Saturday, June 22, 2024

ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ተመራማሪ ጋር ስብሰባ ላይ ተገናኙ]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ?
 • በጣም አሳስቦኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ?
 • የግድቡ ጉዳይ ነዋ፡፡
 • አታስብ፡፡
 • እንዴት አላስብም ክቡር ሚኒስትር?
 • የአገራችንን ጥቅም አሳልፈን አንሰጥማ፡፡
 • አይ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምነው?
 • አቅማችንን እያወቁት፡፡
 • ማለት?
 • ደሃ አገር መሆናችንን አይርሱታ?
 • ደሃ ብንሆንም ግን ጀግኖች ነን፡፡
 • እንዴት?
 • ስማ በጦርና በጋሻ ጣሊያንን እንዳባረርን መዘንጋት የለብህም፡፡
 • የዚያን ጊዜ ትውልድማ ጀግና ነበር፡፡
 • እንዳታስብ አሁንም ቢሆን ለማንም አንበረከክም፡፡
 • ታዲያ የማይመለከታቸው ጉዳይ ውስጥ ገብተው የሚፈተፍቱትን ለምን አታባርሯቸውም?
 • እነ ማንን?
 • ታዛቢ ነን ባዮቹን ነዋ፡፡
 • እ…
 • መቼም እጃቸው ረዥም መሆኑን ለእርስዎ አልነግርዎትም?
 • እሱማ ግልጽ ነው፡፡
 • ይኸው የእኛ ተደራዳሪዎች ላይ ጫና እየፈጠሩባቸው ነው፡፡
 • ማንም አይንበረከክላቸውም ስልህ?
 • ክቡር ሚኒስትር አንችላቸውም ግን እኮ፡፡
 • በምን?
 • በሁሉም ነገር ነዋ፡፡
 • መርሳት የሌለብህ ለእነሱም እኛ እናስፈልጋቸዋለን፡፡
 • ቢሆንም የግድቡን ድርድር እኮ የመካከለኛው ምሥራቅ ችግር መፍቻ እያደረጉት ነው፡፡
 • ማን ይሰማቸዋል ታዲያ?
 • ክቡር ሚኒስትር ከመጀመርያው የእኛው ጥፋት ነው፡፡
 • እንዴት?
 • የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካውያን ነዋ መፈታት ያለበት፡፡
 • መቼ ይቀራል እሱ?
 • ከዚህ በኋላ ይሆናል ብለው ነው?
 • በምንም ዓይነት መንገድ የአገራችንን ጥቅም አሳልፈን አንሰጥም፡፡
 • ግብፅ እኮ የምትፈልገው በዓባይ ውኃ ላይ ምንም ዓይነት ልማት እንዳይኖር ነው፡፡
 • እኛም የምንታገለው እሱን ነው፡፡
 • ለማንኛውም ሕዝቡ ጉዳዩን በጥንቃቄ እየተከታተለው ነው፡፡
 • እኛም በጥንቃቄ እየተከታተልነው ነው፡፡
 • ስለዚህ ምን እንጠብቅ?
 • ከምኑ?
 • ከድርድሩ ነዋ?
 • ድል!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ምዕራባዊ ዲፕሎማት ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • ተገርሜያለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በምኑ?
 • በአገሪቱ ነዋ፡፡
 • እንዴት?
 • በጣም ተለውጣለች፡፡
 • ከዚህ ቀደም መጥተህ ታውቃለህ እንዴ?
 • 20 ዓመት በፊት መጥቼ አውቃለሁ፡፡
 • እንዴት አገኘሃት ታዲያ?
 • ከልቤ ነው የተገረምኩት፡፡
 • ከዚህ በላይ መለወጥ እንደምንችልም አምናለሁ፡፡
 • ከአገሪቱ ዕድገት በላይ የሰዎችም ነፃነት መሻሻሉን ሰምቻለሁ፡፡
 • በቻልነው መጠን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማስፈን እየሞከርን ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ቀጣዩም ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ግንባታ ማሳያ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡
 • ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ለማድረግ እየተዘጋጀን ነው፡፡
 • ለነገሩ እናንተ እንደምታሸንፉ ያስታውቃል፡፡
 • ምኑ ያስታውቃል?
 • ያው የእኛ ድጋፍ አላችሁ ብዬ ነዋ፡፡
 • ምርጫ እኮ የውስጥ ጉዳይ ነው፡፡
 • ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለማንኛውም ተወው፡፡
 • ከእኛም ጋር ወደፊት ብዙ ሥራዎች እንሠራለን፡፡
 • ምን ጥርጥር አለው?
 • መጀመርያ ግን የጀመርናትን መጨረስ አለብን፡፡
 • ምኑን?
 • የግድቡን ድርድር ነዋ፡፡
 • እንግዲህ ሦስቱም አገሮች መግባባት ላይ ስንደርስ መፈራረማችን አይቀርም፡፡
 • ከዚህ በኋላ ምን ቀራችሁ?
 • የእኛ ጥያቄዎች እኮ አልተመለሱም፡፡
 • ጥያቄያችሁ ገንዘብ አይደል እንዴ?
 • ምን ነካህ ለማኞች እኮ አይደለንም፡፡
 • ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • እ…
 • ለማንኛውም ሌላ አማራጭ የላችሁም፡፡
 • ማለት?
 • ከመፈረም ውጪ ማለቴ ነው፡፡
 • ለምን ሲባል?
 • ያለበለዚያ ዕርዳታውን እናቋርጠዋለን፡፡
 • አልገባኝም?
 • ግልጽ ነገር መሰለኝ የተናገርኩት ክቡር ሚኒስትር?
 • አንድ ነገር ልንገርህ፡፡
 • ምን?
 • በዕርዳታ ስም…
 • እ…
 • አገር አንሸጥም!

[ክቡር ማኒስትሩ ከአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጋር ቢሯቸው እያወሩ ነው]

 • ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ሆንክ?
 • እኛ ተቃዋሚዎች ሳንሆን ተፎካካሪዎች ናችሁ አላላችሁንም ነበር እንዴ?
 • ምን ጥያቄ አለው?
 • ታዲያ እርስዎን ለማግኘት ይኼ ሁሉ ቢሮክራሲ ምንድነው?
 • ሥራ ስለሚበዛብኝ ነዋ፡፡
 • ሁሌ ስመጣ ስብሰባ ላይ ናቸው እኮ ነው የሚባለው፡፡
 • ያለብንን ሥራ እያወቅክ?
 • ስብሰባ ከሥራ ሰዓት ውጪና ቅዳሜና እሑድ ይሁን አላላችሁም ነበር እንዴ?
 • ኧረ ለአንተ ጊዜ አናጣም፡፡
 • ታዲያ ለምን እንደዚህ ታሰቃዩኛላችሁ?
 • አንተ እኮ ለእኛ ከተቃዋሚም በላይ አብረኸን የምትሠራ ነህ፡፡
 • እኔም እኮ እሱን ብዬ ነው፡፡
 • ምን አዲስ ነገር አለ?
 • ባለፈው በተነጋገርነው መሠረት አንዳንድ ነገሮችን ከእርስዎ ጋር ለመነጋገር ፈልጌ ነው የመጣሁት፡፡
 • መቀጠል ትችላለህ፡፡
 • እንግዲህ ወደ ምርጫ ቅስቀሳ ልንገባ ነው፡፡
 • እኛም እንከተላችኋለን፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ለምርጫ ቅስቀሳ በምንሰናዳበት ጊዜ ግን ከመንግሥት በኩል ትብብር እያገኘን አይደለም፡፡
 • ምን ዓይነት ትብብር?
 • ከወዲሁ ከሕዝቡ ጋር እንዳንገናኝ ክልከላ እየተደረገብን ነው፡፡
 • ለምን?
 • ያው ሁከትና ብጥብጥ ታስነሳላችሁ በሚል ነዋ፡፡
 • እንዲህማ መደረግ የለበትም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በየአካባቢው ካሉ ካድሬዎች ጋር ግን መግባባት አልቻልንም፡፡
 • በአስቸኳይ ትዕዛዝ እሰጥልሃለሁ፡፡
 • ባለፈውም እንዲህ ቢሉኝም ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን እየባሰባቸው ነው የመጣው፡፡
 • አንተ እኮ ወንድማችን ነህ፡፡
 • እኔም የምለው እሱን አይደል እንዴ?
 • ግን በቅስቀሳህ ስለእኛ ነው የምታወራው?
 • ምን ጥያቄ አለው?
 • አታስብ በቃ ሁሉ ነገር ይስተካከላል፡፡
 • ጥያቄ ግን አለኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • የምን ጥያቄ?
 • የእኔ ትርፍ ምንድነው?
 • ማለት?
 • እናንተ ካሸነፋችሁ ማለቴ ነው፡፡
 • እናካፍልሃለና፡፡
 • ምን?
 • ድምፅ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]

