Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አምራቾች በቢራ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ጀመሩ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የቢራ ሳጥን ዋጋ እስከ 140 ብር ሲጨምር በርሜል ድራፍት ከ300 ብር በላይ ጨምሯል

በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፀደቀው ኤክሳይስ ታክስ መነሻነት አብዛኞቹ የአልኮል መጠጥና የቢራ ፋሪካዎች የዋጋ ለውጥ ባያደርጉም፣ በችርቻሮ መሸጫዎች አካባቢ ጭማሪ እየተደረገባቸው ነው፡፡

ከየካቲት 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ የታወቀው ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ገበያ አንድ ሳጥን ቢራ (24 ጠርሙስ) ከፋብሪካ እንደወጣ የሚያከፋፍልበትን ዋጋ ወደ 430 ብር ከፍ አድርጓል፡፡ ሐበሻ ቢራ በበኩሉ የፋብሪካ ዋጋውን ወደ 415 ብር ከፍ አድርጓል፡፡ ሐይኒከን ቢራ በዋልያ ምርቱ ላይ ከቢጂአይ እኩል የአንድ ሳጥን ቢራ መሸጫ ዋጋውን ወደ 430 ብር አሳድጓል፡፡

የዋጋ ጭማሪው እስካሁን ሲያከፋፍሉበት ከነበረው አኳያ ከ135 እስከ 140 ብር ለውጥ አሳይቷል፡፡ የአንድ ሳጥን ቢራ የማከፋፈያ ዋጋ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ 290 ብር  ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከሰኞ የካቲት 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የዋጋ ለውጥ መከሰቱን የቢራ ምርቶችን ከአከፋፋዮች የገዙ የግሮሰሪና የሆቴል ባለንብረቶች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከጠርሙስ ቢራ ባሻገር ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የታየበት ድራፍት ነው፡፡ ከየካቲት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የአንድ በርሜል ድራፍት የማከፋፈያ ዋጋ ላይ የ345 ብር ጭማሪ ተደርጓል፡፡ እስካሁን ሲከፋፈልበት በነበረው 815 ብር ላይ የ345 ብር ተጨምሮ ታክሎበት፣ በ1,165 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ዋሊያ ድራፍት በበርሜል 340 ብር ጨምሮ 1,600 ብር እንደሚያከፋፍል መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ይህም ሆኖ ሌሎች የቢራ ፋብሪካዎች በበኩላቸው ሰሞኑን ምርታቸውን ከማከፋፈል መቆጠባቸውን ቸርቻሪ ነጋዴዎች ይገልጻሉ፡፡ ይህን ያደረጉትም ዋጋ  እስኪጨምሩ ምርት ለመያዝ ፈልገው እንደሆነ የሚጠቁሙ አስተያየቶች እየተደመጡ ነው፡፡ ቀደም ብሎ በቢራ ዋጋ ላይ ጭማሪ በማድረግ እያሠራጨ የነበረው ቢጂአይ ቢሆንም፣ በችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ማስተካከያ ተደርጎና ተጨምሮ ሲሸጥ የነበረው ግን በሁሉም የቢራ ዓይነቶች ላይ እንደሆነ ተጠቃሚዎች ይገልጻሉ፡፡ ሌሎቹ ፋብሪካዎች ከመቀላቀላቸው ቀደም ብሎም በችርቻሮ ዋጋ ላይ ለውጥ ተደርጎ ነበር፡፡  

ከዚህ ቀደም እንደየአካባቢው ሁኔታ በሆቴሎችና በግሮሰሪዎች በ15 ብር ይሸጡ የነበሩ፣ 330 ሚሊ ሌትር መጠን ያላቸው ቢራዎች ከየካቲት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ 20 ብር እና ከዚያ በላይ እየተሸጡ ነው፡፡ ከ15 እስከ 20 ብር ይሸጡ የነበሩ ግለሰብ ነጋዴዎችና ግሮሰሪዎችም ከ25 እስከ 30 ብር መሸጥ እንደጀመሩ እየታየ ነው፡፡

አዲሱ የኤክሳይስ  ታክስ አዋጅ ከየካቲት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ያለው የገቢዎች ሚኒስቴር በአዋጁ እንደተመለከተው፣ ማንኛውም ቢራ የተጣለበት ኤክሳይስ  ታክስ መጠን 40 በመቶ ወይም በአንድ ሌትር 11 ብር ጭማሪ ኖሮት አሊያም ከሁለቱ አንዱ የበለጠው ታሳቢ ተደርጎ ታክስ ይጣልበታል፡፡

በቢራ ላይ ከዚህ ቀደም የተጣለው የኤክሳይስ  ታክስ መጠን 50 በመቶ ነበር፡፡ ይህ የታክስ መጠን ሥሌቱ የሚያርፈው በማምረቻ ወጪዎች ላይ ነበር፡፡ በአዲሱ ኤክዛይዝ ታክስ አዋጅ መሠረት ግን በቢራ ምርቶች ላይ የተጣለው የ40 በመቶ የኤክሳይስ  ታክስ የሚሰላው ከፋብሪካ ወጪ በሚደረግ ምርት ሽያጭ ላይ ነው፡፡  

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሲጋራ ምርቶች ላይም የዋጋ ጭማሪዎች መታየት ጀምረዋል፡፡ ተጠቃሚዎች እንደሚገልጹት፣ የዋጋ አጨማመሩ የተዘበራረቀ፣ እንደየ አካባቢውና በችርቻሮ እንደሚሸጠው ነጋዴ ሁኔታ ዋጋውም ልዩነት እየታበት ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች