርጉ ዋና ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል፡፡
የመንገድ ግንባታዎቹን ስምምነት የኢትዮጵያ የመንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ከግንባታ ኩባንያዎቹ ኃላፊዎች ፈርመዋል፡፡ ስምምነቱ ሲፈረም የሕዝብ ተወካይ ምክር ቤት አባላት፣ መንገዱ ከሚገኙባቸው አካባቢዎች የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎችና የአስተዳደር አካላት በእማኝነት ተገኝተዋል፡፡