 • አይመጡም ክቡር ማኒስትር?
 • የት?
 • ድግሳችን ላይ ነዋ፡፡
 • የምን ድግስ?
 • እያከበርን አይደል እንዴ?
 • ምንድነው የምታከብሩት?
 • ትግል የጀመርንበትን ቀን ነዋ፡፡
 • እናንተ ግን መቼ ነው የምታቆሙት?
 • ምን?
 • ትግል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ትግል መቼም የሚቆም ነገር አይደለም፡፡
 • ታዲያ በዓሉ እንዴት ነው?
 • ይኸው በደመቀ ሁኔታ እያከናወነው ነው፡፡
 • የትግላችሁ ውጤት ግን አሁን እየተቀለበሰ ነው እኮ?
 • እ…
 • ማለቴ አሁን ድጋሚ መታገል እንጂ ድግስ መደገስ አይደለም ያለባችሁ፡፡
 • ምን አገባዎት እርስዎ?
 • ኧረ ምንም፡፡
 • ለማንኛውም የሁሉም  ነፃነት የታወጀው በዚህ ቀን ከተጀመረው ትግል በኋላ ነው፡፡
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • እርስዎም ይህን የነፃነት ቀን ሊያከብሩት ይገባል፡፡
 • እኔ እንኳን የማከብረው ሌላ ቀን ነው፡፡
 • የምን ቀን?
 • ነፃ የሆንኩበትን ቀን ነዋ፡፡
 • ከምን ነፃ የሆኑበትን?
 • ከእናንተ!

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት ሐዘን ለመድረስ ጎረቤት ተገኝተው ለቀስተኛው በሙሉ የሚያወራው ነገር አልገባ ብሏቸው ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ባለቤታቸውን ስለጉዳዩ እየጠየቁ ነው] 

ጎረቤታችን ሐዘን ለመድረስ ብሄድ ለቀስተኛው በሙሉ በሹክሹክታ ያወራል። ግን የሚያወሩት ነገር ሊገባኝ አልቻለም። ምንድነው የሚያወሩት? እኔ ምን አውቄ? እንዴት? የሚያወሩትን ምንም አልተሰማሽም? እኔ እንድሰማ የፈለጉ አይመስልም ግን ... ግን...

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት የሚታወጁ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ማለቴ ነው። ምን ታወጀ? አንዴ ከዕዳ ወደ ምንዳ አላችሁ፡፡ እሺ? የእሱን ውጤት እየጠበቅን ሳለ ደግሞ... እ...? ኢትዮጵያ ታምርት...

[ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን በተጀመረው አገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ስለተላለፉ መልዕክቶች በተመለከተ ከባለቤታቸው ጋር እያወጉ ነው] 

እኔ ምልህ? እ... አንቺ የምትይው? አለቃህ በምክክር መድረኩ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት አደመጥክ? አዎ፡፡ የሚገርም እኮ ነው አልተገረምክም? ምኑ ነው የሚያስገርመው? ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ምከሩና አምጡ ብለው የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ...