አቢሲኒያ ባንክ ከወለድ አልባ አገልግሎት ያሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ ከ1.7 ቢሊዮን በላይ መድረሱን አስታወቀ፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥበት ልዩ ቅርንጫፍ ሥራ አስጀምሯል፡፡
ባንኩ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎቶችን በተደራጀ አግባብ ለማቅረብ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ አኳያ፣ በአዲስ አበባና በሌሎችም ከተሞች ራሳቸውን የቻሉ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎቶች የሚሰጡ ቅርንጫፎችን በመክፈት ላይ ሲሆን፣ በእነዚህ ቅርንጫፎች ብሎም በመስኮት በኩል ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ከ125 ሺሕ በላይ አስቀማጭ ደንበኞች እንዳፈራ ገልጿል፡፡ ከእነዚህ ደንበኞችም ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ማሰባሰብ እንደቻለ የባንኩ መረጃ ያስረዳል፡፡
አቢሲኒያ ባንክ እስካሁን ወለድ አልባ አገልግሎቶችን ከሚሰጡ ቅርንጫፎች ባሻገር፣ ቅዳሜ የካቲት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ልዩ የወለድ አልባ አገልግሎት እንዲሰጥ የተደራጀውን ቅርንጫፍ ሲያስመርቅ እንደተገለጸው፣ ከዚህ ቅርንጫፍ ባሻገር በአዲስ አበባ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ የሚገኘው ሒላል ቅርንጫፍ፣ መርካቶ አካባቢ የሚገኘው አማና ቅርንጫፍ፣ አየር ጤና ሞቢል አካባቢ የሚገኘው በረካ፣ በክልል ቻግኒ ከተማ ዳሩ ሰላም ቅርንጫፍ፣ ሐሮማያ ከተማ ተውሊድ ቅርንጫፍ፣ ጅግጅጋ ከተማ ገራድ ውልዋል ቅርንጫፍ፣ ከሚሴ ከተማ ቢላል ቅርንጫፍ እንዲሁም በባህር ዳር ከተማ አሊፍ ቅርንጫፍ በአጠቃላይ ስምንት ቅርንጫፎች ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ብቻ በመስጠት ሥራ ጀምረዋል፡፡ ባንኩ ተመሳሳይ ቅርንጫፎችንም ለመክፈት መዘጋጀቱ ስለመሆኑ የጠቀሱት በባንኩ የወለድ አልባ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አብዱርቃድር ሬድዋን፣ ባንኩ ከወለድ ነፃ አገልግሎቱን ለማስፋት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡
አቢሲኒያ ባንክ ሰሜን ሆቴል አካባቢ በራሱ ንብረት በሆነው ሕንፃ ላይ የከተፈው በልዩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ቅርንጫፍ ‹‹አሚን ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት›› በመሰኘት በማዕከል ደረጃ፣ በአዲስ የሠራተኛ አደረጃጀትና የቢሮ ገጽታ እንዲታነጽ ተደርጎ የሕንፃውን የመጀመርያ ወለል ለዚሁ አገልግሎት አውሎታል፡፡ በላይ ዘለቀ የሚል ስያሜ ባለ ሰባት ወለል ሕንፃ ላይ ሥራ የጀመረው ይህ ልዩ ቅርንጫፍ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ልምድ ባላቸው 20 ሠራተኞች የሚያገለግል እንደሚሆን ተጠቅሷል፡፡
ከተቀማጭ ገንዘብም ሆነ ከብድር አገልግሎት አኳያ አጠቃላይ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ሥራዎች ይህን ማዕከል የሚመለከቱና ዋነኛ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጥበት ማዕከል ይሆናል ተብሏል፡፡
ባንኩ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ ወገኖቹን ሳያካትት ሙሉ እንደማይሆን በመገንዘቡ አገልግሎቱን እ.ኤ.አ. ከዲሴምበር 2017 ጀምሮ ተግባራዊ ሲደረግ እንደቆየ ያመለክታል፡፡ የሸሪዓ መርሆችን በመከተል የተቀማጭ ሒሳብ፣ የብድር አቅርቦት፣ የዋስትና፣ ዓለም አቀፍ ንግድ፣ ገንዘብ የማስተላለፍና የውጭ ምንዛሪ አገልግሎቶችን ሲያቀርብ እንደቆየ አስታውቋል፡፡
እንደ አቶ አብዱርቃድር ገለጻ፣ በባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ በትክክለኛና በሸሪዓው የፋይናንስ ድንጋጌ መሠረት ለመሥራት ከታኅሣሥ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የሸሪዓ አማካሪዎችን እንደሰየመ አስታውሰዋል፡፡ አማካሪዎቹ በነፃነት እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡
አሚን የተሰኘውን ይህንን ከወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ልዩ ቅርንጫፍ በክብር እንግድነት ተገኝተው የመረቁት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡
ፕሬዚዳንቱ ተቀዳሚ ሙፍቲህ እንድሪስ በምረቃው ላይ እንደገለጹት እንዲህ ያሉ ኢስላማዊ ባንኮችን እንዲከፈቱ ለፈቀዱልን የዛሬ መሪዎች ምሥጋና ይገባቸዋል ብለው፣ ዜጎች ባሉበት በመሥራት ተጠቃሚ እንዲሆኑም መክረዋል፡፡
አቢሲኒያ ባንክ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ ዕድሜ ካላቸው ባንኮች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ከ4000 በላይ ባለአክሲዮኖች አሉት፡፡ በአሁኑ ወቅት ባንኩ በመላ አገሪቱ 440 ቅርንጫፎች ሲኖሩት፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት ከ1.02 ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፉን መግለጹ ይታወሳል፡፡