የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በግማሽ ዓመቱ ከ197.8 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ሲያስመዘግብ፣ ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ መጠን 759 ሚሊዮን ብር በመድረሱ ከአምናው ሙሉ በሒሳብ ዓመት ካተረፈው ጋር ተቀራራቢ ሆኗል፡፡
ባንኩ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ አምና ሙሉውን ሒሳብ ዓመት ካከናወናቸው ተግባራት ያስመዘገበው ትርፍ ከታክስ በፊት 767 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ግማሽ ዓመት ከታክስና ከሌሎች ተናቃሽ ሒሳቦች በፊት ያስመዘገበው የትርፍ መጠን 759 ሚሊዮን ብር በመሆኑ፣ የስድስት ወራት አፈጻጸሙ ከወዲሁ የዓመት ሙሉ ውጤቱን ከፍተኛ ብልጫ እንደሚያሳይበት ከወዲሁ እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡
ባንኩ ስለዚህ ውጤቱ ያስታወቀው፣ ለውጭ ምንዛሪ ግኝቱ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የባንኩ ደንበኞች ሰሞኑን ዕውቅና በሰጠበት ወቅት ነበር፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ድርቤ አስፋው እንደገለጹት፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማግኘት እየታዩ ያሉት ተግዳሮቶች እየተበራከቱ ቢመጡም፣ ባንካቸው ባደረገው ጥረት በግማሽ ዓመት ውስጥ 197.8 ሚሊዮን ዶላር ማሰባሰብ ችሏል፡፡
‹‹በዚህ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ባንካችን በየደረጃው ላሉ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የሙያ ድጋፍና የምክር አገልግሎት በመስጠት ፋብሪካዎችንና ኢንዱስትሪዎችን በማቋቋም የሥራ ዘርፋቸውን እንዲያሰፉ ባንኩ አስተዋጽኦ አበርክቷል፤›› በማለት ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ በማስቻል ትርፋማ እንዲሆኑ ከማገዝ ጎን ለጎን በውጭ ምንዛሪ ግኝትም ለኢኮኖሚው ሚናቸውን እንዲጫወቱ ባንኩ ማገዙን በመጥቀስ፣ ከግብርና ዘርፍ በተጨማሪ በማንኛውም ወጪ ንግድ ሥራ ከተሰማሩ ድርጅቶች ጋር በመሥራት በዓመቱ አጋማሽ ከወጪ ንግድ፣ ከውጭ ሐዋላና ከውጭ ምንዛሪ በአጠቃላይ የ197.8 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስመዝገብ መቻሉን ፕሬዚዳንቱ አመልክተዋል፡፡
በወጪ ንግድ መስክ ዋናው የውጭ ምንዛሪ ምንጭ የሆነው የቡና ምርት አቅርቦትና ጥራት እንዲሻሻል ትኩረት ሰጥቶ በመሥራትና ዕገዛ በማድረግ አምራቹን ተጠቃሚ ያደረገ የወጪ ንግድ ዕገዛ ሥራዎችን ባንኩ እያከናወነ እንደሚገኝ አቶ ድርቤ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በወጪ ንግድ ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ የመጡትን የቅባት እህሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ እንዲሁም ጫትን ወደ ውጭ በመላክ ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ መሠረታዊ ማኅበራትን፣ የኅብረት ሥራ ዩኒየኖችንና ሌሎች በወጪ ንግድ ላይ የተሠማሩ ደንበኞቹን እያገዘና ትርፋማነታቸውን እያሳደገ የውጭ ምንዛሪ ግኝቶችን እያስፋፋ እንደመጣ ተገልጿል፡፡
አቶ ደርቤ እንደሚሉት፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ላይ በተመሠረተ አሠራር ገንዘባቸውን አሰባስበው በሚንቀሳቀሱት ላይ በአብዛኛው የብድር ማስያዣ የማይጠየቅበት ብድር በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ከቤተሰብ የሚጀመርና የቁጠባ ልማድን በሚያዳብር አሠራር፣ በሒደትም አቅሙ ያላቸው የካፒታል አቅማቸውን በማስፋፋት በኢንቨስትመንትና በወጪ ንግድ መስኮች ላይ እንዲሰማሩ በማገዝ፣ በግብርናና ግብርናን መሠረት ባደረጉ መስኮች ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች የእሴት ሰንሰለትን መሠረት በማድረግ ድጋፍ የሚሰጥት የፋይናንስ አቅርቦት እየተዘረጋ ነው ተብሏል፡፡ እንዲህ ባለ መልኩ ከሚሠራው ሥራ የሚመነጨው የውጭ ምንዛሪ ገቢ እያደገ መምጣቱ የተገለጸ ሲሆን፣ 16 ላኪዎች ላበረከቱት የውጭ ምንዛሪ ግኝት ዕውቅና ሰጥቷል፡፡
ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የግማሽ ዓመት አፈጻጸሙን ይፋ ባደረገበት ወቅት እንዳስታወቀው፣ የሀብት መጠኑ 51.21 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት የሰጠው አዲስ የብድር መጠን ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ በመሆኑ፣ ይህም አጠቃላይ የባንኩን የብድር ክምችት መጠን ከ4.8 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረሱን አመልክቷል፡፡
የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ 40.05 ቢሊዮን ብር መድረሱን ሲገለጽ፣ በመንፈቅ ዓመቱ ያሰባሰበው አዲስ የተቀማጭ መጠን ከ3.8 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ባንኩ በ2011 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ያስመዘገበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 36.17 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡
ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክን ከግል ባንኮች ለየት የሚያደርገው፣ የሒሳብ ደብተር ያላቸው የአስቀማጭ ደንበኞቹ ብዛት ሲሆን፣ በ2011 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ብዛታቸው 5.28 ሚሊዮን የነበሩት ደንበኞቹ በ2012 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ ከ630 ሺሕ በላይ አዲስ ተጨምረውበት በጠቅላላው ወደ 5.91 ሚሊዮን አሻቅበዋል፡፡ ይህ በመሆኑም በባንኩ የሒሳብ መዝገብ ከፍተው የሚገለገሉ ደንበኞች ቁጥር ከግል ባንኮች በእጅጉ ብልጫ አላቸው፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደንበኞች ያሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲሆን፣ ከ23 ሚሊዮን በላይ ሒሳብ የተከፈቱ ደንበኞች እንዳሉት ይታወቃል፡፡
በግል ባንኮች ውስጥ ሒሳብ ያላቸው ደንበኞች ቁጥራቸው ከሦስት ሚሊዮን ያነሰ ነው፡፡ ከትርፉማነት አኳያም ባንኩ በዚህ ዓመት ግማሽ ያስመዘገበው ውጤት በ2011 ዓ.ም. ሙሉ ዓመት ካገኘው ትርፍ ጋር መቀራረቡም ግስጋሴውን አጉልቶታል፡፡
ኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ በአሁኑ ወቅት 14,023 ባለአክሲዮኖች ያሉት የፋይናንስ ተቋም ሲሆን፣ ከባለአክሲዮኖቹ ውስጥ 5,915 የመጀመርያ ደረጃ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ናቸው፡፡ 94 የኅብረት ሥራ ዩኒየኖችና አንድ የኅብረት ሥራ ፌዴሬሽንም የባንኩ ባለድርሻዎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ 60 በመቶ የሚሆኑት የባንኩ ባለድርሻዎች እነዚሁ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየኖች ናቸው፡፡ የተቀረውን 40 በመቶ ድርሻ የሚይዙት 103 ተቋማትና ማኅበራቶች ሲሆኑ፣ የግል ባለአክሲዮኖች 7,910 ናቸው፡፡
የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በግብርና ላይ የተሰማራውን ማኅበረሰብ ለነበረበት የገንዘብ አቅርቦች ችግር መፍትሔ ለመሻት የተቋቋመ እንደሆነ የሚገልጸው የባንኩ መረጃ፣ ከባንኩ የማቋቋሚያ ካፒታል 73 በመቶው ከኅብረት ሥራ ማኅበራት የመነጨ ካፒታል ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ካፒታሉ አራት ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከ408 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣ ከ80 በመቶ በላይ ቅርንጫፎቹ ከአዲስ አበባ ውጭ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